የአፍሪካ መሪዎች የሙጋቤ ስንብት ላይ ይገኛሉ

የዚምቧብዌ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ አስክሬን ሐራሬ በሚገኘው መኖሪያቸው ሲደርስ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የዚምቧብዌ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ አስክሬን ሐራሬ በሚገኘው መኖሪያቸው ሲደርስ

ዚምቧብዌ የቀድሞ ፕሬዝዳንቷን ሥርዓተ ቀብር ከመፈፀሟ በፊት፤ ሮበርት ሙጋቤን ለመሰናበት የአፍሪካ መሪዎች በዋና ከተማዋ ሐራሬ ይሰባሰባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የደቡብ አፍሪካው ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ በርካታ በስልጣን ላዩ ያሉና የቀድሞ የአፍሪካ ርዕሰ ብሄሮችም በስንብቱ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የቀብር ሥርዓቱ በሙጋቤ ቤተሰቦችና በመንግሥት መካከል የአለመግባባት መነሻ ሆኖ ነበር።

“በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማርን ዛሬም፣ ነገም፣ ወደፊትም የምከራከርበት ነው” ገነት ዘውዴ [ዶ/ር]

"ስተዳደር የቆየሁት በዋናነት ለመለስ በሚሰጠው የጡረታ ገቢ ብቻ ነው" ወ/ሮ አዜብ መስፍን

"የአምባቸው ሕልም የተጠናከረ አማራን፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት ነበር" አቶ ቹቹ አለባቸው

የኢኳቷሪያል ጊኒ ፕሬዝዳንት ቲዮዶር ኦቢያንግ ሐራሬ የገቡ ሲሆን፤ ሙጋቤን "በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በአቻነት ለንፅፅር የሚቀርብ መሪ የማይገኝለት" ሲሉ አንቆለጳጵሰዋቸዋል።

ፕሬዝዳንት ኦቢያንግ እኤአ በ1979 ስልጣን ላይ የወጡ ሲሆን፤ ሙጋቤ ስልጣን ላይ ከቆዩበት ዓመት ረዘም ላለ ጊዜ መንበራቸው ላይ የቆዩ ናቸው።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ "መሬቱን ከነጮች ነጥቀው ስለሰጡት ምንግዜም ቢሆን የዚምቧብዌ ሕዝብ ሲያመሰግናቸው ይኖራል" ብለዋል።

ልክ እንደ ፕሬዝዳንቱ ሁሉ በርካታ ዚምቧቤያውያንም ሙጋቤን ከተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስና የኢኮኖሚ ተግዳሮት ውጪ በሠሯቸው መልካም ነገሮች ማስታወስ ይሻሉ።

ሙጋቤን የተኳቸው ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ በቀድሞ መሪያቸው ሞት ሐዘን ለገባቸው ዜጎች፤ በአገሪቱ ብሔራዊ ስታዲየም ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ስታዲየም የሚገኘው ሕዝብም የዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ መለያ ቀለም የሆነውን ለብሰው ይገኛሉ ተብሏል።

ዚምቧብዌ የሙጋቤን ቀብር የምታስፈፅመው በኑሮ ውድነት እና ሥራ አጥነት በከፍተኛ ሁኔታ ተፈትራ በተያዘችበት ወቅት ነው።

"ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩ ደስተኛ ነኝ። ስለምን ቀብራቸው ላይ እገኛለሁ? እንጥፍጣፊ አቅምም የለኝ" ሲሉ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ቃላቸውን የሰጡት አንድ የሐራሬ ነዋሪ ናቸው።

"ከዚህ በኋላ ስለእርሱ ምንም ነገር መስማት አልፈልግም። ለችግራችን ሁሉ መነሻ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ሮበርት ሙጋቤ አስክሬናቸው የሚያርፈው የአገሪቱ ጀግኖች በሚቀበሩበት ሥፍራ እንደሚሆን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።

የ95 ዓመት አዛውንት የነበሩት ሮበርት ሙጋቤ የሞቱት ህክምና እያገኙ በነበረበት ሲንጋፖር ነው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ