ከ22 ዓመት በኋላ በ 'ጉግል ማፕ' አስክሬኑ የተገኘው ግለሰብ

ዊልያም ሞልድት Image copyright National Missing and Unidentified Persons System
አጭር የምስል መግለጫ ዊልያም ሞልድት

ፍሎሪዳ ውስጥ ከ22 ዓመት በፊት ጠፍቶ የነበረ ዊልያም ሞልድት የተባለ ግለሰብ አስክሬን በ'ጉግል ማፕ' አማካይነት ተገኘ። የግለሰቡ አስክሬን የተገኘው 'ጉግል ማፕ' [የተለያዩ አካባቢዎችን የሚያሳይ የስልክ ካርታ] መኪናው ያለበትን ሥፍራ ካሳየ በኋላ ነበር።

በጠርሙስ በላኩት መልዕክት ሕይወታቸው የተረፈው ቤተሰብ

ኦክስፎርድ ከዓለማችን ቀዳሚው ዩኒቨርስቲ ተባለ

የአእምሮ ጤና ሰባኪው ፓስተር ራሱን አጠፋ

ዊልያም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1997 ነበር የጠፋው።

በወቅቱ 40 ዓመቱ ነበር፤ የምሽት ክለብ ውስጥ ሲዝናና ካመሸ በኋላ ለዓመታት የት እንደደረሰ አልታወቀም። ፖሊስም ዊልያምን ፈልጎ ማግኘት አልቻለም ነበር።

'ጉግል ማፕ' ያሳየውን የመኪና ምስል ተከትሎ፤ ፖለሶች ወደ ሥፍራው ሲሄዱ የዊልያምን አስክሬን አግኝተዋል። መኪናው የሚገኝበት ቦታ የታወቀው አንድ ግለሰብ 'ጉግል ማፕ' ላይ ያደረጉትን አሰሳ ተከትሎ ነበር።

Image copyright Google Maps
አጭር የምስል መግለጫ 'ጉግል ማፕ' ላይ የሚታየው የመኪና ምስል

ፓልም ቢች የተባለው ግዛት የፖሊስ ኃላፊ ተሬሳ ባርባራ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ዊልያም ከ22 ዓመት በፊት መኪናውን እያሽከረከረ ሳለ፣ መኪናው ከቁጥጥሩ ውጪ ሆኖ ወደኩሬ ሳይገባ አልቀረም።

"ከዚ ሁሉ ዓመታት በፊት የተፈጠረውን በውል ለማወቅ ያስቸግራል" ብለዋል።

ዊልያም ከ22 ዓመት በፊት ሄዶበት ከነበረው የምሽት ክለብ ከመውጣቱ በፊት ብዙም አልኮል እንዳልጠጣ በወቅቱ የተሰበበሰው መረጃ ያሳያል።

በምሽቱ ዊልያም ለፍቅረኛው ወደቤት እንደሚመለስ ቢነግራትም፤ ዳግመኛ አላየችውም።

አስክሬኑ መገኘቱን ፖሊስ ለቤተሰቦቹ አሳውቋል።