ለኃይማኖት እኩልነት እና ማሕበራዊ ፍትህ የሚታገሉት የሰይጣን አምላኪዎች

ለኃይማኖት እኩልነት የሚታገሉት የሰይጣን አምላኪዎች Image copyright GEMMA PURKISS

'ስለ ሰይጣናዊ አምልኮ የምታውቁት ሁሉ ስህተት ነው።'

ስለ ሰይጣናዊ ቤተ-መቅደስ [ሳታኒክ ቴምፕል] የሚያትት አንድ ዘጋቢ ፊልም የሚለው ይህንን ነው። ስሙ ይመሳሰል እንጂ በ96 [እ.አ.አ.] ከተመሠረተው የሰይጣን ቤተ-አምልኮ ጋር ልዩነት አለው።

የሰው ነብስ መገበር?. . . የለም። ደም መጠጣት?. . . የለም። ጥቁር የለበሱ ሰዎች. . . ይሄስ ይኖረዋል። ቤተ-እምነቱ የተመሠረተው 2013 [እ.አ.አ.] ላይ ነው።

ሃሳባችን ቅንነትና እና ሩህሩህነት ለማበረታታት ነው ይላሉ። አልፎም ጨቛኝ አስተዳደርን ለመቃወም፣ ፍትሕን ለማስፈን እና ግለሰባዊ ፈቃድን ለማጠንከር እንደተቋቋመ መሥራቾቹ ይናገራሉ።

'ሰይጣንን ማመስገን?' በሚል ርዕስ በፔኒ ሊን የተሠራው ዘጋቢ ፊልም የቤተ-እምነቱን ሃሳብ ይዳስሳል። አማኞቹ ክርስትና የአሜሪካውያን ግላዊ ሕይወት ውስጥ በእጅጉ ጣልቃ ይገባል ሲሉ ይተቻሉ።

ለአስሩ ትዕዛዛት ኦክላሆማ ከተማ ላይ ሃውልት እንደተሠራ ሁላ ለእነሱም የሰይጣንን አምሳያ ሃውልት በትልቁ የምናቆምበት ሥፍራ ይሰጠን ሲሉ ይከራከራሉ። ትግላችን የኃይማኖት እኩልነት እንዲሰፍን ነው፤ ማሕበራዊ ፍትህ እና ሰብዓዊ መብትን እናከብራለንም ባይ ናቸው።

«ሰዎች ቆም ብለው እውን አሜሪካ የክርስትያን ሃገር ናት ወይ ብለው እንዲያስቡ እንፈልጋለን። ምክንያቱም አይደለችም» ይላል የቤተ-እምነቱ ቃል አቀባይ ሉሲዬን ግሪቭስ።

50 ሺህ ገደማ አባላት እንዳለው የሚነገርለት 'ሳታኒክ ቴምፕል' አማኞች እየዞሩ ሰዎች ደም እንዲለግሱ ሲያበረታቱ፣ ቤት ለሌላቸው ካልሲ ሲሰበስቡ እና የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችን ሲያፀዱ ፊልሙ ላይ ይታያሉ።

Image copyright GEMMA PURKISS

ትያትር ውስጥ 'ሆረር' ፊልሞችን እያዩ በጥቋቁር ልብሶች ሆነው ሰይጣንን የሚዘክሩ ድርጊቶች ቢያከናውኑም አንዳቸውም በሰይጣን እናምናለን አይሉም። 'የምናምነው በሂብሩ ቋንቋ በተገለፀው ሰይጣን እንጂ' ይላሉ፤ ትርጉሙ ደግሞ ባላጋራ።

ፊልሙ አማኞቹ እንዲተከልላቸው የሚሸቱት ባፎሜት [ባሮሜት] ላይ አትኩሮቱን አድርጓል፤ ሁለት ጣቶቹን ወደሰማይ የቀሰረው ባለፍየል ቀንዱ ሰው መሳይ የነሃስ ሃውልት።

ቃል አቀባዩ ግሪቭስ [ለራሱና ለቤተሰቡ ደህንነት ሲል በተለያዩ ስሞች ይጠራል፤ ትክክለኛ ስሙም አይታወቅም] በየሥፍራው እየሄደ ባፎሜቱን ይሰቅላል። ነገር ግን ይህንን ማድረግ ለእርሱ ቀላል እንዳልሆነ ፊልሙ ላይ ሲናገር ይደመጣል።

ሃውልት ለማስመረቅ ወደ ተለያዩ ሥፍራዎች ሲጓዝ ጥይት መከላከያ ያለው ጃኬት እንደሚታለብስ እና ከብዙ ሰዎች 'የእንገልሃለን' ማስፈራሪያ እንደሚደርሰው አይደብቅም።

'ሳታኒክ ቴምፕል' ወይንም ሰይጣናዊ ቤተ-መቅደስ የተሰኘው እንቅስቃሴ በሰፊው ከሚታወቀው የሰይጣን ቤተ-እምነት [ሳታኒክ ቸርች] በላይ ተወዳጅነትን እያተረፈ ይመስላል። በየሄዱበት ሥፍራም የሚሰበኩትን ቆመው የሚሰሙ በርካቶች ናቸው። ጨርቄን ማቄን ሳይሉ የሚከተሏቸውም አልጠፉም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ