ለምን ወንዶች ከሴቶች በበለጠ እራሳቸውን ያጠፋሉ?

አሳሳቢው የወንዶች ራስን የማጥፋት አባዜ Image copyright Getty Images

የሄለን ሹማኽር ወንድም እራሱን ያጠፋው የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ነበር፤ የ28 ዓመት ወጣት ሳለ። ሄለን ከምታውቃቸውና እራሳቸውን ካጠፉ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ደግሞ ወንዶች ናቸው፤ የገዛ ወንድሟን ጨምሮ። ግን ለምን?

በጣም የሚያሳዝነው ሰዎች እራስን የማጥፋት አባዜ በዓመት አንዴ የሚከሰት አድርገው ማሰባቸው ነው። ነገር ግን እውነታው ወዲህ ነው።

በመረጃ እንደግፈው - የዓለም ጤና ድርጅት ከሦስት ዓመት በፊት ያወጣው ሰንጠረዥ ላይ 793 ሺህ ገደማ ሰዎች እራሳቸውን በማጥፋት የምንኖርባትን ምድር እንደተሰናበቱ ያሳያል። አብዛኛዎቹ ደግሞ ወንዶች።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከ1981 ወዲህ [በግሪጎሪ አቆጣጠር] ዝቅተኛ የተባለለት እራስን የማጥፋት አሃዝ ቢመዘገብም ራስን ማጥፋት አሁንም የሰውን ልጅ ከሚቀጥፉ በሽታዎች እኩል አስጊ ነው። የእንግሊዙ አሃዝ ላይም አንድ ነገር ማስተዋል ይቻላል፤ አብዛኛዎቹ እራሳቸውን የሚያጠፉት ወንዶች መሆናቸውን።

አውስትራሊያ እንዝለቅ። ከሴቶች ጋር ሲነፃፀር ወንዶች በሦስት እጥፍ እራሳቸውን ያጠፋሉ። አሜሪካ 3.5፤ ሩስያና አርጀንቲና ደግሞ አራት እጥፍ።

ኬንያም ቢሆን እራስን ማጥፋት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ወደ ኢትዮጵያ ስንዘልቅም ውሉ የታወቀ ቁጥር ባናገኝም እራስን የማጥፋት ዜና እየተለመደ መጥቷል። አብዛኛዎቹ አሁንም ወንዶች።

ማጣፊያው ያጠራት አሜሪካ እራስ ማጥፋትን የሚከላከል 'ፋውንዴሽን' ካቋቋመች ዘመናት ተቆጥረዋል። የፋውንዴሽኑ ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ጂል ሃርካቪ «እራስ የማጥፋት ክስተት አሃዝን መስበሰብ ከጀመርንበት ወቅት አንስቶ በወንዶች እና ሴቶች መካከል ያለው ልዩነት ሁሌም እንደሰፋ ነው» ይላሉ።

እራስን ማጥፋት በበርካታ ሃገሮች ሰዎች ብዙም የማይነጋገሩበት ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ ምክንያቱን ለማጥናት እንቅፋተ-ብዙ ያደርገዋል። በወንዶች እና ሴቶች መካከል ያለው የቁትር ልዩነት ግን አሁን አነጋጋሪው ጉዳይ ነው።

እርግጥ ነው ሴቶችም እንደወንዶች እራሳቸውን ለማጥፋት ይሞክራሉ። አሜሪካ ውስጥ እራስን የማጥፋት ሙከራ የሴቶች እና የወንዶች ይህን ያህል ልዩነት የለውም። ነገር ግን ወንዶች እራሳቸውን ለማጥፋት የሚጠቀሙበት መንገድ ርህራሄ የለሽ ነው።

ራስን ማጥፊያ መንገዶች በቀላሉ ማግኘት ደግሞ ችግሩን የበለጠ አባብሶታል። ከ10 የጦር መሣሪያ ካላቸው አሜሪካውያን 6ቱ ወንዶች ናቸው።

አንድ ጥናት 4 ሺህ ሰዎችን አሳተፈ። ታድያ እኒህ ተሳታፊዎች እራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረው ያልተሳካላቸው፤ የሆስፒታል ውስጥ ነው የሚገኙት። ይህ ጥናት ካሳተፋቸው መካከል ወንዶቹ እራሳቸውን ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ለምን ወንዶች?

ተግባቦት [ኮሚዩኒኬሽን]።

ሴቶች ችግሮቻቸውን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንደሚያካፍሉ እሙን ነው። ወንዶች ደግሞ ወደ ውስጥ ማመቅ ይቀናቸዋል። ይህ አረፍተ-ነገር ተደጋግሞ ሲነገር ይደመጣል፤ እውነትም ነው።

አደጉም በተባሉት ሆነ በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ወንዶች 'ጠንካራ' እንዲሆኑ እና ችግር ላይ እንዳሉ አምነው እንዳይቀበሉ ተደርገው ነው የሚያድጉት።

«ወንድ ልጅ አያለቅስም ብለን እኮ ነው የምናሳድጋቸው» ይላሉ አውስራሊያዊው የዘርፉ ሰው ኮልማን ኦድሪስኮል። «ስሜትን መግለፅ 'ደካማነት' እንደሆነ አድርገን፤ ወንዶች ልጆቻችን ስሜታቸውን እንዳይገልፁ ገድበን ነው የምናሳድጋቸው፤ »

«እናቶች ከሴት ልጆቻቸው ጋር ስለ ስሜታቸው በግልፅ ያወራሉ። ሴቶች ስሜታዊ እንዲሆኑ ነው የሚጠበቅባቸው።»

አልፎም ወንዶች ባለሙያ ጋር ሄደው ችግሮቻቸውን በማውጋት መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የራሳቸውን መላ መዘየድ እንደሚቀላቸው ጥናቶች ያሳያሉ።

Image copyright Getty Images

ጂል፤ «ወንዶች እኮ ልክ እንደሴቶች ችግር ሳያጋጥማቸው ቀርቶ አይደለም። ነገር ግን ትኩረት አይሰጡትም። ጭንቀት ወይም የአእምሮ ሕመም አጋጥሞናል ብለው አያስቡም» ሲሉ ይተነትናሉ።

ጂል እና ባልደረቦቿ ያካሄዱት አንድ ጥናት እራሳቸውን ካጠፉ አሜሪካዊያን መካከል አንድ ሦስተኛው ብቻ ናቸው የአእምሮ ጤና ችግር እንደነበረባቸው ያረጋግጣል።

«ዕፅ መጠቀምና አልኮል ማዘውተር የወንዶች የጭንቀት ማስወገጃ መንገዶች ናቸው። እነዚህ ተግባራት ጭንቀት እንዳለባቸው ሊነግሩን ይችላሉ። ከዚያ ባለፈ ግን እራስን ወደ ማጥፋት ሊያመሩ እንደሚችሉ ልናስባቸው ይገባል።»

ከቤተሰብ እና ሥራ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ሌሎች ወንዶችን ወደ እራስ ማጥፋት የሚገፈትሩ ምክንያቶች ናቸው። ለምሳሌ በምጣኔ ሃብት የደቀቀች ሃገር ወንዶች ከሥራ ማጣት የተነሳ እራሳቸውን ሊያጠፉ ይችላሉ።

ማሕበረሰባዊ ጫና እና የማንነት ቀውስም ሌሎች ወንዶችን እራስን ለማጥፋት የሚዳርጉ ምክንያቶች ሆነው ተመዝግበዋል። ብዙ ጊዜ ራሳቸውን በዙሪያቸው ካሉ እኩያ ጓደኞቻቸው ጋር የሚያነፃፅሩ ወንዶች ለከፋ አደጋ የተጋለጡ ናቸው።

ወንዶች ጭንቀትን የሚያዩበት መንገድ መጣመም እንጂ ሴቶች በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ያልፋሉ የሚል ሃሳብ የሚያነሱት ጂል ናቸው።

መፍትሄ. . .

እራስን ማጥፋት ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ እንዲሁ በቀላሉ መፍትሄ መዘርዘር የሚቻል አይደለም።

ትልቁና ተመራጩ መፍትሄ ግን ተግባቦትን [ኮሚዩኒኬሽን] ማጠናከር ነው። ሰዎች ስለሕይወታቸው እንዲያወሩ ማድረግ፣ የሚደገፉበትን ትከሻ አለመንፈግ፣ ሙሉ ጆሮ እና ጥሞናን መስጠት።

«ወንዶች ስሜታቸውን መግለፃቸው፤ የውስጣቸውን ማውጋታቸው ትክክል መሆኑን ማሳየት። አልፎም እንዲህ ማድረጋቸው የጥንካሬ መገለጫ መሆኑን እውቅና መስጠት ተገቢ ነው» ይላሉ ኮልማን ኦድሪስኮል።

ሌላው ሊዘነጋ የማይገባው ነገር፤ የወንዶች እራስን የማጥፋት መዘዝ ለሌላውም እንደሚተርፍ ማወቅ አለባቸው። እራስን አለማጥፋት ምርጫ እንደሆነ ማሳየት ባለሙያዎች የሚመክሩት አንዱ የመፍትሄ ሃሳብ ነው። ሰዎች እራሳቸውን ሲያጠፉ ወዳጃ ዘመዶቻቸው ላይ ትቶ የሚያልፈውን ጠባሳ ማስተዋል፤ ሃሳቡ ያላቸው ሰዎች ቆም ብለው እንዲያጤኑ ያደርጋል።

የሴቶችና ወንዶች የኢኮኖሚ እኩልነት እንዴት ይስፈን?

ትኩረት. . .ትኩረት. . .ትኩረት። በበርካታ ሃገራት እራስን ማጥፋት የመኪና አደጋ ከሚያደርሰው በላይ ጥፋት ያደርሳል። ነገር ግን ለመኪና አደጋ የሚሠራውን ያህል ግንዛቤ ስለ እራስ ማጥፋት አይሠራም።

አንዳንድ ቦታዎች እራስ ማጥፋትን በተመለከተ ምክር የሚሰጡና የሚሠሩ ተቋማት መመሥረታቸው እንደበጎ ጅምር እየታየ ነው። ለምሳሌ እንግሊዝ የእራስ ማጥፋት መከላከል ሚኒስቴር አላት። የችግሩ መጠንም በትንሹ መቀነስ አሳይቷል።

ወንድም ሆነ ሴት የሚጠፋው ሕይወት ነው። መዳን የሚችል ሕይወት፤ ምናልባትም በቀላሉ። ሄለንም ወንድሟን ባላጣች፤ ሌሎችም ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እንዲሁ በከንቱ ባልተነጠቁ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ