"የአምባቸው ሕልም የተጠናከረ አማራን፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት ነበር" አቶ ቹቹ አለባቸው

ዶ/ር አምባቸው መኮንን
አጭር የምስል መግለጫ ዶ/ር አምባቸው መኮንን

ሰኔ 15፣ 2011 ዓ. ም በአማራ ክልል በተካሄደው የ "መፈንቅለ መንግሥት" ሙከራ የተገደሉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን በሥራ ገበታቸው ላይ ምን ዓይነት ሰው ነበሩ? በአንድ ወቅት በአማራ ክልል የከተማ ልማት ምክትላቸው ሆነው ያገለገሉትን አቶ ቹቹ አለባቸውን ጠይቀናቸዋል።

ከዶ/ር አምባቸው ጋር መቼ ነው የተዋወቃችሁት?

በትክክል ጊዜውን ባላውቀውም 80ዎቹ አጋማሽ ላይ፣ ከደርግ ውድቀት በኋላ ነው ሁላችንም የተገናኘነው። በክልል አካባቢ በሚደረጉ መድረኮች ላይ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅነው። ከ84. . . 85 እስከ 87 ካሉት ዓመታት መካከል በአንዱ ነው የተዋወቅነው።

ትውውቃችሁ ወደ ጓደኝነት ያደገበትን አጋሚ ያስታውሱታል?

እንደ ታጋይ የተዋወቅነው በአልኩህ ዓመተ ምሕረት ነው። ከ84 በኋላ ከስድስት እስከ ሰባት ባሉት ዓመታት። ያኔ የምንገናኘው እንደ ማንኛውም ታጋይ ነበር። እንደውም ከደርግ ድምሰሳ በኋላ እኔ ጎንደር ስመደብ እርሱ አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው ሸዋ ስለሆነ ብዙ የመገናኘት እድል የለንም። የምንገናኘው እንዲሁ አልፎ አልፎ ትልልቅ መድረኮች ሲመጡ፤ እርሱም ተናጋሪ ስለነበር፣ እኔም በመድረክ ላይ የዚያ ዓይነት ባህሪ ስላለኝ መተዋወቅ ጀመርን። ከዚያ በኋላ በ1990ዎቹ አካባቢ እርሱም እኔም ለትምህርት ሄድን። ከዚያ በኋላ ብዙም ተገናኝተን አናውቅም።

"ስተዳደር የቆየሁት በዋናነት ለመለስ በሚሰጠው የጡረታ ገቢ ብቻ ነው" ወ/ሮ አዜብ መስፍን

ወደመጨረሻ የተገናኘነው 2001 ዓ. ም. ጉባዔ ላይ ይመስለኛል። ያኔ እንግዲህ በቅርበት መነጋገር ጀመርን። አንድ ትልቅ መድረክ ነበረ። ከዚያም በኋላ እንደገና እርሱ ወደ ውጪ ሄደ። ፒ ኤች ዲውን ጨርሶ ሲመጣ ሥራ ተመደበ። በዋናነት ጓደኛ የሆነውና በቅርብ መሥራት የጀመርነው ከ2006 ጀምሮ የእርሱ ምክትል ከሆንኩ በኋላ ነው። ከተማ ልማት ላይ። ከዚያ በኋላ የቅርብ ጓደኛሞች ሆነን ቀጠልን።

በከተማ ልማት በዋናና ምክትልነት ስትሩ የነበራችሁ ግንኙነት ምን ይመስል ነበር?

በዚህ ደረጃ ተቀራርበን እንትን ባንልም በሀሳብ ደረጃ እኔና አምባቸው በመድረክ እንግባባለን። ሀሳቤን ያውቀዋል፤ ሀሳቡን አውቀዋለሁ። ድሮም በመከባበር ላይ የተመሰረተ ወንድማዊና ጓዳዊ ግንኙነት ነበረን። ቢሮም ላይ በጋራ መሥራት ከጀመርን በኋላ የቀጠለው ይኸው ነው። ስለ እውነት በዚህ ጉዳይ ላይ ከድርጅት ጋር ተጋጭቼ ጎንደር ላይ ከኃላፊነት ተነስቼ ነበር። ከኃላፊነት ተነስቼ እርሱ ወደ ከተማ ልማት ሲመጣ ነው እኔ እንደገና ወደ ክልል የመጣሁት። እና እርሱ እዚያ ቢሮ ባይሆን ኖሮ እኔ አልመጣም ነበር።

ዶ/ር አምባቸው እርስዎ እንዲመደቡ ጫና አድርገዋልወይስ?

አጠቃላይ ውሳኔው የድርጅቱ ነው። ድሮም በስህተት ስለተነሳን፣ የተነሳንበት አግብብ ትክክል አይደለም ብሎ ድርጅቱ ሲወስን፣ ይህ ውሳኔ በተወሰነበት አጋጣሚ ሳምንት ወይ ወር አይሞላውም አምባቸው ከተማ ልማት መጥቶ ነበር። ከዚያ በኋላ የሆነ ቦታ ሲፈለግ ከኔ ሙያ ጋርም በቅርበት ሊሄድ የሚችለው የአምባቸው ቢሮ ሆኖ ተገኘ። በርግጥ ለእኔ መጀመሪያ አልነገሩኝም ነበር፤ ግን ጠርጥሬያለሁ።

የሼፎች የበዓል ምግብ ምርጫ፡ ሼፍ ዮሐንስ፣ ጆርዳና እና ዮናስ

እንደሚመልሱኝ ሲነግሩኝ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ተነጋገርኩ። ያሉት ክፍት ቦታዎች ሁለት ናቸው፤ አንዱ ባህር ዳር ላይ ሥራ አስኪያጅና ሁለተኛው ከተማ ልማት። ከተማ ልማት የሚሆን ከሆነ ከአምባቸው ጋር እንደሚሄድ፣ ያ ጓደኛዬ 'እርሱ ጋር ከሆነ ሂድ፤ ሌላ ጋር ከሆነ ግን አትሂድ' አለኝ። እሺ ብዬ ቆየሁና በመጨረሻ ሲነገረኝም የተመደብኩት ከአምባቸው ጋር እንድሠራ ነበር። በኋላ እንደተረዳሁት አምባቸውም የእኔን መምጣት በጽኑ ነው የደገፈው።

በሥራአጋጣሚ ተጣልታችሁ ታውቃላችሁ?

[ሳቅ] እኔና አምባቸው. . . አየህ፤ አንዳንዴ የምታከብረው ሰው አለ አይደል? እርሱም እኔን ማስከፋት አይፈልግም፤ እኔም እርሱን ማስከፋት አልፈልግም። ግን ምንድን ነው? በውሳኔዎች ላይ፣ በተለይ ከመሬት ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ በልዩነት ነው የምንወጣው። መጨረሻ ላይ ትክክል የሚሆነው ሀሳብ የኔ ነው። እርሱ በቅንነት እንሥራ ነው [የሚለው]። እኔ ደግሞ የሕጎች ትንሽም ቢሆን ግንዛቤ ስላለኝ አይሆንም ነው።

ያኔ አምባቸው ቅንነት ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎ የሚበሳጭም ሰው ነው። በነገራችን ላይ መታወቅ ያለበት አንደኛው ባህሪው ይኼ ነው። የአምባቸውን ብስጭት ከእኛ የሚለየው ምንድን ነው? ከአምስት ደቂቃ በላይ በኩርፊያ አይቆይም። እና አይሆንም ስንለው ወዲያው ትንሽ የማኩረፍ፣ በስጨት የማለት ነገር አለበት። በአምስት ደቂቃ ውስጥ እዛው መድረክ ላይ እንዳለን ወርዶ 'ወንድማለም አስቀየምኩህ አይደል?' ብሎ እንደገና ይመለሳል፤ አጀንዳችንን እንቀጥላለን።

እና ብዙ ጊዜ በመሬት ጉዳዮች፣ በተለይ ውሳኔ ላይ አለመግባባት ነበር። እኔ እሱን መሸፈን ነው። አሠራሩንም መጠበቅ ነው። እርሱ ግን ሁል ጊዜም የሚታየው ሥራ ብቻ ነው። ሥራ፣ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ፣ አገልግሎት መስጠት። እኔ ደግሞ ይህንን ማድረግ የምንችለው በአሠራር ውስጥ ስንሆን ነው ስል የተወሰኑ መድረክ ላይ ገጭ ገጭ አለ። ያው የወንድም ግጭት ማለት ነው። በወንድም ሀሳብ አለመግባባት እንዲህ አይነት ጉዳዮች በተደጋጋሚ ገጥመውናል። ግን አንድም ቀን እኔ ለእርሱ ክፉ፣ እርሱ ለእኔ ክፉ ድርጊት ውስጥ ገብተን አናውቅም። እንኮራረፋለን፤ ግን እዚያው መድረክ ላይ እንተራረባለን፤ ብዙ ጊዜ የእርሱ ባህሪ 'ወንድማለም አስቀየምኩህ? ይቅርታ' ብሎ እንደገና መድረኮችን እንቀጥላለን። በዚህ መልኩ የሚገለፁ ብዙ ጉዳዮች አሉ፤ ነበሩ።

"ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት በትንሳኤ በዓል ነበር" የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ እናት

በተለይ የሚያስታውሱት የተጋጫችሁበት ጉዳይ ይኖራል?

በርከት ያሉ ናቸው ሌላ ጊዜ ለመጻፍ እሞክራለሁ። ግን ምንድን ነው? አሁን የማስታውሰው. . . በ2006 ወይንም 2007 ይመስለኛል ሕገወጥ ቤት በፈረሰ ጊዜ. . . በክልሉ ወደ 19ሺህ ቤት ፈርሷል። በዚህ ላይ ልዩነቶች ነበሩን። በእኔም በእርሱም በኮሚቴያችንም ውስጥ። እና የእርሱ ሃሳብ ገዢ ሆኖ፣ እርሱም በርግጥ መነሻ ነበረው፣ ከዚያ በፊት የተወሰደ እርምጃ ስለነበረ ዘንድሮ ሳናፈርስ ብንቀር አግባብ አይሆንም የሚል አቋም ነበረው። የክልሉም መንግሥት የእርሱን ሀሳብ ደግፎ እርምጃ ተወሰደ። ቤት ፈረሰ። ቤት ከፈረሰ በኋላ በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ተፈጠረ። ሰዎችም ሞቱ። ቤታቸው ሲፈርስ። የዚያኔ የክልሉ መንግሥት ሲቸግረው በሕገ ወጥ መሬት የፈረሰባቸውን ሰዎች መሬት እንስጣቸው አለ። ይኼ ሕገ ወጥ አሠራር ነው። ይህንን አምባቸው ከእነ አቶ ገዱ ጋር ከተወያየ በኋላ ከተማ ልማት እንዲያስፈፅም ተብሎ አምባቸው ይዞ መጣ። ወደ ከተማ ልማት ሲመጣ ደግሞ ይህንን ሥራ የግድ የምፈፅመው እኔ ነኝ። ቀጥታ ሚመለከተኝ እኔን ስለሆነ ማለት ነው።

2011፡ በፖለቲካና ምጣኔ ኃብት

አምባቸው ይህንን ጉዳይ ይዞ መጣ። አልፈጽምም አልኩ። እንደማይፈፀምም ነገርኩት። ይህንን ስለው እርሱም ጉዳዩን ወደ ትልልቆቹ አመራሮች ይዞት ሄዶ እነርሱም 'ይህንን ማስፈፀም ያልቻልክ' አይነት ነገር ገጭ አደረጉት መሰለኝ፤ እንደገና ይዞት መጣ፤ እናም አንፈፅምም አልን። በዚህ መካከል ትንሽ መደባበር ነበረ። መጨረሻ ላይ ግን እኔ እምቢ በማለቴ እርሱንም ከስህተት ጠብቄዋለሁኝ። ሌላም ገጠመኝ አለ ይህች ግን የምትጠቀስ ናት።

ከሥራ ውጪ በተለያዩ ማበራዊ ጉዳች አብራችሁ የምትሆኑባቸው ጊዜያት ነበሩ?

በዚህ መልኩ ብዙ የእረፍት ጊዜ የምንለው፣ የምንጫወትባቸው ጊዜያት የሉም። እርሱም ወደ አዲስ አበባ ከሄደ በኋላ እኔም ወደ አዲስ አበባ ከሄድኩ በኋላ ለብቻ አንድ ቀን ተገናኝተን ያወራናቸው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች አሉ። እንጂ እዚህ ሥራ ላይ እያለን እርሱም ጊዜ የለው፤ እኔም ጊዜ የለኝ። እንደዚህ የምንዝናናበት ጊዜ ብዙም አልነበረም። ከተማ ልማት ላይ እያለን ትርፍ ጊዜ አልነበረንም።

ጊዜ አግኝተን ሻይ ቡና በምንልበት ወቅት አምባቸው ተጫዋች ነው። በኢህአዴግ ውስጥ በሦስት ጉዳዮች እንደ አምባቸው የተሳካለት ሰው ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። የመጀመሪያው ነገር ከታች ተነስቶ የደረሰበትን ትምህርት ደረጃ ስታየው እጅግ በጣም የሚገርም ነው። ከታች ነው የተነሳው። ከታች መነሳት ብቻ ሳይሆን ያለፈባቸው መንገዶች እጅግ መሰናክል የበዛባቸው ናቸው። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተነስቶ፣ በኢህአዴግ ውስጥ ታግሎ፣ የኢህአዴግን ፈተና ተቋቁሞ፣ ፒኤችዲ ደረጃ መድረስ. . . ያለፈበትን መንገድ ለምናውቀው ሰዎች እጅግ በጣም የተሳካለት ሰው ነው፤ በትምህርት መስኩ።

በዓመቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች ጥቂቱ

ሌላው አምባቸው የተሳካለት ነው የምለው የአመራር ዘይቤ ነው። አምባቸው በበርካታ ቢሮዎች ሠርቷል። ሁሉም ቢሮዎች ተወዳጅ ሆኖ ነው የወጣው። በማኔጅመንቱም፣ በሠራተኛውም አምባቸውን የሚነቅስ፣ አምባቸውን በክፉ የሚያየይ ገጥሞኝ አያውቅም። ይሄ በአመራር ዘይቤ ይዞት የወጣው ትልቅ ድል ነው ብዬ አስባለሁ።

ሶስተኛው ማኅበራዊ ሕይወቱ ነው። አምባቸው ከማንኛውም ጋር ተግባቢ ነው። በሐዘን ደራሽ፣ በደስታ ደራሽ፣ ችግር ተካፋይ ነው። በእነዚህ ሦስት ጉዳዮች በኢህአዴግ ውስጥ እንደ አምባቸው የተሳካለት ሰው አለ ወይ? ብዬ ሁልጊዜ ሳይ፤ ብዙ ያለ አይመስለኝም። ካሉም ግን አንዱ አምባቸው መሆኑ ነው። እነዚህ ሦስቱ ግን እኔ ሁሌም የምቀናባቸው የአምባቸው የተለዩ ባህሪያት ናቸው።

ስተኛ ዲግሪያቸውን ሲማሩከድርጅቱ ጋር በነበረ አለመግባባት ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ ያደረጉት ጓደኞቻቸው ገንዘብ አዋተው ነው ሲባል እሰማለሁ። ስለዚህ ሚያውቁት ጉዳይ አለ?

እውነት ነው። [ፈገግታ በተሞላው ድምጽ] እርሱ እንዲማር የሄደው ሁለተኛ ዲግሪውን ነበር፣ ለንደን ወይም ኮሪያ ይመስለኛል። ድርጅቱ ተምሮ ይመጣል ብሎ ሲጠብቅ፤ በዛው በራሱ ጥረት ሦስተኛ ዲግሪውን ለመቀጠል እድል አገኘ። እርሱ ወዶት ብቻ ሳይሆን ሁኔታዎችም ናቸው ወደዚያ ያስገቡት። ያኔ የነበሩት የድርጅቱ አመራሮች ይህንን ሲያውቁ፤ 'ከፈለግህ ትተህ ና እንጂ አናስተምርም' ተባለ። ቤቱንም ለመሸጥ፣ ለሌላም ነገር ለመዘጋጀት ጥረት አድርጎ ነበር። ጓደኞቹ የምንችለውን ያህል. . . በርካታ ጓደኞቹ በማዋጣት ተሳትፈዋል። በመጨረሻም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መማሩ እንደማይቀር ሲያውቁ ወጪውን ሸፍነውለታል፤ እውነት ነው።

ርዕሰ መስተዳደር ከነበሩ በኋላ ትደዋወ ነበር?

ርዕሰ መስተዳድር ከሆነ በኋላ እንኳ ብዙ አንደዋወልም። ትንሽ ተኮራርፈን ነበር። የተኮራረፍንበት ምክንያት ባለፈው እንዳነሳሁት [የፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ የፃፉትን ለመጥቀስ ነው] አዲስ አበባ ላይ ለብአዴን ሊቀመንበርነት ታጭቶ፤ በሆነ ምክንያት መክሸፉን መረጃ ይኖርሃል። አዲስ አበባ ተገናኝተን በዚህ ጉዳይ ላይ አውርተን ነበር ለብቻችን። እንደጥሩ አጋጣሚ ወስዶት፤ ካሁን በኋላ የሚፅፋቸው ነገሮች ካሉ እንዲፃፍ፣ ተረጋግቶ እንዲቀመጥና ወደራሱ እንዲመለስ፣ በፍፁም ወደ አማራ ክልል ፖለቲካ ተመልሶ እንዳይሄድ ብዙ ውይይት አደረግን። እኔና እርሱ በዚህ ተስማምተናል። በተለይ ወደ ክልል ፕሬዝዳንትነት እንደማይሄድ የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰን ነበር። እንደ ወንድም። ሳይነግረን፣ ምን ሳይል መጥቶ ፕሬዝዳንት ሆነ። ከዚያ ትንሽ ተደባበርን። አንደኛ እንደዚያ ተነጋግረን፣ ሁለተኛ ሀሳቡን ሲቀይር እንኳ አልነገረንም ብዬ እርሱም ደብሮት፣ እኔም ደብሮኝ አንገናኝም ነበር። በመጨረሻ ከመገደሉ አንድ ሳምንት ምናምን ቀደም ብሎ ተደዋወልን፤ አንድ የግድ የምንገናኝበት ጉዳይ ስለነበርን።

እዚያ ፕሮግራም ላይ በትራንስፖርት ምክንያት ሳንገናኝ ቀረን።

በምን ጉዳይ ላይ ለመነጋገር ነበር ቀጠሮ ያዛችሁት?

ቀጠሯችን በሁለት ጉዳይ ነው። አዲስ አበባ ነበር የተቀጣጠርነው። ምንድን ነው? የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውይይት ነበርና በዚያ እንድሳተፍ ጋበዙኝ። ውይይቱ ውጪ ጉዳይ ነው የነበረው። እርሱም እኔም የምንወቃቀስበት ነገር አለ። ያ ሁለተኛ አጀንዳችን ነበር። በል ሁሉንም እዚያ እናውራው ብለን ነበር ቀጠሮ የያዝነው። እኔም በትራንስፖርት ምክንያት ሳልገኝ ቀረሁ። ሌላ ጊዜ እንገናኝ ብለን ቀጠሮ እንደያዝን አደጋው ደረሰ፤ ቀረ።

ዶ/ር አምባቸው ሕልማቸው ምን እንደነበር እንደጓደኛ አካፍሎዎት ካወቁን ነበር የሚያልሙት?

ብዙ ጊዜ ስንገናኝ የሚያነሳው. . . ቁጭት አለው ታውቃለህ። የአማራ ሕዝብ ያሳለፋቸው በደሎች ላይ ቁጭት ነበረው። ትልቁ እይታው የነበረው ከማኅበረሰብ አንጻር ነበር። ሁል ጊዜ የሚያስበው የተጠናከረ፣ በተለይ በኢኮኖሚ አቅም ያለው አማራን ማየት ነበር። ያለፈው ሥርዓት በዚህ ሕዝብ ላይ ጥሎ የሄደው ነገር ሁል ጊዜ ይቆጨዋል። ከዚያ የተላቀቀ፣ በራሱ የሚተማመን፣ አቅሙ የዳበረ የአማራን ማኅበረሰብ ማየት የአምባቸው የዘወትር ሕልሙ ነበር። ይኼ ሁልጊዜ የማልረሳው፤ ሁልጊዜ የሚያነሳው ጥያቄ ነበር። በታሪክ ላይ ብቻ ተመስርተን እንደማንኖር፤ የቴዎድሮስ ልጅ. . . የማንም ልጅ እያልን መኖር እንደማንችል። ይህንን ለማስቀጠል፣ ከድህነት ተላቀን ሁለንተናዊ አቅም [እንዲኖር]፤ በተለይ 'ኢኮኖሚክ ኢምፓወርንመንት' [በምጣኔ ሀብት ራስን መቻል] ላይ ትኩረት ይሰጥ ነበር። የበለፀገ አቅም የፈጠረ አማራን የማየት ፍላጎት ነበረው።

ከዚያም በላይ ራዕዩ አገራዊ ነው። በዚሁ ልክ የምትለካ፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን. . . የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጎ. . . ይህችን ኢትዮጵያ ማየት ፍላጎቱ ነበር [በረዥሙ ተነፈሱ]።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ