ለዓመታት የተጠፋፉት የወላይታ ሶዶዋ እናትና የኖርዝ ኬሮላይናዋ ልጃቸው

አማረች ከዓመታት በኋላ ከእናቷ ጋር ስትገናኝ

የፎቶው ባለመብት, Amarech

የምስሉ መግለጫ,

አማረች ከዓመታት በኋላ ከእናቷ ጋር ስትገናኝ

አማረች ከበደ እባላለሁ። 20 ዓመቴ ነው። አሁን የምኖረው ኖርዝ ኬሮላይና፤ የተወለድኩት ደግሞ ወላይታ ሶዶ።

ስለ ልጅነት ሕይወቴ ልንገርሽ. . .

ሁለት ታላላቅ ወንድም እና አንድ ታናሽ እህት አለኝ። እህቴ አስቴር ትባላለች። ወላጅ አባታችን ብዙም በሕይወታችን ስላልነበረ አቅመ ደካማ እናቴ ብቻዋን አራት ልጆች ለማሳደግ ትንገታገት ነበር።

እናቴ ቤተሰባችንን ለማስተዳደር ብዙ ውጣ ውረድ አይታለች። ከእኛ ከልጆቿ ውጪ አንዳችም አጋዥ አልነበራትም። ገበያ ወጥቼ አትክልት እገዛና አትርፈን እንሸጠዋለን። ያገኘሁትን ብር ለቃቅሜ ወደ ቤተሰቦቼ እሮጣለሁ።

ያኔ እንደ ሌሎች የሰፈራችን ህጻናት አልጫወትም። [እቃቃ. . . ሱዚ. . . ቃጤ. . . የሚባል ነገር የለም]። በልጅ ጫንቃዬ ቤተሰብ የመደገፍ ኃላፊነት ወደቀብኝ። ታናሽ እህቴን የምንከባከበው እኔ ነበርኩ። እናቴ ስትሠራ እኔ አስቴርን ስለምይዝ ትምህርት ቤት መሄድ አልቻልኩም።

በዚህ በኩል እህቴን መንከባከብ በሌላው እናቴን መርዳት. . . አሁን ሳስበው ይህ ሁሉ ለልጅ በጣም ይከብዳል።

ከታላቅ ወንድሞቼ አንዱ አይነ ስውር ነው። ከሁላችንም በበለጠ የእሷን ትኩረት ይፈልግ ነበር። ልዩ እንክብካቤና ድጋፍ ስለሚያሻው አብዛኛውን ጊዜዋን ትሰጠዋለች። የሚያስፈልገውን ሁሉ ማሟላት ነበረባትና እናቴ ጫናው በረታባት።

ልክ 11 ዓመት ሲሆነኝ ነገሮች እየተባባሱ መጡ። ያኔ አስቴር አምስት ዓመት ሞልቷት ነበር። በቃ! እናቴ እኛን ማሳደግ በጣም ከበዳት. . . እሷ ልትሰጠን ያልቻለችውን ነገር ሁላ እያገኘን እንድናድግ ትፈልግ ነበር።

እኔና አስቴር የተሻለ ሕይወት እንዲኖረን ተመኘች። እዚያው ወላይታ ሶዶ የሚገኝ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ አስገባችን። እኔና እህቴ ከእናታችንና ከወንድሞቻችን ተለያየን!

ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ያለ ፍቅር ስለኖርኩበት ጊዜ ላጫውትሽ. . .

በወላይታ ሶዶ የህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ከቆየን በኋላ አዲስ አበባ ወደሚገኝ ሌላ ማሳደጊያ ተወሰድን፤ ሦሰት ወር ቆይተናል።

በህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ መኖር የመተው ስሜት እንዲሰማሽ ያደርገል። እዚያ ፍቅር የለም። ሁላችንም ድርጅቱ ውስጥ የተገኘነው በማደጎ ለመወሰድ ነው። ሞግዚቶቹም ሆኑ ሠራተኞቹ አይወዱንም። ፍቅር የሚሰጥሽ ሰው የሌለበት ቦታ መኖርን አስቢው. . .

እኔና እህቴ ከአንድ ዓመት በላይ ማሳደጊያው ውስጥ ኖርን።

2010 [በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር] ላይ የሪችመንድ ቤተሰብ የጉዲፈቻ ልጅ ፍለጋ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ አቀኑ።

ያኔ ወደ ድርጅቱ ሲመጡ ወደ አሜሪካ ሊወስዱን እንዳሰቡ አላወኩም። አዲስ አበባ ውስጥ የቆዩት ለአምስት ቀናት ነበር። ወደ አሜሪካ ለመብረር አንድ ቀን ሲቀረን የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ ሆነን ወዴት እንደምንሄድ፣ ለምን እንደምንሄድ ገባኝ። ራሴን መቆጣጠር አልቻልኩም፤ ማልቀስ ጀመርኩ።

ቤተሰቤን፣ አገሬን፣ የማውቀውን ነገር በሙሉ ጥዬ ልሄድ እንደሆነ የታወቀኝ በመጨረሻው ቀን ነበር። ያን ቀን በጣም ስሜታዊ ሆኜ ነበር። የእኔ ከሚሉት ነገር ተለይቶ፤ ወደማይታወቅ ዓለም መጓዝ እንዴት አያሳዝን፣ እንዴት አያስፈራ?

አማረች፣ አስቴር እና የጉዲፈቻ ቤተሰቦቻቸው

የፎቶው ባለመብት, Amarech

የምስሉ መግለጫ,

አማረች፣ አስቴር እና የጉዲፈቻ ቤተሰቦቻቸው

አሜሪካ ገባን. . .

የጉዲፈቻ ቤተሰቦቼ ሦስት ልጆች አሏቸው። ሁለት ወንድና አንድ ሴት። እኔና አስቴር አዲሱን ቤተሰባችንን ተቀላቀልን ማለት ነው።

በመጀመሪያዎቹ ወራት እኔና እህቴ ስላየናቸው አዳዲስ ነገሮች እናወራ ነበር። ለሁለታችንም ትልቅ ለውጥ ነበር። እንዲያውም ለተወሰነ ጊዜ የጫጉላ ሽርሽር ላይ እንዳሉ ሰዎች ሆንን። አሜሪካን ወደድናት።

ከተወሰኑ ወራት በኋላ ግን ሁሉም ነገር አስጠላኝ። ወደ አገሬ፣ ወደ ቤቴ መመለስ ፈለግኩ። ደፍሬ ባልናገረውም አዕምሮዬ ውስጥ የሚመላለሰው የቤተሰቦቼ ጉዳይ ነበር። እናቴ ናፈቀችኝ፤ ወንድሞቼ ናፈቁኝ፤ አገሬ ናፈቀኝ።

የማውቀውን ሕይወት፣ የማውቀውን ሰው፣ የለመድኩትን ምግብ መልሶ ማግኘት ብቻ ነበር የምፈልገው።

ኑሮ አልገፋ አለኝ፤ መላመድ አቃተኝ።

አስቴር ትንሽ ልጅ ስለነበረች እንደእኔ አልተቸገረችም፤ በቀላሉ ከአሜሪካዊ አኗኗር ጋር ተላመደች። ኢትዮጵያ ስላሉት ቤተሰቦቻችን ብዙ ትውስታ ስላልነበራት አዲሱን ሕይወት ማጣጣም ጀመረች። እኔ ግን ተረበሽኩ።

ትምህርት ቤት ስገባም ጓደኛ ማፍራት አልቻልኩም። ክፍል ውስጥ የነበሩት ልጆች እርስ በእርስ ይተዋወቃሉ። ባይተዋርነት ተሰማኝ። በዚያ ላይ እንግሊዘኛ አልችልም። እንዴት ከልጆቹ ጋር ልግባባ?

እንደ ልጅ ሳልጫወት ማደጌን ነግሬሽ የለ? እናም እነሱ በእረፍት ሰዓት ሲጫወቱ ግራ ገባኝ።

ኢትዮጵያ ሳድግ ከቤት ወጥቼ የምጫወትበት ጊዜ አልነበረኝም። ከእድሜዬ በላይ ብዙ ኃላፊነቶች ነበሩብኝ። ታዲያ አሜሪካ ስመጣ እንዴት ልጅ መሆን እንዳለብኝ ማወቅ አልቻልኩም። ጨዋታ መልመድ፣ ልጅነትን መማር ነበረብኝ።

አማረች እና እህቷ

የፎቶው ባለመብት, Amarech

የምስሉ መግለጫ,

አማረች እና እህቷ

የጉዲፈቻ ልጆችን ጓደኛ አደረኩ

ወደሚናፍቀኝ ሕይወት መቼ እንደምመለስ አለማወቄ ይረብሸኝ ነበር። አሜሪካ ያለው ነገር ሊማርከኝ አልቻለም። ምኑም ምኑም!

ሕይወትን በመጠኑ ያቀለለልኝ እንደኔው በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ የመጡ ጓደኞች ማፍራቴ ነው። እነዚህ ልጆች ኢትዮጵያ ሳለሁ ህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ አብረውኝ ኖረዋል።

እናም ጓደኞቼ አሜሪካ እንዳሉና ላገኛቸው እንደምፈልግ ለጉዲፈቻ ቤተሰቦቼ ነገርኳቸው። እኔና እህቴን ወደ አሜሪካ ያመጣን ኤጀንሲ ስልክ ቁጥራቸውን እና የኢሜል አድራሻቸውን ሰጠን።

ከሦስቱ ጓደኞቼ ጋር ዘወትር በስልክ እናወራ፣ እንገናኝም ነበር። ሁላችንንም በተመሳሳይ ነገር ውስጥ እያለፍን ስለነበረ እንግባባለን። አንዳችን ከሌላችን ምን መስማት እንደምንፈልግ እናውቃለን። ዝም ብለን እናወራለን. . . እናወራለን. . . እናወራለን. . . ስቃዩን በወሬ አስተነፈስነው። ወሬያችን እንዴት እንደረዳኝ ልነግርሽ አልችልም።

የአሜሪካን ሕይወት ለመላመድ ድፍን አራት ዓመት ወስዶብኛል።

ታናሽ እህቴ አብራኝ ባትሆን ኖሮ ምን እንደማደርግ አላውቅም። እዚ ያለችኝ ብቸኛ የሥጋ ዘመዴ ናት። አብሬያት ማደጌን እወደዋለሁ። ታናሼ ስታድግ፣ ስትመነደግ በቅርብ ማየት ደስ ይለኛል።

ምን ይናፍቀኝ እንደነበረ ልንገርሽ. . .

ከወንድሞቼ ጋር ብዙ አሳልፈናል። ታሪካችንን መልሶ መላልሶ ማሰብ ያስደስተኛል። ትውስ የሚለኝን ለእህቴ አወራላታለሁ። ትዝታዬን ለእሷ ማካፈል ታሪኬን መዝግቤ የማቆይበት መንገድ ነበር።

ከምንም በላይ ምን ይናፍቀኝ እንደነበረ ታውቂያለሽ? ከእናቴ ጋር የነበረን ግንኙነት። በጣም እንቀራረብ ነበር። ሁሉንም ነገር አብረን እናደርጋለን። እንደሚዋደዱ ጓደኛሞች ነበርን. . . እናቴን ሳላይ መኖር በጣም ከበደኝ።

አማረች ከወንድሞቿ እና ከእናቷ ጋር ስትገናኝ

የፎቶው ባለመብት, Amarech

የምስሉ መግለጫ,

አማረች ከወንድሞቿ እና ከእናቷ ጋር ስትገናኝ

በወንድሞቼ ሕይወት ውስጥ ቁልፍ የሚባሉ ክንውኖች እያመለጡኝ መሆኑ ውስጤን አደማው። ወንድሜ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲጨርስ. . . ታላቄ ከኮሌጅ ሲመረቅ እኔ አልነበርኩም። አሜሪካ ሆኜ ብዙ ውብ ቅጽበቶች እያለፉኝ መሆኑ እረፍት ነሳኝ።

አብሬያቸው መሆን ባለብኝ ቁልፍ ወቅት ተለየኋቸው!

በጄ አላልኳቸውም እንጂ፤ የጉዲፈቻ ወንድሞቼና እህቴ ሊቀርቡኝ ይሞክሩ ነበር። ልቀርባቸው፣ ልቀበላቸው ዝግጁ አልነበርኩም። አፍቃሪ እና ተግባቢ ነበሩ። ፍቅራቸውን በፍቅር መመለስ ግን አልቻልኩም። ፍቅሬን ኢትዮጵያ ላለው ቤተሰቤ መቆጠብ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር።

ያኔ ላቀርባቸው ያልቻልኩት የመተው ስሜት ይሰማኝ ስለነበረ ይመስለኛል። ማንም እንዲጠጋኝ አልፈልግም። ስሜቱ በህጻናት ማሳደጊያ ከዓመት በላይ ከመቆየት የመነጨ ይመስለኛል።

የጉዲፈቻ ቤተሰቦቼ ይወዱኛል። እኔ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቼን እወዳቸዋለሁ። እናቴና ወንድሞቼን ትቻቸው አሜሪካ ስለሄድኩ ሌላ አዲስ ፍቅር አልፈለኩም። ለአዲስ ፍቅር ቦታ አልነበረኝም።

ቤተሰቤን መፈለግ ጀመርኩ. . .

እኔ እና እህቴ ወደ አሜሪካ የተወሰድነው በ 'ክሎዝድ አዶፕሽን' ነበር። [ይህ ማለት በጉዲፈቻ የሚወሰዱ ልጆችና የጉዲፈቻ ቤተሰቦቻቸው ስለ ልጆቹ ወላጆች መረጃ አይሰጣቸውም።]

ከኢትዮጵያ ከወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ቤተሰቦቼ ምንም መረጃ ማግኘት አልቻልኩም። 2011 ላይ እናቴ አንድ ሪፖርት ደርሷታል። ሪፖርቱ ከጉዲፈቻ በኋላ ለወላጆች የሚሰጥ ነው። እና በሪፖርቱ የእኔ እና የእህቴ ፎቶ ለእናቴ ተሰጥቷታል።

2012 ላይ እኔ እና እህቴን ከጉዲፈቻ ቤተሰቦቻችን ጋር ያገናኘን ኤጀንሲ ተዘጋ። ስለ ቤተሰቦቼ ማንን ልጠይቅ? ስለእነሱ ምንም ሳልሰማ ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ። ብቸኛ አማራጬ ፌስቡክ ላይ መፈለግ ሆነ። ግን ምንም ላገኝ አልቻልኩም።

በሕይወት መኖራቸውን፣ ደህና መሆናቸውን ማወቅ አለመቻሌ ያስጨንቀኝ ነበር። አለቅስ ነበር። ስለቤተሰቦቼ ማሰብ ማቆም ስላልቻልኩ ፍለጋዬ ፍሬ ባያፈራም ገፋሁበት። እንደው አንድ ቀን ኢንተርኔት ላይ አገኛቸዋለሁ የሚል ህልም ነበረኝ።

በስተመጨሻ ግን ተስፋ መቁረጥ ጀመርኩ. . .

ቤተሰቦቼን ማግኘት እንደምፈልግ ለጉዲፈቻ ቤተሰቦቼ ነገርኳቸው። ቤተሰቤን ሳላገኝ መኖር አልችልም አልኳቸው። የጉዲፈቻ አባቴ 18 ዓመት ሲሞላኝ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚወስደኝና ቤተሰቦቼን እንደምንፈልጋቸው ቃል ገባልኝ። ግን ከ18ኛ ዓመት ልደቴ በፊት ሕይወቴን የለወጠ ዜና ደረሰኝ።

ለካ እናቴም እኔ እና እህቴን እየፈለገችን ነበር

አንድ ቀን 'መላው ቤተሰብ ይሰብሰብ' ተባለ። የጉዲፈቻ ቤተሰቦቼ ሁላችንንም አንድ ላይ አድርገው 'አስደሳች ዜና አለን' አሉ። እናቴ እኔና አስቴርን እያፈላለገችን እንደሆነ ነገሩን።

እናቴ የጉደፈቻ ሪፖርቱ ሲቋረጥባት እኛን መፈለግ ጀምራ ነበር። ወላይታ ሶዶ ውስጥ ለምትገኝ አንዲት ማኅበራዊ ሠራተኛ ስለእኛ ነገረቻት። ፎቷችንን ሰጠቻት። ቅጽል ስሜ አያኔ መሆኑን፣ ጀርባዬ ላይ 'ማርያም የሳመችኝ' ምልክቱ እንዳለ ሳይቀር አውርታላታለች. . . ያላትን መረጃ ባጠቃላይ ዘረገፈችላት ብልሽ ይቀለኛል. . .

ማኅበራዊ ሠራተኛዋ 'ቤተሰብ ፍለጋ' በሚባል ድርጀት በኩል የጉዲፈቻ ቤተሰቦቼን አገኘቻቸው። ይሄ ሀሉ ሲነገረኝ የደስታ ሲቃ ተናነቀኝ። በጣም ደንግጬም ነበር። እኔ ለዓመታት ስፈልጋቸው ነበር። ታዲያ እንዴት እኔ ሳላገኛቸው ቀድመው አገኙኝ? ያልጠበቅኩት ነገር ነበር።

አማረች፣ እናቷ እና ታላቅ ወንድሟ

የፎቶው ባለመብት, Amarech

የምስሉ መግለጫ,

አማረች፣ እናቷ እና ታላቅ ወንድሟ

ቀጥሎ ምን እናድርግ? ደብዳቤ እንጻፍ? ጥያቄዬን ማከታተሉን ተያያዝኩት. . . እህቴም ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ ተጋብታ ነበር። ዝም ብላ እኔን ትከተል ጀመር።

ከዚያም ደብዳቤ ጽፈን ለቤተሰቦቼ ላክልናቸው። ከሁለት ሳምንት በኋላ ፎቶና ቪድዮ ላኩልን። በዚያ ቅጽበት ሕይወቴ እስከወዲያኛው ተቀየረ።

ከቤተሰቦቼ ጋር ከተገናኘሁ ስምንት ዓመት ተቆጥሮ ነበር። እናቴ እና ታላላቅ ወንድሞቼን ስፈልጋቸው እነሱም እየፈለጉኝ ነበር። እኔንም አስቴርንም። አድራሻቸውን ካገኘሁ በኋላ ያለማቋረጥ ማውራት ጀመርን።

ወደ ሶዶ ተመለስኩ. . .

ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ለመብረር ትኬት ቆረጥኩ። እህቴ 'ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ዝግጁ አይደለሁም' ስላለቺኝ የሄድኩት ብቻዬን ነበር።

ልክ አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ስደርስ በጣም ተጨነቅኩ። ታላቅ ወንድሜ መጥቶ እጄን ቢይዘኝ ተመኘሁ. . . አይገርምም መጀመሪያ ያገኘሁት እሱን ነበር። አቅፎኝ ሊለቀኝ መሰለሽ?

አዲስ አበባ ውስጥ በቆየንባቸው ቀናት እጄን ይዞ ነበር የሚንቀሳቀሰው፤ አለቀቀኝም። እንደ ልጅነታችን ዳግመኛ ተሳሰርን። ከዚያ ወደ ሶዶ ሄድን።

እናቴን ሳያት ዝም ብዬ ማልቀስ ጀመርኩ፤ እሷም አለቀሰች። የደስታ እንባ አነባን። ከአምስት ደቂቃ በላይ ሳንላቀቅ ተቃቅፈናል። እናቴ ስማኝ ልትጠግብ አልቻለችም። እውነት እውነት አልመስልሽ አለኝ. . .

ሁሉም ነገር እንደ ድሮው ተመለሰ። የማውቃቸውን ቤተሰቦቼን አገኘሁ። ሶዶ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስልም እንግዳ የሆንኩ አልመሰለኝም። ሦስት ሳምንትን አሳለፍኩ።

በጉዲፈቻ ባልሰጥ ኖሮ ሕይወቴ ምን ሊመስል እንደሚችል ከእናቴ ጋር አወራን። እኔ እና እህቴን ለጉዲፈቻ መስጠቷ እንደማይጸጽታት ነግራኛለች። እውነት ነው በሕይወቷ ካደረገቻቸው ነገሮች ከባዱ እኛን ለማደጎ መስጠት ነበር። ቢሆንም 'ለጉዲፈቻ የሰጠኋችሁ ያለ ምክንያት አይደለም፤ እንደዚህ በችግር እንድትኖሩ አልፈልግም' አለችኝ።

በእርግጥ ኤጀንሲው ተዘግቶ እኛን ለማግኘት ስትቸገር ለጉዲፈቻ በመስጠቷ ተጸጽታ ነበር። ልጆቿ እንዴት እየኖሩ እንደሆነ ማወቅ ባለመቻሏ ለሳምንታት እንዳለቀሰች፣ በጣም እንደተጎዳችም ጓደኛዋ ነገረችኝ።

እናቴ እንደእኔው እየተሰቃየች እንደነበር ማወቄ ልቤን ሰብሮታል። ለእኔ አሜሪካ መኖር ጥሩ ነው። ቁሳዊ ነገር አላጣሁም። ቤተሰብን ግን አይተካም። የሆነ ነገር እንደጎደለኝ ይሰማኝ ነበር። ለካ እናቴም እንደኔው ነበረች. . .

አሁንማ ሕይወቴ ውብ ነው

አሁን የመጀመሪያ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ ነኝ። ቢዝነስ እያጠናሁ ነው። የጉዲፈቻ ቤተሰቦቼን በጣም እወዳቸዋለሁ። እውነቱን ለመናገር ከእነሱ ጋር ለመላመድ ጊዜ ወስዶብኛል። የማያውቁትን ሰው እማዬ፣ አባዬ፣ እህት ዓለም ወንድም ዓለም ማለት ከባድ መሆኑን አልክድም።

ግንኙነታችንን ለመገንባት ጊዜ ቢወስድብንም አሁን ቤተሰብ ነን።

እናቴ እኔን እና እህቴን ለማደጎ መስጠቷ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብዬ አስባለሁ። ምንም እንኳን መጀመሪያ ላይ ሕይወት ቢከብደኝም. . . እናቴን ተረድቻታለሁ። በጉዲፈቻ ባትሰጠኝ ኖሮ ብዙ መከራ ይጠብቀኝ ነበር።

ከጉዲፈቻ ወንድሞቼ እና ከእህቴ ጋር እንቀራረባለን። ኢትዮጵያ ካሉት ወንድሞቼ ጋርም እንዲሁ። ወንድሞቼን ሳዋራቸው የሆነ ጉልበት አገኛለሁ። ምንም ነገር ላሳካ እንደምችል ይሰማኛል። ያበረቱኛል። ያጠነክሩኛል።

ምን እንደማስብ ታውቂያለሽ? ምናልባትም የጉዲፈቻ ልጅ ያልሆነ ሰው ይሄ አይገባው ይሆንል. . . የጉዲፈቻ ልጆች ስለ ወላጆቻቸው ማወቅ አለባቸው። 'ማንን ነው የምመስለው?' 'ከየት መጣሁ?' እያሉ ሕይወትን መግፋት የለባቸውም። በጥያቄ መሞላት፣ በናፍቆት መማቀቅ የለባቸውም።

ቤተሰቦቼን ካገኘኋቸው በኋላ ሕይወቴ ተቀይሯል። ደስተኛ ሰው ሆኛለሁ። አሁን የማስበው ዲግሪዬን አግኝቼ ጥሩ ሥራ ስለመያዝ ነው። ያለፈ ሕይወቴ ጥያቄዎች ስለተመለሱ ስለ ወደፊቴ ማሰብ እችላለሁ።