የኦሳ 33ኛ ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ተጀመረ

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ኦሮሞ ስተዲስ አሶስዬሽን(ኦሳ) [የኦሮሞ ጥናት ማህበር] 33ኛውን ጉባኤ በአዲስ አበባ በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ ማካሄድ ጀምሯል። በዋነኛነት የኦሮሞን ታሪክ፣ ቋንቋ እና ባህል ለማጥናት የተቋቋመው ኦሳ፤ ላለፊት 32 ዓመታት ጉባኤውን ከኢትዮጵያ ውጪ ሲያካሄድ ነበር።

ዛሬ በተጀመረውና ለሦስት ቀን በሚቆየው ጉባኤ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ፕሬዘዳንት ኩለኒ ጃለታ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ስለ ኦሮሞ ታሪክ ያለውን የተዛባ ትርክት ለማስተካከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በባርነት ከመሸጥ የተረፉት 64 ኢትዮጵያዊያን

"እናቴ ካልመጣች አልመረቅም" ኢዛና ሐዲስ ከማንችስተር ዩኒቨርስቲ

"ገዳ የወደፊቱ የፖለቲካ ስርዓት መሆን ይችላል" ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ

ከኦሮሞ ቋንቋ እና ባህል ውጪ ስለሌሎች ብሔረሰቦች ታሪክ በማጥናት ጽሁፎች ያዘጋጃል። በዚህም የተቀረው ዓለም ስለነዚህ ማህበረሰቦች የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ይረዳል ሲሉ ፕሬዘዳንቷ ተናግረዋል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ እስካሁን የጥናት ተቋሙ ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነዋል። በፖለቲካ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄድ ተገዶ የነበረው የጥናት ተቋምና ደጋፊዎቹ "አሸንፈዋል" ብለዋል።

"ለመላው የኦሮሞ ሕዝብ ልጆቻችሁ እንኳን ተመለሱላችሁ" ብለዋል አቶ ሽመልስ በንግግራቸው።

አሁን ያለው ትውልድ የገዳ ሥርዓት እንዲጠነክር እየተካሄደ ያለው ጥናትና ምርምር እንዲቀጥልበት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።

"ተሳታፊዎች በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል የጀመረው 'የዜግነት አገልግሎት' ሥራ ላይ እንደውል ሊደግፉ ይገባል" ብለዋል።

የኦሳ ፕሬዘዳንት፤ የጥናት ተቋሙ የጥናት ማዕከል ብቻ ሳይሆን ለትውልዱ ፍኖተ ካርታ ማሳየት አለበት ብለዋል።

በጉባኤው ላይ ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሠን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ምሁራን ይታደማሉ።