የኢቦላ መድሃኒት ላይ የተደረገ ሙከራ 90 በመቶ ውጤት አሳየ

የጤና ባለሙያዎች በኮንጎ ለኢቦላ ታማሚዎች እርዳታ በሚሰጥ አምቡላንስ አቅራቢያ መከላከያ ለብሰው Image copyright Reuters

ኢቦላን ማከምና መፈወስ የሚያስችሉ መድሀኒቶች ላይ እየተደረጉ ካሉ ምርምሮች መካከል ሁለቱ በከፍተኛ ሁኔታ ውጤት በማሳየታቸው ወረርሽኙን "መከላከልና ማከም" ያስችላል ሲሉ ተመራማሪዎች ተናገሩ።

የኢቦላ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋበት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አራት መድሃኒቶች በሕሙማን ላይ ሲሞከሩ ቆይተዋል።

እንደጥናቱ ውጤት ከሆነ ከአራቱ መድሐኒቶች ሁለቱ በከፍተኛ ሁኔታ በሽታውን በመከላከል ከፍተኛ ውጤት አሳይተዋል።

እንደ ሕክምና ባለሙያዎች ከሆነ መድሐኒቶቹ አሁን በዲሞክራቲክ ኮንጎ በበሽታው የተያዙ ሕሙማንን ለማከም ይውላሉ።

ኢቦላን የሚያክሙ የጤና ባለሙያዎች የሞት ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው

ምግብ ወሲብን የተሻለ ያደርጋል?

ብጉርን እንዴት መከላከል ይቻላል?

የምርምር ስራውን ካገዙት መካከል አንዱ የሆነው የአሜሪካው ብሔራዊ የአለርጂና የኢንፌክሽኖች ተቋም (NIAID) ውጤቱን ኢቦላን በመዋጋት ረገድ "በጣም መልካም ዜና" ሲል ገልጾታል።

መድሐኒቶቹ አርኢጂኤን-ኢቢ3 እና ኤምኤቢ114 ተብለው የተሰየሙ ሲሆን የኢቦላ ቫይረስ አንቲቦዲዎችን በማጥቃት ይሰራሉ፤ ይህም በሽታው የሰው ልጅ ሕዋስ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ነፃ ማድረግ ያስችላል።

የኤንአይኤአይዲ ዳይሬክተር የሆኑት አንቶኒ ፋውቺ እንዳሉት ከሆነ "በሳይንሳዊ መንገድ ሞትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት ያሳዩ መድሀኒቶች" ናቸው።

ዜድኤምኤፒፒ እና ሬምዴሲቪር የተባሉ ሌሎች ሁለት መድሀኒቶች ውጤታማነታቸው ስላልታየ ከሙከራ ተወግደዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከአለም አቀፍ ተመራማሪዎችን በማስተባበር የኢቦላ መድሀኒቶች ላይ ሙከራ መደረግ የተጀመረው ሕዳር ወር ላይ ነበር።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አራት መድሀኒቶች በ700 ሰዎች ላይ ውጤታማነታቸው የተፈተሸ ሲሆን የ499 ሰዎች ቅድመ ውጤት አልታወቀም ነበር።

ሁለቱ ውጤታማ መድሀኒቶቹ ከተሰጧቸው ግለሰቦች መካከል አርኢጂኤን-ኢቢ3 የወሰዱ 29 በመቶ ኤምኤቢ114 የወሰዱ ደግሞ 34 በመቶ መሞታቸውን የአሜሪካው የምርምር ድርጅት አስታውቋል።

በተቃራኒው ዜድኤምኤፒፒ የተሰጣቸው 49 በመቶ ሰዎች እንዲሁም ሬምዴሲቪርን የወሰዱ 53 በመቶ መሞታቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

በደማቸው ውስጠጥ አነስተኛ የኢቦላ ቫይረስ መጠን ያለ ግለሰቦች አርኢጂኤን-ኢቢ3 ሲሰጣቸው የመዳን እድላቸው 94 በመቶ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ኤምኤቢ114ን የወሰዱ ደግሞ 89 በመቶ የመዳን እድል እንዳላቸው በምርምሩ ተረጋግጧል።

እንደ ምርምሩ ውጤት ከሆነ የጤና ባለሙያዎች ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ቀድመው ሕክምና ከጀመሩ የመትረፍ እድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ "90 በመቶ የመትረፍ እድል ያላቸው ሰዎች ላይ አፅንኦት ሰጥተው ይሰራሉ" ሲሉ የጥናቱ አባል የሆኑት ሳቡኤ ሙላንጉ ተናግረዋል።

Image copyright Reuters

"ያለምንም ጥርጥር ሕይወትን ይታደጋል" ሲሉ የምርምር ስራውን ውጤት ያሞካሹት ደግሞ ትረስት ግሎባል ሔልዝ ቻሪቲ የተሰኘው ድርጅት ዳይሬክተር ጀርሚ ፋራር ናቸው።

የምርምሩ ውጤት የሚያሳየው ይላሉ ሚስተር ፋራር ተመራማሪዎች ኢቦላን "መከላከልና ማከም " ወደሚቻል በሽታነት ለመቀየር ቅርብ መሆናቸው ነው።

አክለውም "ኢቦላን ፈፅሞ ልናጠፋው አንችልም። ነገር ግን ይህንን ወረርሽኝ የብሔራዊም ሆነ የዓለም አቀፍ ስጋት ከመሆን ልናቆመው እንችላለን።"

በኮንጎ ሦስት ዶክተሮች የጤና ባለሙያዎችን በመግደል ተጠርጥረው ተያዙ

ኢቦላ ሊድን የሚችል በሽታ አለመሆኑና በሕክምና ባለሙያዎች ላይ ከተፈጠረ ጥርጣሬ ጋር ተደምሮ በዲሞክራቲክ ኮንጎ በሽታውን ለማቆም የሚደረገውን ጥረት ጎድቶት ነበር።

ዶ/ር ፋኢቺ ሕሙማን የመድሀኒቱን ውጤታማነት ሲያዩ "ሕክምና ፈልገው ለመምጣት ፍላጎት ያሳያሉ" ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል።

ወረርሽኙን ለማቆም ግን "ውጤታማ ክትባት" ማካሄድ የያስፈልጋል በማለት ክትባቱ ለወረርሽኙ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን የመከላከል አቅም ከፍ በማድረግ የሚሰራ መሆኑን አስታውሰዋል።

ባለፈው ዓመት ብቻ 1ሺህ 800 ሰዎች በኢቦላ ተይዘው የሞቱ ሲሆን የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት የታጠቁ አማፂያንና የውጪ የሕክምና ድጋፍ ላይ ያለው ጥርጣሬ እያደናቀፈው ይገኛል።

በአሁን ሰዓት በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የጀመረው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ሲሆን በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ በሃገሪቱ ውስጥ ከተገኘበት ከአውሮፓዊያኑ 1976 ወዲህ ይህ በስፋቱ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ከዚህ በፊት በምዕራብ አፍሪካ ከአውሮፓዊያኑ 2014-16 ድረስ ተከስቶ በነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ 28ሺህ 616 ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 11ሺህ 310 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

አብዛኞቹ የኢቦላ ወረርሽን ተጠቂዎች የጊኒ፣ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን ሃገራት ዜጎች ነበሩ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ