"እማማ አንቺ በሌለሽበት ደስ አይለኝም አለኝ" የኢዛና እናት

ኢዛና ሐዲስ Image copyright Ezana Haddis

ባለፈው ሳምንት ከማንችስተር ዩኒቨርስቲ በፕላኒንግና ኢንቫይሮንመንታል ማኔጅመንት ፒኤችዲውን ያገኘው ኢዛና ሐዲስ ለምረቃ በዓሉ ክብሩም ሆነ ፀጋው የቤተሰቡ በተለይ የእናቱ በቦታው ላይ መገኘት ነበር።

በህይወቱም ሆነ በትምህርቱ ከሱ በላይ መስዋእትነት የከፈሉለትን እናቱን የምረቃ ጋወኑን አልብሶ ፎቶ ማንሳት ዋና አላማው ነበር። የጋወኑ ምልክትነት ደፋ ቀና ብለው ያሳደጉት፣ እዚህ ቦታ ላይ ለመድረስ ከሱ በላይ እሳቸው መስዋዕትነት ከፍለዋል ለሚላቸው እናቱን ማእረጉ ለሳቸው እንደሚገባ ማሳየት ነበር።

ከተማ ይፍሩ፡ ያልተነገረላቸው የአፍሪካ አንድነት ባለራዕይ

"እናቴ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍላለች ሰላሳ አመት ልብስ ስትሰፋ ነበር። ጀርባዋ (ስፖይናል ኮርዷ) ተመዛብሏል። የከፈለችው መስዋዕትነት በቃላት የሚነገር አይደለም። ከኔ በላይ ትልቁን መስዋዕትነት የከፈለችው እሷ ናት" ይላል።

ነገር ግን ብዙ ሳይጓዝ አላማውን የሚያጨናግፈው ጉዳይ ተከሰተ። በልጃቸው ምርቃት ለመገኘት አስበው የነበሩት እናትና አባቱ ቪዛ ተከለከሉ።

በምርቃቱ ላይ የእናቱን አለመገኘት ሊቀበለው ያልቻለው ኢዛና ጉዳዩን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ በመውሰድ "እናቴ ካልመጣች የምርቃት በዓሉ ላይ አልገኝም" አለ።

ትምህርት ላይ ጠንካራ አቋም የነበራቸው እናቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ በኢዛና ቃል 'ፈንድቶ' ትምህርቱን አቋረጠ። ፎቶ ማንሳት እንደሚፈልግ ቢናገርም እናቱ ሊዋጥላቸው አልቻለም፤ በጭራሽ መስማት አልፈለጉም "መማር አለብህ ብላ አስገደደችኝ" ይላል።

በሌላቸው አቅም ገንዘብ ከፍለው ትምህርት ቤት የላኩትም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ማየት ህልማቸው ስለነበር እንደሆነ ኢዛና አበክሮ የሚናገረው ጉዳይ ነው።

“በአሁኗ ኢትዮጵያ በፀረ ሽብር ሕጉ ክስ መኖር የለበትም” ዳንኤል በቀለ

እንዲያው ኢዛና የእናቱ ነገር ስለሚያንሰፈስፈው ነው እንጂ አባቱም "ጫማ ምናምን ለመግዛት ብዙም ፍላጎት የለውም፤ ለመጻሕፍ ከሆነ ግን ግዛ ያልኩትን ይገዛልኝ ነበር" ይላል።

እናም ቤተሰቦቹ አይመጡም ሲባል ልቡ ተሰበረ። ከዚህ በፊት ለአራት ጊዜ የተመረቀው ኢዛና መመረቁ ብርቅና ድንቅ አይደለም፤ ነገር ግን ለቤተሰቦቹ ትልቅ ደስታ መሆኑንም በማወቁ ነው።

የማስተርስ ትምህርቱን በኧርባን ማኔጅመንትና ዴቨሎፕመንት ከሮተርዳም ዩኒቨርስቲ ያገኘው ኢዛና መጋቢት ወር ላይ የፒኤችዲ 'ዲፌንሱን' (ቫይቫ) ጨርሶ ደስታውንም አጣጥሟል።

የምርቃት ፕሮግራም ለቤተሰቦቹ በተለይም ለእናቱ ምን ማለት እንደሆነ ስለገባውም ያለመገኘታቸው ጉዳይ ለሱ ብቻ ሳይሆነ ለቤተሰቡ በተለይ ለእናቱ ወ/ሮ ሮማንም ከፍተኛ ሐዘንን ፈጥሯል።

ቢቢሲ ባናገራቸውም ወቅት ድምፃቸው ሐዘናቸውን በሚያሳብቅ መልኩ "በመከልከሌ በጣም አዝኜያለሁ፤ እኔ እዛ ሄጄ የምቀርበት መንገድ የለኝም፤ እድሜየም ትልቅ ነው፤ ኑሮየም ራሴን የቻልኩኝ ነኝ፤ ችግር አልነበረብኝም፤ አሳዘኑኝ፤ በጣም ነው ያዘንኩት፤ እኔ መገኘት እፈልግ ነበር፤ እንድገኝ አላደረጉኝም" ብለዋል።

ዱባይ ብዙ ጊዜ ተመላልሰው የሚያውቁት እናቱ በእንግሊዝ ኤምባሲ በጭራሽ ይከለከላሉ ብለው አላሰቡም፤ ከፍተኛ ኃዘን ቢሰማቸውም ዋናው ነገር የልጃቸው መመረቅ ነው "ልጄ እንኳን ተመረቀ" ይላሉ።

Image copyright EZANA HADDIS

የአፍሪካውያን ህመም- ቪዛ

በቅርቡ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው እንግሊዝ ከሌሎች አገራት በበለጠ አፍሪካውያንን በእጥፍ ቪዛ እንደምትከለክል የሚያሳይ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ አባላት ባጠኑት ጥናት አፍሪካውያን ላይ ያለው የቪዛ አሰጣጥ ስርአት የተሰበረና የዩናይትድ ኪንግደምና የአፍሪካ ግንኙነትንም የሚያበላሽ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

አፍሪካውያን ላይ ከፍተኛ መድልዎ በሚፈፀምበት በቪዛ አሰጣጥ ስርአት ላይ፤ አፍሪካውያን ሙሉ ወጪያቸውን የሚከፍልላቸው ስፖንሰር ቢኖራቸውም ባንካቸው ውስጥ "በቂ ገንዘብ የለም በሚል ሁኔታ እንደሚከለከሉም ያሳያል።

የኢዛና ቤተሰቦችም አፍሪካዊነታቸው፣ ኢትዮጵያውነታቸውና ጥቁርነታቸው በዚሁ የእንግሊዝ ፖርላማ አባላት "በተሰበረ የቪዛ አሰጣጥ" ስርአት ውስጥ እንደሚጥላቸው ኢዛና በበኩሉ በማሰብ የባንክ ማስረጃ፣ ከቤት አከራዩ ፍቃድ፣ ከትምህርት ቤቱ የድጋፍ ደብዳቤ አስገብቷል።

ካለው ልምድ በመነሳትም ሙሉ ቀን ወስዶ ሁሉን ነገር በጥንቃቄ ቢሞላም የቪዛ ጥየቃ ውድቅ ሊሆንበት የሚችል እድል እንዳለ በማሰብም ወደ ቪዛ ማዕከሉ ከመግባታቸው ከአንድ ቀን በፊት ለናቱም ደውሎ ተስፋቸው ከፍ እንዳያደርጉ ነግሯቸዋል።

"ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው" አሊ ቢራ

የቪዛ ፎርሙን የሞላችው የኢዛና እህት ፌቨን ሐዲስ ከኢዛና ዶክመንቶች በተጨማሪ የቤት ካርታ፣ የጭነት ተሳቢ መኪና ያው ተመልሰው እንደሚመጡ በማስረጃነት ለማሳየት አያይዛ ነበር።

ፌቨን ከቤተሰቦቿ እድሜ፣ ካላቸው የገንዘብ አቅም (ፋይናንሻል ስታተስ) እንዲሁም አባትየው ውጭ አገር ተምረው ከመምጣታቸው አንፃር ይከለከላሉ የሚል ግምት አልነበራትም።

ከቪዛ ማእከሉ ከወጡ በኋላም መኪና ውስጥ ተረጋግታ ስታየው ማመን እንዳቃታት ትናገራለች። "ሁለት ሶስት ጊዜ ማየት ነበረብኝ፤ ማመን ነው ያቃተኝ" ትላለች።

ለኢዛና የቪዛ መከልከሉ ጉዳይ ከቤተቦቹ በላይ መዋቅራዊ ነው በሚለው አሰራር አብረውት የተማሩት አሜሪካውያንና አውሮፓውያን ጓደኞቹ ቤተሰቦቻቸውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመጋበዝ ቀላል መሆኑ የሚያብሰለስለው ጉዳይ ነው።

"አሁንም እንደ ዱሮው ታላቅ አገር፣ ታላቋ ብሪታንያ ብለው ነው የሚያስቡት፤ ለዛም ነው የውጭ ጠል ፖሊሲዎች ያላቸው። የብሬግዚት ችግራቸውም እሱ ይመስለኛል" በማለት ይናገራል።

በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ የሚያበሳጨው እንግሊዝም ሆነ ብዙ የአውሮፓ አገራት የተገነቡበት መንገድ በተበዘበዘ በአፍሪካውያን ጉልበት፣ በቅኝ ግዛት መሆኑን ሲያስበው ነው።

"አገራቸውን የገነቡት ከአፍሪካውያን በተሰረቀ ሀብት (ሪሶርስ) ነው፣ በአፍሪካውያን ደምና ላብ ነው" በማለት ትችቱን ይሰነዝራል።

የቤተቦቹ መከልከል እንደ አንድ ምክንያት ይሁነው እንጂ ይህንን ሁሉ ስርአታዊ ጭቆናም ለመቃወም ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው የምርቃት ፕሮግራሙ ላይ እንደማይገኝ አቋም የወሰደው።

ጉዳዩ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም ትዊተር በመሄዱ ብዙዎች በቪዛ አሰጣጡ ስርአት ላይ ኢትዮጵያውያን የሚያልፉበትን "አሳፋሪ አካሄድ" ተችተዋል።

በተለይም ታዋቂው ገጣሚ ለምን ሲሳይ በብሎጉ ላይ 'እናትህ ለምረቃህ ስትከለከል' በሚል ርዕስ ስለ ኢዛና አስተዳደግ፣ የኢዛናን ስኬት፣ የትምህርት ዝግጁነቱንና የእንግሊዝን የቪዛ ስርአት 'ኢ-ፍትሐዊ' ሲልም ኮንኖታል።

ኢዛናም አገሩ ተመልሶ "ጥሬ ስጋየንና ጠጄን እየጠጣሁ" ከቤተሰቦቹ ጋር አብሮ ለመደሰትም ቀጠሮውንም ያዘ፤ በወቅቱም ለናቱ ምርቃቱ ላይ እንደማይገኝ ነገራቸው።

እናቱስ ምን ተሰማቸው? ወ/ሮ ሮማን በሐዘን በተሰበረ ድምፃቸው "ምክንያቱም እናቴ ከሌለች አልገኝም፤ እኔ ምንም ችግር የለም" አልኩት እሱ ግን በምላሹ "ማማ አንቺ በሌለሽበት እኔ ደስ አይለኝም አለኝ" በማለት ይናገራሉ።

"ኢትዮጵያዊነቴን ያገኘሁት ሙዚቃ ውስጥ ነው" አቨቫ ደሴ

የለምን ሲሳይ በጉዳዩ ጣልቃ መግባት እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በነበረው ጫና ውሳኔው ተቀልብሶ የቪዛቸው ጉዳይ እንደገና እንዲታይ ተወሰነ።

የቪዛውን ጉዳይ የሚከታተል ባለሙያ ከደቡብ አፍሪካ በደወለለት ወቅትም ኢዛና በጣም ተናዶ ስለነበር በኃይለ ቃል ተናግሮታል።

"እናቴን ደስታዋን ስለነጠቃችኋት በጣም አመሰግናለሁ። የሰባ አመት አዛውንቶች እዚህ አገር ምን ሊሠሩ ይቀራሉ ብላችሁ ነው ያሰባችሁት? ቤት ያላቸው፣ ንብረት ያላቸው፣ ልጆች እንዲሁም የልጅ ልጆች ያላቸው እዚህ አገር መጥተው በሳይክል 'ፉድ ደሊቨሪ' ሥራ እንዲሰሩ ነው?"

በተለይም ለኢዛና ያልተዋጠለት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት መደበኛ ያልሆነ (ኢንፎርማል) ኢኮኖሚ በተንሰራፋባቸው ቦታዎች የንግድ ግብይይቶች የሚፈፀሙት እጅ ለእጅ ገንዘብ መሆኑን አፍሪካ ውስጥ ተቀማጭነቱን ያደረገ የቪዛ ባለሙያ አለመረዳቱ ግራ የሚያጋባ ነው።

የባንክ አገልግሎት እንደ አውሮፓውያኑ ባልዳባረበት ሁኔታ የቪዛ አሰጣጥ ስርዓቱ የምዕራቡን የንግድ ሥርዓት ማዕከል በማድረግ ግለሰቦች ባንክ ውስጥ ባስቀመጡት የገንዘብ መጠን በቂ ነው አይደለም ተብለው መከልከላቸው ተገቢ እንዳልሆነም ለግለሰቡ አስረድቷል።

ግለሰቡም አንዳንድ ጥያቄዎች ኢዛናን ከጠየቀው በኋላ ስህተት መሆኑ እንደገባቸው፤ እንዲሁም ለምርቃቱ ሊደርሱ እንደሚችሉ ነገረው።

"የደወሉበት ምክንያት ለምን ሲሳይ በፃፈው ፅሁፍ ምክንያትና ፌስቡክና ትዊተር ላይ ብዙ ሰዎች ስለተጋሩት ነው። ስማቸው በመጥፎ እንዳይነሳ ያደረጉት ነው" ይላል።

ይህም ሁኔታ ምረቃ ፕሮግራሙ ላይ አልገኝም የሚለውን ውሳኔውን አስቀልብሶ ለምርቃት ጋወኑ አምሳ ስድስት ፓውንድ ከፍሎ ለመገኘት የወሰነው።

ፌቨንም ሁለተኛ ፓስፖርታቸውን አስገቡ በተባለበትና በምርቃቱ ቀንም መካከል የነበረው ልዩነት ጥቂት በመሆኑ ተጣድፋ ፓስፖርታቸውን መልሳ አስገባች።

በሁለተኛውም ቪዛውን እንደሚያገኙ በጣም እርግጠኛም ስለነበሩ በረራው እስከ መጨረሻው ቀን ማክሰኞ ሐምሌ 9፣2011 ዓ. ም እንደተያዘ፤ እዛም ሲደርሱ የሚቀበላቸው የታክሲ አገልግሎት፤ ዶሮውንም ሌላውንም ምግብ ተዘጋጅቶ እየጠበቁ ነበር።

ነገር ግን እስከ መጨረሻ ሰዓት ድረስ ቢጠብቁም ለምርቃቱ ቀን ሐምሌ 10፣2011 ዓ. ም ፓስፖርታቸው ሳይደርስ ቀርቷል።

Image copyright EZANA HADDIS

የኢዛና አስተዳደግ

"የምወደው ልጄ ነው፤ ሌሎችም ልጆች አሉኝ ግን ኢዛና የመጨረሻ ልጄ ነው። እሱም ይወደኛል፤ እኔም እወደዋለሁ። በጣም ነው የሚወደኝ" ይላሉ ስለ ልጃቸው ወ/ሮ ሮማን።

የኢዛና ምርቃት ላይ ባለመገኘታቸው ልባቸው እንደተሰበረ የምትናገረው ፌቨን "ምክንያቱም ኢዛና ከነበሩት የጤናና የአስተዳደግ እክሎች የተነሳ፤ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ ማየት በጣም ትልቅ ነገር ነው" ትላለች።

ከአስራ አንድ አመቱ እስከ 27 አመቱ 'ኤፕለፕሲ' በተለምዶ የሚጥል በሽታ ምክንያት አስተዳደጉ ቀላል አልነበረም። ኢዛና በፌስቡክ ገፁ እንዳሰፈረው በመጀመሪያ አካባቢ በማይጥለው የኤፕለፕሲ አይነት ለጥቂት ሰኮንዶች በቀን 30 ጊዜ ያህል በመፍዘዝ ይቸገር ነበር።

በመካነ እየሱስ ሚሽነሪ አንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት የተወሰኑ የክፍሉ ተማሪዎች ይስቁበት እንዲሁም ባስ ሲል ስድብም እንደነበር ያስታውሳል።

"አንዳንዶቹም ይሰድቡኝ ነበር፣ ዘገምተኛ፣ ፉዞ፣ ወዘተ" በማለት ፅፏል።

በማኅበረሰቡ ካለው እምነት ጋር ተያይዞ ህመሙ ከሰይጣን፣ እርግማን፣ መተት ጋር መያያዙ በተለይም አደግ ሲል ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳል። የነበረውን ሁኔታ በራሱ አንደበት እንዲህ ይገልፀዋል።

"ትንሽ ከፍ ስል 15 ዓመቴ አካባቢ ከመፍዘዙ ባሻገር የሚጥለው አይነት ኤፕለፕሲ ይከሰትብኝ ጀመር፤ ያኔ የሰፈር ሰው ማወቅ ጀመረ። እናቴንም ሰው ማግኘት እስኪያስጠላት ድረስ በሰይጣን እንደተለከፍኩ ይነግሯት እና ያስከፏት ነበር።"

"እድለኛ ነኝ" የሚለው ኢዛና እናቱም ሆነ እህቱ እንደ ማንኛውም ህመም ስላዩት ህክምናም አግኝቷል።። መድኃኒቱን በትክክል ከመውሰድ በተጫማሪ ትልቅም ሲሆን የኑሮውን ዘዬ በማስተካከል መጠጥ በደረሰበት ደርሶ አያውቅም።

"መጠጥ ከነጭራሹ አልጠጣም ነበር፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጓደኞቼ ለዚህ ነበር ካንትሪ ወይም ቼጉቬራ ውሐ ይዤ ስጨፍር የነበረው" በማለት አስፍሯል።

ቤተሰቦቹም ሆነ የኢትዮጵያ ኤፕለፕሲ ማህበር ያደረገለትን አስተዋፅኦ የማይረሳው ኢዛና መፍዘዝም ሆነ መጣል ካጋጠመው ስምንት ዓመት አለፈው።

ያ ሁሉ አልፎ ዶክትሬቱን ከሰሞኑ የተቀበለው ኢዛና ቤተሰቡ ባይገኝም ምርቃት ፕሮግራሙ ላይ ጓደኞቹ ተገኝተው ነበር። ማንችስተር ውስጥ የሚገኘው ሁልጊዜም የሚያዘወትሩት የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ልዩ ድግስ በማዘጋጀት፣ ኬክ ቆርሰዋል፣ በሻምፓኝ ተከፍቶላቸዋል፤ በጭፈራም ተደስተዋል።

እናቱም ሳይወዱ በግድ የምርቃት ፕሮግራሙ በቀጥታ ስርጭት በመከታተል የልጃቸውን ምርቃት በትንሹ ለመቋደስ ሞክረዋል።

"ልጄ እንኳን ተመረቀ፤ ዝግጅቱም በጣም የሚያስደስት ነው፤ እንዲያው ብገኝ ደስ ይለኝ ነበር" በማለት ወይዘሮ ሮማን የነበረውን ሁኔታ ይናገራሉ።

ኢዛናም ከምረቃው በኋላ ደውሎላቸው የነበረ ሲሆን "ተሰብስበው እንዳዩት ነገሩኝ፤ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ነው ሲከታተሉኝ የነበረው" ይላል።

እህቱ ፌቨን ወንድሟ በደረሰበት ደረጃ ቤተሰቡ በአጠቃላይ ከፍተኛ ኩራት እንደተሰማቸው ገልፃ ቤተሰቦቿ ቢገኙ ደግሞ የበለጠ ደስታ ከፍ ያለ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ መሆኑን ትገልፃለች።

"ቤተሰቦቼ በቀጥታ የሚተላለፈውን ምርቃት እያዩም እያለቀሱ ነበር። በእንግሊዝ ኤምባሲ በጣም አዝነናል" ትላለች።