በሱዳን ለተቃውሞ ሠልፍ የወጡ ተማሪዎች በመገደላቸው ምክንያት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተወሰነ

በሱዳን የሚገኙ ተማሪዎች ሰኞ ዕለት በኤል ቦይድ የደረሰውን ግድያ በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል Image copyright EPA

በሱዳን በተቃውሞ ሠልፍ ላይ የነበሩ ተማሪዎች በመገደላቸው ምክንያት በሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ወታደራዊው ምክር ቤት ወሰነ።

ሀገሪቱን እየመራት የሚገኘው ወታደራዊ መንግሥት በመላው ሀገሪቱ ዕሮብ ትምህርት ቤቶች በራቸውን እንዲዘጉና አንድም ተማሪ በትምህርት ገበታው ላይ እንዳይገኝ አዟል።

ሰኞ ዕለት የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ከተገደሉ በኋላ ተማሪዎች ዋና ከተማዋ ካርቱምን ጨምሮ በሌሎች አካባቢም አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ሰኞ እለት በኤል ኦቤይድ ለተቃውሞ ወጥተው ከተገደሉ አምስት ሰዎች መካከል አራቱ ተማሪዎች ነበሩ።

የተተከሉት ችግኞች እንዴት ተቆጠሩ?

በአስር ወራት አማርኛ ማንበብና መፃፍ የቻለው ጀርመናዊ

የዱባዩ መሪና ጥላቸው የኮበለለችው ባለቤታቸው ወደ ፍርድ ቤት ሊያመሩ ነው

በሱዳኗ ኤል ኦቤይድ ግዛት በነዳጅና በዳቦ እጥረት ሰበብ ለተቃውሞ የወጡ ነዋሪዎች ላይ አልሞ ተኳሾችና ሌሎች ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ በርካቶች እንደተጎዱ ለማወቅ ተችሏል።

ማክሰኞ ዕለት በካርቱም የትምህርት ቤት የደንብ ልብሳቸውን የለበሱና የሱዳንን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡ ተማሪዎች አደባባይ ለተቃውሞ የወጡ ሲሆን በኤል ኦቤይድ ስለተገደሉ ተማሪዎች ተቃውሟቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል።

በተማሪዎች የተደረገው ተቃውሞ በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችም የተካሄደ ሲሆን ይህንን ተከትሎም በሱዳን የሚገኙ የመጀመሪያም ሆነ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዛሬ ዝግ ሆነው እንዲውሉ ውሳኔ ተላልፏል።

ትዕዛዙ የተላለፈው ሁሉም አፀደሕፃናት፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ሲሆን ሌላ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ ተዘግተው ይቆያሉ መባሉን ሱና የተሰኘው የዜና ተቋም ዘግቧል።

ኤል ኦቤይድ የሆነው ምን ነበር?

Image copyright AFP

በሱዳን ሰሜናዊ ግዛት ኮርዶፋን ውስጥ የምትገኘው ኤል ኦቤይድ የተሰኘችው ከተማ የሚገኙ ተማሪዎች አደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን ያሰሙት የተሻለ የኑሮ ሁኔታን ለመጠየቅ ነበር።

ጥያቄያቸው ግን በተሰማው የተኩስ እሩምታ ተጨናግፏል።

ከሆስፒታል የሚወጡ ምስሎች የሚያሳዩት በደም የተነከሩ ተጎጂዎችን ነው።

እንደ ሱዳን ሀኪሞች ማህበር ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሆነ በኤል ቦይድ አምስት ሰዎች ሲሞቱ 62 ሰዎች ደግሞ የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ተቃዋሚዎቹ በአካባቢው የሚገኘው ፈጥኖ ደራሽ ወታደርን ስለተፈጠረው ተጠያቂ አድርገዋል።

የአካባቢው ባለስልጣናት የአስቸኴይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን ከመሸ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይም ገደብ አስቀምጠዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕፃናት ኤጀንሲ (ዩኒሴፍ) ባለስልጣናት ግድያውን የፈፀሙት ላይ ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂዎቹን ፍትህ ፊት እንዲያቀርቧቸው የሱዳን መንግሥትን ጠይቀዋል።

በመግለጫቸው ላይ አክለው "ማንም ተማሪ የትምህርት ቤት የደንብ ልብሱን እንደለበሰ መቀበር የለበትም" ያሉ ሲሆን በከተማይቱ የተገደሉት ተማሪዎች ዕድሜያቸው ከ15-17 እንደሆነ ተጠቅሷል።

የሱዳን ወታደራዊ ምክርቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሀን ግድያውን አውግዘዋል።

"በኤል ቦይድ የተከሰተው አሳዛኝ ነው፤ ንፁኃንን መግደል ተቀባይነት የሌለውና በፍጥነት ተጠያቂነት ሊወሰድበት የሚገባው ነው" ብለዋል በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ባደረጉት ንግግር።

በኤል ቦይድ ተቃውሟቸውን ያሰሙ የነበሩ ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች የተገደሉት የተቃውሞው መሪዎች ሱዳንን ከሚያስተዳድሯት ጄነራሎች ጋር ለውይይት ለመቀመጥ ቀጠሮ በያዙበት ዋዜማ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ