በአፋር 3.8 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረ ሙሉ የራስ ቅል መገኘቱ ተገለጸ

የፕሮጀክቱ መሪ ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ Image copyright Cleveland Museum of Natural History
አጭር የምስል መግለጫ የፕሮጀክቱ መሪ ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ

በአፋር ክልል 3.8 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረ ሙሉ የራስ ቅል መገኘቱን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

ቅሪተ አካሉ የተገኘው በአፋር ክልል ሚሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ሚሮ ዶራ በተባለ አካባቢ ነው። በአካባቢው የወራንሶ ሚሌ የቅድመ ታሪክ ጥናት ፕሮጀክት የተባለ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችን ያካተተ ቡድን ለሦስት ዓመታት ጥናት እያደረገ ነበር።

የሠላም ተጓዧ ሉሲ (ድንቅነሽ) ምን ደረሰች?

የሉሲ ታላቅ በደቡብ አፍሪካ ተገኘች

በቅሪተ አካሉ ላይ ለሦስት ዓመታት ጥናት እንደተደረገና ዛሬ 'ኔቸር' በተባለው የሳይንስ መጽሔት ላይ ግኝቱ ለዓለም ሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ገልጿል።

አሜሪካ በሚገኘው የክሊቭላንድ የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ኪውሬተርና የኬዝ ዌስተርን ሪዘርቭ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት የፕሮጀክቱ መሪ ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ እንደተናገሩት፤ ግኝቱ 'አውስትራሎፒቴክስ አናመንሲስ' በሚባለው የቀድሞው የሰው ዝርያ ውስጥ ይመደባል።

ዝርያው ያልታወቁ የፊትና የጭንቅላት ቅርፅን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳየ እንደሆነም ዶ/ር ዩሐንስ ገልጸዋል።

Image copyright Cleveland Museum of Natural History
አጭር የምስል መግለጫ የምርምር ቡድኑ

የቀደመው ዘመናዊ ሰው ከአፍሪካ ውጪ ተገኘ

ዶ/ር ዮሐንስ እንዳሉት፤ 'አውስትራሎፒቴክስ አናመንሲስ' በመባል የሚታወቀው የቀድሞው የሰው ዝርያ እስካሁን ድረስ ይታወቅ የነበረው ከ4.2 ሚሊዮን እስከ 3.9 ሚሊዮን ድረስ ነበር። ኤምአርዲ በመባል የሚታወቀው የራስ ቅል ዝርያ እስከ 3.8 ሚሊዮን ዓመት ድረስ እንደሚያሳይም አክለዋል።

የፕሮጀክቱ መሪ ከዚህ ቀደም ከ3.9 ሚሊዮን ዓመት እስከ 3.6 ሚሊዮን ዓመት ድረስ ምንም አይነት የቅድመ ሰው ዝርያ ቅሪተ አካል እንዳልተገኘና የአሁኑ የመጀመሪያው ግኝት እንደሆነ አስረድተዋል።

እስካሁን በመላ ምት ደረጃ የነበረውን የ'አውስትራሎፒቴከስ አናመንሲስ' እና የሉሲ (ድንቅነሽ) ዝርያ የሆነው 'አውስትራሎፒቴከስ አፋረንሲስ' ግንኙነትን በተመለከተ በቂ ደረጃ የሰጠ ግኝት መሆኑንም ዶ/ር ዩሐንስ ተናግረዋል።

Image copyright Matt Crow
አጭር የምስል መግለጫ የተገኘው የራስ ቅል ቅሪተ አካል ከመሆኑ በፊት ይህንን እንደሚመስል ተመራማሪዎች ገልጸዋል

የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ በአየር ፀባይ ይመራ ነበር

በአፋር ክልል እንዲሁም በሌሎችም የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች እስከ 6 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠሩ የቅድመ ሰው ዝርያ ቅሪተ አካላት ተገኝተዋል። ግኝቶቹ ኢትዮጵያን በሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ቀዳሚ ቦታ እንደሰጧት ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

እስካሁን ድረስ ከሚታወቁት ከሀያ የማያንሱ የቅድመ ሰው ዝርያዎች መካከል አሥራ ሦስቱ የተገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የቅድመ ሰው ዝርያ ለሰው ዘር አመጣጥ ጥናት አዲስ መረጃ ከመስጠት ባሻገር ኢትዮጵያ የሰው ዘር ምንጭ እንደሆነች ተጨማሪ ማረጋገጫ እንደሆነ ዶ/ር ዮሐንስ ተናግረዋል።