የበጎ ሰው ሽልማት ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ሀገር ውስጥ ባበረከቱት አስተዋፅኦ ሊሸልም ነው

የበጎ ሰው ሽልማት ኮሚቴ አባላት በከፊል Image copyright YebegoSew

በየዓመቱ የተለያዩ ግለሰቦችን እውቅና በመስጠት የሚታወቀው የበጎ ሰው ሽልማት ዘንድሮ በሚያካሄደው ሥነ-ሥርዓት ከዚህ ቀደም ከነበሩት የሸልማት ዘርፎች በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎችን ሀገር ውስጥ ባበረከቱት አስተዋፅኦ መሸለም የሚያስችል ዘርፍ መጨመሩን የሽልማት ኮሚቴው ፀሐፊ አቶ ቀለምወርቅ ሚደቅሳ ለቢቢሲ ገለፁ።

ፀሐፊው አክለውም የበጎ ሰው ሽልማት ራሱን የቻለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሆኖ መመዝገቡንም ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በተደጋጋሚ ለመመዝገብ ጥያቄ ቢያቀርቡም አለመቻላቸውን የተናገሩት አቶ ቀለምወርቅ አሁን ግን አዋጁ በመሻሻሉና የኤጀንሲውም አወቃቀር ስለተቀየረ መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ ተራዘመ

ከዚህ በኋላ እቅድ በማውጣትና የተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ በመንቀሳቀስ በጎነትን እና በጎ ማድረግን የሚያበረታታ ሥራ እንደሚሰሩ ጨምረው አስረድተዋል።

ዲያስፖራውን መሸለም ለምን?

አቶ ቀለምወርቅ እንደሚሉት ከሆነ በዚህ ዓመት የሚካሄደው የበጎ ሰው ሽልማት ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዘርፎች በተለየ ዲያስፖራውን የሚያካትት ዘርፍ ተካትቶበታል።

ከዚህ ቀደም ምንም እንኳ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ለሀገራቸው የተለያየ ነገር ቢያበረክቱም ከእነርሱ ጋር በመቀራረብ መስራትና ማበረታታት አዳጋች ነበር ያሉት አቶ ቀለምወርቅ፤ አሁን ግን ሀገሪቱ ላይ ያለው ለውጥ ይህንን የሚያበረታታ በመሆኑ ዘርፉ መጨመሩን ገልጸዋል።

የዳያስፖራ ማህበረሰብ ለሀገሩ የተለያየ ነገር ሲያበረክት መቆየቱን ያስታወሱት ፀሐፊው ይህንን እንደ በጎ ሰው ለማበረታታት በማሰብ ዘርፉ መጨመሩን ተናግረዋል።

የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በዚህ ዓመት አበርክቷቸው የሚመዘነው በማንኛውም ዘርፍ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ዳያስፖራውም ልክ እንደ ሌሎች ዘርፎች ሁሉ በዲያስፖራው አባላትና በሌሎች ተጠቁመው ዕጩ እንደሆኑ ገልፀዋል።

የዱባዩ መሪና ጥላቸው የኮበለለችው ባለቤታቸው ወደ ፍርድ ቤት ሊያመሩ ነው

የበጎ ሰው ሽልማት በየዓመቱ እጩ የሚያደርጋቸውን ግለሰቦች ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በስልክ፣ በኢሜል፣ በፖስታ፣ በማህበራዊ ትስስር ገፆች እና በኦንላይን ጥቆማ የሚቀበል ሲሆን አንዳንዴ ጥቆማ የሚሳሳበት ዘርፍ ካለ ሊጠቁሙ የሚችሉ አካላትን ኮሚቴው እንደሚያነጋግር አስታውሰዋል።

ዘንድሮ በሁሉም ዘርፍ በቂ ሰው መጠቆሙን እና የዳያስፖራው ዘርፍም በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በርካታ ጥቆማ መቀበላቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

እጩ የሚሆን ሰው የመጠቆሚያ ጊዜው አንድ ወር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ቀለምወርቅ አሁን በመጠናቀቁ እጩዎቹን ነገ በሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

ከዳያስፖራ ውጪ በሳይንስ፣ በመምህርነት፣ በበጎ አድራጎት፣ በቅርስና ባህል፣ መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በብቃት በመወጣት፣ በንግድና የሥራ ፈጠራ፣ በማህበራዊ ጥናትና ኪነጥበብ ዘርፍ እጩዎች መኖራቸውን አስታውሰው የኪነጥበብ ዘርፍ በርካታ ንዑስ ዘርፎች ስላሉት ዘንድሮ በፎቶ ግራፍ ጥበብ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ብቻ በእጩነት እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

የታዋቂዋ ወጣት አስክሬን ሻንጣ ውስጥ ተገኘ

አስር ዘርፎች ያሉት የበጎ ሰው ሽልማት በኮሚቴው ውሳኔ አንድ ልዩ ተሸላሚ እንደሚኖረውም ጨምረው አስታውቀዋል።

ሽልማቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች

የበጎ ሰው ሽልማት በዓመት አንዴ የሚካሄድ መርሀ ግብር መሆኑን በማስታወስ እስከዛሬ እውቅና የተሰጣቸው ግለሰቦች ሕይወት ላይም ሆነ ሌሎች ላይ ስራችሁ ለውጥ ማምጣቱን እንዴት ታረጋግጣላችሁ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ቀለምወርቅ ተሸላሚዎቹ ራሳቸው ላይ የሚፈጥረው ለውጥ ቀዳሚው መሆኑን አስረድተዋል።

ለሀገር በርካታ ነገር አድርገው የሚሰሩት ነገር 'ትውልዱ ከቁብ አይጥፈውም' የሚል ስሜት የነበራቸው ተሸላሚዎች፣ ከሽልማቱ በኋላ መንፈሳቸው ተነቃቅቶ የተሻለ ስራ መስራታቸውን አምባሳደር ዘውዴ ረታን በምሳሌነት በመጥቀስ አስረድተዋል።

ሕብረተሰቡ ለተሸላሚዎቹ የሚሰጠው ክብርና አመለካከት ራሱ እንደሚቀየር ሲናገሩም የሐረሩን ሼህ አብዱላሂ ሸሪፍን በማንሳት በተቋም ደረጃ ቢገነባ እንኳ ፈታኝ የሚሆነውን የተለያዩ ኃይማኖቶችና ዘርፎች ቅርስ አሰባስበው ሙዚየም ያደራጁ መሆናቸውን ገልፀው ከሽልማቱ በኋላ ክልሉ የተለያየ ድጋፍ እንዳደረገላቸው አስረድተዋል።

ብሔራዊ አገልግሎት መንፈሳዊ ህይወቱን የነጠቀው ኤርትራዊው ዲያቆን

በመንግሥት የሥራ ዘርፍም አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስን በመጥቀስ በዲፕሎማሲው ጎምቱ መሆናቸውን ካስረዱ በኋላ ተገቢውን እውቅና አግኝተው እንደማያውቁ ነገር ግን ከበጎ ሰው ሽልማት በኋላ የተለያዩ እውቅናዎችን ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

አብዛኞቹ ተሸላሚዎች ታሪካቸው እንኳ በአግባቡ ተሰንዶ አይገኝም የሚሉት አቶ ቀለምወርቅ ሽልማት ከተቀበሉ በኋላ ያለፉ ግለሰቦች የሽኝት ስነስርዓታቸው ላይ የሚነበበው የበጎ ሰው ያዘጋጀው የሕይወት ታሪክ መግለጫ እንደሆነ ያስታውሳሉ።

አንዳንድ ተቋማት ለእነዚህ ግለሰቦች ኃላፊነት በመውሰድ በስማቸው የተለያዩ ነገሮች ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ቀለምወርቅ ለዚህም የአቢሲኒያ ባንክን በማንሳት፣ ፊት አውራሪ አመዴ ለማ፣ ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረስላሴ ዘብሔረ ቡልጋን የመሳሰሉ ሰዎች በስማቸው ቅርንጫፍ ተከፍቶላቸው እንደሚገኝ በመግለፅ፣ በተለያዩ የበጎ ሰው ተሸላሚዎች ስም ቅርንጫፎች መሰየሙን ይጠቅሳሉ።

መልካምነት በኮሚቴ

የመልካምነት ሚዛን ከሰው ሰው እንደሚለያይ በማንሳት ለመሆኑ ለእናንተ በጎ ሰው የሚለውን በኮሚቴ መበየን አይከብድም ተብለው የተጠየቁት አቶ ቀለም ወርቅ ሲመልሱ የበጎ ሰው ሽልማት የራሱ የሆነ ቦርድ እንዳለው ገልፀው የምርጫ ሂደቱም እንዲሁ ራሱን በቻለ መንገድ እንደሚታይ ያስረዳሉ።

አምባሳደር ሬድዋን የሹመት ደብዳቤያቸውን ለምን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አላቀረቡም?

ድርጅቱ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥቆማዎችን ከተቀበለ በኋላ ባለሙያዎችን በመቅጠር የሕይወት ታሪካቸው እንዲፃፍ ማድረግ ቀዳሚው ስራው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቀለምወርቅ ግለሰቦቹ ያበረከቱት አስተዋፅኦ አንድ ሁለት ተብሎ ተቆጥሮ፣ ቅርብ የሆኑ ሰዎቻቸው፣ አብረዋቸው የሰሩ፣ የአካባቢያቸው ሰዎችን በማናገር ታሪካቸው እንደሚጻፍ ይገልጣሉ።

ከዚህ ሁሉ በኋላ የበጎ ሰው ሽልማት ኮሚቴ ተሰብስቦ በተፃፈው ታሪካቸው መሰረት የሰሩትን ስራ መዝኖ ሶስት እጩዎችን እንደሚመርጥ ገልፀዋል።

ከዚህ በኋላ አምስት ሌሎች ባለሙያዎች፣ በዚህ ጉዳይም ላይ ዳኝነት እየሰጡ እንደሆነ የማይተዋወቁ፣ ታሪክ ተልኮላቸው ከአንድ እስከ ሶስት ደረጃ በመስጠት ይለያሉ በማለት ሂደቱን ያብራራሉ።

"እነዚህ ዳኞች በሰጡት ነጥብ ነው፥ እኛ የዓመቱ የበጎ ሰው ብለን የምንሸልመው።"

አንዳንድ ጊዜ እጩዎችን ይፋ ካደረግን በኋላ የተጠቆሙ ሰዎች ላይ የተለያዩ ቅሬታዎች ይመጣሉ ያሉት አቶ ቀለምወርቅ እርሱንም ከግምት ውስጥ እንደሚያስገቡ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓና እስያ ሠራተኞችን ልትልክ ነው

የዚህ ዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ነሐሴ 26 ከ7፡30 ጀምሮ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል የሽልማት መስጠት ስነስርዓቱ እንደሚኖር አቶ ቀለምወርቅ ሚደቅሳ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ