መከላከያ የሶሪያ እና የየመን ዜጋ የሆኑ የአይኤስ አባላትን በቁጥጥር ሥር አዋልኩ አለ

የአይኤስ አርማ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የአይኤስ አርማ

የአገር መከላከያ ሠራዊት፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርካታ የጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን-አይኤስ አባላትን በቁጥጥር ሥር አዋልኩ አለ።

የኢታማዦር ሹሙ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ኮለኔል ተስፋዬ አያሌው፤ የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች ጅግጅጋ፣ ድሬ ዳዋ፣ ሞያሌ እና ዶሎ ከተማዎችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ውስጥ መያዛቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተለያየ ሥፍራ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ የተጠየቁት ኮለኔሉ፤ "በቁጥር በጣም ብዙ ናቸው። መረጃው ገና ተጣርቶ አልደረሰንም" ብለዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሶማሊያ፣ የሶሪያ እና የየመን ዜጎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል። "አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች አማርኛ ቋንቋ ተምረው የተላኩ ናቸው" ብለዋል።

መከላከያ በዛላምበሳ ድንበር እንዲቆይ ስምምነት ተደረሰ

የጀማል ኻሾግጂ አገዳደል በዝርዝር ይፋ ሆነ

"ሰዓረ ሙዚቃ በጣም ያዝናናው ነበር" ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ

ከዚህ ቀደም አይኤስ በአማርኛ ቋንቋ የጽሑፍ መልዕክቶችን በቴሌግራም አማካኝነት ማስተላለፍ እንደሚጀምሩ ማስታወቂያ አሰራጭተው እንደነበረ ይታወሳል።

አይኤስ በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት ጫና እያሳደረ ነው? መከላከያስ ይህን ለመከላከል ምን እያደረገ ነው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮለኔል ተስፋዬ፤ "የአገራችን የደህንነት ጥበቃ ጠንካራ ስለሆነ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው መግባት ባለመቻላቸው፤ ፕሮፖጋንዳ ብቻ ነው የሚነዙት። ድንበር አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ጥበቃ እያደረግን ነው" ሲሉ መልሰዋል።

አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች ለድንበር ቅርብ በሆኑ ከተሞች አቅራቢያ ከተቀጣጣይ መሣሪያዎች ጋር መያዛቸውን የሚናገሩት ኮለኔል ተስፋዬ፤ ከዚህ ቀደም የአይኤስ ተጠርጣሪ ነው ተብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋለ አካል እንዳልነበረ ይገልጻሉ።

"ከዚህ ቀደም የአይኤስ አባላት የሆኑ ሰዎችን በሶማሊያ በቁጥጥር ሥር አውለናል። እነሱንም ለሶማሊያ መንግሥት ነው አሳልፈን የምንሰጠው" ብለዋል።

"ስልጠና ሲሰጣቸውና ወደ ኢትዮጵያ ሲላኩም ጭምር መረጃው ነበረን" ያሉት ኮለኔል ተስፋዬ፤ የአይኤስ አባላት እንቅስቃሴን በተመለከተ መንግሥት መረጃ እንደነበረው ጠቁመዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በተለያያ ጊዜ እንደሆነ የተናገሩት ኮለኔል ተስፋዬ፤ ሁሉም የተያዙት አይኤስ በአማርኛ ቋንቋ ጽሑፎችን ማሰራጨት ከጀመረ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።

"ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም፤ ሥራ ፍለጋ ከአገር የሚሰደዱ ወጣቶችን መንገድ ላይ በመያዝ 'ሥራ እንሰጣችኋላን' በማለት እያታለሏቸው ስልጠና እየሰጧቸው ነው" የሚሉት ኮለኔል ተስፋዬ፤ "በኢትዮጵያ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል አብዛኛዎቹ የሶሪያ እና የየመን ፓስፖርት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።