ብሔራዊ አገልግሎት መንፈሳዊ ህይወቱን የነጠቀው ኤርትራዊው ዲያቆን

ዲያቆን ተስፋጋብር ባህታ Image copyright Tesfagaber

ተስፋጋብር ባህታ በወጣትነቱ ተመኝቶ ያጣው ሐይማኖታዊ እና መንፈሳዊ አገልግሎት አሁን በልጆቹ እንዲካካስ ፍላጎት አለው። ከ13 ዓመት በፊት የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት አባል ሳለ ያሳለፈውን ሕይወት በማስታወስ አሁን ኤርትራ በዓለም ማሕበረሰብ የምትከሰስባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲሻሻል፣ የእምነትና ሐይማኖት ነጻነትን ሲከበሩ ማየት ይናፍቃል።

የኤርትራ መንግሥት በአገሪቷ የሚሰጠው ወታደራዊ አገልግሎት የተጀመረበት 25ኛ ዓመት በዚህ ሳምንት በደማቅ ሁኔታ ሲያከብር፤ የብሔራዊ አገልግሎቱ ስኬቶችና የዜጎቹን አስተዋጽኦ በብርቱ ቃላት ማሞካሸቱን በማስታወስ፤ "ባለታሪኮቹ እኛ እኮ አለን?" በማለት መንግሥትን አገልግሎቱን ያንቆለጳጰሰበትን መንገድ ይተቻል።

በፍጥነት እየመጣ ወደነበረ ባቡር በኤርትራዊው የተገፈተረው ታዳጊ ህይወቱ አለፈ

በጎርጎሳውያኑ 1976 በኤርትራ ደቡባዊ ዞን ኮዓቲት በሚባል ቦታ ተወልዶ ያደገው ተስፋጋብር ይህ አገራዊ የውትድርና አገልግሎት መንፈሳዊ ህይወቱን ቀምቶ እንዴት ወደማያውቀው ዓለም እንደወሰደው በራሱ አንደበት ይናገራል።


የቤተክርስትያን አገልጋዮች በውትድርና ሲያገለግሉ

በጎርጎሳውያኑ 1995 መንፈሳዊ ትምህርቴን በመማር፤ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የምሯሯጥ የ19 አመት ወጣት የድቁና ተማሪ ነበርኩ።

ብዙዎች እንደሚሉኝ ታዛዥ፣ እኩዮቼን የምገስፅ፣ አርዓያ አገልጋይ በመሆኔ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ይወዱኝ ነበር።

በአጋጣሚ በዚሁ ዓመትም ህይወቴን የሚቀይር ነገር ተከሰተ። የብዙ ሴት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ወንድ ዲያቆናት ስም ዝርዝር የያዘ ወረቀት በየአውራጎዳናዎቹ፣ በየሱቆቹ ለወራት ተለጥፎ ይነበብ ነበር፤ እዚህ የስም ዝርዝር ውስጥ የእኔም ስም ተካቶ ነበር።

'የቤተክርስቲያን አገልጋይ ወደ ውትድርና!?' ብየ ተደነቅኩኝ፤ ምክንያቱ ምን ይሁን ምን ይህ ለእኔ እንቆቅልሽ ነው። እርግጥ ነው ኤርትራ ባሳለፈችው ረዥም የትጥቅ ትግል ታሪክ ብዙ ዲያቆናትና አባቶች በግድ ተወስደው በረሃ ላይ ቀርተዋል። የእኔም የእዚህ ታሪክ ቀጣይ ክፍል ነበር ማለት ነው።

አምባሳደር ሬድዋን የሹመት ደብዳቤያቸውን ለምን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አላቀረቡም?

Image copyright Tesfagaber

"ኦሮሞ እና ማዳጋስካርን የሚያገናኝ ፖለቲካ እንዳለ አላውቅም" የትነበርሽ ንጉሤ

የተጠራንበት ቀን እንደደረሰ ወታደሮች መጥተው እኔና እኩዮቼን በቁጥጥር ስር አዋሉን። በቀኝ ግዛት ጊዜ ያልተደፈሩ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት በእኔ ዘመን ሲደፈሩ ሳይ እያዘንኩኝ ተገድጄ ወደ ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ሄድኩኝ።

በወታደሮች ጥበቃ ከተወሰድኩባት ቀን ጀምሮ ለ11 ዓመታት እዛው አሳለፍኩኝ። በብሔራዊ አገልግሎቱ ላይ ፈጣን ከሆኑት መካከል አንዱ ነበርኩ። አንድም ስህተት ተገኝቶብኝ ተቀጥቼም እስር ቤት ገብቼም አላውቅም።

ትንሽ ልጅ ብሆንም ያው በእኔ እድሜ ያለው ወጣት የሚያጋጥመውን "ኢ-ሥነምግባራዊ" የምለውን ሕይወት ለማሳለፍ ተገድጃለሁ።

ለብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት በሄድኩበት ወቅት እድሜዬ አፍላ ስለነበር ሱሰኛ ሁኜ ባህሪዬ በሙሉ ተቀይሮ ነበር። በፈጣሪ ፊት የተወገዘ ለሰው ጆሮ የከበደ ነገር ውስጥ ገባሁ።

ሳዋ ላይ ከመጥፎ ነገር የሚከላከልህ ነገር የለም። ቤትህ፣ በተለይ ደግሞ ወጣትም ሆነህ መንፈሳዊ ሰው ከሆንክ፣ ቤተሰብህ፣ ወንድሞችህ፣ ህብረተሰቡ በምክር በተግሳጽ ይጠብቁሀል። በዛም ከብዙ ክፉ ነገር ትሰወራለህ።

የባድመ ጦርነት ላይ ተሰለፍኩኝ። የጥይት ድምፅ ከማያንቀላፋበት፣ አብረውን የዘመቱ እኩያ ጓደኞቼን ካጣሁበት የባድመ ጦርነት በሕይወት ተርፌ ወደቤተሰቦቼ ተመለስኩኝ።

ባድመ ላይ ተማርኬ ስለነበር ደዴሳ ላይ ቆይቼ ሁለቱ አገራት ምርኮኞች ሲለዋወጡ ነበር ወደ ኤርትራ የተመለስኩት።


ይወቴ የተቸገርኩበት ቀን

እንደ ወታደር ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው ከሰው ጋር ሲዋጋ ያየሁት እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 10 1998 በትግራይ ማቲዎስ ምሽግ የነበረው የኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ ተኩስ ስንከፍት ነው።

ጦርነቱ ከቀኑ 10 ሰዓት ነበር የተጀመረው። በብዙ መልኩ ስጋት ነበረኝ። እንደፈራሁትም በሕይወቴ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የወደቅኩበት ቀን ነው። ብዙ ሰው እዚያ የጦርነት አውድማ ላይ ቀረ።

ያን ቀን ማታ 3፡30 ሰአት ላይ አውሎ ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ ዘንቦ የጦር መሳሪያዎች አንደበት ዝም አለ፤ እኛም ወደ ምሽጋችን ተመለስን።

ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራዊት ለማጥቃት በሄድንበት ጊዜ ሳይገባን እናላግጥ ነበር። ሲተረክልን የነበው ጦርነት ደርሶ በአይኔ አየሁት አልኩኝ። ፊታቸው ላይ ስንደርስ ግን ቦንብ እንደቆሎ ተወረወረብን። ጥይት እንደ ዝናብ ተርከፈከፈብን፣ ከፊት ከኋላ ጓደኞቼ ረገፉ። ኦሮማይ! አበቃ!

ሴት አስገድዳ ከወንድ ጋር ወሲብ ብትፈጽም፤ አስገድዶ መድፈር ይባላል?

እውነት ነው "አገር ተወረረ ሲሉን እምቢ አይባልም ሄድን" ግን ጦርነት ኪሳራ ነው። ከመግደል ውጪ ሌላ አታስብም፤ ጠቅላላ ተቀይረህ ሌላ ሰው ትሆናለህ። እኔም ሌላ ሰው ሆንኩኝ።

"ሳልሳይ ወራር" (ፀሐይ ግብዐት ዘመቻ) በምንለው የኢትዮጵያ ሰራዊት ባጠቃበት የመጨረሻው ጦርነት ተማርኬ በህይወት ከቀሩት የሻዕቢያ ሰራዊት አንዱ ነኝ።

ከዚያ በኋላ ለ11 ዓመታት ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ስሰጥ ቆየሁኝ። በደሞዝ፣ በሌላ ሌላ ነገር የሚታይ ዕድገት ባለመኖሩ ተስፋ ቆረጥኩኝ። እኔ ወታደር ነኝ? እስረኛ? የሚል ስሜት ይሰማኝ ነበር።

ከኤርትራ መራቅ አለብኝ ብዬም ወሰንኩ። ከዚያም ከኤርትራ መንገድ አሳብሬ ትግራይ ገባሁ፤ ከትግራይ አዲስ አበባ፤ ከአዲስ አበባ እስራኤል። ከኤርትራ አይደለም እጅና እግሬን አየሩንም ይዤ ብወጣ ደስ ባለኝ።

ኑሮ በስደት ከተማ

በልጅነቴ ሳገለግላት ስለነበረችው ስላሴ ኮዓቲት ቤተክርስቲያን አሁንም እሰማለሁ፤ አባቶቻችን ሁሉም አልፈዋል፤ አገልጋዮችም የሉም።

ካሉም ከመንግሥት ፍቃድ ውጪ መሄድ አይችሉም ሲባል እሰማለሁ። ያው የኤርትራ ህዝብ እያሳለፈው ያለውን ሁሉ ቤተክርስቲያኒቱም እያሳለፈች ነው።

ልጆቼ አስተምሬ አገልጋዮች እንዲሆኑልኝ እመኛለሁ። መንፈሳዊ ህይወት እና ህብረተሰብ እንዲኖረኝም እፈልጋለሁ። ደግሜ መክሰር አልፈልግም።

ብሔራዊ አገልግሎትን ከውጤቱ ስገመግመው ኪሳራ ነበር፤ ችግሩ አገርህን ማገልገል ሳይሆን፤ ወደ ኋላ የመለሰንና ያከሰረን ነው ለማለት እደፍራለሁ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ