ስለ አልጋዎ ማወቅ ያለብዎት 13 ነጥቦች

ጃፓን ውስጥ ለመሬት የቀረበ አልጋ ይዘወተራል
የምስሉ መግለጫ,

ጃፓን ውስጥ ለመሬት የቀረበ አልጋ ይዘወተራል

አልጋን የመሰለ ነገር ምን አለ? ከቤትዎ ለቀናት ርቀው ሲመለሱ የሚናፍቅዎት አልጋዎ ነው። ሲደክምዎ፣ ሲከፉ፣ ሲደሰቱም አልጋ ውስጥ ይገባሉ።

አልጋ አንድ ሰው ራሱን ችሎ መኖሪያ ቤት ሲያገኝ ከሚገዛቸው የቤት ቁሳቁሶች አንዱና ዋነኛውም ነው። ለመሆኑ ስለ አልጋ አመጣጥ ምን ያህል ያውቃሉ?

1. ፍራሽ የዛሬ 77 ሺህ ዓመትም ነበረ

የምስሉ መግለጫ,

የሰው ልጅ ዋሻ ውስጥ ሲኖር የሚተኛው ከእጅ በተሠራ ፍራሽ ላይ ነበር

በድንጋይ ዘመን የሰው ልጅ በፍራሽ ይገለገል እንደነበር የታሪክ ምሁሩ ግሬግ ጄነር ይናገራሉ። ይህም ከ77 ሺህ ዓመት በፊት ገደማ ማለት ነው። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሰዎች በእጃቸው በሠሩት ፍራሽ ላይ ይተኙ ነበር።

"ዋሻዎቹ ምቹ አልነበሩም፤ ሰዎች ራሳቸውን ከነፍሳት ለመከላከልም ፍራሽ ያስፈልጋቸው ነበር" ይላሉ የታሪክ ምሁሩ።

የሚመገቡበትና የሚተኙበት ሥፍራ ተመሳሳይ በመሆኑ ፍራሻቸው በምግብ ቅባት ይርስ ነበር። በቅባት የራሱ ፍራሾች በእሳት ይቃጠላሉ። አርኪዎሎጂስቶችም የተቃጠሉ ፍራሾች አመድ አግኝተዋል።

2. የመጀመሪያው አልጋ የድንጋይ ክምር ነበር?

የምስሉ መግለጫ,

የመጀመሪያው አልጋ የድንጋይ ክምር ነበር

ግሬግ እንደሚናገሩት፤ ከ10 ሺህ ዓመት በፊት ቱርክ ውስጥ ከመሬት ከፍ ባለ ሥፍራ መተኛት መዘውተር ጀመረ። ስኮትላንድ ውስጥ ደግሞ ከ6 ሺህ ዓመታት በፊት ከፍ ባለ ቦታ መተኛት መለመድ ጀመረ።

አልጋ ይሠራ የነበረው ድንጋይ በድንጋይ ላይ በመደራረብ ነበር። ከዛም አነስተኛ ፍራሽ ከላይ ይደረብበታል።

3. ግብጻውያን ለአልጋ እግር ያሠሩ ነበር

የምስሉ መግለጫ,

ባለ ጸጋ ግብጻውያን ለአልጋቸው እግር ያሠሩ ነበር

የጥንት ቱጃር ግብጻውያን ለአልጋ እግር ያሠሩ ነበር። እግሩ በተለያዩ እንስሳት ኮቴ ቅርጽ ከእንጨት ይዘጋጅ ነበር።

የታሪክ ምሁሩ እንደሚሉት እነዚህ አልጋዎች እንደዘመነኞቹ ጠፍጣፋ አልነበሩም። መሀከል ላይ ሰርጎድ ተደርገው ይሠሩ ነበር።

"ይህ ማለት አልጋው ላይ የሚተኛ ሰው ተንሸራቶ እንዳይወድቅ ታቅዶ የተሠራ ነው ማለት ነው።"

4. የምሥራቁ ዓለም የአልጋ ከፍታና የክብር ጥያቄ

ሩቅ ምሥራቅ በተለይም ቻይና ውስጥ አልጋ ከመሬት ከፍ ተደርጎ ሲሠራ የአልጋው ባለቤት በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍ ያለ ቦታ እንዳለው ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

የጃፓናውያን አመለካከት ግን ከዚህ የተለየ ነው። ታማቲ የሚባል ምንጣፍ አንጥፎ መሬት መቀመጥ የተለመደ ነው። በአንዳንድ የካዛኪስታን አካባቢዎች ምንጣፍ ተጠቅሞ መሬት ላይ መተኛት የተለመደ መሆኑን ግሬግ ያስረዳሉ።

ይህ ልማድ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ከሚኖሩ ሰዎች የተወሰደ ሲሆን፤ ሰዎቹ ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላው ሲሄዱ በቀላሉ የሚያጓጉዙት ምንጣፍ ይይዙ ነበር።

5. ሮማውያንና ግሪካውያን የሚመገቡት አልጋ ላይ ነበር

የምስሉ መግለጫ,

ሮምና ግሪክ አልጋ ውስጥ መመገብ የተለመደ ነበር

በጥንታዊ ሮምና በግሪክ አልጋ መተኛ ብቻ ሳይሆን መመገቢያ ሥፍራ ጭምርም ነበር።

አልጋ ላይ ሳሉ አጠገባቸው ከሚገኝ ጠረጴዛ የወይን ፍሬና ሌላም ያሻቸውን እየወሰዱ ይመገባሉ።

6. ጥንታዊ አልጋ ለቤተሰብና ለእንግዳም ይበቃ ነበር

በመካከለኛው ዘመን በሀብት የናጠጡ አውሮጳያን "ታላቁ አልጋ" በሚል አልጋ ያሠሩ ነበር።

"ይህ አልጋ በጣም ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ የአንድ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾችን በአጠቃላይ ይይዛል" ይላሉ ግሬግ።

ይህ አልጋ ተነቃቃይ ስለነበረ፤ ባለ ኃብቶቹ ቤተ መንግሥት ሲቀያይሩ አልጋውን ይዘው ይጓዙም ነበር።

7. ከቃጫ የሚሠራው አልጋ

የምስሉ መግለጫ,

ሕንድ ውስጥ የሚሠራው ቻፕሪ የተባለ አልጋ

የአልጋ እግር ከእንጨት፣ መሀሉ ደግሞ ከቃጫ ይሠራ ነበር።

የታሪክ ምሁሩ እንደሚሉት፤ ቃጫው ሲጠብቅ አልጋው የተሻለ ምቹ ይሆናል።

8. የአልጋ ዙሪያ ቋሚዎች የሀብት ማሳያ ነበሩ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1400s እና 1500 በአራት አቅጣጫ ቋሚ ያለው አልጋ መዘውተር ጀመረ።

አልጋ ዙሪያ የሚሠሩት ቋሚዎች ለአልጋው ተጨማሪ ውበት ያክላሉ።

"እነዚህ ቋሚዎች አንድ ሰው ያል የሀብት መጠን ማሳያ ነበሩ" ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ያስረዳሉ። አንድ ሰው አልጋው ዙሪያ ቋሚ ለማስገጠም ሠራተኞች ያስፈልጉታል። ሠራተኞች መቅጠር የሚችሉ ሰዎች ደግሞ ብዙም አልነበሩም።

9. አልጋና ፖለቲካ

የምስሉ መግለጫ,

የስዊድን ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚገኝ መኝታ ክፍል

ፕሮፌሰር ሳሻ ሀንድሊ እንደሚናገሩት፤ ወደ ዘመናዊ ታሪክ ስንመጣ አልጋና ፖለቲካ እየተሳሰሩ መጥተዋል።

ጥንት ንጉሥና ንግሥት በፈጣሪ ተመርጠው የተቀቡ ናቸው የሚል አመለካከት ነበር። ነገሥታቱ አልጋቸውን የፖለቲካ ሕይወታቸው ማዕከል አድርገው ያስቡ ነበር።

የተለያዩ ሥርዓቶች የሚከናወኑት በነገሥታት አልጋ ዙሪያ ነበር። ነገሥታት ስለሚወዱት አገር ሲናገሩና ሌላም ሥነ ሥርዓት ሲካሄድ አልጋው እንደ መድረክ ያገለግል ነበር።

በነገሥታት የሚወደደዱ አገሮች ልዑካን ነገሥታት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ እንዲመለከቱ ይጋበዙም ነበር።

10. አልጋና ክፉ መንፈስን መከላከል

የምስሉ መግለጫ,

ከአልጋ በላይ ክፉ መንፈስ ያስወግዳሉ ተብለው የሚታመንባቸው ቁሳቁሶች ይሰቀላሉ

ሰዎች ተኝተው ሳለ ክፉ መንፈስ እንዳይጸናወታቸው ከመጸለይ ባለፈ፤ ይህን መንፈስ ያርቀል ብለው የሚያምኑባቸውን ቁሳ ቁሶች ከአልጋቸው በላይ ይሰቅሉ ነበር።

ከክፉ መንፈስ ራሳቸውን ለመከላከል የተኩላ ጥርስ አንገታቸው ላይ የሚያደርጉም አሉ።

ብረት ክፉ መንፈስን ያርቃል ተብሎ ስለሚታመን፤ ከህጻናት አልጋ በላይ የብረት ቢላዎች ይሰቀሉም ነበር።

11. እስከ ስድስት ፍራሽ. . .

ወደ ዘመነኛው ዓለም ስንመጣም ሰዎች ለአልጋቸው ብዙ ገንዘብ ያወጣሉ። አልጋ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ሀብት ተደርጎ የሚወሰድበት ዘመንም ነበር።

ከአንድ እስከ ስድስት ፍራሽ ተደራርቦ አልጋ ላይ ይደረግ ነበር። ከአንድ ሰው ሀብት አንድ ሦስተኛው ይህ ባለ ስድስት ፍራሽ አልጋ ሊሆንም ይችላል።

ይህ አልጋ የኑሮ ደረጃ መለኪያ ተደርጎም ይወሰዳል።

12. ሽግግር ወደ ብረት አልጋ

እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በተለይ በአውሮፓ አልጋ የሚሠራው ከእንጨት ነበር። በ1860ዎቹ እንጨት ለቅጫምና ቅማል መራቢያ ሊሆን እንደሚችል ስለታወቀ አልጋ በብረት መሠራች ጀመረ።

የብረት አልጋ የተሻለ ሆኖ ከመገኘቱ ባሻገር ባለ ስፕሪንግ ፍራሽም የተዋወቀው በዚህ ዘመን ነበር።

13. የልጆች መኝታ ክፍል

የምስሉ መግለጫ,

የልጆች መኝታ ቤት

ታሪክ እንደሚያሳየው ቤተሰብ በአንድ አልጋ ላይ የመተኛት ልማድ ነበረው። እንግሊዝ ውስጥ ቪክቶሪያኖች የልጆች መኝታ ክፍል ያስፈልጋል የሚል ሀሳብን አስተዋወቁ።

የህክምና ባለሙያዎች ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው መተኛት እንዳለባቸው ካስረዱ በኋላ የልጆች መኝታ ክፍል ተለመደ።