በሞቃዲሾ ከንቲባ ቢሮ ላይ በተሰነዘረ የቦንብ ጥቃት ስድስት ሰዎች ተገደሉ

የሞቃዲሾ ከንቲባ አብዲራህማን ኦማር ኦስማን Image copyright Getty Images

በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ከንቲባ ቢሮ ላይ በተሰነዘረ የቦንብ ጥቃት ቢያንስ ስድስት ሰዎች ሞቱ። አጥፍቶ አጥፊዋ በሰነዘረችው ጥቃት የሞቃዲሾ ከንቲባ አብዲራህማን ኦማር ኦስማን ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ባለሥልጣኖች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ አጥፍቶ አጥፊዋ ራሷን በቦንብ ያጋየችው የከንቲባው ቢሮ ውስጥ የፀጥታ ስብሰባ እየተካሄደ ሳለ ነበር።

አል-ሸባብ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዶ፤ ኢላማ ያደረጉት አሜሪካዊውን የተባበሩት መንግሥታት ልዑክ ጄምስ ሳዋን እንደነበር አሳውቀዋል። ሆኖም ልዑኩ ጥቃቱ ከመድረሱ አስቀድሞ ከከንቲባው ጋር ተገናኛተው ከቢሮው ወጥተው ነበር።

በሞቃዲሾ ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር ከ270 በላይ ደርሷል

በሶማሊያ በአንድ ሆቴል ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 26 ሰዎች ሞቱ

የጋዜጠኛዋ መገደል ለምን የዓለም መነጋገሪያ ሆነ?

ሶማሊያ የተመድ መልዕክተኛን አባረረች

አጥፍቶ አጥፊዋ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠበቀውን የከንቲባ ቢሮ ቅጥር ጊቢ ውስጥ እንዴት ልትገባ እንደቻለች እስካሁን አልታወቀም።

አል-ሸባብ ከዚህ ቀደም በፈጸማቸው የአጥፍቶ መጥፍት ጥቃቶች ሴቶችን በብዛት አይጠቀምም።

በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈው አምስት ወንዶችና አንድ ሴት የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች እንደሆኑ የማስታወቂያ ሚንስትሩ ዳሂር ሞሀመድ ጌሌ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስጠባቂዎችና አሜሪካ ያሰለጠነቻቸው የሶማሊያ ወታደሮች በሞቃዲሾ ቢኖሩም፤ አል-ሸባብ የሶማልያን ማዕከላዊ መንግሥት ለማፍረስ በተደጋጋሚ ከተማዋ ውስጥ ጥቃት ሲሰነዝር ነበር።

ከአል-ቃይዳ ጋር ትስስር ያለው አል-ሸባብ፤ በተለይም በገጠሪቱ ሶማልያ በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀሳል።

ተያያዥ ርዕሶች