ዘሩባቤል ሞላና በአነቃቂ መንፈስ የታሸው 'እንፋሎት' አልበሙ

የዘሩባቤል ሞላ እንፋሎት የተሰኘው አልበም ሲዲ

ዘሩባቤል ሞላ፤ እንፋሎት በተሰኘ አዲስ አልበም ብቅ ብሏል። እንፋሎቱ ደግሞ ከአዲስ አበባ እስከ ናይሮቢ፤ ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ ሁሉን እያዳረሰ ነው።

አልበሙ 15 ሙዚቃዎችን ይዟል። ሃገርን፣ ፍቅርን፣ ጉበዝናን፣ ሕይወትን፤ በመንፈሳዊ ቃና ይዳስሳል፣ ያነሳሳል፣ በግጥም ብቻ ሳይሆን በዜማም ይፈውሳል፤ እንፋሎት።

እንፋሎት መቼ ተፀነሰ? ቢቢሲ አማርኛ ለዘሩባቤል ሞላ ያቀረበው የመጀመሪያው ጥያቄ. . .

«ያው እንግዲህ አርቲስት ስትሆን፤ ወይም ደግሞ ጊታር ይዞ እንደሚጫወት አንድ ዘፋኝ ራስህን ካየህ አንድ ዓላማ ይኖርሃል፤ አልበም የሚባል። ነጠላ ዜማም ሊሆን ይችላል። ይህንን ሥራ ለመሥራት ወደ አምስት ዓመት ገደማ ፈጅቶብናል። ወደ መጨረሻ አካባቢ ላይ የገቡ አዳዲስ ሥራዎችም አሉ። ሙዚቃዎቹን ከሠራን በኋላ አሁን በቅቷል፤ እንፋሎቱ ወጥቷል፤ ሰው ሊመገበው ወይም ሊሰማው ይገባል ብለን ስናስብ ነው ይህንን አልበም ያወጣነው። ግን በጠቅላላው አምስት ዓመት ገደማ ፈጅቶብናል፤ ያው አንዱን ስንጥል አንዱን ስናነሳ።»

ድምፅ ፈታዮቹ መረዋዎች

የመካኒሳ ሴሚናሬ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ልጅ ነው ዘሩባቤል። መቅረዝ የተሰኘው የፕሮቴስታንት እምነት የሙዚቃ ቡድን አባልም ነበር። ሚካኤል በላይነህ 'የነገን ማወቅ' ብሎ ባቀነቀነው ሙዚቃ ቪድዮ ክሊፕ ላይ ጊታሩን ይዞ ሲወዛወዝ ብዙዎች ተመልክተውታል። ወገኛ ነች፣ እስከመቼ፣ እንደራሴ፣ ልብሽ ይፋካ. . . ከዘሩባቤል ቀደምት ሥራዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

«ሙዚቃን በሥርዓቱ የያዝኩት፤ ወይም የእኔ የተሰጠኝ ችሎታዬ ይሄ ነው ብዬ ያመንኩበት ሰዓት መቅረዝ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ እያለን ነው፤ ረዘም ያለ ጊዜ ነው። አስራምናምን ዓመት ገደማ መሆኑ ነው።»

«ሁሉም ሥራዎቼ መንፈሳዊ ናቸው. . .»

ዘሩባቤል ሙዚቃን 'ሀ' ብሎ የጀመረው መቅረዝ ውስጥ ነው፤ መንፈሳዊ ሙዚቃ በመጫወት። 'መንፈሳዊ ተብሎ ከሚታወቀው የሙዚቃ ዘርፍ ወደ ዓለማዊው መጥቻለሁ ብለህ ታስባለህ?'

«እውነት ለመናገር ለእኔ ሁሉም መንፈሳዊ ናቸው። ዓለማዊ ተብሎ የሚታሰበውም መንፈሳዊ ነው። የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድነው የሚለው ነው። ዓለማዊ የተባለውም እኮ ዓለማዊ ያስባለው ከበስተጀርባው ያስተላለፈው ደስ የማይል መልዕክት አለ ማለት ነው።»

እንፋሎት፤ መነሳሳትን የሚሰብኩ፤ ጥንካሬን የሚያጋቡ፤ መልካምነትን የሚያስተጋቡ ሙዚቃዎች ስብስብ ነው። እንደው ይህ መንፈስ የመጣው ሥራዎቼ መንፈሳዊ ናቸው ብለህ ከማሰብህ ነው ወይ? ለዘሩባቤል ያነሳንለት ጥያቄ።

ባህልን በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ የቀመመው ሮፍናን

«አዎ። ሰው አልበምህን ሰምቶ ያዘነ እንዲፅናና፣ የደከም እንዲበረታ፣ የወደቀ እንዲነሳ፣ በአንተ ዘፈን፤ አንተ በሠራኸው ሙዚቃ ይህንን መልዕክት ማስተላለፍ ካልተቻለ. . .እንግዲህ ምንድነው መፈጠራችን ዋናው ዓላማው። ሰው ሲሰማው መፅናናትን ካላገኘ፤ የአልበም ማውጣት ምንድነው ጥቅሙ? ይሄ የእኔ እምነት ነው ከድሮም ጀምሮ። አንድ የሆነ ይዘት ያለው ሙዚቃ ይዘህ መጥተህ ሰው ሲስቅ፣ ሲዝናና፣ ሲነሳሳ ማየት በጣም ትልቅ ደስታ ነው፣ ዕድልም ነው፤ እውነት ለመናገር።»

ዘሩባቤል ከአልበሙ በፊት የለቀቃቸው ነጠላ ሥራዎቹ በቪድዮ ክሊፕ ተቀምረዋል። ታድያ እኒህ ቪዲዮዎች በጎ መልዕክትን ለማስተላለፍ ያለሙ ናቸው።

«አንዳንዴ ቤት ቁጭ ብዬ ከቤተሰብ ጋር የማያቸው የሙዚቃ ክሊፖች እጅግ በጣም የሚያሳፍሩና አባቴን ቀና ብዬ እንዳላየው የሚያደርጉ ናቸው። እኔ የምሠራቸው ክሊፖች ማንም ሰው ሊያያቸው የሚችሉ፤ እናት ከልጇ ጋር ቁጭ ብላ፤ አባት ከልጁ ጋር ቁጭ ብሎ ሊያያቸው የሚችላቸው መሆን አለባቸው ብዬ ነው የማምነው። ቤተ-ዘመድ እያየው የማያፍርበት ቪዲዮ መሆን አለበት። መልዕክት ያለው ቪዲዮ መሥራት ነው የሚያስደስተኝ።»

መንፈሳዊና ዓለማዊ ሙዚቃ የምትለየው ቀጭን መመር

ዘሩባቤል 'አባቴ ዘፈን ሐጥያት ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ነው' ሲል አጫውቶኛል። ይህ እምነታቸው ደግሞ የመጣው ከመፅሐፍ ቅዱስ ነው። ከእንደዚህ ዓይነት ቤተሰብ ውጥቶ 'ዓለማዊ' ተብሎ ወደሚታሰበው ሙዚቃ መምጣት ነገሩን አያፈርሰውም ወይ? በመንፈሳዊ እና ዓለማዊ ሙዚቃ መካከል ያለችው ቀጭን መሥመር ምንድን ነች? ለዘሩባቤል የቀረበ ጥያቄ።

«እኔ ምንድነው የማምነው. . . ዘፈን ሐጥያት አይደለም እያልኩ አይደለም። ለምሳሌ አመፅን የሚያነሳሱ ዘፈኖች፣ አድመኝነት የሚያነሱና ዝሙትን የሚያበረታቱ ሐጥያት የሆኑ ዘፈኖች አሉ። ግን መልካም ነገር ዘፍነህ፤ ፍቅርን ሰብከህ፤ የዋህነትን አስተምረህ ሐጥያት የሚሆንበት መንገድ እኔ አይታየኝም። ሳነብም በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የሚቃወመኝ ቦታ የለም። ማንም ሰው የሠራው ሥራ የሚያንጽ ከሆነ ይሄ መልካም ዘፈን ነው።»

"ኢትዮጵያዊነቴን ያገኘሁት ሙዚቃ ውስጥ ነው" አቨቫ ደሴ

«ይህን ቀጭን መስመር የሆነ ቀን ሳነብ ገባኝ፤ ተረዳሁ። አንደኛው የአንደኛውን ጎሣ የማይነካበት፤ አንደኛው የአንደኛውን ሚስት የማይነካበት፤ አመፅ የማያስነሳበት የትኛውም ዘፈን ልክ ነው ማለት ነው።»

«'እንደ ቢራቢሮ ሁሉን አትቅሰሚ' ሲል ምክር እየሰጠ ነው፤ ሌላውን እንዳትመኚ እኮ እያላት ነው። አንድ ሰው ይሄ ሐጥያት ነው ሲኦል ያስገባሃል ካለ አንድ የሆነ የሳተው ነገር አለ ማለት ነው። 'ተማር ልጄ እያለ' የሚመክርህን ይህ ሐጥያት ነው የሚል ከሆነ አሁንም ችግር አለ ማለት ነው። አባቴ ባይቃወመኝም እኔ ማለት የፈለግኩት ሃሳብ እየገባው የመጣ ይመስለኛል።»

ባቲና ብሉዝ

ብሉዝ [ስም ቀየርንለት እንጂ ባቲ እኮ ነው ይላል ዘሩባቤል]፣ ጃዝ፣ ለስለስ ያለ ሮክ. . .እንፋሎት ውስጥ ከምናደምጣቸው ቀለመ-ብዙ ዜማዎች ጥቂቶቹ ናቸው። እኒህ ዜማዎች ለኢትዮጵያዊ ጆሮ እምብዛም የተለመዱ አይደሉም። ዘሩባቤል ግን ይዟቸው ብቅ ብሏል፤ ለዚያውም በመጀመሪያ አልበሙ። መሰል ዜማዎችን ይዞ በመጀመሪያ አልበም መምጣት እንደው ድፍረት አይጠይቅ ይሆን?

ተፈራ ነጋሽ፡ "በነገራችን ላይ ሙዚቃ አልተውኩም"

«እውነት ለመናገር ይህንን ነገር አንትም ሆነ ሌሎች አድማጮች ሲሉት ነው የሰማሁት እንጂ እኔ አላውቀውም። እውነት ለመናገር ለእኔ የምዘፍነው አዘፋፈን ሃገርኛ፣ ኢትዮጵያዊኛ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። ብሉዝን ለመሥራት ስፈልግ ብሉዝ አድርጌ እሠራለሁ። ለምሣሌ 'ውሃና ዘይት' የተሰኘወ ሥራዬ የኢትዮጵያ ዜማ ሆኖ 'ሳውንዱ' ግን ብሉዝ እንዲሆን አድርገነዋል። ለእኔ ግን ባቲ ነው። ስሙን ቀያየርነው እንጂ ባቲ ስትሰማ ብሉዝ ሰማህ ማለት ነው። እኔ ኢትዮጵያዊኛ አድርጌ ለመዝፈን የማስበውም፤ አድርጊያለሁ ብዬ የማምነውም እንደዚያ ነው።»

«ሳድግም እንደዚህ ዓይነት ሙዚቃ እየሰማሁ ነው ያደግኩት። አጎቴ እንዲህ ዓይነት ዜማ ይከፍት ነበር። ጋሽ ጥላሁንን፣ እነ ጋሽ መሃሙድን፣ እነ ጋሽ አለማየሁን . . .ሌሎችንም ትልልቅ አርቲስቶችን ይከፍት ነበር። ወታደር ነበር፤ ዶክተርም ነው። ካርታ እየተጫወተ እኒህን ሙዚቃዎች ያደምጥ ነበር። ኢትዮጵያዊ ቃና እየሰማሁ ነው ያደግኩት፤ እኔም ደግሞ አሁን ሠራሁት ብዬ የማስበው ይህንኑ ነው።»

ጊታር ተጫዋቹ ዘሩባቤል

'ኢትዮጵያዊያን ዘፋኞች መዝፈን ብቻ እንጂ የሙዚቃ መሣሪያ አይጫወቱም' በአለፍ ገደም የምንሰማው ትችት ነው። ይህ ሃሳብ ጊታር አሳምሮ ለሚጫወተው ዘሩባቤል አንድ ጥያቄ እንዳነሳ አስገደደኝ። የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ነገሮችን ቀለል ያደርጋል?

«ምንድነው መሰለህ እያየህ ማከም እና ዓይንህን ጨፍነህ እማከም ማለት ነው፤ ለእኔ። አንድ የሙዚቃ መሣሪያ አወቅክ ማለት የዜማው አካሄድ ይገባሃል። የሚያቀናብርልህ ሰው የሚናገረው ቋንቋ ምን እንደሆነ ይገባሃል። ታላላቅ የሚባሉ ዘፋኞች፤ ትልልቆቹን ጨምሮ ከብዙ ሂደት በኋላ የሙዚቃው ቋንቋ፤ የሙዚቃው አካሄድ ስለገባቸው ነው በሰሉ የሚያስብላቸው። የሙዚቃ መሣሪያ ማወቅ ይህንን ነገር ያሳጥርልሃል። መዝፈን የሚፈልግ ሰው የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ቢማር በጣም ይጠቅመዋል ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ እኔ ጊታሬን ይዤ ቁጭ ባልኩበት ዜማ ይመጣልኛል። ጊታሬን ባልይዝ ላይመጣልኝ ይችላል። ቢመጣም ያ ነፍስን የሚነካ፤ ውስጡ ነፍስ ያለውን ነገር ላትሠራ ትችላለህ። ይሄ የእኔ አመለካከት ነው።»

Image copyright YouTube

የልፋት ውጤት ማ

የዘሩባቤል እንፋሎት ኢትዮጵያ ውስጥ በሲዲ በውጭ ሃገራት ደግሞ በበይነ መረብ ባሉ እንደ 'አይቲዩንስ'፣ 'ስፖቲፋይ' እና 'ሳውንድክላውድ' ዓይነት የሙዚቃ ሥራዎች ማጋሪያ ላይ እየተኮመኮመ ይገኛል።

እንደው አንድ ነገር መረዳት ፈለግኩና ለዘሩባቤል ሃሳቤን ጀባ አልኩ። 'አዲስ አበባ ውስጥ መኪና ውስጥ ሆነህ፣ አልበምህ በሲዲ ሲዞር ስታይ፤ ሰዎች ሲዲህን እያገላበጡ ሲመለከቱ ስታይ፤ ምን ዓይነት ስሜት ተሰማህ ይሆን?'

ሙዚቃ ሳይሰሙ መወዛዋዝ ይችላሉ?

«እህ. . . እውነት ለመናገር ብዙ ልፋት፣ ትግል፣ የሰው ፊት ማየት፣ ንቀት ማየት. . .እንግዲህ ይህን የምናገርበት ምክንያት ለማነፃፀርና ሰውን ስለሚያስተምር እንጂ አሁን እዚያ መንፈስ ውስጥ ሆኜ አይደለም። ካለፍክበት መከራ ወይም ደግሞ ከተራራው ትልቅነት አንፃር ስታየው፤ አልበሙ ሰዎች እጅ ላይ ደርሶ፤ ሰዎች አገላብጠው ወደዉት ስታይ በጣ...ም የተለየ ስሜት አለው። እንደውም ለተወሰነ ጊዜ ስሜታዊ አድርጎኝ ነበር። ሲዲውን አዟሪዎች እጅ ላይ ሳይ፣ ፖስተሮች ተለጥፈው ሳይ፣ በቃ እግዚአብሔርን አደንቅኩ። ለሁሉም ጊዜ አለው የሚባለውን በፊት በመስማት ነበር የማውቀው አሁን ግን በዓይኔ አየሁት። ለእኔ በጣም ለየት ያለ ስሜት ነው ያለው።»

እንፋሎት አልበም ብዙ የሙዚቃ ሰዎች ተሳትፈውበታል። በያምሉ ስቱዲዮ የተሠራው እንፋሎት ዘሩባቤል፤ ከግጥምና ዜማ ደራሲነት በተጨማሪ ጊታር በመጫወት ተሳትፎበታል። ሚክሲንግ፣ ማስተር እና ቅንብሩን የዘሩባቤል ወንድም የሆነው ወጣቱ የሙዚቃ ሰው ያምሉ ሞላ ተወጥቶታል። ሌላኛው ጉምቱ የሙዚቃ ሰው ኤልያስ መልካ ደግሞ በዜማ በግጥም እና በማቀናበር እንፋሎት ላይ አሻራውን አሳርፏል። ዳዊት ተስፋዬ ሌላኛው የዜማና ግጥም ደራሲ ነው። ሳክፎኑን አብይ፣ ማሲንቆውን ደግሞ ሃዲንቆ ተጫውተውታል።

ከፍ. . .የሚያደርጉ ዜማዎች

እንፋሎትን ማድመጥ አለብኝ ብሎ የመጀመሪያውን 'ትራክ' የከፈተ ሰው አንድ ነገር ማስተዋሉ ግድ ነው። የዘሩባቤል ግጥሞች ብቻ ሳይሆኑ ዜማዎቹም ጭምር መንፈሳዊ መነቃቃትን ለመስበክ ቆርጠው እንደተነሱ።

አውታር - አዲስ የሙዚቃ መሸጫ አማራጭ

«ለምሳሌ ክትፎን መብላት የለመድነው በጣባ ነው አይደል? ግጥሙን እንደ ክትፎ እይልኝ [ብዙዎቻችን ክትፎ እንወዳለን ብዬ ነው ክትፎ ያልኩት]፤ ጣባውን ደግሞ እንደ ዜማ አስብልኝ። አንድ የምትወደውን ምግብ በተገቢው ሁኔታ ሲቀርብ የመብላት ስሜትን ከፍ ያደርጋል። ልክ እንደዚያው የሚያምር ግጥም ሠርተህ ለዜማው ካልተጨነቅክ አድማጭህ ይጨነቅብሃል። ዜማ ውስጥ ነብስ አለች፤ ያንን ተረድተህ መሥራት መቻል አለብህ። ዘፈኑ ሳይጨንቅህ ጀምሮ፤ ሳታስበው ከፍታ ላይ ወጥተህ ሳታስበው ማለቅ አለበት።»

ዘሩባቤል እኔ ሙዚቃዬን የሠራሁት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ይላል። ዘፈኖቹ ማንም በዕድሜም ሆነ በሌላ መለያ ሳይገደብ እንዲያደምጣቸው ይፈልጋል። እስካሁንም ሥራዎቹን በመግዛት እያደመጡ ላሉት ሰዎች «ጎንበስ ብዬ ምሰጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ፤ እግዚአብሔር ይስጥልኝ!» ይላል።

ተያያዥ ርዕሶች