“ትርጉም ያለው ሕይወት የምንለው ለሌሎች አገልግሎት ሲኖር ነው” ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
አጭር የምስል መግለጫ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ውስጥ ከተሾሙት ሃያ ሚኒስትሮች መካከል የገቢዎች ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አንዷ ናቸው። ወደ ሚኒስትርነት ቦታ ከመምጣታቸው በፊት በአዳማ ከንቲባነት እንዲሁም የኦዴፓ ማዕከላዊ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

አርሲ ዞን የተወለዱት ወ/ሮ አዳነች የትምህርት ዝግጅታቸው ሲታይ በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተምረው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት የነበሩ ሲሆን እያስተማሩም ዲፕሎማቸውን እንዲሁም ዲግሪያቸውን በሕግ ይዘዋል።

በኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ በአቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም በ1997 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ከተመረጡ በኋላ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል። ለስድስት ዓመታትም ያህል የኦሮሚያ ልማት ማኅበርን መርተዋል። ቢቢሲ አማርኛ ከገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በዓልንና ሌሎች ጉዳዮችንም በተመለከተ ቆይታ አድርጓል።

ከነፍስ የተጠለሉ የዘሪቱ ከበደ ዜማዎች

አብዛኛውን ጊዜ በዓልን እንዴት ነው የሚያሳልፉት?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ በዓል እንደሁኔታው ነው። የበዓል ዝግጅት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይዘጋጃል። ከዛ ውጭ አንዳንድ ጊዜም ሥራ ሊያጋጥም ይችላል። ቤትም ውስጥ ዝግጅት እያለ ሥራ ቦታ አቻችየ ያለፍኩበት ጊዜ አለ። ከዛ ውጭ ከቤተሰብም፣ ከዘመድ ጋር ብዙ ጊዜ አሳልፋለሁ።

ሚኒስትር እንደ መሆንዎ መጠን እርስዎን የሚፈልጉ አስቸኳይ ራዎች ይኖራሉ። የበዓላትና የቤተሰብ ጊዜን የሚሻማበት የለም?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ ይኖራል። በሚኖርበት ሰአት አንደኛ ቤተሰብ ራሱ ሁኔታውን እንዲረዳ የማድረግ ሥራ ቀድሜ ሰርቼያለሁ። ሰው ወደ ኃላፊነት ሲመጣ የቤተሰብ ብቻ አይደለም፤ የሕዝብም ጭምር ስለምትሆኝ፤ እንዲህ አይነት ሁኔታ በሚያጋጥመን ሰአት አብረን የምንገኝባቸው ከሆኑ ቤተሰቤን ይዤ እገኛለሁ። ነገር ግን ደግሞ ድንገተኛ ምክክር አጋጥሞ ከሆነ ደግሞ ሄጄ ተገኝቼ ያንን ጨርሼ ከቤተሰብም ጋር ማምሻችን ቢሆን አብረን እናከብራለን።

ለርስዎ የተለየ በዓል የትኛው ነው?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ አዲስ ዓመትን በተለየ ሁኔታ ነው የምወደው

ለምን ይሆን? ከልጅነትዎ ጋር የተያያዘ ይሆን?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ በርግጥ አዲስ ዓመት ከልጅነት ጋር ይያዛል። አዲስ ዓመት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሴት ልጆች የእንቁጣጣሽ ዘፈን ዘፍነናል፣ አደይ አበባ ወጥተን ለቅመናል። እሱን ደግም ለዘመድ አዝማድ ለጎረቤት እንኳን አደረሳችሁ እያልን አበባየሆይ እየዘፈንን እንሰጣለን።

የሼፎች የበዓል ምግብ ምርጫ፡ ሼፍ ዮሐንስ፣ ጆርዳና እና ዮናስ

ሁልጊዜ አዲስ ዓመት በሚመጣበት ሰአት ሁሉ ነገር አዲስ ነው። ቤተሰብም አዲስ ልብስ ያለብሳል። ሁሉን ነገር አዲስ አድርገን እንድናየው የሚያደርግ አጠቃላይ የማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ስላለ አዲስ ዓመትን በተለየ ሁኔታ እወደዋለሁ።

ብዙ ሰው አዲስ መት ሲመጣ ያቅዳል። እርስዎስ?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡አዎ! ማኅበረሰባችን ውስጥ የሚደረገውን በልጅነቴ የማውቀውን አንድ ጉዳይ ላንሳ። ጳጉሜ ወር ላይ የጳጉሜ ውሃ ሳያልፍ፤ ብለው በየእለቱ ማለዳ ሌሊት እየተነሱ ገላቸውን ይታጠባሉ፣ ገላችንንም እንድንታጠብ ያደርጋሉ።

ለምንድን ነው? ባለፈው ዓመት የነበረ መልካም ያልሆነ፣ ቆሻሻ የሆነ ጥሩ ያልሆነ ነገር አብሮን ወደ አዲሱ አመት አብሮን ሊሻገር አይገባም።

አዲስ ሆነን ነው ማለፍ ያለብን የሚል አስተሳሰብና እምነት አለ። ባለፈው አመት የነበረብን ድክመት አብሮ መሻገር የለበትም። እንዴት አድርገን መፍታት እንዳለብን ከባለፈው አመት ተምረን ለሚቀጥለው አመት በተሻለ ሁኔታ ለመስራት ድካሞቻችንን ለማረም፤ ጠንካራ ጎናችንን አጠናክረን ለመቀጠል የምናቅድበት ጊዜ ስለሆነ ሁልጊዜም አዲስ አመት በሚመጣበት ሰአት አዲስ መንፈስ፣ መነቃቃት ያድራል። ከዚህ የተነሳ እኔም አቅዳለሁ። ሌሎችም እንደዛ የሚያደርጉ ይመስለኛል።

በዓል ሲነሳ ብዙ ጊዜ የሚነሳው ምግብ ነው እና እርስዎ የሚወዱት ምግብ አለ? በአጠቃላይ የሚወዱት ምግብ ምንድን ነው?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ ያው ለበአላት ባህላዊ ምግቦች ይዘጋጃሉ። ያው በግሌ ከመውደድ አንፃር ጭኮና ጨጨብሳ እወዳለሁ።

ጭኮ በምን?

ጭኮ ነው ያልኩት ቆጮ አላልኩም (ሳቅ) በአል ሲሆንና ጊዜ ሲኖር ገባ ብዬ እሳተፋለሁ። ከሰአት አንፃር ካልሆነ በስተቀር ማዘጋጀት የማልችል እንዳይመስልሽ (ሳቅ)

በትርፍ ጊዜዎ ምን ማድረግ ደስ ይልዎታል?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ የተለያዩ ነገሮች ነው የማደርገው፤ ያው በዚህ ደረጃ በኃላፊነት ስትቀመጪ፤ ሁልጊዜ ሥራሽን እያያሻሉ መሄድም ያስፈልጋል። መረጃዎች ያስፈልጋሉ። አነባለሁ። ሁለተኛ ነገር ደግሞ እግዚአብሔርን ማምለክ በጣም እወዳለሁ። ያለኝን ትንሽ ሰአት ለሁለቱ አካፍላለሁ። ከቤተሰቤ ጋር ቡና መጠጣት፣ ማውራት፣ ውሏችን፣ ሕይወታችን አንዳንድ ነገሮች እናወራለን።

በወቅቱ እያነበቡት ያለ መጽሐፍ አለ? ወይም የሚወዱት መጽሐፍ?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡የማነበው መጽሐፍ አለ። ከሥራዬ ጋር ግንኙነት ባለውና መረጃ ስፈልግ የማነበው አለ።

ራዎ ውጭስ ያሉ ልብወለድ ወይም ታሪካዊ መጻሕፍትን ያነባሉ?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ ሁልጊዜ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ የሚነገርለት መጽሐፍ ያጋጥምሻል። ታሪኩን ቀንጨብጨብ ባለ ሁኔታ ስሰማ ሙሉውን ማንበብ እፈልጋለሁ። በእንደዛ አይነት ሁኔታ አነባለሁ።

በህይወትዎ ትልቅ ስፍራ የሚሰጡት መፅሀፍ ይኖር ይሆን?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ "Inspiration and the wisdom for challenging times" የሚለው የማርቲን ሉተር ኪንግ መፅሀፍ፣ ' A king on leadership' አጠቃላይ ለመንግሥት ሥራ መምራት ብቻ ሳይሆን የራስንም ሕይወት ጭምር አስተዋፅኦ ሊያደርግ የሚችል ፅሁፍ ነው ብዬ በግሌ ተጠቅሜበታለሁ።

ፊልም ያያሉ? ሙዚቃ ያዳምጣሉ

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ እዛም ላይ ብዙ አይደለሁም።

የሚወዱት ጥቅስ አለ? እንደ ይወት መርህ የሚከተሉት?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ የምወደው ጥቅስ አለ። በተለይ የህንዱን ማህተመ ጋንዲ "ትርጉም ያለው ሕይወት የምንለው ለሌሎች አገልግሎት ሲኖር ነው" ውስጤን ይነካኛል። መኖር ከራስ በላይ መሆን እንዳለበት ብዙ እንዳሰላስልና እንዳስብ፤ ከራስ በላይ መኖር ምን ማለት ነው? ለሌሎች አገልግሎት መኖር የሚለውን ፈልጌ የበለጠ እንድረዳውና እንዳነበውም ያደረገኝ ጥቅስ ነው።

ያዘኑበትና የተደሰቱበትን ቀን የሚያስታውሱት አለ?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡በተለየ ሁኔታ የማልረሳው ብየ እንደዚህ የማስታውሰው የለም። በህይወት ውስጥ ያው ውጣ ውረድ አለ። በራስሽ ጉዳይ ብቻ አታዝኚም፤ በራስሽ ጉዳይ ብቻ አትደሰችም። እንደማንኛውም ሰው የማዝንበትም የምደሰትበትም ያጋጥመኛል፤ እያጋጠመኝ ነው የኖርኩት፤ የተለየ ሁኔታ ፈጥሮብኝ ያለፈ አሁን የማስታውሰው የለኝም።

ይወትዎ ምን ሲያዩ ያስደስትዎታል? በስራም፣ በቤተሰብም እንዲሁ በአጠቃላይ ባለው?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ በአጠቃላይ ባለው እንደ ፍትህ የሚያስደስተኝ ነገር የለም። የተዛባ ነገር፣ አረዳድ ሊሆን ይችላል። በፍርድም እጦት ሊሆን ይችላል። ያ ነገር ሲፈታ የተለየ ነገር ይፈጥርብኛል፤ የተለየ ስሜት የሚሰጠኝ እሱ ነው።

መከላከያ የሶሪያ እና የየመን ዜጋ የሆኑ የአይኤስ አባላትን በቁጥጥር ሥር አዋልኩ አለ

ለኢትዮጵያ ምን ይመኛሉ?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ ለኢትዮጵያ ካለብኝ ኃላፊነት የራሷን ወጪ በራሷ መሸፈን የምትችል ሃገር እንድትሆንና እንደገናም እዛ ላይ መድረስ እንድንችል እመኛለሁ። እንደ አጠቃላይ እንደ ሃገር ጥንታዊ ታሪክ ያላት ብትሆንም ነገር ግን እድገቷም ዛሬ ያለችበትን በምናይበት ሰአት ወደኋላ ከቀሩ ሃገራት ተብላ የምትጠቀስ ሃገር ናት። ስለዚህ ለሃገሬ እድገትና ብልፅግና የዜጎቿን መበልፀግና መለወጥ ማየት እፈልጋለሁ።

ለበአሉ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡ አዲሱ አመት የለውጥ በግላችንም በማህበረሰቡም ሆነ በኢትዮጵያም፣ በአስተሳሰባችንም ሆነ በተግባራችንም ተለውጠን አዲስ ነገር የምናይበት አመት ይሁንልን። አዲስ ውጤት የምናስመዘግብበት፣ ፍቅራችን፣ አንድነታችን የሚለመልምበት አመት እንዲሆንልን እመኛለሁ። መልካም አዲስ ዓመት!

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ