በአስር ወራት አማርኛ ማንበብና መፃፍ የቻለው ጀርመናዊው ዳዊት

ዳዊት

ቱሪስት ሆቴልን ያውቁታል? የአራት ኪሎውን ሳይሆን፤ የአርባምንጩን። የከተማይቱ ዘመናይ እና ፈር ቀዳጅ ሆቴል። ፊታቸውን ለአረንጓዴ ተፈጥሮ [ለእግዜር ድልድይ] ሰጥተው በርካታ ሆቴሎች [ሎጆች] ከመሰደራቸው በፊት የነበረ።

የተለመደ አርብ፤ በአርባ ምንጭ ጎዳና፤ በቱሪስት ሆቴል። ጎብኚ ብርቋ ያልሆነው አርባ ምንጭ ደርሶ ይህንን ሥፍራ ሳይጎበኝ የመጣ ተፈልጎ የሚገኝ አይመስልም። እዚህ ሥፍራ የውጭ ኃገር ዜጎችን በተለይም ነጮችን ማየትም የተለመደ ነው።

እኔና ባልደረባዬም ቡና እየጠጣን ቀና ስንል በዙሪያችን ካሉ ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ነጮች ሆነው ብናገኝ አልተደናገጥንም፤ ስሙስ ቢሆን ቱሪስት ሆቴል አይደል።

"እናቴ ካልመጣች አልመረቅም" ኢዛና ሐዲስ ከማንችስተር ዩኒቨርስቲ

ነገር ግን አንድ ሰው ቀልባችንን ገዛው፤ አንድ ወጣት ነጭ። አስተናባሪውን 'ማነህ ወዳጄ፤ የበግ ወጥ አላችሁ?' ብሎ ሲያዝ ስንሰማ ከተተከልንበት የሞባይል ስክሪን ቀና ልንል ግድ ሆነ።

'ጆሮዬ ነው ወይስ. . .?' የሁለታችንም ፊት ላይ የሚነበብ ጥያቄ። ትንሽ ቆይቶም የእጅ ስልኩን አንስቶ 'ሃሎ' ማለት ነው። አሁን ይለያል ጉዱ. . . 'ሃሎ? ሰላም ነው?. . .አለሁ፤ ደህና ነኝ።'

አሁን ጠጋ ብዬ ላናግረው ቆረጥኩኝ። ልክ ስልኩን ከመዝጋቱ ከፊት ለፊቱ ቆሜ ለሰላምታ እጄን መዘርጋት። ፊቱ ላይ ትንሽ መደናገጥ ቢነበብም እጅ አልነሳኝም።

"እንደው አማርኛ አቀላጥፈህ ስትናገር ስሰማ ጊዜ ነው. . .።" ለአንደዚህ ዓይነት ክስተት አዲስ ያልሆነው ዳዊት ወንበር ስቦ አስቀመጠኝ፤ በሰው ድግስ እኔም ጓደኛዬን ጠርቼ ቁጭ ማለት።

ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓና እስያ ሠራተኞችን ልትልክ ነው

ዴቪድ ቢሆንም ስሙ ኢትዮጵያን ባወጡለት ዳዊት ነው የሚጠራው፤ ጀርመናዊ ነው። ኢትዮጵያ መኖር ከጀመረ 10 ወራት ሆኖታል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተልዕኮ የሶሲዮሎጂ እና የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ ነው። እንዳው 10 ወሩን ከሰዎች ጋር በምን ቋንቋ ተግባብቶ ቆየ? ብለው ቢጠይቁ በአማርኛ ነዋ. . .መልሱ።

አማርኛን ቋንቋ በደንብ አድርጎ መናገር ይችላል፤ ይፅፋል፣ ያነባል፣ ያደምጣል። ከኢትዮጵያዊያን ጓደኞቹ ጋር በስልክ የሚያወራው በአማርኛ ነው፤ የፅሑፍ መልዕክት የሚለዋወጠውም እንዲሁ በአማርኛ።

«አማርኛ መጀመሪያ እራሴን ያስተማርኩት ጀርመን ውስጥ ነው። አንድ መፅሐፍ ገዝቼ ማጥናት ጀመርኩኝ። ያንን መፅሐፍ ሙሉውን ጨረስኩት። በተጨማሪ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጣሁ በኋላ ማጥናት ጀመርኩኝ። አማርኛ ለውጭ ዜጎች የሚል ኮርስ አለ።»

ጀርመን እያለ ለ6 ወራት ገደማ አማርኛ አጥንቷል። ኢትዮጵያ መኖር ከጀመረ ደግሞ 10 ወራት። በጠቅላላው ወደ 1 ዓመት ተኩል ገደማ ነው አማርኛ ለመናገርና ለመፃፍ የፈጀብኝ ይላል።

«እውነት ለመናገር ዋናው ጥረት ነው። ቀን በቀን እለማመዳለሁ። ሌላው ደግሞ ለእኔ ቋንቋን ለማወቅ ዋናው መሠረታዊ ነገር ፊደላቱን ማወቁ ይመስለኛል።»

«አማርኛ ማውራት ስጀምር ለቡና ይጋብዙኛል»

ዳዊት በደህና ጊዜ በተማራት አማርኛ ብዙ ነገር አይቶባታል። አማርኛ አይሰማም ብለው ከሚያሙትና ከሚዘልፉት ጀምሮ፤ አማርኛ መስማቱን ሲያውቁ ተደናግጠው የሚገቡበት እስከሚጠፋባቸው ሰዎች ድረስ።

«አማርኛ ቋንቋን ማወቄ በጣም ጠቅሞኛል። መንገድ ላይ አግኝተውኝ በእንግሊዝኛ ሊያናግሩኝ ሲሞክሩ እኔ ደግሞ በአማርኛ አናግራቸዋለሁ፤ ብዙዎቹ ይደነግጣሉ። ከዚያ ቡና እንጠጣ ብለው ይጋብዙኛል። ብዙዎች ደጋጎች ናቸው።»

እኔም 'የበግ ወጥ አለ?' ሲል አይደል የደረስኩበት፤ ብዙ ጊዜ ምግብ ቤት ውስጥ እነሱ በእንግሊዝኛ ሊያወሩኝ ሲሞክሩ እኔ በአማርኛ ሳወራቸው ግራ ይጋባሉ ይላል ዳዊት።

«ለምሳሌ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ገብቼ አንድ ጉዳይ ላስፈፅም በእንግሊዝኛ ሳናግራቸው ማንም ምላሽ አይሰጠኝም። ነገር ግን በአማርኛ ማውራት ስጀምር ሁሉም ሊተባበሩኝ ወደ'ኔ ይመጣሉ።» ይላል

ዳዊት አርባ ምንጭ የተገኘው ጓደኛውን ፍለጋ ነበር፤ ጀርመናዊ ጓደኛውን። ጓደኛው ከሞያሌ ወደ አርባ ምንጭ እየመጣ ነው። ከእርሱ ጋር ተያይዘው አንድ ምሽት አርባ ምንጭ፤ አንድ ምሽት ደግሞ ሻሸመኔ አሳልፈው አዲስ አበባ መግባት ነው ዕቅዳቸው። ነገር ግን ጓደኛው የውሃ ሽታ ሆኖበት ቱሪስት ሆቴል ምሳ እየበላ ሊጠብቀው ጎራ ይላል።

"ኦሮሞ እና ማዳጋስካርን የሚያገናኝ ፖለቲካ እንዳለ አላውቅም" የትነበርሽ ንጉሤ

ታድያ ግራ ተጋብቶ ወዲያ ወዲህ ሲል የተመለከተው አንድ ሰው 'ይህ ደግሞ የማን ቀውላላ ነው?' ሲለው ይሰማል። ግን ይህ ለእርሱ አዲስ አይደለም።

«በየቀኑ ያጋጥመኛል [ሳቅ. . .] አማርኛ እንደማልሰማ ስለሚያስቡ ስለእኔ የሆነ ነገር ይናገራሉ፤ መልካምም ይሆን ክፉ። ብዙ ጊዜ ስለእኔ የሚያወሩት ይገባኛል። ባይገባኝ እንኳ ስለእኔ እያወሩ እንደሆነ እረዳለሁ።»

ምን ቋንቋ ብቻ

ዳዊት ቋንቋችንን ብቻ አይደለም በርካታ ታሪካዊ ቦታዎችንና ከተማዎችን ያውቃል።

«ላሊበላ፣ አክሱም፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ጥቁር አባይ ፏፏቴ፣ ላንጋኖ፣ ሐይቅ ሐረር. . .» ኧረ በቃ። እኔ ኢትዮጵያዊው እንኳን እንደሱ አልተጓዝኩም።

ምግብና መጠጡንስ. . .?

«የበዓል ምግብ በጣም ነው የምወደው፤ ዶሮ ወጥ በጣም ይጣፍጣል። ግን ደግሞ ሸክላ ጥብስ በጣም ነው የምወደው። አንድ የወንድ ማሕበር አለን። ከእኔ በቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ቅዳሜ ቅዳሜ እንገናኛለን። ሥጋ ለመብላት፤ ቢራ ለመጠጣት [ሳቅ. . .]።»

«ከኢትዮጵያዊያን መጠጥ ደግሞ ጠጅ በጣም እወዳለሁ።»

«አውሮፓ ውስጥ ቡና እንጠጣ ብሎ ነገር የለም»

ጀርመናዊው ዳዊት አውሮፓ ውስጥ በርካታ ሃገራትን ተዛዋውሮ ተመልክቷል። እዚያ የሌለ ኢትዮጵያ ውስጥ ያስተዋልኩት አንድ ትልቅ ነገር አለ ይላል።

«አውሮፓ ውስጥ፤ በተለይም ጀርመን ሃገር ሰው ሁልጊዜ ሩጫ ላይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሰዎች ቁጭ ብለው ቡና እየጠጡ ይጫወታሉ። ቁጭ ብሎ ቡና መጠጣት የሚባል ነገር እዚያ የለም። አረፍ ብሎ ቡና እየጠጡ መጫወት በጣም አሪፍ ነገር ነው። ተቀራርበህ ማውራት ደስ ይላል።»

"በጎጃም ማርያም ቤተክርስቲያን ለመስጊድ 3ሺ ብር ረድታለች' ተባልኩኝ" ሐጂ ዑመር ኢድሪስ

ይሁን እንጂ ዳዊት እንደዚያ ተቀራርባችሁም የማታወሯቸው ነገሮች ይበዛሉ ይለናል። ክርኔን ጭኔ ላይ አስደግፌ፤ የጀበና ቡናዬን ፉት እያልኩ እየሰማሁት ነው።

«ለምሳሌ እኔ ከአባቴ ጋር ቢያንስ በሳምንት አንድ ሁለቴ በስልክ ልናወራ እንችላለን፤ በዚህ ወቅትም ሁሉን ነገር እነግረዋለሁ። እያሳለፍኩት ስላለሁት ሕይወት፤ ስለ ፍቅር ሕይወቴ ሳይቀር. . .ኢትዮጵያዊያን ግን ምናልባት ለጓደኞቻቸው እንጂ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አብረው ቁጭ ብለው ቢበሉም ብዙ በግልፅ ሲያወሩ አላስተዋልኩም ይላል።»

ዳዊት ስለኢትዮጵያ ለማወቅ ካለው ጉጉት የተነሳ በርካታ በአማርኛ የተፃፉ መፃሕፍትን እንዳነበበ ነግሮኛል።

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚተነትኑ የፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ [Oromo Democracy: An Indigenous African Political System]ና ሌሎችንም።

እና ወደፊት ኢትዮጵያ የመኖር ሃሳብ አለህ? መቼስ አሁንስ ጨቀጨቀኝ ይለኝ ይሆናል።

«አንድ ምክንያት ካለኝ በጣም። ለምሳሌ ፍቅር ሊሆን ይችላል ወይም ሥራ . . .ግን ሃሳብ አለኝ።»

ተያያዥ ርዕሶች