በባርነት ከመሸጥ የተረፉት 64 ኢትዮጵያዊያን

በ1888 በየመን የናህር ዳርቻ አቅራቢያ ከባሪያ ነጋዴዎች የተያዙት እና በሼክ ኦቶማን እንክብካቤ ሲደረግላቸው የነበሩ የኢትዮጵያ ሕፃናት Image copyright Sandra Shell
አጭር የምስል መግለጫ በ1888 በየመን የናህር ዳርቻ አቅራቢያ ከባሪያ ነጋዴዎች የተያዙት እና በሼክ ኦቶማን እንክብካቤ ሲደረግላቸው የነበሩ የኢትዮጵያ ሕፃናት

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር መስከረም 1888 ሮያል የባህር ኃይልን የሚያገለግለው ኤችኤምኤስ ኦስፕሬይ መርከብ፤ መቀመጫውን የመን ኤደን አድርጎ በቀይ ባህር ላይ ባካሄደው የፀረ ባርነት ዘመቻ ከኢትዮጵያ የባህር ዳርቻ የተነሱ ሦስት ጀልባዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

እነዚህ ጀልባዎች ከራሃይታ እና ታጁራ የተነሱ ሲሆን፤ 204 ወንዶችና ሴቶችን በአረብ ገበያ ለባርነት ለመሸጥ እየተጓዙ ነበር። ሕጻናቱ ከኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች፤ ከአሁኑ ኦሮሚያ ክልል የተወሰዱ ነበሩ።

ሕጻናቱ በርካታ መቶ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው ነበር ከባህር ዳርቻው የደረሱት። የፀረ ባርነት ዘመቻውን የሚመራው ቡድን እነዚህን ሕጻናት ከነጋዴዎች መንጋጋ ፈልቅቆ ካወጣ በኋላ በቀጥታ የወሰዳቸው ወደ ኤደን ነበር።

በዚያም ሕፃናትና ታዳጊዎቹ በፍሪ ቸርች ኦፍ ስኮትላንድ ሚሲዮን አማካኝነት በሼክ ኦትማን አስፈላጊው እንክብካቤ ሁሉ ተደረገላቸው።

ክልልነት ለጠየቀው ሁሉ ቢሰጥ ችግሩ ምንድነው?

ከ43 ዓመት በኋላ የተገናኙት ኢትዮጵያዊ እናትና ስዊድናዊ ልጅ

ጉዞው አካላቸውን አጣምኖ፣ መንፈሳቸውንም አዳክሞ ነበር። ወባና አስቸጋሪው የአየር ጠባይ እንኳን ለታዳጊ ባይተዋር ሕጻን ቀርቶ ለብርቱ የባህር ላይ ቀዛፊም ከባድ ነበር።

በ1890 ከሞት አፍ የተረፉት 64ቱ ኢትዮጵያዊያን ሕጻናት ደቡብ አፍሪካ በምሥራቃዊ ኬፕ በምትገኘው አሊስ ውስጥ ወደሚገኘው ፍሪ ቸርች ኦፍ ስኮትላንድ ላቭዳሌ ተቋም ተሸጋገሩ።

ከሕጻናቱ መካከል ሙስሊሞቹን የአካባቢው ማህበረሰብ በማደጎ ወሰዳቸው። በዚያው ዓመት መጨረሻ ላይ የአየር ጸባዩን ባለመቋቋምና በሌላም ምክንያት ከሕጻናቱ መካከል የ11ዱ ሕይወት አልፏል።

የመን እያሉ የስኮት ሚሲዮናዊያን ከባርነት ነፃ የወጡትን ሕጻናት መጠይቅ ይዘው ማነህ? ከየት ነሽ? ሲሉ ጠየቁ።

ዛሬ የእነዚህ 64 ሕፃናት ታሪክ በምሥራቃዊ ኬፕ በኮሪ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ተሰንዶ ይገኛል።

ይህንን ለህትመት ብርሀን ያበቃችው የታሪክ ተመራማሪዋ ሳንድራ ሼልስ (ዶ/ር) "ዘ ችልድረን ኦፍ ሆፕ" የተሰኘውን የምርምር ሥራዋን ባሳተመችበት መጽሐፍ ውስጥ ነው።

Image copyright SANDRA SHELL
አጭር የምስል መግለጫ ቶሎሳ ወዬሳ በላቭዴል

ቶለሳ ወዬሳ

ቶለሳ ወዬሳ የወዬሳና የሀታቱ ልጅ ነው። በባርነት ተሸጦ በየመን ቃሉን ሲሰጥ እድሜው 13 ተገምቷል። እትብቱ የተቀበረው ጊቤ ወዲያ ማዶ ጅማ፣ ቲባ እንደሆነ ሰነዶች ያሳያሉ።

አባቱ ብዙ ጋሻ መሬት የሚያርሱ የኮሩ ገበሬ ነበሩ። ሀያ በሬዎች፣ አስራ አምስት በጎችና ፈረሶችም ነበሯቸው።

ቶሎሳ በወቅቱ ከሰጠው ቃል መረዳት እንደሚቻለው አንድ ቀን በቤቱ አቅራቢያ እየተጫወተ እያለ ሦስት ሰዎች መጥተው ፈረስ አይቶ እንደሆን ጠየቁት። እሱም በቀና ልቦና፣ በትሁት አንደበት ፈረሱ በየትኛው አቅጣጫ እንደሄደ መለሰላቸው።

"በጎጃም ማርያም ቤተክርስቲያን ለመስጊድ 3ሺ ብር ረድታለች' ተባልኩኝ" ሐጂ ዑመር ኢድሪስ

ግን የጥርጣሬ ነፋስ ሽው አለው፤ ወዲያው የለበሰውን የቆዳ ልብስ ወርውሮ በቀጫጭን እግሮቹ ወደ ቤቱ መሮጥ ጀመረ። እግሮቹ የልቡን ያህል አልሮጡለትም፤ ሰዎቹ ደርሰው ያዙት።

አፉን በእጃቸው ግጥም አድርገው አፍነው፣ ወደ ጫካ ውስጥ ገቡ። እርሱንም፣ ቶሎሳንም የጫካው ሆድ ውጦ ዝም አለ።

ሰዎቹ ጎዳዋራቤሳ የሚባል አካባቢ ወስደው ለባሪያ ነጋዴ እንደሸጡት በወቅቱ በሰጠው ቃል ላይ ሰፍሮ ይገኛል። እነዚህ ነጋዴዎች ደግሞ ከሁለት ሳምንት ጉዞ በኋላ ቢሎ የሚባል ገበያ ወስደው አተረፉበት።

Image copyright Lovedale Collection
አጭር የምስል መግለጫ ቢሾ ጃርሳ

ቢሾ ጃርሳ- በበቆሎ የተለወጠችው ታዳጊ

በ1874 እንደተወለደች ተገምቷል፤ የ16 ዓመቷ ቢሾ። አባቷ ጃርሳ እናቷ ደግሞ ዲንጋቲ ይባላሉ። እናትና አባቷ በተመሳሳይ ወቅት ነው የሞቱት።

ከ1887-1892 በኢትዮጵያ ውስጥ ብርቱ ረሀብ ተከስቶ እንደነበር የታሪክ ሰነዶች መዝግበውት ይገኛሉ። ይህ ረሀብ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በበርካታ የአፍሪካ አገራት የተከሰተና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ነበር።

በወቅቱ በአገሪቱ በገባው ጽኑ ርሀብ ሰውም ከብትም አልቆ ነበር። የእነ ቢሾ ከብቶችም ከዘመኑ ክፉ እጣ አልተረፉም።

ቢሾ ወንድሞች አሏት፤ ሁለት። አባቷን የሞት ብርቱ ክንድ ሲነጥቃት የአባቷ ባሪያ የነበረ ግለሰብ ይንከባከባት ነበር [ያኔ ይሆን 'ቀን እስኪያልፍ የአባቴ ባሪያ ይግዛኝ' የተተረተው]።

ያኔ አገሩ ሁሉ በቸነፈር በተመታበት ወቅት ቢሾ ከሰዎች ጋር ወደ ገበያ ተላከች፤ ጎቡ የሚባል፤ ያው የሚላስ የሚቀመስ ፈላልጋ እንድትመጣ ነበር የታዘዘችው።

ምግብ ወሲብን የተሻለ ያደርጋል?

ገበያ ስትደርስ ታዲያ ለእነሱ እህል ለመሸመት እሷን በበቆሎ ለወጧት፤ በአካባቢው ነጋዴ የነበረ ግለሰብ ገዛት፤ በበቆሎ። ይህ ቀን የወጣለት ሲራራ ነጋዴ በየወቅቱ እዚህ አካባቢ እየተመላለሰ ልጆችን ለባርነት ይገዛል።

ቢሾ ተሸጣ ወራካላ ወደሚገኝ አንቻሮ የሚባል ስፍራ ተወሰደች። ከዚያም በርካታ ሕጻናትን ለባርነት ገዝተው ላከማቹ ሌሎች ነጋዴዎች ተሸጠች። እነሱ ደግሞ አዳል ለሚገኝ ሌላ ነጋዴ ሸጧት፤ ከዚያ በታጁራህ በኩል አድርገው ወደ ዳዌ ወሰዷት።

ያኔ ነው በጀልባ ጭነዋት ከሌሎች አምስት ጀልባዎች ጋር ባህሩ ላይ በመቅዘፍ ጉዞ የጀመሩት።

ነገር ግን ብዙ ርቀት አልሄዱም፤ አንዲት በቅኝት ላይ የነበረችና የጠበንጃ አፈሙዝ የደገነች ጀልባ ተመለከቱ። ሁለቱ ጀልባዎች ወዲያውኑ ቀኝ ኋላ ዞረው ተመለሱ። ከዚያም ያሳፈሯቸውን ሕጻናት አውርደው ለስድስት ሳምንት ያህል ተደብቀው ቆዩ። አገር አማን ብለው ባመኑበት ሰዓት ዳግም መቅዘፍ ጀመሩ።

በድጋሚ ያቺ አሳሽ ጀልባ አገኘቻቸው። ከሁለቱ በአንዱ ጀልባ ቢሾ ተሳፍራ ነበር። ከሁለቱም ጀልባ በሕይወት የተረፉት ወደ ኤደን ተወሰዱ።

በኤደንም ቃላቸውን የተቀበሏቸው ሚሲዮናውያን የቢሾን ታሪክ እንዲህ አስቀሩልን።

ቢሾና ቶሎሳ ምን ደረሱ?

ይህ ሁሉ የሆነበት ዘመን የሸዋው ንጉሥ፣ ንጉሥ ምንሊክ በሥልጣን ላይ የነበሩበት ዘመን ነበር። ንጉሥ ምንሊክ ከፈረንሳዮች መሣሪያ ለመግዛት እንዲያስችላቸው ገንዘብ በብርቱ ይፈልጉ ነበር። ለዚህም ግዛታቸውን አቋርጠው በባሪያ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችንም ሆነ በአገር ውስጥ ባሪያ ንግድ ላይ የሚሳተፉት ላይ ቀረጥ ጥለውባቸው ነበር።

በተሰበሰበው ቀረጥም ከፈረንሳይ መሣሪያ መሸመታቸው ሳንድራ ሼልስ በመጽሐፏ ላይ ጠቅሳለች።

በዚህ መካከል ታሪክ በሰነድ ያስቀመጠልን 64 ታዳጊዎች በባርነት ከመሸጥ ተረፉ። ከእነሱም ውስጥ ቢሻና ቶሎሳ ከሌሎች በመቶ ከሚቆጠሩ የእድሜ አቻዎቻቸው ጋር በመሆን በየመን የባህር ዳርቻ አቅራቢያ በብሪታኒያ የጦር ኃይል ከባሪያ ንግድ ነፃ ወጡ።

"ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው" አሊ ቢራ

በወቅቱ እንግሊዝ የባሪያ ንግድን ለማስቀረት ወስና ይህንንም የሚያስፈፅም ጦር በኮማንደር ጊሲንግ እየተመራ የቀይ ባህር የንግድ መስመርን ይቆጣጠር ነበር።

ቢሾ ጃርሳ በየመን የወደብ ከተማ በባርነት ከመሸጥ የብሪታኒያ ባህር ኃይል ከታደጋት በኋላ በቀጥታ የሄደችው ወደ ደቡብ አፍሪካ ነበር።

የመን የባህር ዳርቻ ላይ በባርነት ልትሸጥ ስትል የአፍ መፍቻዋ ኦሮምኛ ነበር፤ ጆሮዋን ቢቆርጡት ሌላ ቋንቋ አትሰማም።

Image copyright Sandra Shell
አጭር የምስል መግለጫ የቢሻ ጃርሶ የልጅ ልጅ ኔቪል አሌክሳንደር (ዶ/ር ) በ2008

በኋላ ግን እንግሊዘኛን ታቀላጥፈው ገባች። በርግጥ ኦሮምኛንም አልረሳችም። ወደ ደቡብ አፍሪካ ከሄደች በኋላ በሎቬዳሌ መምህርት ሆነች። በርግጥ መጀመሪያ የቤት ውስጥ ሥራ እንድትሠራ ነበር ስልጠና ያገኘችው። ነገር ግን ብርታቷን ያዩ ከአንዲት የአገሯ ልጅ ጋር መምህርነት አሰለጠኗት።

በ1911 ፍሬድሪክ ስቺፐርስ የተባለ አንድ ማኅበረ ምዕመናን ውስጥ የሚያገለግል ሰው አግብታ አራት ልጆች አፍርታለች።

ከቢሻ ልጆች አንዷ ዲምቢቲ ትዳር መስርታ ኒቬል አሌክሳንደርን ወለደች። የቢሻ የልጅ ልጅ ለደቡብ አፍሪካ ነፃነት የታገለ፣ ኔልሰን ማንዴላ በታሠሩበት የሮቢን ደሴት ላይ ለአስር ዓመታት ታስሯል።

ለደቡብ አፍሪካ ነፃነት ሲታገል ኢትዮጵያዊ ደም እንዳለው አያውቅም ነበር። ቆይቶም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ደም እንዳለው በተረዳ ጊዜ ደስታው ታላቅ እንደነበር በአንድ ወቅት ለቢቢሲ ገልጿል።

ቶሎሳ ወዬሳ ደቡብ አፍሪካ ከሄደ በኋላ በትምህርቱ ብርቱ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናም ሸጋ ውጤት ነበር ያስመዘገበው።

በወቅቱ ግን ትምህርቱን ከመቀጠል ይልቅ በአንግሎ ቦየር ጦርነት ወቅት (1899-1902) የብሪታኒያ ጦርን ተቀላቅሎ አገልግሏል። ነገር ግን በጦርነቱ ውስጥ ባየው ነገር አእምሮው ታወከ። በኋላም ከጦርነት ተመልሶ ከጅቡቲ ድሬዳዋ የባቡር መንገድ ሲገነባ በአስተርጓሚነት አገልግሏል።

ታሪኩን የመዘገቡ ጸህፍት በወቅቱ በእንግሊዝና በፈረንሳይ መካከል የነበረውን የበላይነት ፍላጎት በማቻቻል ጥሩ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራቱን መስክረዋል።

የቶሎሳ የልጅ ልጅ፤ ብሩክ ተረፈ ኑሮውን በካናዳ አድርጎ ይገኘኛል። አቶ ብሩክ ተረፈ በአሁኑ ሰዓት ዕድሜው 50ዎቹ ውስጥ የሚገመት ሲሆን፤ የእሱ የቅርብ ዘመዶች ደግሞ ኑሯቸውን በአዲስ አበባ አድርገው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

የጋዜጠኛዋ መገደል ለምን የዓለም መነጋገሪያ ሆነ?

የእነ ቢሾና የ64ቱ ሕጻናት ታሪክ ደቡብ አፍሪካንና ኢትዮጵያ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለመተሳሰራቸውን ቋሚ ምስክር የሆነ የኢትዮጵያ ግዙፍ ታሪክ አካል ነው።

ወደ ደቡብ አፍሪካ ከተወሰዱት 64 ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች መካከልም ወደ እናት ምድራቸው የተመለሱ እንዳሉም መረጃዎች ያሳያሉ።

ከባርነት ንግድ ከተረፉትና ደቡብ አፍሪካ ከነበሩት መካከል የሎቬዴል አስተዳደሮች ወደ አገራችው ለመመለስ ፍቃደኛ የነበሩትን 17 ኢትዮጵያዊያን፤ የጀርመን አማካሪዎች ከአፄ ምኒልክ ጋር ተነጋግረው በ1909 እኤአ ወደ ኢትዮጵያ መልሰዋቸዋል። ከነዚህ መካከል ጉዴ ቡልቻ፣ አማኑ ፊጎ፣ ድንቂቱ ቦኤንሳ፣ ፌእሳ ገሞ፣ ሊበን ቡልቱ ጥቂቶቹ ናቸው።

'አሰቃቂ' ተብሎ በሚጠራው አፍሪካውያንን እንደ እቃ የማጋዝ 'ባርያ ንግድ' እንግሊዝ ከፍተኛ ስፍራ ነበራት። በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ16ኛው ክፍለ ዘመን በተጀመረውና ከሁለት መቶ አመት በላይ በቆየው ንግድ ከአስር ሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ተሽጠዋል፤ ብዙዎችም ሞተዋል።

እንግሊዝ የባርያ ንግድን በህግ ከከለከለች በኋላም ለባርያ አሳዳሪዎቹ ሃያ ሚሊዮን ፓውንድ ካሳ ተከፍሏቸዋል።

አጭር የምስል መግለጫ የመጽሐፉ ሽፋን

ሳንድራ በአዲስ አበባ

"ዘ ችልድረን ኦፍ ሆፕ" የተባለውን የእነዚህን በባርነት የተጋዙ ኢትዮጵያዊያንን ታሪክ የጻፈችው ሳንድራ ሼልስ (ዶ/ር) ተወልዳ ያደገችው ዝምባብዌ ነው። በኋላም የዩኒቨርስቲ ትምህርቷን በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኬፕታውን ተከታትላለች። የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪዋን በታሪክ ትምህርት ተከታትላ አጠናቅቃለች።

ሳንድራ ሼልስ በዚህ ዓመት አዲስ አበባ ውስጥ በሚካሄደው 33ኛው የኦሮሞ ስተዲስ አሶሲየሽን (ኦሳ) ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ተሳታፊ እንደምትሆን የተሰማ ሲሆን፤ ከዓመት በፊት ለውጪው ዓለም አንባቢ የቀረበው መጽሐፏም ኢትዮጵያ ውስጥ በቡክ ወርልድ ታትሞ ለገበያ እንደሚቀርብ ተነግሯል።

የኦሳ ፕሬዝዳንት ኩለኒ ጃለታ፤ የዚህ ዓመት ጉባኤ በኦሮሚያ፣ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ያለመ መሆኑን ገልፃለች።

ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ባደረገችበት ወቅት እንደገለፀችው፤ ለዘመናት በወንዶች የበላይነት ይታወቅ የነበረው ማኅበሩን በሴቶችና በወጣቶች ለመተካት ዓላማ እንዳላትም ገልፃ ነበር።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ