2011፡ በፖለቲካና ምጣኔ ኃብት

ጉልት Image copyright Anadolu Agency

የ2011 ዓ.ምን ስንብት አስታክከን የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ መልክዐ ምድር የኋሊት ስንገመግም ዓመቱ የስክነትም የውዥንብርም ነበር ማለት እንችላለን።

የቀዳሚውን 2010 ዓ.ም ገሚስ ስልጣን ላይ ያሳለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እና መንግሥታቸው ወራቱን ትንፋሽ ለመሰብሰብ እንኳን ፋታ ይሰጥ በማይመስል እንቅስቃሴ፤ በርካታ ስር ነቀል እርምጃዎችን አከታትለው ሲከውኑ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ተችሯቸው ነበር።

ሞቅታው ሊረግብ ግን ጊዜ አልፈጀበትም።

የንግድ ሽርክና ከኤርትራ ጋር?

ወሳኝ ምጣኔ ሃብታዊ እርምጃዎች በ100 ቀናት

"ለዋጋ ግሽበት የውጪ ምንዛሪ ማሻሻያው ምክንያት ነው"

ተከትሎ የመጣው እና አሁን ሊጠናቀቅ ጫፍ ላይ የደረሰው ዓመት ግን ገና በማለዳው ፈንጠዝያው ሰከን ብሎ መረር ያለ እውነታ የተተካበት ሆኗል።

በአዲስ አበባ ዳርቻዎች እና በአጎራባች ቡራዩ አካባቢዎች በዓመቱ መባቻ የተከሰቱት የብሔር መልክ ያላቸው ግጭቶች እና ጥቃቶች፣ የዜጎች መፈናቀል፤ ወራት እየተተካኩ ሲሄዱ በበርካታ የአገሪቱ ስፍራዎች ተደጋግመው የዓመቱ አይነተኛ ምልክት ሆነዋል።

በርካቶች ተገድለዋል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ታዳጊዎች ከትምህርታቸው ተነጥለዋል።

መንግሥት ለነዚህ ችግሮች የሰጠው ምላሽ የቁጥር ሙግት ውስጥ ከመግባት አንስቶ፤ በተለይ በሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች እርቅን እስከማከናዎን በኋላም ተፈናቃዮችን ወደ መነሻ ቀየዎቻቸው እስከመመለስ የሚደርስ ነው።

በክረምት መባቻ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ከሚል መንግሥታቸው ሁሉንም ተፈናቃዮች የመመለስ ዕቅድ እንዳላቸው መናገራቸው ይታወሳል።

ከዚህም በዘለለ ለሞት እና መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል የተባሉ አካላትን ለፍርድ ማቅረብ መንግሥት አድርጌዋለሁ የሚለው ሌላኛው እርምጃ ነው።

ፍርድ ቤቶች እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ በዚህም ዓመት የትኩረት ማዕከል ነበሩ።

ጥቁር ገበያውን ማሸግ መፍትሄ ይሆን?

አየር መንገድንና ቴሌን ለሽያጭ ለማቅረብ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው?

ከአንድ ዓመት በፊት በመስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ለመደገፍ በተጠራው ሰልፍ ላይ በተፈፀመና የሁለት ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው ፍንዳታ ጋር በተያያዘ ከተከሰሱ ሰዎች አንስቶ፤ የሃገርን ሐብት በመመዝበርና ያላግባብ በስልጣን በመባለግ ችሎት እስከተገተሩ ሰዎች ድረስ፤ በኋላም በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ በተፈፀሙ የከፍተኛ ባለስልጣናት እና ወታደራዊ መኮንኖች ግድያዎች ጋር በተገናኘ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች የችሎት ሒደቶች አትኩሮትን ይዘው ነበር።

አንዳንድ ክሶችን የተደበቀ ፖለቲካዊ ዓላማ አላቸው ሲሉ ትችት የሚያሰሙ የመኖራቸውን ያህል የችሎት መጓተት እና የቀጠሮዎች መደጋገምን የቅድመ-ዐብይ ጊዜያትን ያስታውሳል ብለው የሚነቅፉም አሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተዳደር ክፉኛ ከፈተኑ ጉዳዮች መካከል የአስተዳደራዊ አሃድ ጥያቄዎች ናቸው።

ገንነው የተስተዋሉት ክልል የመሆን ጥያቄዎች ሲሆን የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ የበርካቶችን ሞትና ጉዳት አስከትሏል።

በወርሃ መጋቢት አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው 'የአዲስ ወግ' መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዋናው ቁምነገር ዋልታ የረገጡ አመለካከቶችን ወደ መካከል ማምጣት እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ያለፈው ዓመት ግን ተቃርኖዎች እምብዛም ሲለዝቡ አልተስተዋሉበትም።

Image copyright EDUARDO SOTERAS

እርሳቸው በሚመሩት እና አገሪቷን እያስተዳደረ ባለው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ውስጥ ያለ ተቃርኖ ገሃድ የወጣበትም ዓመት ነው።

በተለይም በግንባሩ ሁለቱ ቀዳሚ አባል ፓርቲዎች ህወሃት እና አዴፓ መካከል ያለው ግልጽ የሆነ የቃላት ጦርነት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚያነሱት የፓርቲ ውህደት የሚጣጣሙ አይመስሉም።

ፍትጊያው የጎንዮሽ በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ብቻ አልነበረም፤ ኢሕአዴግ ሙሉ በሚያስተዳድረው ፌደራል መንግሥት እና የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በሚያስተዳድሯቸው የክልል መንግስታት ጭምርም እንጅ።

ይህም ፌደራላዊው መንግሥት የአስፈፃሚነት አቅም አንሶታል ለሚሉ ትችቶች ተዳርጓል።

2011 የሰልፍ ዓመትም ጭምር ነበር።

ሐኪሞች፣ መምህራን እንዲሁም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎቻችን አልተመለሱም ያሉ በርካታ ዜጎች አደባባይ ወጥተዋል።

በምጣኔ ኃብት ረገድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ ገዥው ፓርቲ ከዚህ ቀደም እከተለዋለሁ ይለው ከነበረው መንግሥታዊ ተሳትፎን የሚያበረታታ ፖሊሲ ማፈንገጥ መጀመሩ በተንታኞች ይወሳል። የተገባደደው ዓመት ይህን የፖሊሲ ለውጥ የሚያመላክቱ እርምጃዎች ሲወስዱ የተስተዋለበት ሆኖ አልፏል።

በአንድ በኩል መንግሥት ለወትሮው አይነኬ መሆናቸውን ይናገርላቸው ከነበሩ የልማት ድርጅቶች እና ዘርፎች መካከል አንዳንዶቹን ለግል ባለሃብቶች ክፍት እንደሚያደርግ ካሳወቀ በኋላ በተሰናባቹ ዓመት የክንውን ዕቅዱን በተመለከተ በአንፃራዊነት የተሻለ መረጃ ሰጥቷል።

በዚህም መሰረት ለምሳሌ የግል ባለሃብቶች ከግዙፉ ኢትዮቴሌኮም ድርሻ መገብየት እንደሚቻላቸው ይህም ተቋም በከፊልም ቢሆን ወደግል በመዛወር በቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል። ትርፋማው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለግል ባለሃብቶች ክፍት ይሆናል መባሉ ግን ከተለያዩ ተችዎች ነቀፌታን አስተናግዷል።

በሌላ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የንግድ ክንውን ለማሳለጥ ያግዛሉ የተባሉ የሕግ እና የአሰራር ማዕቀፎችን ለመቅረጽ ብሎም ወደስራ ለመግባት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የተደረጉ ውይይቶችን ለሕዝብ ሲያሳውቅ ቆይቷል።

Image copyright NurPhoto

ይሁንና እነዚህን መሰል ለግሉ ዘርፍ ይሰጥ የነበረውን አትኩሮት የሚጨምሩ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ጨምሮ ዘርፉን የሚጋብዙ የፖሊሲ መስመሮች፣ በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይተገብሩትና ተተኪያቸው ሃይለማርያም ደሳለኝ አስቀጥለውት ነበር ከሚባለው ድሃ ተኮር የምጣኔ ኃብት ፖሊሲ ትሩፋቶች ላይ ውሃ የሚቸልስ ነው ሲሉ የሚተቹት አልታጡም።

የመንግሥት የምጣኔ ኃብት ባለሟሎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የምጣኔ ሃብት ቁመና የነበረውን ጎዳና ይዞ መቀጠል የማይቻል በመሆኑ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል ይላሉ።

2011 ዓ.ም እንደሌሎች የቅርብ ዓመታት ሁሉ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ኢትዮጵያን ሰንጎ የሸሸበትም ነበር።

የዕጥረቱ ዳፋ በተለይ ከውጭ የሚመጡ ጥሬ ዕቃዎችን ለሚጠቀሙ አምራቾች እንዲሁም ቁሳቁሶችን ከውጭ በማስመጣት ላይ ለተሰማሩ ነጋዴዎችና የንግድ ድርጅቶች ፈተና አብዝቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በውጭ አገራት የሚገኙና ብዛታቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያ የዘር ግንድ ያላቸው የውጭ አገር ዜጎችን የምጣኔ ኃብቱን በማነቃቃት ረገድ ሚና እንዲጫወቱ ፍላጎት እንዳላቸው መገንዘብ አያዳግትም።

ሆኖም ያሳለፍነው ዓመት በዚህ ረገድ ምን ያህል ስኬትን አስጨብጧቸዋል የሚለው ብዙም ግልፅ አይደለም።

ለምሳሌ በወርሃ ግንቦት የግብርና ዘርፍን ከማዘመን ጋር በተያያዘ በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ በውጭ አገራት ካሉ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ የዘር ግንድ ካላቸው የሌሎች አገራት ዜጎች በ'ኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ' በኩል ለመሰብሰብ የታሰበውን ያህል ገንዘብ ማግኘት እንዳልተቻለ አምነዋል።

ተሰናባቹ ዓመት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ምርቃት ቢያስተናግድም፣ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ መንግሥታዊ ፕሮጀክቶች እምብዛም ከነበሩበት ፈቀቅ ሲሉ አልታዩም።

ከዚያ ይልቅ በተለይ መዲናዋን አዲስ አበባን ማዕከል ያደረጉ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይፋ ተደርገዋል።