የአረብ አገራት እስራኤልን ኮነኑ

ቤንጃሚን ኔታንያሁ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቤንጃሚን ኔታንያሁ

የአረብ አገራት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከዌስት ባንክ ይዞታ ከፊሉን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ማቀዳቸውን ተችተዋል።

የሚቀጥለው ሳምንት የሚካሄደውን የእስራኤል ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ፤ እቅዱ እንደሚተገበር ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል። የጆርዳን፣ የቱርክ እና የሳዑዲ አመራሮች እቅዱን በጥብቅ ተችተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በእቅዳቸው የጠቀሷቸው ጆርዳን ቫሊ እና ዴድ ሲ የዌስት ባንክ አንድ ሦስተኛ ይዞታ ሲሆኑ፤ የአረብ ሊግ እቅዱን "አደገኛ" እና "ኃይል የተሞላው" ሲል ኮንኖታል። ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚጻረር እቅድ ነውም ብለዋል።

አሜሪካ ፍልስጤምን አስጠነቀቀች

እስራኤል በፍልስጤም ይዞታ ሥር የሚገኙ ቤቶችን እያፈረሰች ነው

የፍልስጤሙ ዲፕሎማት ሳዒብ ኤራካት "ይህ እርምጃ ወንጀል ነው፤ የሰላም ጭላንጭልን ያዳፍናል" ብለዋል።

እስራኤል ከጎርጎሮሳውያኑ 1967 ጀምሮ ዌስት ባንክን ይዞታዋ ብታደርግም በቁጥጥር ሥር ግን አልዋለም ነበር። ፍልስጤም ነፃ አገርነቷን ስታውጅ ይህ ቦታ ግዛቷ እንደሚሆን ትገልጻለች።

እሰራኤል ደህንነቷን ለመጠበቅ ስትል በጆርዳን ያላትን ይዞታ እንደማትለቅ ጠቅላይ ሚንስትሩ መናገራቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እቅዳቸውን ይፋ ያደረጉት ከምረጡኝ ቅስቀሳቸው ጋር በተያያዘ ነው። የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ካደረጉ፤ በዌስት ባንክ ያሉ የአይሁዳውያን ሰፈራዎችን እንደሚጠቀልሉም ገልጸዋል።

ኔታንያሁ የሚመሩት ፓርቲ ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ከፍተኛ ፉክክር እያደረገ ይገኛል። የቢቢሲ የመካከለኛው ምስራቅ ተንታኝ ቶም ቤትማን እንደሚለው፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ እቅድ የቀኝ ዘመሞችን ድጋፍ ለማግኘት ያለመ ነው።

"ሰዓረ ሙዚቃ በጣም ያዝናናው ነበር" ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ

''አባቴ የቼልሲ ደጋፊ ነበር'' የሜጄር ጄኔራል ገዛዒ አበራ ልጅ

ከኔታንያሁ ፓርቲ በተቃራኒው ያለው የ 'ብሉ' እና 'ዋይት' ፓርቲዎች ጥምር መሪ ያሪ ላፒድ "እቅዱ ያለመው ድምፅ ለማግኘት እንጂ ግዛት ለማግኘት አይደለም" ብለዋል።

የጆርዳን ጠቅላይ ሚንስትር አይማን ሳፋዲ እቅዱ "አካባቢውን ዳግመኛ ወደ ቀውስ የሚወስድ ነው" ብለዋል።

የቱርክ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሜቩልት ካቩስጎሉ እቅዱን "ዘረኛ" ሲሉ ኮንነውታል።

የሳዑዲ አመራሮችም እቅዱን ተችተው የ 'ኦርጋናይዜሽን ኦፍ ኢስላሚክ ኮኦፕሬሽን' 57 አባል አገራትን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።