"የት ይቀርልሃል!? አፈር ድሜ ትበላለህ...!" ጋሽ አበራ ሞላ

ሙዚቀኛ ስለሺ ደምሴ

ክራር አናጋሪው ሙዚቀኛና የአካባቢ ተቆርቋሪው ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ለ17ኛው የኢትዮጵያ ባሕልና ስፖርት ፌስቲቫል ስዊዘርላንድ ዙሪክ በተገኘበት ሰሞን ክሎተን በተባለ ቀበሌ፣ አንድ የሕዝብ መናፈሻ ውስጥ አግኝተነው ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ አድርገናል። በአመዛኙ ያወጋነው ከሙዚቃ ይልቅ በወቅታዊ አገራዊ፣ ፖለቲካዊና ከተማዊ ጉዳዮች ላይ ነበር ማለት ይቻላል።

ዙሪክ ብዙ ችግኝ ተተክሏል መሰለኝ.. እንደምታየው ዙሪያ ገባው ሁሉ አረንጓዴ ነው...(ሳቅ)

[እውነትህን ነው] አራት ቢሊየኑ እዚህ የተተከለ ነው'ኮ የሚመስለው (ሳቅ)

በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ፌስቲቫል፡ ሙዚቃ፣ ኳስ፣ ፍቅርና ቡጢ..

ይሄን ይሄን አይተህ ቁጭት አንገብግቦህ ነበር እንዴ ያኔ ጠቅለህ ወደ አገር ቤት ገብተህ አገሩን በዘመቻ ያመስከው? አዲስ አበባን ጄኔቭ የምታደርግ መስሎህ ነበር?

(ሳቅ) እም...ይሄን አይቼ ሳይሆን በፊት ልጅ በነበርንበት ጊዜ፤ ከዚያ በፊት በአያት በቅድም አያቶቻችን ጊዜ ኢትዮጵያ 60 እና 65 እጅ ያህል ደን የነበረበት አገር ነበር [የነበረን]። ለም የሆነ አገር። ከዚያ በኋላ የተለያዩ ሥርዓቶች ያንን ሊያስጠብቁ አልቻሉም። የሕዝቡ ቁጥር እየጨመረ መጣ፤ ልቅ የሆነ ሥርዓት ተከተለ። ከሥርዓቱ የሚመጡ አስከፊ ሁኔታዎች ድርቅ አስከተሉ። የአየር ንብረቱ ተዛባ። ሕዝቡም ደኑን መጠቀሚያ አደረገው...

ላቋርጥህ ጋሽ አበራ...ከኋላህ አንድ ወጣት ውሻው መንገድ ላይ ስለተጸዳዳ እሱን ጎንበስ ብሎ እያጸዳ ነው፤ እንደምታየው በእጁ የላስቲክ ጓንት አጥልቆ...ይህን አጋጣሚ አልለፈው ብዬ ነው። የት እንደሚጥለው እንመልከት...(ጋሽ አበራ ፊቱን አዙሮ መታዘብ ጀመረ)፣ እንዳየው በቅርብ ርቀት መጣያ አለ። በስተቀኝህ ደግሞ የሕዝብ መጸዳጃ አለ። እዚህ አጠገባችን እጅግ ያማረ ሌላ ቆሻሻ መጣያ ይታያል...። አንተ እነዚህን ነገሮች በአገር ቤት ለመሥራት በተወሰነ ደረጃ ሞክረህ ነበረ። የገነባኻቸው ሽንት ቤቶች ፈርሰዋል። መናፈሻዎችህ የቆሻሻ መጣያ ሆነዋል? ለመሆኑ ራስ መኮንን ድልድይ ስትሄድ ምንድነው የሚሰማህ? መሸነፍ? ተስፋ መቁረጥ?

አይ ተስፋ አልቆርጥም ግን ለምን ይሆን ብዬ እጠይቃለሁ።

የምታገኘው ምላሽ ምንድነው?

መጀመርያ አካባቢ ለምን እንደዚህ ሆነ? ምንድነው ችግሩ እያልኩ እብሰለሰል ነበር። ግን መጨረሻ ላይ ያገኘሁት መልስ ምንድነው፣ አንደኛ ባህሪያችንን መለወጥ አልቻልንም፤ በዕውቀት ማደግን አላወቅንበትም።

ለአንድ አገር ሥርዓት ወሳኝ ነው። መልካም ሥርዓት ለአንድ ከተማ ምን እንደሚያስፈልግ [ጠንቅቆ ይገነዘባል]። አሁን ተመልከት...መንገዱን ያየኸው እንደሆነ፣ መሻገሪያውን ያየኸው እንደሆነ፣ ምልክቶችን ያየኸው እንደሆነ [እያንዳንዷ ነገር ታስባ የተሠራች ናት]።

ተነግረው ያላበቁት የ'ጄል' ኦጋዴን የሰቆቃ ታሪኮች

ተመልከት ይሄን ቆሻሻ መጣያ...ተመልከተው በደንብ... ሲጋራ መተርኮሻ ሁሉ አለው [በቅርብ ርቀት የተተከለ የቆሻሻ መጣያን እያመላከተ]። በዚህ ደረጃ ታስቦበት ነው የሚሠራው።

ይሄን አግዳሚ የሕዝብ መቀመጫን ተመልከተው። ይሄን የእግረኛ መንገድ እይ፣ እዛ ጋ ተመልከት የሆነ በዓል አለ..ድንኳን ተክለዋል...ተመልከት ሕጻናት ሲቦርቁ ወዲያ ደ'ሞ...እያንዳንዱ ነገር ታስቦበት ነው። ሁሉ ነገር በሕግ፣ በደንብና በሥርዓት ነው ያለው። ለምን ይሄ ሆነ ብለህ ጠይቅ።

የሥርዓቱ ችግር ነው እያልክ ነው?

እንግዲህ ምንድነው፤ የሰለጠነ አስተሳሰብ ያስፈልጋል። አንድ ባለሥልጣን ስንል ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣኑን ከያዘ በኋላ የእሱ ምቾትና ሥልጣኑን ማስቀጠል እንጂ [ሌላው አያሳስበውም።] ሥልጣን የሚለው ቃል ሥልጣኔ ማለት ነው።

አንድ ባለሥልጣን እዚህ ቁጭ በል ሲባል ስለሠለጠንክ ሥልጣኔህን ተጠቅመህ ሕዝብ አስተዳድር እንደማለት ነው። እሱ ግን የሚመስለው በቃ ገዢ ሆኖ፣ የበላይ ሆኖ፣ አዛዥ ሆኖ፣ ቁጭ ብሎ፣ መኪና ነድቶ፣ ቁርጥ በልቶ፣ ውስኪ ጠጥቶ መኖር ነው።

ሥልጣን ይዘው የተቀመጡ ሰዎች የሥልጣኔ ባህሪውም የላቸውም። ካልሠለጠነ አእምሮ ሥልጡን የሆነ ሥርዓትን እንዴት ትጠብቃለህ?

የቅድሙን ጥያቄ መልሼ ላምጣው። ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ ስትሄድ አበቦቹ ደርቀው፣ ግኞቹ ከስመው፣ አረንጓዴ ያደረከው ቦታ የቆሻሻ ቁልል ሆኖ ስታይ ምን ይሰማኻል? ዕድሜህን ያባከንክ አይመስልህም?

ነገርኩህ እኮ ያን ያደረጉ ሰዎች አልሠለጠኑም፤ ከአፍንጫቸው አርቀው አያስቡም። ለእኔ አይደለም መታዘን ያለበት፤ ለእነሱ ነው እኔ የማዝነው።

እነዚህን ሰዎች እንዴት ማሠልጠን ይቻላል? ነው ጥያቄው። በአጠቃላይ ሕዝቡን ሳይሆን ሥርዓቶች ናቸው። አንድ ሥርዓት ወድቆ ሌላ ሥርዓት ሲመጣ የተሻለ ነገር ይዞ ከመምጣት ይልቅ በድንቁርና ላይ የተመሠረተ አመራር ነው [የሚከተለው]... ሕግን፣ ደንብን፣ ሥርዓትን ተከትሎ የሚሠራ አስተዳደር ነው የሚያሻው።

በመሀል የሆነ ጊዜ ላይ ጨርሶኑ ጠፍተህ ነበር።በሥርዓቱ አኩርፈህ ነበር ልበል? "ጋሽ አበራ ሞላ ጋሽ አበራ ሞላ፤ አበደ ይሉል ጉዳይህ ሳይሞላ..." የምትለው ነገር ባንተም የደረሰች ይመስልኻል...?

እንደዚያ አይደለም። ሁኔታውን ታየውና ዘዴህን ትቀይራለህ። መንግሥት በዚህ ነገር ካልተሳተፈ እንዴት ግለሰቦችን ታሳትፋለህ? ባለሀብቱን እንዴት ታሳትፋለህ? ተማሪዎች ስለጽዳት እንዴት ግንዛቤያቸው ሊያድግ ይችላል እያልክ ታስባለህ። ዘዴ ለውጠህ ትሠራለህ። ተስፋ ቆርጬ የተቀመጥኩበት ጊዜ አልነበረም።

ቅድም እንዳነሳኸው የደከምንባቸውን ቦታዎች ቆሻሻ መጣያ ሆነዋል። መሬቱን ለመሸጥ፣ ለሆነ ካድሬ ለማስተላለፍ፣ ወይም ደግሞ እከሌ ሠራው የተባለ እንደሆነ መንግሥትን አሳጣ ከሚል መጥፎ ሐሳብ የመነጨ ስለነበረ እኛ በየጊዜው ዘዴያችንን እየለወጥን ቆይተናል። ለዚያም ነው ብዙ እውቅና ያገኘነው።

የወንድሙን ገዳይ ለመበቀል ወደ ፈጠራ ሥራ የገባው ኢትዮጵያዊ

የእንግሊዝ ፓርላማ ውስጥ ከአፍሪካ አንደኛ ወጥቼ ግሪን ጎልድ አዎርድ አግኝቻለሁ። ከዚያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሽልማትን አገኘን።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ ከአዲስ አበባ መነሳት አለበት። አዲስ አበባ ቆሻሻ ናት፤ ተስቦ፣ ማሌሪያ፣ ኮሌራ፣ ታይፈስ፣ ታይፎይድ ከጽዳት ማነስ የሚመጡ በሽታዎች ስላሉ የአፍሪካ ከተማ ከዚህ ተነስቶ ትሪፖሊ መሆን አለበት ብለው እነ ጋዳፊ ዘመቻ በከፈቱበት ሰዓት ነው እንግዲህ ያን ያህል እየታገልን የነበረው።

እንዳልኩህ ግፊያው አለ፤ ምቀኝነቱ አለ፤ ሥርዓቱ ተጨመላልቋል። ያም ሆኖ ተስፋ አልቆረጥንም።

ከተማውን ያስተዳደሩ የነበሩ ሰዎች ላይ ቅሬታ ያለህ ይመስላል

የከተማው አስተዳዳሪዎች በጣም በሚገርም ሁኔታ ለየት ያሉና ዕውቀቱ የሌላቸው፣ ከተማን የማስተዳደር ባህሪ ጨርሶውኑ ያልነበራቸው ነበሩ። እነሱ ሲመጡ የሠራነው ሁሉ እየፈራረሰ መታየት ጀመረ።

አርቆ አለማሰብ አለ፤ ትንሽ ነበር አስተሳሰባቸው፤ መኪና፣ ልብስ፣ አጊጦ መታየት ከዚህ ያልራቀ ዓይነት አመለካከት እያለ ይሄ ይሄ ነው እንግዲህ ችግሮችን ይዞ የቆየው።

ይሄ የሰሞኑ ችግኝ ተከላ፤ በችግኝ ቁጥር ክብረ ወሰን መሰበሩ ወዘተ ሰሞነኛ ሆይሆይታ ሆኖ ነው የሚሰማህ ወይስ?

አነሳሱ ጥሩ ነው፤ ቀጥሎ ምን ይሆናል የሚለው ነው የሚያሳስበኝ። በእርግጥ 4 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል ወይ የሚለው አንድ ትልቅ ጥያቄ ነው። 4 ቢሊዮን ችግኝ ሁለት ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሐሳብ ታስቦ ተተከለ ለማለት ያስቸግራል።

ለ20 ዓመታት ዴንማርካዊት እህቱን የፈለገው ኢትዮጵያዊ ሀኪም

በዚህ ላይ እኛ ልምዱ አለን፤ ብዙ ተክለናል፤ አገሩን ማስተባበር ችለናል። ይሄን በተለያየ ጊዜ ለመንግሥት ሰዎች እንነግራቸዋለን። ነገር ግን የመስማትና የመቀበል ሁኔታቸው ዝቅተኛ ነው። እንኳን አብሮ ለመሥራትና ዕውቅና ሊሰጡህም ፍቃደኛ አይደሉም።

ሕዝቡ ምንድነው የሚለው "ይሄንን ነገር የጀመርከው አንተ አይደለህም ወይ?" ይላል። ይሄ ሁሉ እየሆነ በማማከር ደረጃ እንኳ አብረን እንሥራ የሚልህ የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካባቢ እንድታማክር ወይ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ አልቀረበልህም? ቅሬታ ያለህ ይመስላል።

አንድ መንግሥት ሲመጣ አማካሪ ሆነው አብረው መሥራት የሚፈልጉን ሰዎችን ያየኻቸው እንደሆነ...አሁን አንዱ ትልቁ ቅሬታዬ ትናንትና የነበሩ ሰዎች ናቸው ዛሬ ያሉት። ትናንትና በተለያየ ቦታ ላይ ሲያስቸግሩኝ የነበሩ ሰዎች ዛሬም አሉ፤ ትናንት ቀይ ኮት ለብሰው ነበር፤ ዛሬ አረንጓዴ ኮት ለብሰው ቁጭ ብለዋል። ከእነኚህ ሰዎች ምንድነው የምጠብቀው?

በአርቱ አካባቢም ብታይ ትናንትና ሆይ ሆይ ሲሉ የነበሩ ዛሬ 'ቅኝት ቀይረው' ምናምን ብለው እያዜሙ ነው። እና ይሄ 'ህልም ነው ቅዠት ነው?' ምናምን ትላለህ።

ዕውቅና ስላልተሰጠህ ቅሬታ ያለህ ይመስላል።

ምንድነው መንግሥት እኔን "ሪኮግናይዝ ባለማድረጉ" [ዕውቅና ባለመሥጠቱ] እኔ ምንም እንትን አይሰማኝም። እኔን 'ግናይዝ' ባለማድረጉ የራሱን ሥራ 'ሪከግናይዝ' እንዳይደረግ አድርጎት ይሆናል እንጂ እኔን ምንም እንትን ያለኝ ነገር የለም። የጋሽ አበራ ሞላን ሥራ ሰዉ ቀርቶ ጅቡም ያውቃል። መንግሥት ዕውቅና ሰጠኝ አልሰጠኝ ብዬ አልልም።

ምን እያሰብክ ነው በቀጣይነት?

ከጥቂት ወራት በኋላ ትልቅ ፕሮጀክት ይኖረናል። ሲቪል ሶሳይቲ ይኖረናል። እኛ ከወጣቱ ጋር ከሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብ ጥሩ ግንኙነት አለን። ለእኛ ቅን አስተሳሰብ አላቸው። በብሔር በጎሳ የተጠረነፉ ሳይሆኑ ይህቺን አገር ትልቅ ለማድረግ ቁጭቱ ያላቸው ብዙ ጉልበት ያላቸው ሰዎች አሉ።

ስለዚህ ምንድነው ፕሮጀክትህ ማለት ነው?

ሲቪል ሶሳይቲ [መመሥረት] ነው የሚሆነው። አገሪቱ እንዲህ የሆነችው ለምንድነው ያልክ እንደሆነ ኢህአዴግ አንድ ፓርቲ ነው። አጣኙም፣ ቀዳሹም፣ ቄሱም ዘማሪውም እሱ ነው።

ኢህአዴግ እንዲህ አደረገ ተብሎ ለሰው ይነገረዋል እንጂ ሰው ይህ ይደረግ አይልም። በዚህ በኩል መንገድ ይውጣ ከተባለ፣ ሰው ተማክሮ ነው እንጂ ማዘጋጃ ቤት ስለፈለገ መሆን የለበትም። የሕዝብ ተሳትፎ መቅደም አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ይሄ የለም።

የሕዝብ ተሳትፎን ካነሳህ አይቀር አሁን ይሄ ማዘጋጃ ቤት አጠገብ ያለው ሜዳ መጀመርያሜድሮክ ፎቅ ሊሠራበት ነበር። አሁን ደግሞ አድዋ ፓርክ ሊደረግ ነው፤ መልካም ተነሳሽነት ቢሆንም ቅሉ ከዲዛይኑ ጀምሮ የሕዝብ ተሳትፎ አያሻውም ወይ? የከተማ ፈርጥ የሚሆን ነገር እንዲሁ ማዘጋጃው ስለፈለገ...

እሱን ነው የምልህ። አንተ ያልከው ነገር ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከተማው ውስጥ ያሉ ግንባታዎች። አምጥቶ እብድ የሚያህል ፎቅ ይገደግድብኻል። ለእግረኛ ማለፊያ የለው፤ መኪና ማቆምያ የለው፤ አረንጓዴ ቦታ የለው...የዛሬ 40 እና 50 ዓመት ያለው ሕዝብ አይደለም አሁን ያለው። ክፍት ቦታ የለም። ፎቅ መገጥገጥ ነው...ያስጨንቅሃል።

ይሄው ተመልከት (አንዲት ሴት ልጇን በተንቀሳቃሽ አንቀልባ እየገፋች ታልፋለች) ይቺ ሴትዮ ጋሪውን ከእግረኛው ጥርጊያ ለማውረድ ትንሽዬ (ራምፕ) ተሠርቶላታል። ተመልከት እንግዲህ...ይቺ ሁሉ ሳትቀር ታስባ ነው።

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት የፓርላማውን ውሳኔ ተቃወመ

ይኸን ተወው...ይቅር። አሁን አንዱ ተነስቶ ሕንጻ ሲሠራ ባለቤቱ ይመጣና ጠጠሩን አሸዋውን ይደፋል፤ ትራኩ ምኑ.. ትርምስ ነው፤ የእግረኛ ማለፊያ የለ፣ ምን የለ፣ ፎቅ ብቻ...ሕግ ደንብና ሥነ ሥርዓት ያለው አገር አይመስልም።

እኛ ጋር ዝም ተብሎ ነው የሚሠራው። ቀበሌው ምን ይሠራል? ክፍለ ከተማው ምን ይሠራል? ከተማውን አስተዳድራለሁ የሚለው አካል የት ነው ያለው? ግራ ነው የሚገባህ።

አረንጓዴ የነበረው ቦታ ቆሻሻ መጣያ ሲሆን፣ አገር ጉድ ሲል፣ እዚያ የአረንጓዴ ልማት ቢሮ የተቀመጠው ሰው ቁጭ ብሎ ያያል። ስለዚህ ምን ማለቴ ነው፣ ሕዝቡ ይሄ ያንተ ከተማ ተብሎ ድርሻ እየተሰጠው እየተሳተፈበት፣ የእኔ ነው እያለ ሲሆን ነው ነገሩ መልክ የሚይዘው።

ሁን ስናወራ የተረዳሁት በአገሪቱ ብቁ አመራር እንደሌለና ይህም ያሳሰበህ ይመስላል። አንተ ከዚህ በፊት ሕዝብን ማንቀሳቀስ ችለል። ተምሳሌት መሆንም ችለል። አንዳች ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ፍላጎት አይብሃለ። ለምን ለከንቲባነት አትወዳደርም? ምንድነው ችግሩ? ትፈራለህ ፖለቲካ?

አይ አይ እኔ እንኳን ይሄ ሥልጣን ምናምን አይሆነኝም።

ግን እኮ ለውጥ ለማምጣት የምር የምትሻ ከሆነ...

አይ...!አይ..! አይሆንም። አንደኛ እኔ እንደዛ ዓይነት ነገር አልወደውም፤ መሆንም አልፈልግም። ቢሮ ውስጥ ተቀምጬ የወረቀት ሥራ ምናምን ለዚያ የምሆን አይደለሁም።

ምን መሰለህ? ሐሳቦች አሉ። ሐሳቦችን ማፍለቅ ነው ዋናው። ከሁሉም በላይ የሚልቀው ሐሳብ ነው። ሐሳብህን ወደ ዲዛይን የሚለውጥ አለ። ዲዛይኑን ወደ ተግባር የሚለውጥ አለ። ለዚህ ነው ቅድም ሲቪል ማኅበረሰብ መኖር አለበት ያልኩህ።

"እራት ለመመገብ አይደለም የምንሄደው" በላይነህ ክንዴ

በአንድ አገር የሲቪል ማኅበረሰብ ከሌለ ማንኛውም ነገር ሊሠራ አይችልም። መንግሥት አጣኙም እሱ፣ ቀዳሹም እሱ፣ ሰጪውም እሱ፣ ነሺውም እሱ፣ ተጠያቂውም እሱ ይሆናል። በአዲሱ አስተዳደር እነዚህ ሁሉ ነገሮች መልክ መያዝ አለባቸው ነው እያልኩህ ያለሁት። ለዚህ ነው የሲቪል ማኅበረሰብ የሚያስፈልገው።

ባለፈው የኢህአዴግ ጊዜ የሲቪል ማኅበረሰብ ለማቋቋም ብለን እነ ብርሃኑ ነጋ፤ ክቡር ገና አንድ አራት አምስት የምንሆን ሰዎች በጋሽ አበራ ሞላ ተነሳሽነት ከተማዋን ለማጽዳት፤ ለማልማት ሲቪል ሶሳይቲ ብንመሰርት ገንዘብ ይዋጣል፤ በእውቀት መንግሥትን ያግዛል ብለን አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ውስጥ ትልቅ ስብሰባ ተደረገ።

ማታውኑ...! ማታውኑ መለስ ዜናዊ ጠርቷቸው "እናንተ ምንድናችሁና ነው [እኔን አልጠራኝም] ምን አግብቷችሁና ነው ሲቪል ሶሳይቲ ብላችሁ እንደዚህ የምትሰባሰቡት? ሕዝብ ልታሳምጹ ነው?" ተብለው እነኛን ሰዎች ማታውኑ አስፈራርተው ሰደዷቸው።

አንተ ለምን አልተጠራህም?

እኔ ስብሰባ ውስጥ ተጠራሁ። እሱ ያመጣው ሐሳብ ትልቅ ሐሳብ ነው። በአንድ ግለሰብ የመጣ ሐሳብ አገር ለውጧል። ይሄ ሁሉ ኅብረተሰብ ደግሞ ቢሳተፍበት ምን ያህል ለውጥ ሊመጣ ይችላል በሚል...

ስለዚህ የሲቪል ማኅበረሰብ የሆነ አካል ሲኖር የበለጠ ብዙ ነገር ሊሠራ ይችላል። ይሄንን እናዳብረው ነው እንግዲህ። ዲያስፖራው ይመጣል። ዕውቀት ያለው ይመጣል፤ ጉልበት ያለው ይመጣል፤ እነዚህ እነዚህ በሙሉ ታሰባስብና ለውጥ የሚመጣበትን ሁኔታ ታመቻቻለህ። እና የዚያን ጊዜ እንደዚያ ሆኖ [ከሸፈ]።

አሁንም መታወቅ ያለበት ሕዝብ ተዋናይ እንጂ ተመልካች መሆን የለበትም።

አንተ አብዝተህ በእግር ስለምትንቀሳቀስአሁን መገናኛና ሜክሲኮ አካባቢ ስትሄድ ምንድነው የሚሰማህ?

[ምን አ'ርግ ነው የምትለኝ? በሚል ስሜት በረዥሙ ተነፈሰ]...ምን እኮ... ያው እንደምታየው ነው። መገናኛና ሜክሲኮ ብቻ ሳይሆን የትስ ቦታ ብትሄድ...! ጉድ ነው እኮ!

የሕዝቡ ብዛት፣ ውጥንቅጡ...ትርምሱ...ቅድም እኮ አወራን...። እዚህ ተመልከት፤ እያንዳንዱ ነገር እኮ በቀመር ነው የተሠራው፤ በአጋጣሚ አይደለም።

አገሩ በሙሉ ነቅሎ ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምሥራቅ፣ ከምዕራብ፣ ገበሬው፣ ወጣቱ፣ እናቱ፣ ምኑ ምኑ ሳይቀር በየቀኑ ይገባል ወደ አዲስ አበባ።

እኔ የሚገርመኝ እነዚህ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በዚህ እየተጋፉ ነው የሚሄዱት፤ ግን መኪና ውስጥ ናቸው። መኪና ውስጥ ቢሆኑ አሁን የከተማው አስተዳዳሪዎች ይሄን ሁሉ ትርምስ ሲያዩ ምንድነው የሚሰማቸው? እላለሁ።

እኔ እውነት ለመናገር አንድ እግዚአብሔር የነሳን አንድ የሆነ ነገር አለ? እንዳናይ ያደረገን?

የጠቅላይ ሚኒስትሩ 200 ሚሊዮን ችግኞች

እንጂ ዓለም እዚህ በደረሰበት ሰዓት እኛ እንዲህ ትርምስምስ ባለ ጎሳዊ፣ ጎጣዊ፣ ግላዊ አመለካከት ውስጥ እንሆን ነበር? ምን ለማለት ፈልጌ ነው...መንገዱ ላይ ስትሄድ የለማኙ ብዛት ቁጥር ስፍር የለውም። አልፎ ተርፎ ልጅ እየወለዱ መንገድ ላይ ሺህ የሚሆኑ አራሶች ግራና ቀኝ ተደርድረው ይታያሉ። ሽማግሌዎች ሲለምኑ ታያለህ።

ቅድም እንዳልከው መገናኛና ሜክሲኮ ስትሄድ ከሆነ ፕላኔት ላይ የወረድን ሰዎች እንጂ የምንመስለው እውነት በምጣኔ ላይ ተመሥርተን ተወልደን በሥርዓት አድገን ለመኖር የመጣን ሰዎች አንመስልም።

የሳልቫጁ እቃ ራሱ አብሮ ከሰማይ የወረደ ነው የሚመስለው፤ ሻጩም አብሮ የወረደ ይመስላል፤ ገዢውም አብሮ የወረደ ይመስላል። ዱብ ዱብ ብለው የወረዱ ነው የሚመስለው። ማታ ደግሞ ስታያቸው የሉም። ከሌላ ስፔስ የመጡ እኛን የሚመስሉ ሰዎች ናቸው ወይስ? ትርምሱ እየገረመኝ እተክዛለሁ።

እና እኔ'ንጃ...ደንብ፣ ሕግ ሥርዓት ያለን ሕዝቦች አንመስልም ብቻ...

እንደምታየው እንዲህ እያወጋን አዛውንቶች ሕጻናት እዚህ መናፈሻ ላይ ደስ የሚል ጊዜ እያሳለፉ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ አረጋዊያን የት ይሂዱ፤ ሕጻናት የት ይጫወቱ?

አረጋዊያኑ ቤት ይዋሉ፤ ሕጻናቱም ቤት ነው የሚቀመጡት፤ ምናልባት ለወደፊት ቤቱ ሲሞላ ጣሪያም ላይ ሊቀመጡ ይችላሉ (በምጸት ዓይነት)። ምክንያቱም ቦታ የሚባል ነገር የለማ።

ቅድም እንዳልኩህ ነው። በየቦታው [የበሬ ግንባር] በምታህል ቦታ እንኳ ስትገኝ ፎቅ ነው። መሬትን መሸጥ ነው የተያዘው። በተሸጡ መሬቶች መሀል እንኳ ምናለ እንደው 50 ካሬ እንኳ ለአዛውንት ለሕጻናት ተብሎ ቢተው።

አሁን እንደዚህ ከሆንን ከዚህም በላይ ቁጥራችን እየበዛ በሚሄድ ጊዜ ምን ልንሆን ነው ብዬ አስባለሁ።

የወንዝ ዳር ልማቱ ተሳክቶ አንተ በነዚያ መናፈሻዎች የእግር ጉዞ የምታደርግ ይመስልሃል? ቢሊዮን ችግኞች ጸድቀው በሕይወትህ የምታያቸው ይመስልሃል?

አሁን ያልናቸው ነገሮች የሚሳኩ ከሆነ፤ ሕዝቡን የምታሳትፍ ከሆነ ለምን አይሆንም?

አሁን በዚህ በወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት አለሁበት። የአካባቢዎቹን ታሪኮች የጻፍኩት እኔ ነኝ። እንጦጦ ምንድነው? አፍንጮ በር ምንድነው? 6ኪሎ፣ ቃሊቲ፣ አቃቂ የሚሄደው ይሄ ሁሉ የወንዝ ዳር ፕሮጀክት በአካባቢው ስም፣ በአካባቢው ምሳሌ፣ በአካባቢው ተረት፣ ያንን ወዙን፣ ያንን ለዛውን፣ ያንን ማዕረጉን፣ ያንን ታሪኩን፣ ዘይቤውን፣ እንቆቅልሹን ይዞ የሚሄድ እንዲሆን በሚያስችል መንገድ ነው የጻፍኩት።

ችግኝን በዘመቻ መትከል መቼ ተጀመረ?

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ደስ ብሏቸው ተጀምሯል። ትልቅ ፕሮጀክት ነው። የጨርቆስም ትልቅ ፕሮጀክት ነው። እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ ህልም አላቸው። ግን እዚህ ላይ የሚያማክሩ አብረው የሚሠሩ ሰዎችን ቅድም እንዳልኩህ ሲቪል ማኅበራት ያስፈልጋሉ። ወጣቱ አዛውንቱ ሁሉ መሳተፍ ይኖርበታል።

ችግኙም እንደዚሁ። ዝም ብሎ ይሄንን ያህል ተተከለ ለማለት ሳይሆን ችግኝ ስትተክል አእምሮ ውስጥ ነው መጀመርያ የምትተክለው።

እኔ እንደሚመስለኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ 4 ቢሊዮን ችግኝ ሲል የሕዝብ አእምሮ ላይ ለመትከል ያሰበው እቅድ ነው የሚመስለኝ። እንጂ ዝም ብሎ የችግኝ ቁጥር አይመስለኝም። የአረንጓዴነት ስሜቱንና አስተሳሰቡን ሰው አእምሮ ውስጥ ለመትከል ያሰበ ነው የሚመስለኝ።

እስኪ ጋሽ አበራ አሁን ደግሞ በአጫጭር ጥያቄዎች እረፍት እናድርግ። ለመጨረሻ ጊዜ ሱፍ የለበስከው መቼ ነው?

ለብሼ አላውቅም እኔ። አንድ ቀን ብቻ ኦፕራህ ዊንፍሬይ የመጣች ቀን ልበስ ተብዬ ለበስኩ። ከዚያ ሰዎች ሲፈልጉኝ አጡኝ። እኔኮ አጠገባቸው ተቀምጫለሁ። ለካስ እነሱ በሱፍ አያውቁኝም። (ሳቅ)

መኪና አለህ ጋሽ አበራ ሞላ?

መኪና ይኖራል ግን...

ምንድነው አቅም ማነስ ነው? ሕዝቡ ማዋጣት ካለበትም ይነገረው...

(ሳቅ) አይ እኔ መኪና የሌለኝ ስለምቸኩል ነው።

በቀን ውስጥ ምን ያህል ኪሎ ሜትር በእግር ትጓዛለህ በአማካይ?

ለምሳሌ አያት አካባቢ ነው ሰፈሬ። እንግዲህ ቦሌ መሄድ ካለብኝ ጠዋት እነሳለሁ፤ አንድ 15 ወይ 20 ኪሎ ሜትር በየቀኑ?

ሥጋ ...ቁርጥ እንደዚህ ነገር ትበላለህ?

ሥጋ እበላለሁ ግን እስከዚህም ሥጋ በላተኛ አይደለሁም። አልፎ አልፎ ከሰዎች ጋር ካልሆነ...ብዙም...

ታዲያ የምታዘወትረው ምግብ ምንድነው?

እኔ ከምግብና ከገንዘብ ጋር ብዙም ግንኙነት የለኝም።

ብዙ ጊዜ እስጢፋኖስ ቤ/ክርስቲያን ፊትለፊት ካፌ ቁጭ ብለህ እመለከትሃለሁ፤ ጥሞና ታበዛለህ። ምንድነው የሕይወት ፍልስፍናህ?

ያው እንግዲህ እኔ ምድር ላይ ብኖር 575 ዓመት ነው። ለዚህች አጭር ዕድሜዬ ብዬ ብዙ አልጨነቅም (ሳቅ)፤ እናንተ 70/80 ዓመት ለመኖር ነው የምትጨነቁት። እኔ ቀስ እያልኩ ነው የማረጀው፤ እናንተ ቶሎ ታረጃላችሁ።

የምር ፍልስፍናህን ንገረኝ..

አየህ ሰዎች ሱስ ውስጥ ይገባሉ። ምን ዓይነት ሱስ መሰለህ... ማቴሪያል የመውደድ ሱስ። ወይ መኪና የመውደድ፣ ወይ ኑሮ ማለት ለነሱ ገንዘብ የማከማቸት።

አእምሯቸውን፣ ልባቸውንና አጠቃላይ ሕይወታቸውን ወደ ውጭ አውጥተው እዚያ ላይ ያስቀምጡታል። ሕይወት ግን ወደ ውስጥ ነው።

የተተከሉት ችግኞች እንዴት ተቆጠሩ?

መጀመሪያ ሕይወት ያለው አንተ ውስጥ ነው። ያንን ሕይወት፣ ሕይወት ልታደርገው የምትችለው አንተ ነህ እንጂ፣ ውጭ ያለው ነገር አይደለም ላንተ ሕይወት የሚሰጥህ። ራስህን አውጥተህ ስትሰጥ ማንነትህን እያጣህ ትመጣለህ። ውስጥ ያለው መንፈስህ እየወጣ፣ እየደከምክ አቅም እያጣህ ትመጣለህ። ከዚያ ጭንቀት ይቆጣጠርሃል። ተጠራጣሪና ፈሪ ትሆናለህ። ከሰው ጋር ለመግባባት ትቸገራለህ።

ስለ ገንዘብ ምን ታስባለህ?

እኔ ገንዘብን ብዙም አላቀርበውም፤ እዚያ ጋ ይቀመጣል፤ ከዚያ ስፈልግ "ና እዚህ ጋ" እለዋለሁ። ቤት ኪራይ ይከፍላል፤ ይሄዳል።

ገንዘብ ይታዘዝልኛል እያልከን ነው?

አዎ! (ሳቅ)

ገንዘብ አልሰበሰብ እያለ አስቸግሮህ፤ ሩቅ ሆኖብህ እንዳይሆን?

ሩቅ ሆኖብኝ አይደለም። በአንድ በኩል ሩቅም ነው። አሁን እነዚህ ሚሊዮን ብር ያላቸው...አንድ ሰው ይሄን ብር ከየት ያመጣል? ካልሰረቀ ካልዘረፈ በስተቀር። ሠርቶ የሚያገኘው ምናልባት ጥቂት ሰው ነው የሚሆነው።

አእምሮን መንፈስን ኮራፕት አድርገን ተላምደን ኖረናል ለብዙ ጊዜ። ይሄንን ኖርማል አድርገን ይዘነው ነው ብዙዎች ሀብታም ነን የሚሉት። [እንጂ] ከየት ያመጣሉ? የትኛው ዕውቀታቸው ነው ይሄን ያህል ገንዘብ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው? የትኛው ነጋዴ ነው? እንዴ እናውቃለን እኮ...እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እኮ ያውቃል። ማን ብሩን እንዴት እንዳገኘው።

ሀበሻ ፍልስፍናው በተረት ውስጥ ነው ያለው። አንድ ተረት ልንገርህ...

ሰጎን አሉ... መሀል በረሃ ላይ ይቺን የምታክል አፏን አሸዋ ላይ ቀብራ አንገቷና ሰውነቷ ውጭ ነው ያለው። ኋላ ሰው ሄደና "ሰጎን! ሰጎን! ምን እያረግሽ ነው? አፍንጫና ዓይንሽን ቀብረሽ ሰውነትሽ ዝሆን አክሎ ቢሏት... 'ሰው እንዳያየኝ ተሸሽጌ ነው አለች' አሉ።

እነኚህ ሰዎች ይሄንን ሚሊዮን ብር ከየት እንዳመጡት የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃል። ነገር ግን አንገቱን የቀበረው ሰውዬ ስለ'ኔ ሰው አያውቅም ብሎ አንገቱን እንደ ሰጎን አሸዋ ውስጥ ቀብሮታል። በንጽሕና የተገኘ ሀብት የለም እያልኩህ ግን አይደለም። ጥቂት ነው።

አጭር የምስል መግለጫ ስዊዘርላንድ፤ ዙሪክ

ኅብረተሰባችን የሞራል ልልናው እየተሸረሸረ ይመስልል?

በጣም እንጂ! ህልውናውን ያጣበት ዘመን ነው፤ ታዲያ ህልውናውን ባያጣ በሄድክበት...

ከዚህ በፊት ሐዋሳ [መሄድ ስታስብ] ኤጀቶ እንደዚህ ያደርገኛል፤ ኦሮሚያ ብትሄድ ቄሮ እንዲህ ይለኛል፣ አማራ ብትሄድ ፋኖ ምናምን ይለኛል [ትላለህ እንዴ?] ወጣቱ ሁሉ በዘር በሃይማኖት በጎሣ ተበጣጥሶ እያንዳንዱ ሰው እየጠበበ፣ ዱላ እየያዘ እርስ በርሱ ይደባደባል እንዴ? ከዚህ የበለጠ ህልውና ማጣት ምን ይኖራል? ምን ያልሆነው አለ እስቲ አሁን? ሰው እየሰቀልን? ሰው እየቆራረጥን፤ ሰው እየገደልን፤ ሺህ ሰው እያፈናቀልን! ምን ያልሆነው አለ?! እስቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንድነው ያልተሆነው? ንገረኝ?

እንዴት በአንድ ጊዜ እዚህ ደረስን ግን?

በአንድ ጊዜ አይደለም። ትንሽ ዓመት ነው እንዴ? እስኪ አስበው። በደርግ ጊዜ ተጀመረ። በኢህአዴግ ጊዜ አለቀ። 30 ዓመት በለው የኢህአዴግን ዕድሜ። ያ 17 ዓመት...ወደ 50 ዓመት ሊሆን እኮ ነው። ግማሽ ክፍለ ዘመን ቀላል ነው እንዴ ታዲያ?

50 ዓመት ጆሮው ላይ ስለክፍፍል ሲጮኽበት የነበረ ሰው እንዴት አድርጎ ነው ልዕልና የሚኖረው?

ተጠላልፈን በድንበር ተከፋፍለን፣ 99 ባንዲራ አሲዘውን......አእምሯችን ላይ ድንበር ሠርተው፣ በሃይማኖት አጥረውን፣ በክልል አጥረውን፣ በጎሣ አጥሮን አንተ እንዴት እኔን ትወደኛለህ? ይሄ ኅብረተሰብ ቪክቲም (ሰለባ) ነው። የዚህ ድምር ሥርዓት ውጤት ነው። ታዲያ በምን ሂሳብ ነው የተሻለ ነገር የምትጠብቀው? አረም ዘርተህ ስንዴ ትጠብቃለህ እንዴ?

ትሰጋለህ? ይቺ አገር እልቂት ውስጥ ትገባለች ብለህ?

[ዘለግ ካለ ትካዜ በኋላ....] ሶሪያ ምን ሆነ? የመን ምን ሆነ? ሶማሌ ምን ሆነ? ጎረቤትህ እኮ ነው። የግድ አንተ ቤት መምጣት አለበት እንዴ? ጎረቤትህ ምን እየሆነ እንዳለ እያየህ አንተ "ምን ሆንን እኛ?" ብለህ የተቀመጥክ እንደሆነ የት ይቀርልሃል? አፈር ድሜ ትበላለህ...ቀልድ እንዳይመስልህ። የሚመጣውን መገመት የማትችል ከሆነ ሲኦል ነው የምትገባው።

ማነው ተጠያቂው ግን?

አሉ የዘር በሽታ የያዛቸው። ኦሮሞ በል፣ አማራ በል፣ ትግሬ በል..[በለው!] እያሉ በቃ በዘር የተለከፉ በሽተኞች አሉ፤ እነኚህን በሽተኞች መለየት ያስፈልጋል። አሉ እዚህ... ምንም የማይሻሻሉ፤ እዚህ የሰለጠነ ዓለም እየኖሩ እንኳ ያልሰለጠኑ ሰዎች አሉ። እነኚህን በሽተኞች ወደዚያ አግልለህ...

ወዴት?

በሕግ፣ በደንብ በሥነ ሥርዓት ጠፍንገህ ታስረዋለሃ። [ቆጣ ባለ ስሜት] ምን ያረጋል መንግሥት? ኃላፊነቱ ይሄ አይደለም እንዴ?

ይሄን ሁሉ መከራና አመጽ የሚያመጡ ሰዎች እኮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አይደሉም። ጥቂት ሰዎች ናቸው። እዚህና እዚያ...ጥቅማቸው እንዳይቀርባቸው ነው ክብሪት እየለኮሱ ብዙኃኑን የሚያፈናቅሉ። እነኚህ ሰዎች በደንብ ይታወቃሉ። ምንጫቸው ይታወቃል። ምንጩን ማድረቅ አለብህ።

እነዚህ የምትላቸውን ማሰር ወደ ባሰ ቀውስ አይከተንም? ብዙ ወጣት ተከታይ አላቸው እኮ

እሱ ልክ ነህ፤ ሁለት ነገር አለ። ዛሬ ስንት እጁ ነው ወጣት? ምን ያህሉ ነው ሥራ ያለው። ሁሉም ቦዘኔ ነው።

ትግራይ ብትገባ ያ ሁሉ ወጣት ሥራ የለውም፤ ግን እዚያ ያለው ሥርዓት ምን ይለዋል ልክ እሱ አርበኛ እንደሆነ፣ ጀግና እንደሆነ፣ በወሬ እያሞካሸ አንተ እንደዚህ ነህ እያለ ዝም ብሎ ያወጣዋል ያንን ወጣት።

አዲስ አበባም በለው የትም የትም እንደዚህ ነው የሚያደርጉት። ጀሌውን የሚመራውን ነው መያዝ፤ ፋኖ ነኝ፣ ኤጄቶ ነኝ፣ ቄሮ ነኝ ምንድነኝ የሚለው ሌሎች ይጠቀሙበታል እንጂ ሥራ ነው የሚፈልገው። ድሃ በመሆኑ ነው ሊጠቀሙበት የሚፈልጉት፤ ድሃ ባይሆንማ ዝም ብሎ አይነሳላቸውም።

ግን ጋሽ አበራ ነጻና እውነተኛ ዲሞክራሲ ቢኖር ምርጫ አትወዳደርም? እርግጠኛ ነህ?

አይ አላደርገውም፤ እውነት ለመናገር እኔ እዚያ ነገር ውስጥ ብገባ እኔነቴን አጣዋለሁ። ሁሉም ሰው ሥልጣን አይዝም። ሁሉም ሰው ቤት አይሠራም፤ አንዱ ቤት ይሠራል፤ ሌላው ቤት ይከራያል።

ተያያዥ ርዕሶች