ቻይናዊቷ የ118 ልጆች የጉዲፈቻ እናት የ20 ዓመት እሥር ተፈረደባት

ሊ ያንዢያ Image copyright Weibo

118 ልጆች በጉዲፈቻ በማሳደግ ስትሞገስ የነበረችው ቻይናዊ ሴት የ20 ዓመት እሥር ተፈረደባት። የ54 ዓመቷ ሊ ያንዢያ፤ ገንዘብ በማጭበርበር፣ በማታለል፣ ሀሰተኛ ሰነድ በመሥራትና ማኅበራዊ ሥርዓትን በማወክ ጥፋተኛ ተብላለች። 388,000 ዶላር ቅጣትም ተጥሎባታል

በአንድ ወቅት "የፍቅር እናት" በሚል ቅጽል ስም ትጠራ የነበረችው ሊ፤ የህጻናት ማሳደጊያ ነበራት። ከሷ በተጨማሪ የወንድ ጓደኛዋን ጨምሮ 15 ተባባሪዎቿም ጥፋተኛ ተብለዋል።

በባርነት ከመሸጥ የተረፉት 64 ኢትዮጵያዊያን

ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓና እስያ ሠራተኞችን ልትልክ ነው

"እናቴ ካልመጣች አልመረቅም" ኢዛና ሐዲስ ከማንችስተር ዩኒቨርስቲ

ከግብረ አበሮቿ ጋር በመሆን የህጻናት ማሳደጊያውን ጠቀም ያለ ገንዘብ ለማግኘት እንዳዋለችው ፍርድ ቤቱ ተናግሯል። የወንድ ጓደኛዋ ዡ ኪ 12 ዓመት እሥራት የተፈረደበት ሲሆን፤ ሌሎቹ ተባባሪዎቿ እስከ አራት ዓመት የሚደርስ እሥራት ይጠብቃቸዋል።

"የፍቅር እናት" ማናት?

ሊ ያንዢያ ዝነኛ የሆነችው በቻይና ሀይቤይ ግዛት በምትገኝ ውዋን በምትባል አነስተኛ ከተማ ውስጥ በርካታ ልጆች በጉዲፈቻ መውሰድ ስትጀምር ነበር።

የቀድሞ ባለቤቷ ልጃቸውን ለሕገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች እንደሸጠው ለመገናኛ ብዙሀን ተናግራ ነበር። ልጇን ካስመለሰች በኋላ ሌሎች ህጻናትንም ለመርዳት እንደወሰነችም ገልጻ ነበር።

በጊዜ ሂደት በትውልድ ቀዬዋ ውዋን የናጠጠች ሀብታም ሆነች። እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ በማዕድን አውጪ ድርጅት ኢንቨስት ካደረገች በኋላ የድርጅቱ ባለቤት ሆናለች።

"አምስት ወይም ስድስት ዓመት የሚሆናት ልጅ በማዕድን ቁፋሮው አካባቢ ስትሯሯጥ እመለከት ነበር። አባቷ ሞቷል፤ እናቷ ኮብልላለች፤ ስለዚህም ልጅቷን ለማሳደግ ወሰንኩ። በጉዲፈቻ የወሰድኳት የመጀመሪያ ልድ እሷ ናት" በማለት ለአንድ ጋዜጣ ቃሏን ሰጥታ ነበር።

ደኢሕዴን የሐዋሳና የሲዳማ ዞን አመራሮችን አገደ

የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት በ92 ዓመታቸው አረፉ

ብዙ ልጆችን በማደጎ ከወሰደች በኋላ "የፍቅር መንደር" የተባለ የህጻናት ማሳደጊያ ከፈተች። የቻይና መገናኛ ብዙሀን በተደጋጋሚ ሽፋን ሰጥተዋታል። ካንሰር ይዟት እንደነበረም ተነግሮ ነበር።

2017 ላይ "አንዳች የሚያጠራጥር እንቅስቃሴ አይተናል" ያሉ ግለሰቦች ለፖሊስ ጥቆማ አደረሱ።

ፖሊስ 20,000 ዶላር ተቀማጭ ገንዘብ፣ ላንድ ሮቨርና መርሰዲስ ቤንዝ እንዳላት 2018 ላይ ደርሶበታል። ከ2011 አንስቶ ሕገ ወጥ ተግባሮች እንደፈጸመችም ታውቋል።

የጉዲፈቻ ልጆቿ ላይ ብዝበዛ ታደርስ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ልጆች ሆነ ብላ የግንባታ ሥራ እንዲያስተጓጉሉ ካደረገች በኋላ የግንባታ ተቋራጮች እንዲከፍሏት ታስገድድ ነበር።

"የፍቅር መንደር" የተባለውን የህጻናት ማሳደጊያ ለመገንባት በሚል በርካታ ገንዘብ አጭበርብራለች። በቁጥጥር ሥር በዋለችበት ወቅት ማሳደጊያው ውስጥ የተገኙት 74 ልጆች ብቻ ነበሩ።

ልጆቹ ወደተለያዩ የመንግሥት ተቋሞችና ትምህርት መስጫዎች ተወስደዋል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "የበግ ለምድ የለበሰች ነብር" ሲሉ ብዙዎች አውግዘዋታል። ዊቡ በተባለው የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች አንዱ "አጎቴ ለህጻናት ማሳደጊያዋ ድጎማ አድርጎ ነበር፤ በጣም አሳፋሪ ናት" ይላል።

"በአንድ ወቅት 'የፍቅር እናት' ብዬ መጥራቴ ይጸጽተኛል። ስለ ፍቅር የምታውቀው ነገር የለም። ስሙም አይገባትም" በማለት የወቀሳት ግለሰብም ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች