“በአምስት የዓለም ዋንጫዎች ወርቅ እንዲመጣ ምክንያት ነኝ” አትሌት ገብረእግዚአብሔር

አትሌት ገብረእግዚአብሔር Image copyright EMMANUEL DUNAND

አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም ተወልዶ ያደገው በትግራይ ክልል በቀድሞዋ ሐውዜን፣ በአሁኗ ሳዕሲዕ ጻዕዳ እምባ ወረዳ ነው፤ ልዩ ስሟ ጻንቃኔት በተባለች አካባቢ ነው።

በ1976 ዓ.ም. የተወለደው ገብረእግዚኣብሄር፤ ገና ታዳጊ እያለ በ16 ዓመቱ ጊዜውም በ1992 ዓ.ም ሩጫን ሀ ብሎ የጀመረው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ 2003 ኒው ዮርክ በተካሄደው ማራቶን ላይ ተሳትፎ የወርቅ ሜዳልያ አገኘ።

"ሥልጣን ለደም ግፊት አጋልጦኛል" ኃይሌ ገብረሥላሴ

ለቁጥር በሚያዳግቱ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ውድድሮች በግሉም እንዲሁም በሃገርም ደረጃ ተሳትፎ ብዙ ወርቆችን ያስገኘ አትሌት ነው።

በአሁኑ ወቅት ከሩጫው ባሻገር በአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኦሎምፒክ ኮሚቴ ምክትል ኃላፊነት እያገለገለ ሲሆን፤በይፋ ጫማ ባይሰቅልም እምብዛም በሩጫ መድረክ ላይ ሲሳተፍ እየታየ አይደለም።

ለዚህም ገብረእግዚአብሔር ምላሽ አለው "ሩጫ እንደሚታውቀው ብዙ ትኩረት የሚጠይቅ ነው። ቢዝነስን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እሳተፋለሁ። ከዚህ በተጨማሪም በዕድሜም እየገፋሁ ነው። በይፋ ጫማ ባልሰቅልም አሁን ወደዛው ነኝ።"

በዚህና ወቅታዊ ስፖርታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ቢቢሲ ከገብረእግዚአብሄር ጋር ቆይታ አድርጓል።

ለመሆኑ እንዴት ነበር ወደ ሩጫው የገባው?

አትሌት ገብረእግዚአብሄር ሩጫ በጀመረበት ወቅት ሩጫ በአለም አቀፍ ደረጃ በውድድር ደረጃ ስላለው ስፍራ የጠለቀ እውቀት አልነበረውም። ትምህርቱን የተማረው እንደ ብዙው የኢትዮጵያ የገጠር ልጅ በእግሩ እየሄደ ነበር፤ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ርቀቷን በሩጫ ፉት ይላታል።

ስለ አቶ ዱቤ ጅሎ ሽልማት ምን እናውቃለን?

"እኔ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ። ወላጆቼ ያዘዙኝን በሙሉ ሰርቼ በሰዓቱ ትምህርት ቤት ለመድረስ ስለማልችል እየሮጥኩ ነበር የምሄደው። ከትምህርት ቤት ስመለስም እንዲሁ በሩጫ ነበር።" ይላል

ይሄ የአብዛኛው የአርሶ አደር ልጆች ታሪክ ቢሆንም ለገብረ እግዚአብሄር ግን የተለየ ዕድል እንደፈጠረለት ይናገራል።

"አጋጣሚው ተፈጥሯዊ አቅምን ፈጥሮልኛል።"

ሩጫን ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ በፍጥነት ለመድረስ እንጂ በስፖርቱ አለም ያለውን ስፍራም አልተረዳውም ነበር። "በስፖርት ይሄን ያህል ታዋቂነት እንደሚገኝም አላውቅም ነበር" ይላል።

ውድድር ማካሄድ የጀመረው በትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት ሲሆን፤ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ በትምህርት ቤቱ በተጀመረው ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ አንደኛ ወጥቶ የምስክር ወረቀትም አግኝቷል።

ጊነስ ዎርልድ ሪከርድስ፡ «ስለተተከሉት ዛፎች ከኢትዮጵያ የደረሰን መረጃ የለም»

ከትምህርት ቤቱ በተጨማሪ ሌሎችን ውድድሮችን ማካሄድ የጀመረው ገብረእግዚአብሔር በ1993 ዓ.ም. የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖም አዲግራት አቅራብያ በምትገኘው ዕዳጋ ሐሙስ ከተማ ትምህርት ቤቱን ቀጢን ቃላይ' ወክሎ ነበር የተወዳደረው፤ አንደኛም ወጣ።

ቀጥሎም ወረዳውን ወክሎ 1500 ኪሜ ተወዳደሮ ማሸነፉን ያስታውሳል። ለመጀመርያ ግዜ ከምስክር ወረቀት በተጨማሪ ሽልማት ያገኘበት መሆኑም ልዩ ያደርገዋል።


Image copyright sampics

አትሌት ገብረእግዚአብሄር

  • 1994-2006 የብሄራዊ አትሌቲክስ ቡድን ኣባል
  • በ1994 በአየርላንድ የአገር አቋራጭ በባዶ እግሩ የ800 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ
  • በ2001 ዓ/ም በኒው ዮርክ ማራቶን የወርቅ ሜዳልያ
  • በ2000 ዓም በኢትዮጵያ ሚሊኒየም የአፍሪካ ሻምፒዮን የወርቅ ሜዳልያ አምቷል።

አትሌት ገብረ እግዚአብሄር በተለይ ለእነዚህ ሶስቱ ድሎች [የአየርላንድ፣ የኒው ዮርክና አፍሪካ ሻምፒዮን] የተለየ ቦታ አለው። በተለይ ደግሞ የአፍሪካ ሻምፕዮን በኢትዮጵያ የተካሄደ በመሆኑና ከፍተኛ ዝናብ የጣለበት ፈታኝ ውድድርም ስለነበር ከፍ ያለ ትርጉም ይሰጠዋል።

"የት ይቀርልሃል!? አፈር ድሜ ትበላለህ...!" ጋሽ አበራ ሞላ

"በኢትዮጵያ የመጀመርያ ውድድርም ስለ ነበር ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ወርቅ እንዲያመጡ ጉልበት የሆናቸው ይመስለኛል" የሚል እምነት አለው።

የአትሌት ገብረ እግዚአብሄር አርአያ ማን ነው?

ገብረእግዚአብሄር ሩጫን በአጋጣሚ ቢጀምርም በትምህርት ቤት ስለ እነ አትሌት ምሩጽ ይፍጠርና አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ የሩጫ ገድል ሲሰማ በሩጫ ላይ የተለየ ፍላጎት እንዳደረበት ይናገራል። አበበ ቢቂላም ሌላኛው የገብረእግዚአብሄር አርአያ ነው።

ለሶስቱ አትሌቶች የተለየ ክብርና አድናቆት እንዳለው ነው የሚናገረው ገብረእግዚአብሄር፤ "ሩጫን ለዓለም በደንብ ያስተዋወቅነው እኛ ኢትዮጵያውያን ነን" የሚል አቋም አለው።

ገብረእግዚአብሄር ከሁሉም በላይ ለኃይሌ ገብረ ስላሴ ያለው ቦታ ከፍ ያለ እንደሆነ ይናገራል። በሩጫ ማሸነፉ ብቻ ሳይሆን በሩጫው ለረዥም ግዜ የቆየበት ፅናቱን እንደ ምሳሌ ይቆጥረዋል። እንዲሁም ደግሞ ከሩጫው በተጨማሪ በቢዝነስ የሚያደርገው እንቅስቃሴና ስኬትም ሌላ የሚያደንቅበት ጉዳይ ነው።

Image copyright Michael Steele

"አትሌት ምሩጽ ይፍጠር አባቴ ነበር"

አትሌት ምሩጽ ይፍጠር በአንድ ኦሎምፒክ ሁለት የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት መሆኑን ከፍተኛ ስፍራ ከመስጠቱ በተጨማሪ ለመጀመርያ ጊዜ ሩጫን በውድድርነት ሲሰማ የአትሌት ምሩጽ ይፍጠርን ድል ነበር የሰማው።

የስድስተኛ ክፍል የሳይንስ መምህሩ ስለ አትሌት ምሩጽ ይፍጠር ማርሽ ቀያሪነት በሚነግሯቸው ወቅት መጀመርያ የሚያወሩት ስለመኪና ማርሽ ይመስለው እንደነደበር በፈገግታ ያስታውሰዋል።

"ምሩጽ ስሙም ምርጥ ማለት ነው፤ ተግባሩም ምርጥ ነበር። በአካል ሳላውቀው ለረዥም ግዜ በውስጤ ይመላለስ ነበር፤ ምን ዓይነት ሰው ይሆን ብዬ ሁሌ አስብ ነበር" ይላል።

በኋላም በአካል ተገናኝተው ከተዋወቁ በኋላ ያላቸው ግንኙነት ጠንክሮ እንደ ልጅና አባት ይተያዩ እንደነበር ይናገራል።

ዘሩባቤል ሞላና በአነቃቂ መንፈስ የታሸው 'እንፋሎት' አልበሙ

"በህይወት ሳለ እንደ አብሮ አደጎችም ነበር የምንቀራረበው። እንደ አባቴ ነበር የማየው። የሃገሪቱም ሆነ ዓለም ክብር ነበር" በማለት በኃዘኔታ ያስታውሳል።

ለተወሰኑ ዓመታት አሰልጣኙ እንደነበርም ይናገራል። በተለያዩ ማሕበራዊ ጉዳዮችም ያማክረው እንደነበር ገብረእግዚአብሄር ያስታወሳል።

ወቅታዊ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ

ተተኪ አትሌቶችን ከማፍራት ባለፈ የመቀሌ ከተማና ሌሎች በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን ማስተዋወቅ አላማ ያለው 'ናትና ስፖት' በሚል ከባለቤቱ ከአትሌት ወርቅነሽ ኪዳነ ጋር ባቋቋሙት ተቋም አማካኝነት ሶስተኛው 'ናትና' የጎዳና ሩጫ ባለፈው ወር መቀሌ ላይ ተከናውኗል።

"ትግራይ ክልል በደንብ ከተሰራበት ለስፖርት አመቺ የሆነ ሁኔታ አለ" የሚለው ገብረእግዚአብሄር ከሩጫው በሚገኘው ገቢ ሶስት የአትሌቲክስ መንደሮች ለማቋቋም አስቧል።

የመቀሌ ሰብዓ እንደርታ እግር ኳስ ቡድን ዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫን ሲያነሳ በክልሉ የታየው መነቃቃትና መነሳሳት ደግሞ ስፖርት ምን ያህል ጉልበት እንዳለው የሚያሳይ እንደሆነም ያስረዳል።

የስፖርት መርህ ሰላምና ፍቅር መሆኑን የሚናገረው አትሌት ገብሬ በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ ግጭቶችና አለመግባቶች ስለስፖርት ምንነት ጠንቅቆ ካለማወቅ የመነጨ እንዳሆነ ይገልጻል።

Image copyright Awetehagn Birhane

ኢንቨስትመንትና ማህበራዊ ኃላፊነት

ከአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አገኘኋት በሚለው ተሞክሮ ባገኛት "ሳንቲም" ኢንቨስት ማድረጉን ይናገራል።

አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት ሕንጻዎች ሲኖሩት መቀሌ ከተማ ውስጥ ደግሞ ለሆቴል የሚሆን ሕንፃ እያስገነባ እንደሆነ ነግሮናል።

ከዚህም በተጨማሪ የስፖርት አልባሳትን ከውጭ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት የተሰማራው ገብረእግዚአብሄር የመቀሌ ሰብዓ እንደርታ ማልያ በእርሱ ኩባንያ በኩል እንደሚመጣ ይናገራል።

አትሌት ገብረ እግዚአብሄር በተለያዩ ሃገራዊ ኃላፊነቶችም በማገልገል ላይ ይገኛል። በአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኦሎምፒክ ኮሚቴ ውስጥ በአመራርነት ይሳተፋል።

በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ፌስቲቫል፡ ሙዚቃ፣ ኳስ፣ ፍቅርና ቡጢ..

ቢሆንም "በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መሳተፌ ውጤታማነቴ ላይ ድክመት እንዳያስከትልብኝ እፈራለሁ" ይላል።

"ሆኖም በምሰራቸው ስራዎች ደስተኛ ነኝ። ሃገራዊ ግዴታዬን መወጣቴ ደስ ያሰኘኛል። የአንድ ሰው ህይወትም ቢሆን ከቀየርኩ ደስተኛ ነኝ።"

ፖለቲካ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ጥያቄ የቀረበለት ገብረእግዚአብሄር ምላሹ አጠር እና ፈርጠም ያለ ነበር፤ "በፍጹም ፍላጎት የለኝም" የሚል።

"ሆኖም" ይላል ገብረእግዚአብሄር "ሰዎች ለውጥ ያመጣል ብለው ካመኑብኝ እሠራለሁ። የወከለኝን ሰው አላሳፍርም። አቅም አለኝ ብየ ግን አይደለም።"

"መስዋእትነት ነበር የምንከፍለው።"

'ወርቄ' እያለ አቆላምጦ የሚጠራት ባለቤቱ ወርቅነሽ ኪዳኔም ከሩጫውም ከሚድያውም ርቃለች።

"ወርቄ ለሀገሯ ብዙ ሠርታለች። ለዛውም ከፍተኛ መስዋዕትነትን እየከፈለች። አሁን ግን እኔም እሷም ወደ መተው ደረጃ ደርሰናል። የምንችለውን አድርገናል ብየ ነው የማስበው።"

በተለያዩ የአትሌቲክስና ኦሎምፒክ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን በቡድን ስራ የተዋጣ ስራ ሲሰሩ እንደነበር አትሌት ገብረ እግአዚአብሄር ይናገራል።

ሆኖም ወርቅ ላመጣ ብቻ የሚሰጠው እውቅናና ክብር ግን ያንን የቡድን ስራ ዋጋ እንዳይቀንሰው ይሰጋል።

"እኛ፤ እኔም ሆነ ቀነኒሳ፤ ጥሩነሽ ሆነች ወርቅነሽ ሁላችንም የምንሰራው ኢትዮጵያ ወርቅ እንድታገኝ ነው። በእኛ ምክንያት ሃገር ማፈር የለባትም ብለን ነው። ስለሆነም ቀነኒሳ ወርቅ አምጥቶ ባንዲራ አንስቶ ሲሮጥ፤ ሁላችንም ተነስተን በደስታ እንጨፍራለን።"ይላል።

ነገር ግን ወርቅ ያመጣው ላይ ብቻ ከፍተኛ ትኩረት ስለሚሰጥም በመንግሥትና በሚድያዎች ላይ መጠነኛ ቅሬታ እንዳለው ግን አልደበቀም።

"ወደ አገር ስትመጣ ለእንዲህ ዓይነት የቡድን ስራ ክብር ሲሰጥ አይታይም። ወርቅ ላመጣ ብቻ ክብር መስጠት ራሱን የቻለ ችግር አለበት። ይህንን ደጋግመን ነግረናቸዋል" ይላል።

አክሎም "በእርግጥ እኛ ተሰምቶን አያውቅም። የምንችለውን አድርገናል። መስዋዕትነት ነበር የምንከፍለው። ይሄ ከየት የመጣ ነው - ካልከኝ ከወከለን ህዝብ አደራ ነው።"

"በአምስት የአለም ዋንጫዎች ተሳትፌያለሁ። በአምስቱም ወርቅ አላመጣሁም። ወርቅ እንዲመጣ ግን ምክንያት ነኝ። በሁለት ኦሎምፒክ ተሳትፌያለሁኝ። በሁለቱም ወርቅ እንዲገኝ ምክንያት ነኝ። ወርቄ [ወርቅነሽ] ደግሞ በተመሰሳይ በስድስት የዓለም ዋንጫና በሶስት የኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች። እሷም እንደዚሁ። ወርቅ እንዲመጣ የመጀመርያ ተጠሪ እሷ ነች። 'ዘ ካንትሪ ዉማን' ይሉዋታል። ወደፊት ወጥታ ለሁለትና ለሶስት ቆርጣ ደረጃ ታወጣባቸዋለች። ከተሸላሚዎቹ በላይ ወርቅ እንዲመጣ ምክንያት ነች። እነሱም ያምናሉ። ወደ መንግሥት ስትመጣ ግን ሌላ ነው፤ ይሄ የአስተሳሰብ ጠባብነት ነው የሚመስለኝ።" ይላል

በሩጫ ውድድር ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሌሎች አገራዊ ዘርፎችም እንደዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ችግር እንዳለና መስተካከል እንዳለበት ያሳስባል ገብረእግዚአብሄር

"ለሁሉም በተለይ ደግሞ መስዋዕትነት ለሚከፍለው ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው። ጥቅም አይፈልግም" በማለት ሃሳቡን ይቋጫል።

ተያያዥ ርዕሶች