ከ125 በላይ የተጠፋፉ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችን ያገናኘችው አሜሪካዊት

አንድርያ ከጉዲፈቻ ልጆቿና ከባለቤቷ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Andrea Kelley

የምስሉ መግለጫ,

አንድርያ ከጉዲፈቻ ልጆቿና ከባለቤቷ ጋር

አሜሪካዊቷ አንድርያ ኬሊ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ልጆች አሏት። የአብራኳ ክፋይ ባይሆኑም እናታቸው ናት።

ከ19 ዓመት በፊት እሷና ባለቤቷ ወንድ ልጅ በማደጎ ተረከቡ። ልጁን ወደቤታቸው የወሰዱበት ቀን ከአንድርያ ህሊና አይጠፋም። ልክ ልጁን ስትታቀፈው በደስታ ብዛት ትንፋሽ አጠራት።

ቀናት ሲገፉ፤ ልጁን አምጣ የወለደችው እናት የት ትሆን? ብላ ታስብ ጀመር። አንድ እናት የዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ልጇ የት እንደደረሰ ሳታውቅ እንዴት ሕይወት ይገፋላታል? የዘወትር ጥያቄዋ ነበር።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2002 ላይ ከባለቤቷ ጋር ሁለተኛ ልጅ በጉዲፈቻ ለመውሰድ ወሰኑ። አሜሪካ ውስጥ በሚገኝ የህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ 'ወላጅ አልባ' ተብላ የተመዘገበች ኢትዮጵያዊት ልጅን ተረክበው ወደ ቤተሰቡ ቀላቀሏት።

አንድርያ ስለሁለቱ የጉዲፈቻ ልጆቿ እናቶች ማሰብ ማቆም አልቻለችም። ነገሩ በጣም ሲያስጨንቃት የጉዲፈቻ ልጆቿን ቤተሰቦችን መፈለግ ጀመረች።

"ልጆቹ ደህና እንደሆኑ ለወላጆቻቸው ማሳወቅ እንዳለብኝ ወሰንኩና ፍለጋ ጀመርኩ" ትላለች።

"የልጆቼን ወላጆች ስፈልግ 'ቤተሰብ ፍለጋ' ተመሰረተ"

አንድርያ የጉዲፈቻ ልጆቿን ቤተሰቦች መፈለግ የጀመረችው በምትኖርበት አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን 'ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው የሚገኘው እንዴት ነው?' እያለች በማጠያየቅ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Andrea Kelley

የምስሉ መግለጫ,

የአንድርያ የጉዲፈቻ ልጅ፤ ወላጅ እናቷን ኢትዮጵያ ውስጥ ስታገኝ የተነሳ ፎቶግራፍ

እድለኛ ሆና አንድ ኢትዮጵያዊ ሊረዳት ፈቀደና ሴት ልጇ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ስትወሰድ የተሰጧትን ሰነዶች አዲስ አበባ ለምትኖር እህቱ ላከ። እህቱም፤ ልጅቷን ለማደጎ የሰጠችው የልጅቷ እናት ጓደኛ እንደሆነች፤ እናትና ልጅን ማገናኘት እንደሚቻልም አሳወቀችው።

በወቅቱ ልጅቷ ሁለት ዓመት ሞልቷት ነበር።

የአንድርያ የጉዲፈቻ ልጅ ስድስት ዓመት ሲሆናት ወደ ኢትዮጵያ ሄዳ ከወላጅ እናቷ ጋር ተዋወቀች። አንድርያና የልጅቷ እናት በቋንቋ ባይግባቡም አንዳቸው የሌላቸውን ደስታ ከፊታቸው ለማንብ እንዳልተቸገሩ ታስታውሳለች።

"ያኔ የጉዲፈቻ ልጄ ህጻን ስለነበረች ነገሩ ብዙም ስሜት አልሰጣትም ነበር። ከፍ እያለች ስትመጣ ግን ከእናቷ ጋር መጠያየቅ፣ መቀራረብም ጀመረች።"

ልጇ አሁን 17 ዓመቷ ነው። የ11ኛ ክፍል ተማሪ እና ቫዮሊን ተጫዋች ናት። እናቷን ወደ ኢትዮጵያ እየሄደች ትጠይቃለች፤ አዘውትረውም በስልክ ያወራሉ።

ከዚህ በተቃራኒው የአንድርያ የጉዲፈቻ ወንድ ልጅ ቤተሰቦቹን እስካሁን አላገኘም። አንድርያ እና ባለቤቷ ልጁን ማሳደግ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ወላጆቹን ቢያፈላልጉም አልተሳካላቸውም።

"ቤተሰቦቹን ፍለጋ ደጋግመን ወደ ኢትዮጵያ ሄደናል፤ አፈላላጊ ቀጥረናል፤ በቴሌቭዥን፣ በራድዮ፣ በጋዜጣ የአፋልጉኝ ማስታወቂያ አውጥተናል. . . ያልሞከርነው ነገር የለም. . . የወላጅ አልባ ህጻናት ድርጅት፣ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ፣ ፖሊስ ጣቢያ፣ ፍርድ ቤት. . . ያልረገጥነው ቦታ የለም. . . ወደ 19 ሺህ ዶላር አውጥተናል።"

የፎቶው ባለመብት, Andrea Kelley

የምስሉ መግለጫ,

እስካሁን ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቹን ማግኘት ያልቻለው የአንድርያ የጉዲፈቻ ልጅ ህጻን ሳለ የተነሳው ፎቶግራፍ

ላለፉት 19 ዓመታት የጉዲፈቻ ልጃቸውን ቤተሰቦች ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ውጤት ባያስገኝም፤ አሁንም ተስፋ አልቆረጡም።

አንድርያ የጉዲፈቻ ልጆቿን ቤተሰቦች ስታፈላልግ፤ በኢትዮጵያውያን ወላጆች እና በጉዲፈቻ በሰጧቸው ልጆች መካከል ሰፊ ክፍተት መኖሩን አስተውላለች።

ለሀያ፣ ለሠላሳ ዓመታት እና ከዚያም በላይ ቤተሰብን መፈለግ፤ የአንድርያ የጉዲፈቻ ልጅ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሺዎች ታሪክ ነው። ልጄ የት ናት? ልጄን መቼ አየው ይሆን?. . . የበርካታ ወላጆችን ልብ የሚሰቅል ጥያቄ ነው።

"ወላጆች ስለልጆቻቸው፤ ልጆችም ስለወላጆቻቸው ማወቅ ይገባቸዋል። ከራሴ ተሞክሮ ተነስቼ 'ቤተሰብ ፍለጋ' የተባለ ወላጆችና ልጆችን የሚያገናኝ ድርጅት ያቋቋምኩትም ለዚህ ነው።"

ቤተሰብ ፍለጋ ወይም Ethiopian Adoption Connection በተለያየ ምክንያት በጉዲፈቻ የተሰጡ ልጆችና ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቻቸውን ማገናኘት ከጀመረ አምስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፤ ከ125 በላይ የተጠፋፉ ቤተሰቦችንም አገናኝቷል።

ፍለጋ. . .

ልጇን የምትፈልግ እናት፣ እህቱን የሚፈልግ ወንድም. . . ብዙዎች ፍለጋውን ከየት እንደሚጀምሩ ግራ ይገባቸዋል።

ልጆችን ለጉዲፈቻ የሚሰጡ ድርጅቶች፤ ልጆቹ ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ ስለልጆቹ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ። ልጆቹን የሚቀበላቸው ድርጅት ወይም አሳዳጊ ቤተሰብ መረጃ መስጠት የሚያቋርጡበት አጋጣሚም አለ። አንዳንድ ቤተሰቦች፤ ልጆቻቸው በምን መንገድ ከኢትዮጵያ እንደወጡ፣ የት አገር እንደሚኖሩ እና እንዴት ሊያገኟቸው እንደሚችሉም አያውቁም።

'ቤተሰብ ፍለጋ' ይህንን ክፍተት ለመሙላት ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ልጅ፣ እህት፣ ወንድም ወይም የቅርብ ዘመድ የመፈለግ ሂደቱ እንዲህ ነው. . . በመጀመሪያ ቤተሰቦች ስለልጁ/ልጅቷ ያላቸውን መረጃ ባጠቃላይ ለ'ቤተሰብ ፍለጋ' ይሰጣሉ። ልጆቹ ሲወለዱ የወጣላቸው ስም፣ ለጉዲፈቻ የተሰጡበት ዓመተ ምሕረት፣ የልጅነት ፎቶ፣ በጉዲፈቻ የተወሰዱበት አገር፣ ለጉዲፈቻ የሰጣቸው ድርጅት መጠሪያ ወዘተ. . .

ከዚያም በጉዲፈቻ ስለተወሰደው ወይም ስለተወሰደችው ልጅ የተሰበሰበው መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ ይሰራጫል። በዋነኛነት በ'ቤተሰብ ፍለጋ' የፌስቡክና የትዊተር ገጽ ላይ ልጆቹ ይፈለጋሉ። አሜሪካ እና አውሮፓ የሚሠሩ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪዎች በማፈላለግ ሂደቱ ድጋፍ ያደርጋሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ቤተሰብ መረጃ የሚያቀብሉ ኢትዮጵያዊ ማኅበራዊ ሠራተኞችም አሉ።

የልጆቹን የጉዲፈቻ ቤተሰቦች አልያም ልጆቹን ለማግኘት ከሳምንታት እስከ ዓመታትም ሊወስድ ይችላል። ሁሉንም ሰው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማግኘት አይቻልምና የሚፈለጉት ልጆች ወይም የጉዲፈቻ ቤተሰቦቻቸው አንድ ቀን መረጃውን እስኪያዩት መጠበቅ ግድ ይላል።

'ቤተሰብ ፍለጋ' ባዘጋጀው የመረጃ ቋት (ዳታቤዝ) ላይ የልጆቹ መረጃ ተመዝግቦ ስለሚቀመጥ በየትኛውም ጊዜ 'ጉግል' ሲያደርጉ ያገኙታል። አንድርያ እንደምትናገረው፤ እስካሁን በ 'ዳታቤዝ' ውስጥ 700 የሚደርሱ 'ኬዞች' (የተጠፋፉ ቤተሰቦች) ተመዝግበዋል።

የፎቶው ባለመብት, Andrea Kelley

የምስሉ መግለጫ,

ከ43 ዓመት ፍለጋ በኋላ ልጇን ያገኘችው ሀሊማ ሀሰን ከልጇ ሁሴን ፈይሰል እና አንድርያ ኬሊ ጋር

"ዳታቤዝ ውስጥ ያለው መረጃ ልጆቹ እስከሚገኙ ድረስ አይጠፋም። አንዳንድ ቤተሰቦች ልጆቹ የት አገር እንደተወሰዱ ስለማያውቁ ፍለጋው ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ብዙ አገሮች ውስጥ የሚያግዙን በጎ ፍቃደኞች አሉ።"

"ፍለጋው ስሜታዊ ነው፤ እንቅልፍ ይነሳኛል"

ከማን ማህጸን ተፈጠርኩ? ማንን ነው የምመስለው? ወላጆቼ ለምን ለጉዲፈቻ ሰጡኝ?. . . ልጄ በሕይወት አለችን? ልጄን በዓይነ ሥጋ ሳላየው ብሞትስ?. . . የልጆችም የወላጆችም ሕይወት በእነዚህ ጥያቄዎች መዋጡ አይቀርም።

ልጆች ቤተሰቦቻቸውን፤ ወላጆች ልጆቻቸውን ለዓመታት ይፈልጋሉ. . . ፈላጊዎች ከተፈላጊዎች ወገን ስለሚኖረው ምላሽ ባያውቁም ከመፈለግ አይቦዝኑም።

የፍለጋ ሂደቱን የምታስተባብረው አንድርያ እናቶች፣ አባቶች፤ 'ፈጣሪ ይመስገን! ልጄ በሕይወት አለ!' ሲሉ እንደመስማት የሚያስደስታት ነገር የለም። ደስታዋን የሚያደበዝዙ ታሪኮችም ብዙ ናቸው።

"የምደሰትበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ የማዝንበት ወቅትም አለ። ሥራዬ ቀላል አይደለም። የአንዳንድ ቤተሰቦች ጉዳይ እንቅልፍ ይነሳኛል።"

አንዳንድ የጉዲፈቻ ቤተሰቦች የልጆቻቸው ወላጆች እየፈለጓቸው እንደሆነ ሲያውቁ ይበሳጫሉ። ልጆቹን ከወላጆቻቸው ጋር ለማገናኘትም አይፈቅዱም። በሌላ በኩል፤ ልጅ ፍለጋው ገንዘብ ማሳደድ እንደሆነ የሚሰማቸው ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር መገናኘት አይሹም።

"ከሁሉም በጣም የሚከብደው ልጆች ወላጆቻቸውን 'አንፈልግም' ሲሉ ነው። 'ልጅሽን አፈላልገን አግኝተነዋል፤ ነገር ግን ሊያገኝሽ አይፈልግም' የሚል ዜና ለወላጅ መንገር አስጨናቂ ነው" ትላለች።

የየቤተሰቡ የፍለጋ ታሪክ ይለያያል. . . ውጤቱም እንደዚያው።

አንዲት ሴት 'የጉዲፈቻ ልጅሽ ወላጅ እናት እየፈለገችው ነው' የሚል መልዕክት ሲደርሳት፤ 'የልጄን ቤተሰቦች ማግኘት ብፈልግ እኔው እፈልጋቸው ነበር፤ እናንተ ምን ጥልቅ አደረጋችሁ!' ብላ መቆጣቷን አንድርያ ታስታውሳለች።

የኋላ ኋላ ልጁ ስለ ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቹ መጠየቅ ጀመረ። የጉዲፈቻ እናቱ ነገሩ ባይዋጥላትም 'ልጄ ስለወላጆቹ እየጠቀኝ ነውና የእናቱን አድራሻ ስጪኝ' ብላ ለአንድርያ ኢሜል ላከች።

ሁለት ልጆቻቸው በጉዲፈቻ ወደ አውሮፓ ተወስደው ለዓመታት በፍለጋ የባዘኑ የአንድ አዛውንት ታሪክም አይረሳትም። አኚህን አባትም ከልጆቻቸው ጋር ማገናኘት መቻሏ ያኮራታል።

የፎቶው ባለመብት, Andrea Kelley

የምስሉ መግለጫ,

ከዓመታት በኋላ ወላጅ እናቷን ያገኘችው አማረችና አንድርያ

"ልቤን ከሰበሩት ታሪኮች አንዱ የእነዚህ ጥንዶች ነው. . . ጥንዶቹ ልጅ የወለዱት ወጣት ሳሉ ነበር። ለቤተሰቦቻቸው መናገር ፈሩ፤ እንዳያሳድጓት ደግሞ ገንዘብ አልነበራቸውም። ሕይወታቸውን ፈር አስይዘው ማሳደግ እስኪችሉ ድረስ ልጃቸውን ለህጻናት ማሳደጊያ ሰጧት።

"ከጥቂት ጊዜ በኋላ ልጃቸውን ለመውሰድ ወደ ህጻናት ማሳደጊያው ሲመለሱ ልጃቸውን አጧት። የማሳደጊያው ሠራተኞች የጥንዶቹን ፍቃድ ሳይጠይቁ በጉዲፈቻ ሰጥተዋት ነበር. . .

". . . ጥንዶቹ ልጃቸውን እንድንፈልግላቸው ከነገሩን ቀን ጀምሮ እናትየዋ በየቀኑ ቢያንስ ሦስቴ ትደውልልኝ ነበር። ከብዙ ልፋት በኋላ የልጅቷን የጉዲፈቻ ቤተሰቦች አገኘናቸው። ነገር ግን ከወላጆቿ ጋር ሊያገናኟት ፍቃደኛ አልሆኑም። በጣም ተናደድኩ፤ ለሳምንታት ተጨነቅኩ፤ ታመምኩ። እናትየዋ 'የልጄ አሳዳጊዎች ልጄን የሚወዷት ከሆነ ለምን እኔን መቀበል ከበዳቸው? እኔ'ኮ የልጄ አካል ነኝ!' ስትለኝ የምመልስላት ነገር አጣሁ. . ."

አንድርያ ይህን መሰል ታሪኮች የሚፈጥሩባትን ሀዘን፤ ለዓመታት ሲፈላለጉ የነበሩ ቤተሰቦች ተገናኝተው፣ ጥሩ ግንኙነት መስርተው ስታይ በሚሰማት ደስታ እየሻረች ሕይወትን ተያይዛዋለች. . .