የኢትዮጵያ ሙዚቃ- ከመስከረም እስከ መስከረም

የ2011 ዓ. ም. ኢትዮጵያ ሙዚቃ ቅኝት

ይህ ዓመት ቴዲ አፍሮ አድናቂዎቹን በሚሌኒየም አዳራሽ ሰብስቦ የተሳካ ሥራውን ያቀረበበት እንደሆነ ባለሙያዎች መስክረዋል።ሮፍናን በመዲናዋ ሸገርና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞችም ምስጋና የተቸረው ኮንሰርት ያቀረበበት እንደነበርም ተነግሯል።

ለዓመታት የተጠበቁት የአስቴር አወቀ እና የጎሳዬ ተስፋዬ የሙዚቃ ሰንዱቆችም አድማጭ ጆሮ የደረሱት ልንሰናበተው ሽራፊ ዕድሜ በቀረው 2011 ዓ. ም. ነው። የዓመቱን የኢትዮጵያ ሙዚቃ አክራሞት በወፍ በረር ምልከታ ቃኝተነዋል።

ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት ኢትዮጵያ፤ የሙዚቀኞች ቁጥር እጅግ ውስን ነው። በየዓመቱ የሚቀርቡ የሙዚቃ ድግሶችም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ይህ ደግሞ ካለው የሙዚቃ ሀብት አንፃር አነስተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በዚህ ዓመት (2011 ዓ. ም.) የቀረቡት ሥራዎች በአገሪቱ ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል በተወሰኑት ብቻ የተዘጋጁ ናቸው። ይህም ሙያተኞች በተለያዩ ቋንቋዎች ሥራቸውን እንዲያቀርቡ የቤት ሥራ የሚሰጥ ነው።

ድምፅ ፈታዮቹ መረዋዎች

በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ፌስቲቫል፡ ሙዚቃ፣ ኳስ፣ ፍቅርና ቡጢ..

ነሺዳም ሆነ መዝሙር፣ ብሎም ዘፈን በተለያዩ ቋንቋዎች ቢቀርቡ ሰሚ ጆሮ፣ አመስጋኝ ልብ፣ ተዝናኝ መንፈስ አያጡም።

ሥራዎቹ ኖረው 'የጆሮ ያለህ!' ቢሉ እንኳን በአግባቡ ሰንዶ የሚያስቀምጣቸው ባለሙያ እጥረት መኖሩ ቁጥራቸው በልው እንዳይታወቅ አድርጓል።

የ 'ለዛ' የሬዲዮ መሰናዶ አዘጋጅና አቅራቢ የሆነው ብርሃኑ ድጋፌ፤ በአገሪቱ መንፈሳዊ ዜማዎች በአግባቡ ስላልተሰነዱ በዚህ ዓመት የወጡ ሥራዎች እነዚህ ናቸው ብሎ ለመናገር እንደሚያስቸግር ይገልፃል።

"እኛም እነዚህን ሥራዎች ለማግኘት፣ ስለመውጣታቸው እንኳን ለማወቅ ተቸግረናል" በማለት ነሺዳም ሆነ መዝሙር ሲወጣ ለሬዲዮ ጣቢያዎች የሚሰጥ ባለሙያ ገጥሞት እንደማያውቅ ይናገራል።

ምንም እንኳን መረጃ የመሰብሰብ ክፍተት ቢኖርም፤ በ2011 ዓ. ም. ከ17 በላይ የሙዚቃ አልበሞች ለገበያ እንደቀረቡ ብርሀኑ ተናግሯል።

ይህ መረጃ ታዲያ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ታትመው ለአድማጭ ጆሮ የደረሡ የሙዚቃ ሠንዱቆችን ታሳቢ ያደረገ አይደለም።

የነገረን የሙዚቃ ሰንዱቆች በአማርኛ የተቀነቀኑ፣ በትግርኛ የተዘፈኑና በኦሮምኛ የተሞዘቁ ናቸው። እነዚህም ስም ካላቸው ከእነ አስቴር አወቀና ከጎሳዬ ተስፋዬ ጀምሮ እስከ አዳዲስ ጆሮ ፈላጊዎች ያካትታሉ።

በዚህ ዓመት በሙሉ አልበም የአድማጭ ጆሮን ካንኳኩ ድምፃውያን መካከል አስቴር አወቀ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ልዑል ኃይሉ፣ ዮሐና፣ ሳሚ ዳን፣ ጃኪ ጎሲ፣ ዳግ ዳንኤል፣ ቼሊና፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ዳዊት ነጋ፣ ኃይለየሱስ ፈይሳ፣ ጃሉድ፣ በኃይሉ ታፈሰ (ዚጊ ዛጋ)፣ ዳዊት ሰንበታ፣ ዘሩባቤል ሞላ እና አቡሽ ዘለቀ ይገኙበታል።

አጭር የምስል መግለጫ ዘንድሮ ገበያ ላይ ከዋሉ የሙዚቃ አልበሞች ሁለቱ

እንደው በዚህ ዓመት ከወጡት የሙዚቃ ሥራዎች የትኛው የአድማጭ ቀልብ ገዛ? የቱስ ጥሩ ገበያ አገኘ? ብለን ብርሀኑን ስንጠይቀው፤ መለኪያችን ምንድን ነው? በማለት ጥያቄያችንን በጥያቄ መልሷል። 'የእከሌ ሥራ በዚህ ሳምንት አንደኛ ነው፤ የእከሌ ደግሞ ይከተላል' ብሎ የሚመድብ ተቋም በሌለበት፤ ተወዳጅነትን ለመመዘን እንደሚከብድ ይናገራል።

"ተደማጭነት በተለያዩ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመጫወት ነው ብለን የምንወስድ ከሆነ፤ ዘሩባቤል ሞላና አስቴር አወቀ አየሩን ተቆጣጥረውት ይታያሉ" ሲል ይገልጻል።

የትኛው የሙዚቃ ሰንዱቅ በሚገባ ተደመጠ? ብሎ ለመተንተን ጥናት ያስፈልጋል የሚለው ብርሃኑ፤ ዘንድሮ እንደ ከዚህ በፊቱ የሙዚቃ አድማጩ በአንድ አልበም ላይ ብቻ አለማተኮሩን ያስረዳል።

እንደ አስቴር አወቀ ያሉ አንጋፋ ድምፃዊያንን ሥራዎች በርካቶች ተስማምተውበት የሚያደምጡ ሲሆን፤ የወጣቱን ቀልብ የሚገዙ፣ በተለያየ ዘውግ የተዘጋጁ የቸሊናን፣ የዘሩባቤልን እና የሳሚ ዳንን የመሰሉ አልበሞችም ወጥተዋል።

የ 'አውታር' መምጣት

Image copyright Awetar MultiMedia
አጭር የምስል መግለጫ የአውታር መልቲ ሚዲያ አርማ

በብርሃኑ አስተያየት፤ በዚህ ዓመት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ የተጨመረው አዲስ ነገር በኢንተርኔት ሙዚቃ መገበያየት የሚያስችለው አውታር መተግበሪያ ሥራ መጀመሩ ነው።

ዓለማችን የዲጂታል ዘመን ላይ በመሆኗ፤ ሙዚቃ ሻጭም ሆነ አከፋፋይ ሳያስፈልግ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ አልበሞችን ለአድማጮች ማድረስ ይቻላል። የኢትዮጵያ ሙዚቃም በአውታር በኩል አንገቱን ወደዚህ የዲጂታል ዓለም ማስገባቱን ይመሰክራል።

አውታር ከአሳታሚ፣ ከአከፋፋይና ከሻጮች ጋር ያለውን ውጣ ውረድ የሚያቀል፣ የሽያጭ ሥርዓቱን በግልፅ የሚያሳይ መተግበሪያ ከመሆኑም በላይ በባለቤትነት የተያዘው በሙዚቀኞች በመሆኑ፤ ለሙዚቀኛው የደራ ገበያ እንደሚፈጥርም ያስረዳል።

አውታር - አዲስ የሙዚቃ መሸጫ አማራጭ

ባህልን በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ የቀመመው ሮፍናን

"አውታር በአገር ውስጥ ሆነው የኢንተርኔት አቅርቦት ላላቸው ጥሩ የመገበያያ አማራጭ ነው" የሚለው ብርሃኑ፤ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ትልቅ ችግር ለነበረው የኮፒራይት መብት ጥሰትና የባለቤትነት ጥያቄ መፍትሔ ይሰጣል ይላል።

አውታር የቀደምት ሥራዎችም ሆነ የአዳዲስ ሥራዎች መረጃ በሚገባ ተካቶበት፣ ሙያተኛውም ገቢ የሚያገኝበት እንደሆነ ያብራራል።

'ለዛ' የተሰኘውን የሙዚቃ ሽልማት ከዘጠኝ ዓመት በፊት የጀመረው ብርሀኑ፤ ያኔ ሽልማቱ ሲጀመር የሙዚቃ ኢንደስትሪው የተቀዛቀዘ እንደነበር ያስታውሳል። ካለው የኮፒራይት መብት ጥሰትና የገቢ ማነስ አንፃር እንዲህ ዓይነት የማበረታቻ ሽልማቶች ቢበራከቱ፤ ሙያተኛው ይነቃቃል በማለት ሽልማቱ እንደተጀመረ ይናገራል።

በዚህ ዓመት የወጡትን ሥራዎች አወዳድረው የሚሸልሙት የሚቀጥለው ዓመት በጥቅምት ወር በስድስተኛው ቀን ሲሆን፤ ሽልማቱ ከሐምሌ 2010 ዓ. ም. እስከ ግንቦት 30፣ 2011 ዓ. ም. ድረስ የወጡትን ያካትታል።

የዩቲዩብ ዓለም- ከሆፕ ኢንተርቴይመንትና ከምነው ሸዋ

ዩቲዩብ ላይ የሚጫኑ ሙዚቃዎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ሙዚቃ አድናቂዎችን በመድረስ ረገድ ፈጣን መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አንድ ሙዚቃ በዩቲዩብ ሲጫን፤ ዩቲዩብ ለጫነው አካል ክፍያ ይፈፅማል። ይህን የሚያደርገው የዩቲዩብ ቻናል በእነዚህ ገጾች ላይ ማስታወቂያ ለመልቀቅ ስለሚፈልግ ሲሆን፤ ለዚህም በማለት የሥራው አጋር ያደርጋቸዋል።

ዩቲዩብ እነዚህን ቻናሎች አጋር ሲያደርግ ያላቸውን ተከታይ (ሰብስክራይበር) እንደሚመለከት በሥራው ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ የሙዚቃ አፍቃርያን ወደ ቻናሎቹ መጥተው ሙዚቃ ባደመጡና ባዩ ቁጥር ዩቲዮብ ማስታወቂያ የሚለቅ ሲሆን፤ ለድርጅቶቹ ደግሞ በስምምነታቸው መሰረት ክፍያ ይፈፅማል።

በኢትዮጵያ ስማቸው ገኖ ከሚሰማና የተለያዩ አዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎች በየጊዜው ከሚጫንባቸው ቻናሎች መካከል ሆፕ ኢንተርቴይመንት፣ አድማስ እና ምነው ሸዋ ይገኙበታል።

Image copyright Minew Shewa Tube
አጭር የምስል መግለጫ የምነው ሸዋ ኢንተርቴይመንት አርማ

ብርሃኑ እንደሚለው፤ በዩቲዩብ ከተለቀቁና በርካታ አድማጮች ካገኙ ነጠላ ዜማዎች መካከል የትግርኛ ሙዚቃዎችን የሚያክል የለም።

የሆፕ ኢንተርቴይመንት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዮሴፍ ኃይሉ በበኩላቸው በዩቲዩብ ቻናላቸው በዚህ ዓመት ከተጫኑ የሙዚቃ ቪዲዮዎች መካከል ከፍተኛ ተመልካች ያገኘው ጆሲ (ዮሴፍ ገብሬ) እና ኤርትራዊቷ ድምጻዊት ሚለን ኃይሉ በጋራ ያቀነቀኑት ሙዚቃ መሆኑን ይናገራሉ።

ይህ የሙዚቃ ቪዲዮ ከ7 ሚሊየን በላይ ተመልካች እንዳለው ያስታወሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ የጌትሽ ማሞ 'ተቀበል'፣ የሰላማዊት ዮሐንስ 'ሰናይ' እና የወንዲ ማክ 'አባ ዳማ' የተሰኙት ሥራዎች በቅድመ ተከተል መቀመጣቸውን ይጠቅሳሉ።

ሆፕ ኢንተርቴይመንት በዚህ ዓመት ብቻ ከ600 በላይ የሙዚቃ ቪዲዮዎችን በቻናሉ ላይ መጫኑን የተናገሩት አቶ ዮሴፍ፤ ሥራዎቹ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎ፣ የታዋቂና ጀማሪም ድምፃውያን መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቻናላቸው ላይ በእይታ ብዛት ቀዳሚ የሆነው የእነ ጆሲ ሙዚቃ በአንድ ቀን ስድስት መቶ ሺህ ተመልካች ያገኘ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

"ከፍተኛ እይታ ያላቸው በየትኛውም ወቅት ከፍተኛ ተከፋይ ናቸው" የሚሉት አቶ ዮሴፍ፤ ሙዚቃዎ በእነርሱ ስም ዩቲዩብ ቻናላቸው ላይ ከተጫኑ ባለ ሙሉ መብት ስለሆኑ የመብት ጉዳዮችንም ለማስከበር ድርጅታቸው ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ዘሩባቤል ሞላና በአነቃቂ መንፈስ የታሸው 'እንፋሎት' አልበሙ

''አዝማሪዎቻችን የሙዚቃ ሳይንቲስቶች ናቸው"

የምነው ሸዋ ኢንተርቴይመንት ኮንቴንት ማናጀር የሆኑት አቶ ነብዩ ይርጋ፤ በቀን ሁለት ሙዚቃ በቻናላቸው ላይ እንደሚጭኑ ይናገራሉ። በቻናላቸው በዚህ ዓመት በብዛት የታየው የድምጻዊት ራሄል ጌቱ 'ጥሎብኝ' የተሰኘው ሙዚቃ መሆኑን በመጥቀስ እስከ 9 ሚሊየን ድረስ እንደታየ ይናገራሉ።

ከራሔል ጌቱ ሥራ በተጨማሪ፤ የአሕመድ ተሾመ (2.9 ሚሊየን)፣ የጃምቦ ጆቴ (2.4 ሚሊየን)፣ የአብነት አጎናፍር (1.8 ሚሊየን)፣ የሚካኤል መላኩ (1.8 ሚሊየን)፣ የቤቲ ጂ (1.5 ሚሊየን) ተመልካች ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህ ዓመት በምነው ሸዋ ኢንተርቴይመንት ከ628 ሙዚቃዎች በላይ መጫናቸውን የተናገሩት አቶ ነብዩ፤ ለክፍያ ሦስት ዓይነት መስፈርት እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

እነዚህም የሙዚቃ ሥራውን ሙሉ በሙሉ መግዛት፣ ቅድመ ክፍያ ከፍሎ መግዛት ወይንም ዩቲዩብ ቻናሉ ላይ ከተጫነ በኋላ የሚገኘውን ክፍያ ሀምሳ ሀምሳ መካፈል መሆናቸውን ይናገራሉ።

ይህ ዓይነቱን የክፍያ ሥርዓትን ሆፕ ኢንተርቴይመንትም የሚጠቀም ሲሆን፤ ቅድመ ክፍያ የተከፈላቸው ሥራዎች፤ የቅድመ ክፍያ ገንዘቡ ከዩቲዩብ ከሚገኘው ክፍያ ከተካካሰ በኋላ ቀሪው ከዩቲዩብ ገቢው ሀምሳ ሀምሳ የሚካፈል መሆኑን አቶ ነብዩ ጨምረው አስረድተዋል።

Image copyright Hope Music Ethiopia
አጭር የምስል መግለጫ የሆፕ ኢንተርቴይመንት የዩቲዩብ ገጽ

ከምነው ሸዋ ጋር ውለታ የገቡ ድምፃውያን ውለታቸው ለሁለት ዓመት እንደሚቆይ የሚናገሩት አቶ ነብዩ፤ ሙሉ በሙሉ ግዢ ካልፈፀሙ የቅድመ ክፍያ ወይንም በታየ ቁጥር እንዲከፈል ለተስማሙ ድምፃውያን በየስድስት ወሩ ከዩቲዩብ ያገኙትን ክፍያ እንደሚያካፍሉ አክለዋል።

የዚህ ዓመት የሙዚቃ ድግሶች ምን መልክ ነበራቸው?

"አንድ ሙዚቀኛ አልበሙን ለገበያ ካቀረበ በኋላ ተስፋ ያደርግ የነበረው" ይላል የለዛ መሰናዶ አዘጋጁ ብርሃኑ፤ "ተስፋ ያደርግ የነበረው የሰንዱቁ ሽያጭ ገቢን አይደለም።"

የአልበም ሽያጭ በቂ አይደለም የሚለው ብርሃኑ፤ የሙዚቃ ድግሶች ከአድማጭ ጋር ለመገናኘትም ሆነ ገቢ ለማግኘት ሁነኛ መላ ተደርገው ይወሰዳሉ ይላል።

ነገር ግን ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ስላልነበር ተዘዋውሮ ኮንሰርቶች ለማቅረብ አዳጋች ሆኗል ይላል። ይህንን ዓመት ጨምሮ በአዲስ አበባም በጣት የሚቆጠሩ ኮንሰርቶች ብቻ መዘጋጀታቸውን ይናገራል።

በዚህ ዓመት ከገጠመው ፈተና አንዱ የቢራ አምራቾች የሙዚቃ አልበሞችን ስፖንሰር ለማድረግ አለመቻላቸው መሆኑን የሚያስታውሰው ብርሃኑ፤ የሙዚቃ ባለሙያው ሥራዎቹ በአድማጮችና በአድናቂዎች ቢሰማለትም ጥሩ ገቢ ስለማያገኝበት የሙዚቃ ድግሶችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማዘጋጀት ገቢውን ለማካካስ ያስብ ነበር ይላል።

"የሙዚቃ ድግሶች ላይ በጣም በጣም መቀዛቀዝ አለ" ሲል ሁኔታውን የሚገልፀው ብርሃኑ፤ በዚህ ዓመት ክፍለ ሀገር የተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ ሥራዎቹን ያቀረበ ሙዚቀኛ ሮፍናን ብቻ መሆኑን ይናገራል።

ሮፍናን ባህርዳር፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ አዳማና አዲስ አበባ ኮንሰርት ማቅረቡን በመግለፅም፤ አዲስ አበባ ውስጥ ከቴዲ አፍሮና የጎሳዬ ተስፋዬ ኮንሰርት እንዲሁም በዓላትን በማስታከክ ከሚቀርቡ አውደ ርዕዮች ውጪ ሌሎች ትልልቅ የሙዚቃ ድግሶች እንዳልነበሩ ያስረዳል።

የኤ ፕላስ ኤቨንትና ፕሮሞሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ጌታቸው፤ የሙዚቃ ድግሶችን በማዘጋጀት ከ9 ዓመት በላይ ሠርተዋል። ከ15 በላይ ትልልቅ የሙዚቃ ድግሶች ላይ ተሳትፈዋል።

በዚህ ዓመት መግቢያ ላይ የተካሄደው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ላይ ከ20ሺህ በላይ ትኬት መሸጡን የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ፤ የሮፍናንና የጎሳዬ ኮንሰርቶች የተካሄዱት ጊዮን በመሆኑ እስከ አስር ሺህ ሰዎች ታድመዋል ሲሉ ቦታው የሚይዘውን የሰው ብዛት ከግምት በማስገባት ያስረዳሉ።

የኤርትራ ዘፈኖች በኢትዮጵያዊ አቀናባሪ

ተፈራ ነጋሽ፡ "በነገራችን ላይ ሙዚቃ አልተውኩም"

የጆርካ ኤቨንትስ ኤንድ ፕሮሞሽንስ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አጋ አባተ፤ ከ2007 ጀምሮ በርካታ ኮንሰርቶችን በመሥራት ስማቸውን የተከሉ ናቸው።

ፌስቲቫሎችን፣ የስፖርታዊ ዝግጅቶችንና የአልበም ምርቃቶችን ጨምሮ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ20 በላይ ኮንሰርቶችን ያዘጋጀው ጆርካ ኤቨንትስ ኢትዮጵያዊ ኮንሰርት፣ አዲስ ኮንሰርት ፣ ሄሎ መቀሌና ጊዜ ኮንሰርትንም አዘጋጅቷል።

አቶ አጋ የድምፃውያንና ሌሎች የሙዚቃ ባለሙያዎች ክፍያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መምጣቱን በማስረዳት፤ በዚህ ዓመት ከሥራው ላለመውጣት ብቻ ከሙዚቃ ድግሶች ይልቅ ባዛር ላይ ማተኮራቸውን ይናገራሉ። ባዛሮቹ ከ15 እስከ 20 ቀን የሚቆዩ መሆናቸውን በመጥቀስም እስካሁን ድረስ ሦስት ባዛሮች ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

"ለአንድ ድምፃዊ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሚከፈልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው" የሚሉት የጆርካ ኤቨንትስ ሥራ አስኪያጅ ለመድረክ እስከ 300 ሺህ ብር እንደሚከፈል፣ ለማስታወቂያም ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ ይናገራሉ።

የኮንሰርት መግቢያ ዋጋ ዛሬም ድረስ ባለበት እንዳለ በማስረዳት፤ ከአምስት ዓመት በፊት አንድ ዶላር 18 ብር እያለ በ300 ብር ይገባ የነበረ የሙዚቃ ድግስ ዛሬም በዛው ዋጋ እንደሚታይ በመጥቀስ የኮንሰርት ሥራ ፈተናን ያሳያሉ።

"በርካታ ሥራዎች ሠርተናል ነገር ግን ከትርፉ ኪሳራው ያመዝናል" የሚሉት የጆርካ ኤቨንትስ ሥራ አስኪያጅ አቶ አጋ፤ በዚያ ምክንያት ከኮንሰርቶች ይልቅ ወደ ባዛሮችና ፌስቲቫሎች ላይ ማተኮራቸውን ተናግረዋል።

አቶ አጋ አክለውም በዚህ ዓመት የሙዚቃ ሥራዎች ዋነኛ አጋር የነበሩት የቢራ አምራቾች የሙዚቃ ድግሶችን መደገፍ ላይ በመቀዛቀዛቸው ሥራው አብሮ መፋዘዙን ይጠቅሳሉ።

ከቢራ አምራቾች ውጪ የድርጅቱን ስምና ምርት ለማስተዋወቅ ደፍሮ ወደ ኮንሰርት አዘጋጆች የሚመጣ እንደሌለ የሚናገሩት አቶ አጋ፤ እነርሱም ሲሄዱ ተቀባይነት እንደማያገኙ ያስረዳሉ።

በዚህ ዓመት ከአገሪቱ ጠቅላላ ሁኔታ አንፃር የተቀዛቀዘ ቢሆንም የተወሰኑ የሙዚቃ ድግሶች መደረጋቸውን ይናገራሉ።

የኤ ፕላሱ አቶ ኤርሚያስ፤ የቢራ ፋብሪካዎች ማስታወቂያቸውን በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የሚያቀርቡበት ሰዓት ላይ ገደብ ቢደረግም የሙዚቃ ድግሶችን ከመደገፍ ወደኋላ ያሉ አይመስለኝም ይላሉ። ከዚያ ይልቅ በተደጋጋሚ የነበሩ መሰረዞች በዚህ ዓመት የሙዚቃ ድግሶች ለመቀዛቀዛቸው አንዱ ሰበብ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ። የአዳዲስ አልበሞች አለመውጣት ለመቀዛቀዙ ሌላ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።

አንድ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ከሚያስፈልገው የሥራ ፈቃድ ባሻገር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጸጥታና ደህንነት ሲባል መገኘት ያለበትን ፈቃድ ለማስጨረስ ያለው ውጣ ውረድ ራሱን የቻለ ራስ ምታት እንደሆነ የሚናገሩት የጆርካ ኤቨንትስ ሥራ አስኪያጅ፤ በዚህም የተነሳ በርካታ ሥራዎች ይሰረዛሉ ይላሉ።

የከተማ አስተዳደሩ ለኮንሰርቶች ፈቃድ የሚሰጠው የሙዚቃ ድግሶች መተዋወቅ ከጀመሩ በኋላ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ ቀኑ እየተቃረበ ሲመጣ የሚኖረው የፀጥታና የደህንነት ጉዳይ ተገምግሞ ስጋት ይኖራል ከተባለ እንደማይፈቀድ ያብራራሉ።

ይህ ደግሞ ለተለያዩ ዝግጅቶች ቀድመው የወጡ ወጪዎች ላይ ኪሳራ እንደሚያስከትል አፅንኦት ይሰጡታል።

ኮንሰርቶች ሲሰረዙ ለማስታወቂያ የወጡ ከፍተኛ ወጪዎች መና እንደሚቀሩ የሚያስረዱት አቶ ኤርሚያስ፤ ከተሰረዘ በኋላ ራሱ መሰረዙን ለታዳሚያን ለመንገር ወጪ እንደሚወጣም ያብራራሉ።

የኮንሰርት አዘጋጆች በተደጋጋሚ ስለተሰረዘባቸው ዘንድሮ እጃቸውን ሰብሰብ እንዳደረጉ በማስረዳት፤ የቢራ አምራቾችም እንደ ከዚህ ቀደሙ የሚሰጡትን ገንዘብ እንደቀነሱ ይናገራሉ። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ደጋፊ አካላት በመገናኛ ብዙኀን ስማቸው አለመጠራቱና ቢልቦርዶች እንደ ከዚህ ቀደሙ አለመሰቀላቸው ነው። የሙዚቃ እቃዎች ኪራይ፣ የቦታ ኪራይ እና የባለሙያዎች ዋጋ ውድ መሆን ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር ሲደራረብ ኮንሰርቶች በመግቢያ ትኬት ሽያጭ ብቻ አትራፊ እንዳልሆኑ ያስረዳሉ።

የኤ ፕላሱ አቶ ኤርሚያስ 2012 ዓ. ም. ተስፋ ይዞ ይመጣል ይላሉ። ሮፍናን ሌሎች ድምፃውያን ያልደፈሩትን የክፍለ አገር የሙዚቃ ድግስ ጉዞ ውጤታማ ሆኖ ማጠናቀቁ እንዲሁም አዳዲስ አልበሞች መውጣታቸው ዋና ዋና ከተሞች ላይ የሙዚቃ ድግስ ለማዘጋጀት ተስፋ እንደሚሰጡ ይጠቅሳሉ።

በአዲስ አበባም ቢሆን የተለያዩ ድምፃውያን አድናቂዎች በጉጉት የሚጠብቋቸው ኮንሰርቶች ሊዘጋጁ እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ይናገራሉ።

በዚህ ዓመት ከፍተኛ የአማራ ክልል ባለስልጣናት እና ወታደራዊ ሹማምንት ላይ በተፈፀመ ግድያ ምክንያት ታንዛኒያዊው ዳይመንድ ይገኝበታል ተብሎ ቀጠሮ የተያዘለት የሙዚቃ ድግስ ወደሌላ ጊዜ ተዛውሯል ሲሉ ሳይካሄድ ስለቀረው ኮንሰርት አቶ አጋም ሆኑ አቶ ኤርሚያስ ያስረዳሉ።

ተያያዥ ርዕሶች