የትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ላይ ቅሬታ አቀረበ

የትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤትን ላይ ቅሬታ አቀረበ Image copyright Tigrai Mass Media Agency
አጭር የምስል መግለጫ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኢንጅነር ገብረመስቀል ካህሳይ

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ላይ ቅሬታውን አቀረበ።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኢንጅነር ገብረመስቀል ካህሳይ ብሔራዊ ፈተናው በተሰጠበት ወቅት "በአንዳንድ የሃገሪቱ ክፍሎች የፈተና አሰጣጥ ሥነ-ምግባር ጉድለት" ነበር ብለዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኢንጅነር ገብረመስቀል ካህሳይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "በክልላችን ፈተናው ሲካሄድ የፈተና አወሳሰድ ስነ-ምግባርን ጠብቆ ነበር። ይሁን እንጂ በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች ስርዓቱን የጠበቀ አልነበረም" ብለዋል።

"በተለይ በአንድ ክልል ከኩረጃ የፀዳ ስላልነበር ፈተናው እንዳለቀ ማጣራት እንዲካሄድ ጥያቄ አቅርበን የተሰጠን ምለሽ እናየዋለን የሚል ነበር" ሲሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

ዶ/ር ኢንጅነር ገብረመስቀል ካህሳይ በወቅቱ ተስተውሏል ስላሉት የፈተና አሰጣጥ ስነ-ምግባር ጉድለት ለትምህርት ሚንስቴር አሳወቀው እንደነበረ ተናግረዋል።

"ከክልላችን እና ከሌሎች አከባቢዎች የተነሳው ቅሬታ ምላሽ ሳያገኝ ውጤቱ ይፋ ሆኖዋል። በዚህም ቅሬታ አለን።" ብለዋል።

ዶ/ር ኢንጅነር ገብረመስቀል "የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ የፈተና ውጤቱን አልቀበልም አለ" ተብሎ የተዘገበው ስህተት ነው ሲሉም አክለዋል።

የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገ/እግዚአብሄር በበኩላቸው በውጤቱ ላይ ለሚነሱ ቅሬታዎች በሙሉ አስፈላጊው ማጣራት ከተካሄደ በኋላ ምላሽ ይሰጠዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አርዓያ ጨምረው እንደተናገሩት ከፈተና አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የቀረበ ቅሬታ የለም።

"ተማሪዎች ያጠቆሩትን ወረቀት ነው ማሽን የሚያነበው። ሆኖ ተብሎ የተማሪን ውጤት መቀየር አይቻልም" የሚሉት አቶ አርዓያ ዘንድሮ የተሰጠው ፈተና "ጥብቅ በሆነ ክትትል" የተከናወነ ነው ብለዋል።

የ12ኛ ከፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ትናንት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ከስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ፈተና ውጤት ጋር በተያያዘ ሰፊ ቅሬታ ተነስቶ ነበር።

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲም በስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ የፈተና ውጤት ላይ ከተማሪዎች፣ ከወላጆች እና ከመምህራን የቀረበውን ቅሬታ ለማጣራት ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል።

አቶ አርዓያ ኮሚቴው አስፈላጊውን ማጣራት አድረጎ የመጨረሻ ውጤቱን "በአምስትም ይሁን በአስር ቀናት ውስጥ" ያሳውቃል ብለዋል።

የዘንድሮውን ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ ከፍተኛ ውጤት 645 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ ከ600 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር 59 ነው።

የዩንቨርስቲ መግቢያ (የ12ኛ ክፍል) ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡት 322 ሺህ 717 ተማሪዎች መካከል 319 ሺህ 264 የሚሆኑት ፈተናውን መውሰዳቸውን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ተያያዥ ርዕሶች