የማልታ ስደተኞች፡ ብቸኛው ከሞት ተራፊ ኢትዮጵያዊ ያሳለፈውን እንዲህ ይተርካል

የማልታ ስደተኞች፡ ብቸኛው ከሞት ተራፊ ሰው ያሳለፈውን እንዲህ ይተርካል Image copyright TIMES OF MALTA

«ጀልባዋ ላይ 15 ሰዎች ነበርን። እኔ ብቻ ነኝ በሕይወት የተፈርኩት» ሲል ሞሐመድ አደም ኦጋ ማልታ ከሚገኝ ሆስፒታል አልጋ ላይ ያጋጠመውን ይናገራል።

እያንዳንዳቸው ስደተኞች ለሕገ-ወጥ ደላሎች 700 ዶላር ከፍለዋል። ከሊቢያ በሜድትራኒያን ባሕር በኩል ወደ አውሮጳ ለመዝለቅ።

የጉዟቸው አጋማሽ ላይ ግን ጀልባዋ ነዳጅ ጨረሰች። ምግብና ውሃም መገባደድ ያዘ። ጀልባዋ ላይ አንዲት ነብሰ ጡር ሴት እንደነበረች ሞሐመድ ያስታውሳል።

«ባሕር ላይ 11 ቀናት አሳልፈናል። የምንጠጣው ውሃ ሲገባደድብን የባሕር ውሃ መጠጣት ያዝን። ከአምስት ቀናት በኋላ ሁለት ሰዎች ሞቱ። ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት በየቀኑ ሁለት ሁለት ሰዎች መሞት ያዙ።»

አንዲት አነስተኛ ጀልባ ሜዲትራኒያን ላይ ስትዋልል የተመለከቱት የማልታ ወደብ ጠባቂዎች በሄሊኮፕተር ታግዘው ሞሐመድን ሊያድኑት ቻሉ።

ሞሐመድ በሕይወት ጀልባዋ ላይ በተገኘበት ወቅት አንድ ሌላ ሰው አብሮት ነበር፤ በሕይወት አልነበረም እንጂ።

«አምላክ ነው የማልታ ሰዎችን የላከልኝ» ሲል ነበር ሞሐመድ ሁኔታውን የገለፀው።

የ38 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ሞሐመድ ሃገር ቤት ያለውን ፖለቲካ ሸሽቶ እንደተሰደደ ይናገራል። እርሱ በተሰደደ ወቅት ኦነግ በመንግሥት ዓይን በቁራኛ ይታይ ነበር። ከዚያ ጀርመን የሚገኙ ዘመዶቹን ለመቀላቀል ስደት ያዘ።

ሞሐመድ አብረዉት ጀልባዋ ላይ የነበሩት ሁለት ጋናውያን፣ ሁለት ኢትዮጵያዊያን እና 11 ሶማሊያውያን እንደነበሩ ያወሳል።

Image copyright TIMES OF MALTA

ለጉዞ የያዙት ምግብ፣ ውሃ እና ነዳጅ ካለቀ በኋላ እርዳታ ፍለጋ ለአላፊ አግዳሚ መርከቦች እና ሄሊኮፕተሮች ቢያውለበልቡም እጅ የሚዘረጋላቸው ግን አልተገኘም።

«ጅልባዎችን ስናይ 'ሄልፕ፤ ሄልፕ' እያልን እጃችንን ብናውለበልብም እያዩን ሲያልፉ ነበር። አንድ ሄሊኮፕተር መጥቶ ጥሎን ሄደ።»

ሞሐመድ ጅልባዋ ላይ እያሉ ሕይወታቸው ስላለፈ የስደት አጋሮቹ ሲናገር እንባ እየተናነቀው ነው። «ጀልባዋ ላይ ሳሉ ነበር የሞቱት። ሶማሊያዊው አጋሬ ኢስማኤል ሬሳዎቹን ወደ ባሕር ከመግፋት ያለፈ አማራጭ የለኝም አለኝና ያንን አደረግን። ሽታ አምጥተው ነበር።»

«ኢስማኤል፤ ሁሉም ሰው ሞቷል። የእኛስ ዕጣ ምንድነው? አለኝ። እንደውም አብረን ነው መሞት ያለብኝ ብሎኝ ነበር። እኔ መሞት አልፈልግም ብትፈልግ ብቻህን ሙት ስለው ነበር።»

አሁን ሞሐመድ ማልታ ውስጥ የሕክምና እርዳታ እያገኘ ነው። የጀልባዋን የመጨረሻ ቀናት እንደ ሕልም ነው የማስታውሳቸው ይላል። ኢስማኤል መሞቱንም የተረዳው ሆስፒታል አልጋው ላይ ሆኖ ነው። የማልታ ድንበር ጠባቂዎች በሄሊኮፕተር ሲያነሱትም ሆነ ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ የሚያስታውሰው ነገር የለም።

ወደ ኢትዮጵያ ቢመለስ እሥር ሊገጥመው እንደሚችል ይገምታል። ከ15 ዓመታት በፊት ከሃገር ቤት የተሰደደው ሞሐመድ ኤርትራ እና ሱዳን በርካታ ዓመታት ኖሯል።

'እንደው ይህንን ጉዞ በማድረግህ የሚቆጭህ ነገር ይኖር ይሆን?' ለሞሐመድ የቀረበለት ጥያቄ፡ «ኧረ እንዲያውም፤ በሕይወት በመኖሬ ደስተኛ ነኝ።»

በዚህ ዓመት ብቻ ሞሐመድን ጨምሮ 40 ሺህ ገደማ ስደተኞች ሜዲትራኒያንን ባሕርን አቋርጠው አውሮጳ ገብተዋል። የተባበሩት መንግሥታት መረጃ 839 ሰዎች የባሕር ሲሳይ መሆናቸውን ያሳያል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ