ቅዱስ ሲኖዶስ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ ጥያቄን አወግዛለሁ አለ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ Image copyright Sergei Fadeichev
አጭር የምስል መግለጫ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ቅዱስ ሲኖዶስ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ ጥያቄን እንደሚያወግዝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ።

ፓትርያርኩ በመግለጫቸው "ጥያቄውን ያቀረበው ቡድን ከአድራጎቱ እንዲቆጠብ ሲኖዶሱ በጥብቅ ያሳስባል" ብለዋል።

ቤተክርስቲያኒቱ ባህልን፣ ቀለምን፣ ቋንቋ እና ብሔርን መሠረት ሳታደርግ፤ ያለ ምንም መድልዎ አገልግሎት ትሰጣለች ያሉት ፓትርያርኩ፤ ሃይማኖታዊ የትምህርት መጻሕፍት በኦሮምኛ ቋንቋ መዘጋጀታቸውን አጣቅሰዋል። የተነሳውን ጥያቄም "አገርና ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል" ነው ሲሉ አውግዘውታል።

ከኦሮሞ ሕዝብ የተገኙ ሊቃነ ጳጳሳት አገልግሎት የሚሰጡባቸው በአገረ ስብከት ሥር ያሉ በርካታ ጽህፈት ቤቶች እንዳሉም አቡነ ማትያስ ተናግረዋል።

አክለውም ጥያቄውን "የተከበረውና የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለውለታ የሆነው የኦሮሞ ሕዝብን ቤተ ክርስቲያን እንዳገለለችውና አቅዳ እንደበደለችው ለማስመሰል ያቀደ" ሲሉ ገልጸውታል።

ቅዱስ ሲኖዶስ የኦሮሚያ ቤተክህነት ፅህፈት ቤት ጥያቄን በሰላሳ ቀናት እንዲመልስ ተጠየቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ የኦሮሚያ ቤተክህነት አደራጅ ኮሚቴ የጠራውን መግለጫ መንግሥት እንዲያስቆም ጠየቀ

የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት ለማዋቀር ጥያቄ ያቀረቡት ግለሰቦች፤ ለቅዱስ ሲኖዶስ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ ተጠይቀው ውይይት እንዳደረጉ ፓትርያርኩ ገልጸው፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉዳዩ ተጣርቶ ውሳኔ እንሰሚሰጥ ቢያሳውቅም፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅናና ፈቃድ ውጭ ግለሰቦቹ መግለጫ መስጠታቸው አግባብ አይደለም ብለዋል።

ግለሰቦቹም ይህንን አምነው "ይቅርታ ለመጠየቅ ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተን እንመለስ" ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለዛሬ ጳጉሜን 2፣ 2011 ዓ.ም. ጠዋት ቢቀጠሩም የኮሚቴው ሰብሳቢ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን እንዳልተገኙና ሁለት የኮሚቴው አባላት ዘግይተው እንደደረሱ ፓትርያርኩ ተናግረዋል።

አቡነ ማትያስ አክለውም፤ ግለሰቦቹ ሕጋዊ ሥልጣን ሳይኖራቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አርማ፣ ማህተምና መጠሪያ ስያሜ በመጠቀማቸው አስፈላጊው እርምጃ መወሰድ አለበት ብለዋል።

ፓትርያርኩ "የጽህፈት ቤታችን የሕግ አገልግሎት መምሪያ፤ በሕገ ወጥ ግለሰቦች ላይ ክስ በመመስረት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ያስከብር ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶሱ በጥብቅ አዟል" ብለዋል።

ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በትዊተር ገፁ ላይ አስታውቋል።

የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት በክልል ደረጃ እንዲዋቀር ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ቅዱስ ሲኖዶሱ በ30 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቃቸው፤ ይህ ተግባራዊ ካልሆነ ግን አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስዱ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ በላይ መኮንን ማስታወቃቸውም የሚታወስ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ