ለ20 ዓመታት ዴንማርካዊት እህቱን የፈለገው ኢትዮጵያዊ ሀኪም

የፎቶው ባለመብት, Mulugeta Asmamaw

የምስሉ መግለጫ,

ሙሉጌታ እና እህቱ ከ20 ዓመት በኋላ ሲገናኙ

ስትወለድ ቤተሰቦቿ ያወጡላት ስም ትዕግስት ነበር፤ ትዕግስት አስማማው።

ትዕግስት የአንድ ዓመት ህጻን እያለች እናቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። አባቷ እሷንና የተቀሩትን ሦስት ልጆቻቸውን ማሳደግ ስላልቻሉ ትዕግስትን ለጉዲፈቻ ሰጧት።

በጉዲፈቻ የት አገር እንደተወሰደች፣ ማን እንደወሰዳት ግን የሚያውቁት ነገር አልነበረም። የትዕግስት ታላቅ ወንድም ሙሉጌታ አስማማው ነፍስ ካወቀበት ጊዜ አንስቶ እህቱን ከመፈለግ አልቦዘነም።

ሙሉጌታ አሁን ባለትዳርና የአንዲት ልጅ አባት ሲሆን፤ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የውስጥ ደዌ ስፔሻላይዜሽን ይማራል።

ታሪኩን እንዲህ አጫውቶናል. . .

የአሶሳው ልጅ- ሙሉጌታ

ለቤተሰቤ ሁለተኛ ልጅ ነኝ። ከእኔ በላይ ታላቅ እህቴ አለች። ከእኔ በታች ወንድሜና ትዕግስት አሉ። ሁላችንም የተወለድነው በሦስት ዓመት ልዩነት፤ አሶሳ ውስጥ ነው።

የአባቴ ወንድሞች አዲስ አበባ ይኖሩ ስለነበረ ከአሶሳ ወደ አዲስ አበባ ሄድን። አዲስ አበባ ገብተን ብዙም ሳንቆይ እናቴ ታመመች። ታናሽ እህታችን አንድ ዓመት ሊሞላት አካባቢ ነው እናታችን ያረፈችው።

እናቴ ከሞተች በኋላ አባቴ እኛን ማሳደግ ከበደው። አባቴ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ቄስ ነበር። ቋሚ ቤት ስላልነበረን አራታችንንም ይዞ ከቦታ ቦታ መዘዋወር አልቻለም።

ያኔ እህቴ በጣም ታማበት ነበር፤ ኩፍኝ መሰለኝ። አባቴ አማራጭ ሲያጣ እህቴን ስድስት ኪሎ አካባቢ ለሚገኙ ሚሽነሪዎች ሰጣት። እኔ ስድስት ዓመቴ ነበር። ብዙ ነገር አላስታውስም. . .

ትንሽ ትንሽ ትውስ የሚለኝ እህቴ ስታለቅስ ነው። በጣም የማዝነው የእናቴ ምስል ራሱ ብዙ ትዝ አይለኝም። እህቴ ህጻን እያለች ስታለቅስ ግን የተወሰነ ትዝ ይለኛል. . .

አባቴ ስለ ሚሽነሪዎቹ የነገረኝ ካደግኩ በኋላ ነው። ቀጨኔ መድኃኔዓለም አካባቢ ሳለ፤ ሰዎች ሚሽነሪዎቹ የት እንዳሉ ጠቆሙት። እህቴን ከሞት ሊያተርፋት የሚችለው ለእነርሱ በመስጠት ብቻ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር።

አድጌ ላቀረብኩለት ጥያቄ መልሱ 'ልጄ እጄ ላይ ከምትሞት. . . ሁላችሁም ከምትሞቱብኝ. . . ያለኝ አማራጭ እሷን መስጠት ብቻ ነው' የሚል ነበር።

ሚሽነሪዎቹ ልጁን ተመልሶ መጠየቅ እንደማይችል ሲያስጠነቅቁት ተስማማ። እህቴን ሰጥቷት ሲመለስ ግን ታላቅ እህቴ ተቆጣች፤ መጨቃጨቅ ጀመሩ። በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ሳምንት ወደ ሚሽነሪው ሄዶ 'ልጄን መልሱልኝ' ሲል ውጪ አገር እንደሄደች ነገሩት።

ባዶ እጁን ወደ ቤት ተመለሰ!

በወቅቱ እህቴ ከአባቴ ጋር ትጣላ እንደነበር ነግራኛለች። 'ካላመጣሀት' እያለችው ትግል ውስጥ ገቡ።

አባቴ እናታችንን ሲያጣ ብዙ ነገሮች ድብልቅልቅ ብለውበት ነበር። የልጁ መሄድ ሲጨመርበት ደግሞ የሚያደርገው ጠፋው። ልጁ ወዴት አገር እንደሄደች፣ ማን እንደወሰዳት የሚያውቀው ነገር አልነበረም።

እህቴ እንደነገረችኝ ከሆነ፤ አባቴ ሚሽነሪዎቹን ተመላልሶ ቢጠይቃቸውም ስለ ልጁ ምንም ፍንጭ አላገኘም።

ለጉዲፈቻ ሲሰጣት በጣም ታምማ ስለነበረ በሕይወት የምትቆይም አልመሰለውም። እኔ ግን ከፍ እያልኩ ስመጣ እህቴ አንዳለች ቀልቤ ይነግረኝ ነበር። የሆነ 'ሴንስ' የምታደርጊው ነገር አለ አይደል?. . .

የፎቶው ባለመብት, Mulugeta Asmamaw

የምስሉ መግለጫ,

የሙሉጌታ እህት

ሙሉጌታ- የመርካቶው አትክልት ነጋዴ

አባቴ ለእኛ ባይነግረንም በእህቴ ምክንያት ሰላሙን አጥቷል። በጣም ይጨነቅ ነበር። ሁሌም የሚፀፀትበት ነገር የእርሷ መሰጠት ጉዳይ ነበር። ነገሮች የተበለሻሹበት ከዛ በኋላ ይመስለኛል። አዕምሮውን ማረጋጋት አልቻለም። መጠጥም ስለሚወስድ በቤተሰቡ መካከል ትንሽ አለመግባባት ነበር።

አባቴ የቀረነውን ልጆችም አንድ ላይ ማሳደግ ከበደው።... በቃ ተበታተንን።

መጀመሪያ ላይ ከአባቴ ታላቅ ወንድም ጋር መኖር ጀመርኩ። ግን ብዙ አልቆየሁም። መርካቶ ጀላቲ [በረዶ] ከሚሸጡ ሴት ጋር እኖር ጀመር። እኔም ጀላቲ እየሸጥኩ ማለት ነው። ሴትየዋ የቀጠሩኝ በሠላሳ ብር ነበር. . . ጀላቲ ለመሸጥ በወር 30 ብር. . .

ከዚያ አንዲት ትልቅ ሴት 'እኔ አሳድገዋለሁ' ብለው ወሰዱኝ። አትክልት ነጋዴ ነበሩ። እኔም ካሳደጉኝ እናቴ ጋር አትክልት እየሸጥኩ የማታ ትምህርት ቤት ገባሁ።

የምሠራው እንደ ልጅ አልነበረም። ጫናው ከባድ ነበር። ማለዳ 12 ሰዓት ተነስቼ ወደ ሥራ እሄዳለሁ። እስከ 11 ሰዓት ሠርቼ ወደ ትምህርት ቤት፤ ማታ 2፡30 ላይ ወጥቼ ደግሞ ወደ ቤት. . . የእለት ከእለት ሕይወቴ ይህ ነበር።

እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ እየነገድኩ ተማርኩ። ስምንተኛ ክፍል ስገባ በመምህራኖቼ ግፊት ወደ ቀን ተማሪነት ተዘዋወርኩ። የቀን እየተማርኩ ክረምት ላይ እሠራ ነበር። የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ በትርፍ ጊዜዬ አስጠና ነበር።

ያሳደጉኝ እናቴ በዛሽ ኃይሌ አሁን በሕይወት የሉም። እዚህ ለመድረሴ ትልቅ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ቤተሰቦቼ መካከል ናቸው። አብረውኝ ያደጉት እህቶቼ ሙሉ ዳኜ፣ ዝናቧ ዓለማየሁ፣ መሰረት ካሳና ትዕግስት ዓለማየሁ ይባላሉ። እነሱና ሌሎችም ቤተሰቦቼ አሁን ያለሁበት ለመድረሴ ምክንያት ናቸውና አመሰግናቸዋለሁ።

እህቴ ትኖር የነበረው ደግሞ ከአንዲት ነጋዴ ጋር ነበር። ለስድስት ወር እኔ ጋር መጥታ ኖራ ነበር. . . ከዚያ በኋላ ቶሎ ወደ ትዳር ገባች። የመጀመሪያ ልጇን ስትወልድ 17 ዓመት የሚያልፋት አይመስለኝም።

ታናሽ ወንድሜ ለተወሰነ ጊዜ ከአባቴ ጋር ኖሯል። ግን አልተስማሙም። ወንድሜ አፈንግጦ ወጣና ብቻውን መኖር ጀመረ። የወንድሜ አስተዳደግ ከባድ ነበር። አዋዋሉ ጥሩ አልነበረም። አሁንም ያለበት ሁኔታም ጥሩ አይደለም።

እኔ ደህና ኑሮ እየኖርኩ፣ ጥሩ አልጋ ላይ እየተኛሁ ወንድሜ ውጪ እያደረ እንደሆነ ማሰብ ለእኔ ከባድ ነበር። መርካቶ እየሠራሁ ታናሼን በገንዘብ ለመደገፍ እሞክር ነበር።

እኔም፣ እህቴም፣ ወንድሜም መርካቶ ስንሠራ እንገናኝ ነበር። ግን አንድ ቤት አልኖርንም። አብረን አላደግንም። የቤተሰቡ መበታተን፣ እኔም ከእህትና ወንድሜ ተነጥዬ ማደጌ ከባድ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል።

ታላቅ እህቴና እኔ እህታችንን እንዴት መፈለግ እንደምንችል ባናውቅም ስለእርሷ እናወራ ነበር። ያኔ እህታችንን ስለምንፈልግበት ቴክኖሎጂ የምናውቀው ነገር የለንም። ጥያቄው አንድና አንድ ነበር፤ በሕይወት አለች?

እህቴም አባቴም በሕይወት ትኖራለች ብለው አያስቡም ነበር። እኔ ግን እንዲሁ መኖሯ ይሰማኝ ነበር።

ሙሉጌታ- የዩኒቨርስቲ ተማሪው

ነፍስ ካወቅኩበት ጊዜ ጀምሮ እህቴን መፈለግ እንዳለብኝ አስባለሁ። በእርግጥ ቤተሰባችን እድለኛ አይደለም። ተበታትነን ነው ያደግነው። ቢሆንም እኔ፣ እህቴና ወንድሜ መገናኘት እንችል ነበር። እሷ ግን ማንነቷን አታውቅም. . . ቤተሰብ ይኑራት አይኑራት አታውቅም. . . ይህንን ሳስብ ሰላም አጣለሁ።

አባቴ ሊያገኛት እንደማይችል ነበር የሚነግረን። እሱ ተስፋ ቢቆርጥም እኔ ግን ተስፋ ነበረኝ። ሁሌም የማስበው፣ የምፀልየውም እሷን ከእኛ ጋር ስለመቀላቀል ነበር። ህልሜን የማሳካበትን መንገድ አስባለሁ. . . የሆነ አገር ሄዶ እሷን መፈለግ ቢኖርብኝም፤ ይሁን. . .

በተለይ ዩኒቨርስቲ ስገባ እህቴን መፈለግ ብቻ ሳይሆን ቤተሰባችንንም መሰብሰብ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። ግቢ ስገባ እንዴት ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደምችል አወቅኩ። እናም ጎንደር ዩኒቨርስቲ ህክምና እያጠናሁ ጎን ለጎን እህቴን መፈለግ ጀመርኩ።

የጓደኛዬ አባት ጠበቃ ስለሆኑ ስለ እህቴ በምን አይነት መንገድ መጠየቅ እንዳለብኝ [ለጉዲፈቻ የሰጣትን ድርጅት] እሳቸውን አማክር ነበር። ለጉዲፈቻ የተሰጠችበትን ቀን በትክክል ስለማላውቀው ፋይል አገላብጬ መፈለግ አልቻልኩም። በዚያ መንገድ ብዙ መቀጠል እንደማልችል ሲገባኝ ኢንተርኔት ላይ ማፈላለግ ጀመርኩ።

ብዙ መረጃዎችን ማሰስ ጀመርኩ። ከኢትዮጵያ በማደጎ የተወሰዱ ልጆች የሚገኙባቸው 'ሳይቶች' ላይ በስም ዝርዝር ፈለኳት። ምንም የለም።

የህክምና ትምህርት ትኩረት ይሻል። ፍለጋውም ጊዜ ይጠይቃል። ሁለቱን ማመጣጠን በጣም ከባድ ቢሆንም ያለኝን የእረፍት ጊዜ ሁሉ እጠቀምበት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Mulugeta Asmamaw

የምስሉ መግለጫ,

ሙሉጌታ እና እህቱ ኡጋንዳ ሲገናኙ

ታላቅ እህቴ የእህታችን ነገር ሁሌም ያሳዝናታል። ግን በትምህርት ስላልገፋች እንዴት እንደምትፈልጋት አታውቅም። ከቤተሰቡ የተማርኩት፣ ዩኒቨርሲቲ የገባሁትም እኔ ብቻ ነኝ። ስለዚህ ኃላፊነቱ የእኔ ነበር። ያ ኃላፊነት ፍለጋውን በደንብ አጠንክሬ እንድይዘው አደረገኝ። ሁሌም እህቴን አግኝቼ ቤተሰቦቼ ሲደሰቱ ማየትን አልማለሁ።

የት አገር እንደሄደች ስለማላውቅ፤ በአንድ አገር ሳልወሰን 'ዳታቤዞች' ላይ እፈልጋት ነበር። በጣም በጣም አድካሚ ነበር። ያው ግን ላያስችል አይሰጥም። አንዳንዶቹ ሳይቶች በጉዲፈቻ ስለተሰጠው ልጅ 'ፕሮፋይል' ይጠይቃሉ። አንዳንዶቹ የስም ዝርዝር ይሰጣሉ።

ትዕግስት የልጅነት ፎቶ አልነበራትም። የእኛ ቤተሰብ ጸጉር ሉጫ የሚባል ነው። የሁላችንም ይመሳሰላል። እና ፎቶዋን ባይ በጸጉሯ እንደምለያት አስብ ነበር። እውነት ነው የሰው ገጽታ እድሜ ሲጨምር፣ የአኗኗር ሁኔታ ሲቀየርም ይለወጣል። ግን ባያት አውቃታለሁ።

ስድስት ዓመት ፈልጌ... ፈልጌ ሳላገኛት ከዩኒቨርስቲ ተመረቅኩ።

ሙሉጌታ - ሐኪሙ

ከተመረቅኩ በኋላም ፍለጋውን ቀጠልኩበት።

ኢንተርኔት ላይ በጉዲፈቻ የተወሰዱ ልጆችን ስፈልግ ከመጡልኝ ገጾች አንዱ 'ቤተሰብ ፍለጋ' የሚል ነበር። በቀረበልኝ ፎርም ላይ ስለ እህቴ ያለኝን መረጃ ሞላሁ።

ፎርሙ ላይ ካሉት ጥያቄዎች መካከል እህቴ የተወለደችበት እና በጉዲፈቻ የተሰጠችበት ቀን ይገኝበታል። እኔ ስለማላውቀው አባቴን ጠየቅኩት። ሊያስታውስ አልቻለም። የማስታውሳቸውን ዓመተ ምህረቶች እያጠጋጋሁ ሞላሁ።

ከአንድ ወር በኋላ 'ቤተሰብ ፍለጋ' ከሚሠሩ ሰዎች ስልክ ተደወለልኝ። 'አንተ በምትፈልገው [ፕሮፋይል] አንተን የሚፈልግ ሰው አለ' ተባልኩ። እህቴን በምፈልግበት ገጽ ላይ እሷም ፎርም ሞልታ እኛን እየፈለገች እንደሆነ ነገሩኝ።

እህቴ ብትሆንም ባትሆንም እኔ በምፈልገው [ፕሮፋይል] ሰው በመገኘቱ በጣም ደስ አለኝ። ደመ ነፍሴ እህቴ እንደሆነች ቢነግረኝም መጠራጠሬ አልቀረም። ግን ደግሞ ከጥርጣሬ ጋር አብሮ ደስ የሚል ነገር ተሰማኝ።

የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ. . . አንድ ቀን ሥራ ጨርሼ፣ ከሆስፒታል ወጥቼ ወደ ቤት እየሄድኩ ፌስቡክ ላይ 'ፍሬንድ ሪኩዌስት' (የጓደኝነት ጥያቄ) ደረሰኝ። ዴንማርክ ከሚኖር ሰው። በዚያ ወቅት ከውጪ አገር የሚደርሰኝ መልዕክት ከእህቴ ጋር የተያያዘ እንደሚሆን ስለማውቅ 'ሪኩዌስቱን' ተቀበልኩት። የእህቴ ፍቅረኛ ነበር።

ከዚያ እሷም 'ፍሬንድ ሪኩዌስት' ላከችልኝ። መጀመሪያ ምን ብላ እንደጻፈችልኝ አላስታውስም ግን "Hello" ያለችኝ ይመስለኛል። ማውራት ጀመርን. . . የምትኖረው ዴንማርክ ነው. . . ስለ ቤተሰቡ ብዙ ጥያቄዎች ታቀርብልኝ ነበር። እርግጠኛ ለመሆን 'ዲኤንኤ' ማስመርመር እንደምትፈልግም ነግራኛለች።

እህቴ ትዕግስት በሚለው ስሟ አትጠራም። ስሙን አሁን ከምትጠራበት ስም አስከትላ ነው መሰለኝ የምትጠቀምበት። ልጅ እያለች ያማት የነበረው፣ ያ ኩፍኝ የመሰለኝ በሽታ ጠባሳ እንደጣለባት ነግራኛለች።

በ'ኢሞ' እየደወለቸልች ከሁለት ሰዓት በላይ እናወራ ነበር። ቤተሰባችን ምስቅልቅል ያለ መሆኑን ነግሬ ላስጨንቃት ስለማልፈልግ 'ሁሉም ደህና ናቸው፤ ሥራ ይሠራሉ' እላታለሁ። ጊዜው ሲደርስ ራሷ መጥታ ብታየው ይሻላል ብዬ አስባለሁ።

አባቴ ያደረገው ነገር አይዋጥላትም። መቀበል አትፈልግም። የነበረበትን ሁኔታ እየነገርኩ፤ ለማስረዳት፣ ለማሳመን እሞክራለሁ። 'እሺ' ትልና. . . መልሳ ደግሞ አይዋጥላትም። ለመቀበል ይከብዳታል።

የፎቶው ባለመብት, Mulugeta Asmamaw

የምስሉ መግለጫ,

ሙሉጌታ እና እህቱ

እህቴ እንደነገረችኝ ከሆነ፤ ቤተሰቦቿ እንደሞቱ ቢነገራትም ልንኖር እንደምንችል ታስብ ነበር። የማንነት ጥያቄዎቿ እንዳሉ ሆነው ያደገችው ጥሩ ቤተሰብ ውስጥ ነው። በጣም የሚያሳዝነኝ እህቴ 'ኢዲኤስ' [Ehlers-Danlos syndromes] አለባት። ቆዳ እና የአጥንት መገጣጠሚያ የሚያጠቃ የጤና ችግር ነው።

እህቴ 23 ዓመቷ ነው። ዩኒቨርስቲ ገብታ ህክምና መማር ፈልጋ ነበር። ግን በበሽታው ምክንያት አልቻለችም። አሁን በሌላ ዘርፍ የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ናት።

እስካሁን ድረስ ከእኔ ውጪ ከሌሎቹ ቤተሰቦቼ ጋር አላወራችም። ፎቶዎች ልኬላታለሁ። እንዳገኘኋት ለአባቴ ስነግረው 'ከአሁን በኋላስ ብሞትም አይቆጨኝም' አለ። ለታላቅ እህቴ ስነግራት 'እውነት ግን እህታችን ናት?' ብላ ጠየቀችኝ። ለማመን ተቸግራ ነበር።

በሕይወቴ ካደረኳቸው ነገሮች ሁሉ ትላቁ ስኬቴ እህቴን ማግኘቴ ነው። የውስጥ ሰላም አግኝቼበታለሁ። ሁሉንም ቤተሰብ የመሰብሰብ ህልሜ ገና አልተሳካም። ያው ቤተሰቡን ለመሰብሰብ ቤት ያስፈልጋል። በእኛ አገር ሁኔታ ይህን ማሳካት በጣም ከባድ ነው።

የእህቴ ፍቅረኛ ኡጋንዳዊ ነው። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ለእረፍት ወደ ኡጋንዳ ሲሄዱ ጋበዙኝና ወደ ካምፓላ አቀናሁ።

ልክ ካምፓላ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ስንተያይ 'ዲኤንኤ ማስመርመር አልፈልግም' አለችኝ። በቃ! አንድ ቤተሰብ እንደሆንን አወቅን. . . ተቃቅፈን እያለቀስን ከሠላሳ ደቂቃ በላይ ቆየን።

አንድ ቀን ኢትዮጵያ መጥታ ከተቀረው ቤተሰብ ጋር አገናኛት ይሆናል. . .