የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ 200 ሚሊዮን ችግኞች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ችግኝ ሲተክሉ

አርቲስት ደበበ እሸቱ በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር በነበረው አጭር ቆይታ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባዘጋጁት 'ገበታ ለሸገር' የእራት ግብዣ ላይ በሕንድ ተይዞ የነበረውን በመላ አገሪቱ ዛፍ የመትከል ክብረ ወሰን ለመስበር የሚያስችል ዘመቻ ለማካሄድ ማሰባቸውን እነሰለሞን ዓለሙ እንዳጫወቱት ይናገራል።

"ሕንድ 100 ሚሊዮን ዛፍ በመትከል ክብረ ወሰኑን ይዛለች። እኛ በመላ አገሪቱ ሁለት መቶ ሚሊዮን ችግኝ ለምን አንተክልም?" ነበር ያሉት። ያኔ ታዲያ ደበበ ሐምሌ 21/2011 ዓ. ም ይህንን ለማድረግ እንዳሰቡ ጨምሮ ተናግሮ ነበር።

ይህ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ ሀሳብ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ዕቅድ በአንድ ሰምሮ ሁሉም ዶማና አካፋውን እንዲሁም ችግኙን ይዞ በየቦታው ደፋ ቀና እያለ ነው።

የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ብሔራዊ የደን ልማት ንቅናቄ የችግኝ ተከላ እንደሚከናወንና ይህም ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ጳጉሜ ድረስ እንደሚዘልቅ አሳውቋል።

በዘንድሮው የክረምት ወቅትም 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ መቋቋሙ ተነግሮ ነበር።

ሁሉም ነገር ወደ...

ዛሬ ሐምሌ 22/2011 ዓ. ም በመላ አገሪቱ ሙሉ ቀን ዛፍ በመትከል ክብረ ወሰን ለመስበር ማለሙን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

በኦሮሚያ 126 ሚሊዮን፣ በአማራ 108 ሚሊዮን፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል 48 ሚሊዮን፣ በትግራይ ዘጠኝ ሚሊዮን ችግኞች ሊተከሉ እቅድ ተይዞ፣ ቦታ ተመርጦ፣ ጉድጓድ ተቆፍሮ መዘጋጀቱ ተነግሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በሁሉም ወረዳዎች 3 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችለው ዝግጅት መጠናቀቁን በምክትል ከንቲባው የትዊተር ገፅ ላይ አስፍሯል።

ምክትል ከንቲባው በአንድ ቀን ብቻ 1.5 ሚሊየን ጉድጓዶች መቆፈራቸውንም በመግለጽ "ለከተማችን ያለንን ፍቅር በሥራ ብቻ እናሳይ" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

"የአራዳ ልጅ ዛፍ ይተክላል" በትዊተር ላይ የተጀመረ ዘመቻ ነው። የዚህ ዘመቻ አስተተባሪዎች "ዛፍ መትከል ጤናን መገብየት ነው" በሚል በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ዛፍ ለመትከል ጥሪ እያቀረቡ ነው።

ሐምሌ 22 ቀን በአንድ ጀንበር 200 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ለተያዘው እቅድ 54 ሚሊየን ብር መመደቡንም የገለፀው ይህንኑ ዘመቻ የሚያስተባብረው ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ነው።

የዛፍ መትከል ዘመቻዎች

አቶ ሞገስ ወርቁ የለም ኢትዮጵያ የአካባቢና ልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ማኅበሩ ከተቋቋመ 28 ዓመት እንደሆነው ጠቅሰው፤ የማኅበሩ መስራቾች ዛፍ ከመትከል አስቀድሞ የሰው አእምሮ ላይ ጤናማ ችግኝ መትከል የተሻለ፤ የተራቆተውንና የተጎዳውን የአገሪቱን መሬት በደን ለመሸፈን ያስችለናል የሚል ጠንካራ እምነት እንደነበራቸው ይናገራሉ።

ይህንን ማኅበር የመሰረቱት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ ከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያዎች መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ወርቁ፤ እነዚህ የችግኝ ተከላ ዘመቻዎች ግንዛቤን በመፍጠር ረገድ የማይናቅ ሚና እንዳላቸው ይገልፃሉ።

የመልካ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሠለሞን ከበደ ድርጅቱ ከተመሰረተ ከ10 ዓመት በላይ እንዳስቆጠረ ተናግረው፤ በአገራችን አካባቢ ተጠብቆ መቆየት የቻለው ማኅበረሰቡ ለአካባቢ ባለው ባህላዊ እሴትና ጥበቃ ነው ብሎ እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

ይህ የማኅበረሰብ እውቀት ለአካባቢ እንክብካቤ አስተዋፅኦ ስላደረገ እውቀቱ መጠበቅ፣ እንክብካቤ ማግኘትና ማደግ አለበት በሚል ከሳይንሳዊ እውቀት ጋር በማዛመድ ዘላቂ ውጤት ማምጣት በሚያስችላቸው የተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ይናገራሉ።

ከዚህ ሥራቸው መካከል አንዱ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል የሚያከናውኑት የአካባቢ ልማት እንክብካቤ የችግኝ መትከልን ያጠቃልላል። አክለውም በአሁኑ ወቅት በዘመቻ የሚደረጉ የዛፍ ተከላዎችም ግንዛቤ ከመፍጠር አንፃር አስተዋፅአቸው ከፍ ያለ መሆንን ያስታውሳሉ።

ነገር ግን ክረምት በመጣ ቁጥር እየተነሱ ችግኝ መትከል ደግመን ልናጤነው የሚገነባ ጉዳይ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ሠለሞን፤ እንደ አገር ይላሉ "ፍኖተ ካርታ ያስፈልገናል ምክንያቱም የችግኝ ተከላ ከአንድ ዛፍ ተከላ ያለፈ ነው" ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ስላሉ ለዛፍ መጨፍጨፍ ምክንያት የሆኑት ተቋማት ዛፍ የመትከልና የመንከባከብ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ እነሱን ማሳተፍ ተገቢ መሆኑን ያሰምሩበታል።

"እንዲህ በዘመቻ ችግኝ መትከል አዲስ አይደለም" ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ የሚገኙት አቶ ከድር ይማም መሐመድ ናቸው።

በቀድሞው ወታደራዊ መንግሥትም ሆነ ኢህአዴግ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ዛፍ በዘመቻ መትከል የኖረ ባህል ቢሆንም፤ ከዚያ ይልቅ ማስተዋል የሚኖርብን የምንተክላቸው ችግኖች ምን ያህል ይፀድቃሉ? የሚለው ላይ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።

የአቶ ከድርን ሀሳብ የሚጋሩት በአምቦ ዩኒቨርስቲ የግብርና ኮሌጅ የተፈጥሮ ኃብት አያያዝ መምህርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በአፈር አጠባበቅ ላይ እየሠሩ ያሉት አቶ መሀመድ እንድሪያስ ናቸው።

እንደ አገር ለተለያዩ የተፈጥሮ ችግሮች መጋለጣችንን የሚጠቅሱት አቶ መሐመድም ሆኑ የለም ኢትዮጵያው አቶ ሞገስ ለዚህም ምክንያቱ የደን መመናመን መሆኑን ይጠቅሳሉ። ለዚህም መንግሥት አረንጓዴ ልማት በማለት በየዓመቱ ዛፍ መትከሉን በበጎ ያዩታል።

ጥያቄው ይላሉ አቶ መሐመድ፤ እንዴት ተደርጎ እየተተከለ ነው? የሚለው ነው በማለት የችግኝ ተከላው ላይ ያላቸውን ስጋት ይሰነዝራሉ።

አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የመሬት መራቆት፣ የአፈር መከላት፣ በብዛት እንደሚታይ አስታውሰው እነዚህ ሁሉ ችግሮች ከደን ሀብት መመናመን ጋር ተያይዞ የመጡ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

ታዲያ ከሚሌኒየም ጀምሮ በዘመቻ እየተከልን የአገሪቱ የደን ሽፋን መጠን አለመሻሻሉን የሚናገሩት አቶ መሐመድ፤ እንዲያውም "መረጃዎች የሚያሳዩት እየቀነሰ መሆኑን ነው" ይላሉ።

በ1990ዎቹ አካባቢ የአገሪቱ የደን ሽፋን መጠን 15 ሚሊዮን አንድ መቶ አስራ አራት ሔክታር ነበር የሚሉት መምህሩ፤ በ2000 ላይ 13 ሚሊዮን ሰባት መቶ አምስት አካባቢ መሆኑን በመጥቀስ፤ በ2010 ላይ አስራ ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ ዘጠና ስድስት፤ በ2018 ላይ ደግሞ አስራ ሁለት ሚሊዮን 147 ሔክታር አካባቢ ሽፋን መኖሩ ይጠቅሳሉ።

በየዓመቱ በዘመቻ እየተከልን የአገሪቱ የደን ሽፋን ግን ከመሻሻል ይልቅ መቀነስ ታይቶበታል። ስለዚህ የተተከለው እየፀደቀ ነውን? ብሎ መጠየቅ ያሻል ይላሉ።

አቶ ሠለሞንም የመምህሩን ጥያቄ የሚጋሩ ሲሆን፤ የመንግሥትን መረጃ በመጥቀስ የአገሪቱ የደን ሽፋን በአሁን ሰዓት ከ15 እስከ 20 በመቶ እንደሚሆንና የዘንድሮው ዘመቻ ከተሳካ ወደ 30 በመቶ ከፍ ይላል ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ያስቀምጣሉ።

የተከልነው እንዲፀድቅ. . .

ሐምሌ 22/2011 ዓ. ም 200 ሚሊዮን ዛፎችን ለመትከል መንግሥት ያለውን እቅድ ይፋ ሲያደርግ፤ በዚህ ክረምት ብቻ 4 ቢሊየን ችግኞችን እተክላለሁ ሲል ሁሉም ክልሎች ዘመቻውን በአንድ ድምፅ ተቀላቅለዋል።

ይህ በዘመቻ የሚደረግ ተከላ ግን የአምቦ ግብርና ኮሌጅ መምህሩን ምን ያህል ዝግጅት ተካሂዷል? የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓል።

ይህን ያህል ችግኝ ለመትከል፤ ያውም በአንድ ቀን ክብረ ወሰንን ከመስበር ባለፈ ሊነሱ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉበት በማስታወስ የጉድጓድ ዝግጅት፣ የተከላ ቦታ መረጣ፣ አስፈላጊ በጀትና የሰው ኃይል፣ የችግኝ መረጣ እና ማጓጓዝ ቀድሞ ከግንዛቤ ሊገቡ የሚገቡ ነገሮች ናቸው ይላሉ።

በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት የለም ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጁ አቶ ሞገስ፤ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።

"መትከል ዝም ብሎ ቁጥር ማስመዝገብ ብቻ አይደለም" የሚሉት አቶ ሞገስ፤ ተቋማት የሚተክሉት ችግኝ ቁጥር ተሰፍሮና ተቆጥሮ ስለተሰጣቸው ብቻ እሱን ለማሟላት መትከል ችግኙ እንዲያድግ አያደርገውም ይላሉ።

አንዳንዱ በዚህ ዘመቻ በመንግሥት መኪና፣ ከባልደረቦቹ ጋር በመሄዱ የደስታ ስሜት ውስጥ የገባ እንጂ የችግኝ መትከልን መሰረታዊ እውቀት ይዞ በሥፍራው አይገኝም ሲሉም ትዝብታቸውን ያጋራሉ።

ልክ እንደ አቶ ሠለሞን ሁሉ አቶ መሐመድም የተሳተፉባቸውን የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሮች በማስታወስ በዘመቻ ችግኝ መትከል ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ ለመትከልና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለማድረግ እንደማይረዳ ይጠቅሳሉ።

"አተካከላችን ሳይንሱን የተከተለ፣ በግንዛቤ እና በጥናት ቢሆን ውጤታማ እንሆናለን" የሚሉት አቶ ሠለሞን፤ የተተከሉባቸው ቦታዎች ላይ መልሶ መትከል፣ ያለ ባለሙያ እገዛ መትከል አዋጭ አለመሆኑን ያሰምሩበታል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በእሳቸው መታሰቢያነት የተተከሉ በርካታ ችግኞች፣ ሌላ ሥፍራ ከተተከሉት በተሻለ ጸድቀዋል ያሉት ደግሞ የአምቦ ዩኒቨርስቲው መምህር አቶ መሐመድ ናቸው። "ይህ የሚያሳየን ችግኝ ተከላው ተቋማዊ ቢሆን ውጤታማ እንደሚሆን ነው" ይላሉ።

ችግኝ ተከላ ሳይንሳዊ መንገድን መከተል አለበት በማለትም ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።

እስካሁን ድረስ የሚተከሉ ዛፎች በዘመቻ መሆናቸው ለአቶ መሐመድ ሳይንሳዊ መንገዶችን ስለመከተላቸው ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል። "በዘመቻ የሚተከሉ ዛፎች ላይ በቂ የሆነ የሰው ኃይል ማሰማራታችንን፣ በተገቢው ጥንቃቄ ማጓጓዛችንን እርግጠኛ መሆን አለብን" የሚሉት አቶ መሐመድ፤ ስለ አተካከሉም ተሳታፊዎች በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያስታውሳሉ።

ኢትዮጵያ የተለያየ አግሮኢኮሎጂ እንዳላት የሚያስታውሱት አቶ መሐመድ፤ ችግኞቹን ከመትከላችን በፊት ለተከላ ደርሷል ወይ?፣ ለሚተከሉበት አካባቢ አግሮኢኮሎጂ ተስማሚ ናቸው? የሚለው በሚገባ መስተዋል እንዳለበትም ይናገራሉ።

አገር በቀል ዛፎችን መትከል እጅጉን ተመራጭ ነው የሚሉት አቶ መሐመድ የችግኙ ቁመት፣ ከበሽታ የፀዳ መሆኑ ከግምት ቢገባ ለመጽደቅ በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ይላሉ።

በተጨማሪም የቦታ መረጣ ላይም ያላቸውን ስጋት ሲያነሱ፤ ዛፎችን የሚተከሉት ብዙ ጊዜ ማኅበረሰቡ በጋራ የሚጠቀመው መሬት ላይ በመሆኑ አርሶ አደሩ ከብቶቻቸውን ለግጦሽ የሚያሰማሩበት ስለሆነ የመጽደቅ እድላቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን የሚያነሱት አቶ መሐመድ፤ ይህ ደግሞ ግብርና እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑን ያስታውሳሉ። አዳዲስ የሚታረስ መሬት ፍለጋ አንዳንድ አካባቢ ተራራ የሚቧጥጥ፣ ደን የሚያቃጥል አርሶ አደር መኖሩን በማስታወስ የችግኝ ተከላው አርሶ አደሩን ያሳተፈ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ።

በገጠሩ ክፍል ከደን ሽፋን ይልቅ እርሻ መሬቶች እየተስፋፉ መሆናቸውን በማንሳት ከፊታችን የተደቀነው አደጋ አሳሳቢ ነው የሚሉት ምሁሩ፤ በተለይ የሰሜኑ የአገራችንን ክፍል ሲመለከቱ "ከተሞች በተሻለ አረንጓዴ ለብሰው ይታዩኛል" በማለት ብዙ ሥራ መሰራት እንዳለበት ያብራራሉ።

በጎጃምና በትግራይ እየተሠራ ያለው "ዊ ፎረስት" የተባለውን ፕሮጀክት እንደ መልካም ተሞክሮ መውሰድ እንደሚቻልም ያስቀምጣሉ። ፕሮጀክቱ የዛፍ ተከላን 'ጥምር እርሻ' የሚል ጽንሰ ሀሳብ በመጠቀም ከእርሻቸው ጎን ለጎን ለገበያ የሚሆኑ ምርት የሚሰጡ የዛፍ ችግኞችን አፍልቶ በማቅረብ ገበሬው በማሳው ውስጥ ተክሎ በገንዘብ እንዲጠቀም እግረ መንገዱንም የአካባቢ ጥበቃ ላይ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ያነሳሉ።

በችግኝ ተከላ ወቅት በርካታ ጥንቃቄዎች መደረግ አለባቸው የሚሉት አቶ ሞገስም ሆኑ አቶ መሐመድ ጉድጓዱ ከሁለት ሳምንት በፊት መዘጋጀቱን፣ አተካከሉም ላይ ችግኙን ከነላስቲኩ አለመትከልና ሥራቸው አለመታጠፉን እርግጠኛ መሆን አለብን ሲሉ ይመክራሉ።

የቦታ መረጣው በሚተከለው ችግኝ አይነት ይወሰናል የሚሉት አቶ መሐመድ፤ ለማገዶ፣ ለአፈር እቀባ፣ ለጥምር እርሻ፣ ለመኖ የሚተከሉ የዛፍ ችግኞች የት ቦታ ይተከሉ የሚለው በሚገባ መስተዋል እንዳለበት ይመክራሉ።

ለችግኞቹ የተዘጋጀው ጉድጓድ ውስጥም ውሃና ሌሎች ባዕድ ነገሮች አለመኖራቸውን ማረጋገጥና ከተተከለም በኋላ ውሃ እንዳይተኛበት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑና በአካባቢው ሥነ ምህዳር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የማያሳድሩ ዛፎች መተከል አለባቸው ያሉት ደግሞ የመልካ ኢትዮጵያ ዳይሬክተሩ አቶ ሠለሞን ናቸው።

የሚተከሉ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጡ መሆን አለባቸው በማለት፤ ንብ ማነብ የሚያስችሉ፣ ለከብት መኖ፣ መሬትን ለማልማት የሚሆኑ እና ለመኖና ለማገዶ የሚሆኑትን በመለየት መትከል ተገቢ መሆኑን ይመክራሉ።

የሚተከሉት ችግኞች ምን ውጤት እንደሚያስገኙ መታወቅ አለበት የሚሉት አቶ ሠለሞን፤ ይህን ማወቅ የሚተከልበትን ቦታ በመለየት ረገድ አስተዋፅኦ እንዳለው ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በርግጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕቅድ ሳካል?

አቶ መሐመድ ለዚህ ምንም ጥርጥር የላቸውም። ዓለም ላይ እንዲህ አይነት ተሞክሮዎች መኖራቸውን በመጥቀስ ጀርመናዊው የዘጠኝ ዓመት ታዳጊን የተከላቸውን 1 ሚሊዮን ችግኞች እንዲሁም ዋንጋሪ ማታይ በኬኒያ የተከሏቸውን 30 ሚሊዮን ችግኞችን በማንሳት ሊሳካ እንደሚችል ይናገራሉ። ነገር ግን ቅድመ ዝግጅቶች ወሳኝ መሆኑን አበክረው የሚናገሩት ጉዳይ ነው።

የለም ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ እንደሚሉት፤ ለቀጣይ አስር ዓመት የትኛው ችግኝ የት ቦታ ይተከል? የሚለውን አጥንተው ቢተከል ይሻላል በማለት በአንድ ጊዜም አገሪቷን በአጠቃላይ በደን አለብሳለሁም ብሎ መነሳት ስህተት መሆኑን ያስረዳሉ።

ቀስ በቀስ ሊሳካ የሚችል ግብ ማስቀመጥ፣ ሥራዎችን እያጠናከሩ ከስህተት እየተማሩ ለመሄድ ያስችላል በማለትም ምክራቸውን ይለግሳሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ዘመቻ ስኬታማ ለማድረግ ዛፍ በመተከል ኃላፊነት ያላቸውን ዘርፎች በሙሉ ወደ ሥራው ማምጣት ያስፈልጋል የሚሉት ደግሞ የመልካ ኢትዮጵያ ዳይሬክተሩ አቶ ሠለሞን ናቸው። ኢትዮጵያ ያለው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ከዘርፉ ተቋማት ጋር ያልተያያዘ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህም ውጤታማነቱ ላይ ወገቡን እንዲያዝ ያደርገዋል በማለት ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

"ዛፍ ተከላ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ ነው" የሚሉት አቶ ሠለሞን መጀመሪያ መሆን ያለበት ዓላማን ግልፅ አድርጎ ማስቀመጥ መሆኑን ያስረዳሉ።

"አንድ የጋራ ብሔራዊ ራዕይ ያስፈልገናል" በማለትም ብሔራዊ ራዕዩን ለማሳካት ግልፅ ያሉ ስልቶችንና ግቦች እንደሚያስፈልጉም ያስታውሳሉ።

ዛፍ ከሚቆረጥበት ዘርፍ አንዱ ግብርና መሆኑን በመጥቀስ፤ ግንባር ቀደሙ ዛፍ ተካይ ተቋም መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ። ግብርና ከዛፍ ተከላ ጋር በፕሮግራሙ ውስጥ ካልተቀናጀ፣ "የግብርና ሥራን በየቦታው እንደምንከታተለው የዛፍ ተከላንም ጎን ለጎን ካልተከታተልነው የችግኝ ተከላ ጥረታችን በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው" ይላሉ።

አንድ ባለ ሀብት 100 ሺህ ሄክታር አለማለሁ ሲል፣ መቶ ሺህ ሔክታር ደን ይቆርጣል የሚሉት አቶ ሠለሞን፤ ባለሀብቱ ይህንን እንዴት ነው የሚያካክሰው? ሲሉም ይጠይቃሉ።

ግብርናው መስኖ አለማለሁ፣ የአፈር መሸርሸርን እከላከላሁ የሚል ፕሮግራም ካለው ደን ተከላ ውስጥ መግባት አለበት በማለት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የችግኝ ተከላ ዘመቻ ውጤታማ ለማድረግ መወሰድ ስላለባቸው ዘርፈ ብዙ ምላሾች ያስረዳሉ።

ሌላው ደን የሚጨፈጨፍበት ዘርፍ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫዎች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ሠለሞን፤ ግድብ ያለበትን አካባቢ በደን በመሸፈን ውሀ እንዲመነጭ ማድረግ፣ ትነትን መቀነስ፣ ወደ ግድቡ የሚገባውን ደለልም መቀነስ ይቻላል ይላሉ።

ግልገል ጊቤ ሦስትን ብንወስድ ይላሉ አቶ ሠለሞን ሀሳባቸውን በምሳሌ ሲያስረዱ፣ ውሀ የሚንጣለለው 150 ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ፣ 140 ሜትር ከፍታ ላይ መሆኑን በማስታወስ 150 ኪሎ ሜትር በአጠቃላይ ወይ ደን የነበረበት አልያም ሸለቆ የነበረ መሆኑን ማስታወስ እንደሚገባ ይናገራሉ።

የሕዳሴ ግድብም ቢሆን ውሀው የሚጠራቀምበት ቦታ ደን የነበረበት ቦታ ነው የሚሉት አቶ ሠለሞን "ስለዚህ ውሀው የሚተኛበትን ዙሪያ በደን እንዲሸፈን ካላደረግን አንደኛ የተቆረጠው ደን የውሃ አቅርቦቱን ይቀንስበታል። በዙሪያው ችግኝ ብንተክል ግን ሃይድሮ ፓወሩ ከውሀ ተፋሰሱ ዙሪያ ውሀ ያገኛል፤ በዚያውም ወደ ግድቡ የሚገባው ደለል ይቀንሳል" በማለት በአንድ ድንጋይ በርካታ ወፍ መምታት እንደሚቻል ያስረዳሉ።

አቶ ሞገስ በአቶ ሠለሞን ሀሳብ በመስማማት በርግጥ አሁን ያለው የኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥ በውሀ እጥረት የተፈጠረ ብቻ ሳይሆን ግድቦች በደለል በመሞላታቸው ጭምር ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ በግድቦች ዙሪያ ያለውን የደን ሽፋን ማሳደግ እንደሚገባ ያስረዳሉ።

አቶ ሠለሞን የመንገድ ግንባታውንም በማንሳት በከተማም ሆነ በገጠር መንገዶች ሲገነቡ ትልልቅ ዛፎች ተገንድሰው መሆኑን ይናገራሉ። ይህ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ከመንገዱ ግራና ቀኝ የዛፍ ተከላ ፕሮግራምን ማካተት መቻል አለበት ሲሉ እያንዳንዱ ልማት ከዛፍ ተከላ ጋር መተሳሰር እንዳለበት ይጠቅሳሉ።

የቤቶች ግንባታም በደን ላይ ተጽእኖ አለው የሚሉት አቶ ሠለሞን "የቤቶች ልማት በከተማ ውስጥ ዛፍ ቆርጦ ቤት ከሠራ፣ በሚሠራቸው ቤቶች በረንዳዎች አገር በቀል ዛፍ እንዲተክል በሕግ ማስገደድ ይቻላል" በየሰፈሩ ውስጥ በሚሠሩ መንገዶች ግራና ቀኝ ዛፍ እንዲተክልም በሕግ ማስገደድ እንደሚገባ ይገልፃሉ።

የማበረሰብ ተሳትፎ

እስካሁን ድረስ በታየው ይላሉ የአምቦ ዩኒቨርስቲው አቶ መሐመድ፤ ችግኝ መትከል ላይ ምንም ችግር እንደሌለ ጠቁመው ከተተከሉ በኋላ ግን መጠበቁ ላይ ድክመት እንዳለ ያስረዳሉ።

ላለፉት 10 ዓመታት ችግኝ ተክሎ የደን ሽፋን ከመጨመር ይልቅ መቀነስ የታየው መንከባከብ ላይ ችግር ስላለ ነው የሚሉት መምህሩ፤ "ችግኝ ማለት ልጅ ነው በማለት እንዲፀድቅ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት እንክብካቤ ይፈልጋል" ይላሉ።

ችግኝ ለማፍላትና ለመትከል የሚወጣው ጉልበት፣ ገንዘብ ያህል ለእንክብካቤውም ማውጣት እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተው የሚናገሩት አቶ መሐመድ፤ በኃላፊነት እና በተጠያቂነት የሚመራና በየክልሉ የፀደቁትን የሚከታተል ተቋም መኖር እንዳለበት ያሰምሩበታል።

የመልካ ኢትዮጵያው አቶ ሠለሞን በበኩላቸው በአንዳንድ ግምቶች ይህ የመንግሥት ተነሳሽነት 548 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይንም 16 ቢሊየን ብር ገደማ ያስፈልገዋል መባሉን መስማታቸውን ጠቅሰዋል።

"ይህንን ያህል በጀት አለ ወይ?" ብለው በመጠየቅ የመንግሥትን ሸክም ለመቀነስ ችግኝ መትከልን የተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ ኢንቨስትመንቶች፣ እንዲወጡት ቢደረግ በበጀት ረገድም የራሱ ሆነ እፎይታ እንደሚኖረው ይናገራሉ።

አክለውም የሚተከለው ደን ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ከሆነ ማኅበረሰቡ ለሚያገኘው ጥቅም ሲል እየተንከባከበ ስለሚያሳድገው ሕዝብ አሳታፊ ስልትን ነድፎ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ የእንክብካቤ ወጪንም ይቀንሳል የሚሉት አቶ ሠለሞን፤ መንግሥት ጫናውን ለሌሎች ማካፈል እንዳለበት ይመክራሉ።

አቶ መሐመድ በበኩላቸው የተተተከሉትን ችግኞች ለተከታታይ ሦስት ዓመት መንከባከብ ካልተቻለ አሁን የወጣውን ጉልበትና ገንዘብ ውሃ በልቶት እንደሚቀር ያሳስባሉ።

አቶ ሞገስና አቶ ከድር በበኩላቸው የኃይማኖት ተቋማት የማኅበረሰብ ተሳትፎን በማረጋገጥ ረገድ ያላቸው ሚና ቸል መባል እንደሌለበት በማስታወስ፤ ተቋማቱ በአስተምህሯቸውም ሆነ በእስከ ዛሬ ልምዳቸው ዛፍን መንከባከብ፤ በተለይ የአገር በቀል ዛፎችን ጠብቆ በማቆየት ምስክር ስለሆኑ ከእነሱ ጋር መሥራት ዘላቂ ጥበቃ ላይ አስተዋጽኦ እንዳለው ያስታውሳሉ።