ከሲዳማ ዞን የተፈናቀሉ 457 ግለሰቦች በኦሮሚያ ጉጂ ዞን ቦሬ ወረዳ ተጠልለዋል

ከሲዳማ ዞን ተፈናቅለው በቦሬ ወረዳ ከተጠለሉ መካከል በከፊል

ከሲዳማ ዞን ተፈናቅለው በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ቦሬ ወረዳ የተጠለሉ ግለሰቦች ወደ 457 መድረሳቸውን የቦሬ ወረዳ አስተዳደርና ጸጥታ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ታፈሰ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ባለፉት አራት ቀናት ከሲዳማ ተፈናቅለው በቦሬ ወረዳ የተጠለሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ከወረዳው አቅም በላይ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ኃላፊው ገልጸዋል። አሁን መንግሥት ለተፈናቃዮች የህክምና ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፤ የቦሬ ነዋሪዎች ደግሞ ለተፈናቃዮች ምግብና ልብስ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በቤተ እምነት ውስጥ ከተጠለሉት ተፈናቃዮች ውጪ በዘመድ ቤት የተጠለሉም ስላሉ የተፈናቃዮች ቁጥር ከ457 ሊበልጥ እንደሚችልም አክለዋል። የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የመፀዳጃ ቤት እጥረት እንዳጋጣማቸውም ኃላፊው ገልፀዋል።

ሐሙስ ሐምሌ 11 2011 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ ተቀስቅሶ ወደ ሌሎች የሲዳማ ዞን አካባቢዎች የተዛመተው ሁከት ከባድ የንብረት ውድመትን ማስከተሉን በወንዶ ገነት፣ ሀገረ ሰላም፣ ይርጋለም ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችና የመንግስ ኃላፊዎች መናገራቸውን በወቅቱ ዘግበን ነበር።

በወንዶ ገነት ከተማ በነበረ ተቃውሞ 3 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

ከሐዋሳ ተነስቶ በሌሎች አካባቢዎች ጉዳት ያደረሰው ሁከት

በሲዳማ ዞን ተወልደው ቤተሰብ እንዳፈሩ የሚናገሩ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በብሔራቸው ምክንያት ከሲዳማ ዞን፣ ይርጋለም ከተማ ሀምሌ 12፣ 2011 ዓ. ም. ተፈናቅለዋል።

የሌላ ብሔር ተወላጆች ከአካባቢው መፈናቀል የጀመሩት ሀምሌ 11፣ 2011 ዓ.ም. አመሻሽ አካባቢ መሆኑን የሚናገሩት ግለሰቡ፤ "ትልቅ ጥፋት የተፈጸመው ከከተማ ይልቅ በገጠር ነው" ብለዋል።

"ከተማ አካበቢ ቤት እናቃጥላለን በሚሉበት ጊዜ ሌሎች 'ተዉ አታቃጥሉ፤ እነሱ ሲሄዱ እንኖርበታለን' እያሉ ነበር። በገጠር ግን ቤቶችን አቃጥለዋል፤ የቤት እንስሳት ዘርፈዋል፤ በዘመቻ እንስሳት አርደው በልተዋል" ሲሉ ይናገራሉ።

አክለውም "ሌሎች ብሔሮችን ለይቶ የሚያፈናቅሉት ሰዎች አብረን በፍቅር ስንኖረ የነበረውን የሲዳማን ሕዝብ አይወክሉም" ብለዋል።

በብሔራቸው ምክንያት ከአገረ ሰላምና ይርጋለም የተፈናቀሉት ሰዎች አሁን በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን፣ ቦሬ ወረዳ በቤተ እምነቶች ተጠልለው እንዳሉና የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ ስለመጣ በመቃብር ቤቶችም እየተጠለሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው ተፈናቃይ "ያላስተዋልነውና ጉዳት እስከሚደርስብን የጠበቅነው እኛ ነን እንጂ አስቀድመውም ሲያስጠነቁን ነበር" ሲሉ ገልጸዋል።

"ከአንድ ወር በፊት ሀምሌ 11፣ ሀምሌ 11 እያሉ ሲፎክሩብን ነበር።" ያሉት ግለሰቡ፤ "እነሱ በዛን ቀን ሌሎች ብሔሮችን ለማፈናቀል አቅደው ነበር። እኛ ግን ለክልል ጥያቄያቸው መልስ ለማግኘት መስሎን ነበር የተቀመጥነው" ብለዋል።

ቤተ እምነቶችና የሌላ ብሔር ተወላጆች "ለሲዳማ ክልልነት እንዳይሰጥ ብር እያሰባሰባችሁ ለመንግሥት አካላት ስትሰጡ ነበር" የሚል አሉባልታ መወራት መጀመሩን አክለዋል።

"እኛ ገንዘብ አላሰባሰብንም ብንላቸውም ጉዳዩ እስከ ወረዳ አስተዳደር ደርሶ የሲዳማ ተወላጆች ብቻ በዝግ ስብሰባ ሲመክሩበት ነበር። በኋላ እኛም ፈርተን ወረዳውን ስንጠይቅ አትፍሩ ፖሊስ መድበናል እንጠብቃችኋለን እያሉ ተስፋ ሰጥተውን ነበር" ብለዋል።

የይርጋለም ነዋሪ የነበሩና ተፈናቅለው ቦሬ ተጠልለው የሚገኙ እናት እንዳሉት፤ ከቀያቸው ከተፈናቀሉ በኋላ ሦስት ልጆቻቸው እስካሁን የት እንዳሉ እንደማያውቁ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሀምሌ 12፣ 2011 ዓ.ም. ማታ የተደራጀ ቡድን ቤታቸውን ሲያቃጥል ከቤተሰባቸው ጋር ሸሽተው መውጣታችን ይናገራሉ።

መድሃኒት የሚቋቋም የወባ በሽታ በደቡብ ምስራቅ ኤሲያ እየተስፋፋ ነው

ሲዳማ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ መኖራቸውን የሚናገሩት እናት፤ ከሲዳማ ሕዝብ ጋር በፍቅር ሲኖሩ እንደነበርና ልጆቻቸው ከሲዳማ ተወላጆች ጋር በጋብቻ እንደተሳሰሩም ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ "መንግሥት ለሕይወታችን ዋስትና ሰጥቶን ወደ ቀያችን እንዲመልሰን እንፈልጋለን" ብለዋል።

አጭር የምስል መግለጫ በሲዳማ ዞን ግጭት እና ውጥረት ሰፍኖ የነበረባቸው ስፍራዎች

"ሦስት ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል፤ ሦስት ቤተክርስተያን ተዘርፏል"

በሀገረ ሰላም ወረዳ ስር የሚገኙ ሦስት አብያተ ክርስትያናት ላይ ሙሉ በሙሉ ቃጠሎ መድረሱን የሲዳማ ጌዲኦ አማሮ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቢ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ መርጊያ ለቢቢሲ ተናገረዋል።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም ተጨማሪ ሌሎች ሦስት አብያተ ክርስትያናት መዘረፋቸውንና ንዋየ ቅዱሳቶቻቸው መቃጠላቸውንም ተናግረዋል።

በቃጠሎ ሙሉ በሙሉ የወደሙ አብያተ ክርስትያናት ዶያ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን፣ ጌታማ ገብረክርስቶስ ቤተክስርስትያንና ጭሮኒ ቅዱስ አማኑኤል ቤተክርስትያን መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ መጋቢ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ ገልጸዋል።

"አዲስ አበባ የምንወዛገብባት ሳትሆን በጋራ የምንኖርባት ከተማ ናት" ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ

አሜሪካ ስደተኞችን ፍርድ ቤት ሳታቀርብ ወደመጡበት አገር መመለስ ልትጀምር ነው

ዘረፋ የተፈፀመባቸውና ንዋየ ቅዱሳቶቻቸው የተቃጠሉባቸው ሀገረ ሰላም ደብረ ገነት ቅዱስ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስትያን፣ ሎዳ ቅዱስ ገብርኤል እንዲሁም በንሳ ዳዬ ወረዳ ስር የሚገኘው ጭሬ አማኑኤል ቤተክርስትያን መሆናቸውን ሥራ አጅኪያጁ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ሦስቱ ቤተክርስቲያኖች ላይ ቃጠሎ የደረሰው አርብ ሀምሌ 12፣ 2011 ዓ. ም. መሆኑን የተናገሩት መጋቢ ጥበባት ቀሲስ ሞላልኝ፤ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስትያን ላይ ዘረፋ የተፈፀመው በነጋታው ቅዳሜ ሀምሌ 13፣ 2011 ዓ. ም. መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

በአገልጋዮች ላይ ድብደባ ስለመፈፀሙም መረጃ እንዳላቸው ጨምረው ገልፀው፤ "ጥቃቱ የደረሰው በተደራጁ ወጣቶች ነው ነው" ብለዋል።

በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስጊ ስለሆነ ጥቃት የደረሰባቸውን አብያተ ክርስትያናትን ሄዶ ለመመልከት እንዳልቻሉ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ካህናቱ ሸሽተው አላታ ወንዶ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን የደቡብ ክልል ባለስልጣናትን በተደጋጋሚ ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።