ከባህላዊ ጃንጥላ እስከ እንጀራ ማቀነባበሪያ፡ የ2011 ዓ.ም አበይት ፈጠራዎች

ሰብለወንጌል ብርቁና ሔዋን መርሀ
አጭር የምስል መግለጫ ሰብለወንጌል ብርቁና ሔዋን መርሀ

በ2011 ዓ. ም. በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ከተመዘገቡ የግብርና ምርቶች መካከል የጅሩ ሰንጋ፣ የይፋት ደብረሲና ቆሎ፣ የምንጃር ጤፍ፣ የአረርቲ ሽምብራ፣ የመንዝ በግ፣ የአንጎለላና ጠራ ወተት የሚገኙ ሲሆን፤ የወሎ ጋቢና የደሴ ሳፋ በምዝገባ ሂደት ላይ እንደሚገኙ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ለቢቢሲ አረጋግጧል።

በተጨማሪም በርካታ የሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ጥበብና ሌሎችም የጥበብ ውጤቶች እንዲሁም የንግድ ምልክቶችም ተመዝግበዋል።

ባህላዊ ጃንጥላ እና እንጀራ 'ፕሮሰሰር' [እንጀራን አቡክቶ የሚጋግር መሣሪያ]፤ ባሳለፍነው ዓመት በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ከተመዘገቡ የፈጠራ ሥራዎች መካከል ይገኙበታል። እኛም የፈጠራዎቹን ባለቤቶች እንግዳችን አድርገናል።

የወንድሙን ገዳይ ለመበቀል ወደ ፈጠራ ሥራ የገባው ኢትዮጵያዊ

የኢትዮጵያ ተረት ገፀ-ባህሪን በአኒሜሽን

የአለማየሁ ተፈራ ፖለቲካዊ ካርቱኖች

"ድሮ ነጠላቸውን ቆልፈውበት ይሄዱ ነበር"

ሔዋን መርሀ 24 ዓመቷ ነው። ያጠናቸው 'ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ' ሲሆን፤ 'ዳታ ኢንኮደር' ናት።

ሔዋን "እጇ የማይቦዝን" የምትባል አይነት ሰው ናት። የረዘመ ልብስ ታሳጥራለች፣ ጨሌ ሰብስባ የእጅ ጌጥ ትሠራለች ወዘተ. . .

"ባህላዊ ነገር ደስ ይለኛል" የምትለው ሔዋን፤ በተለይ ነጠላ ካገኘች ደስታዋ ወደር የለውም። ትቀደዋለች፣ ትሰፋዋለች፣ አንዱን ዘርፍ ከሌላ ጋር ታስተሳስራለች።

"ከልጅነቴ ጀምሮ በጣም ልብስ እቀዳለሁ። [የገዛሁትን ልብስ ቀድጄ] በራሴ 'ሙድ' አደርገዋለሁ። ከሰፋኝ አጠባለሁ፤ ከጠበበኝ አሰፋለሁ። እጁ ካልተመቸኝ ቆርጬ ሌላ ቦታ አደርገዋለሁ"

ታዲያ ይህን ልማዷን ቤተሰቦቿ እምብዛም አይደግፉትም ነበር። በተለይ እናቷ "እሷ ነጠላ ካገኘች አትቻልም" እያሉ ከቤት ሲወጡ ነጠላቸውን ቆልፈውበት ይሄዱ እንደነበር ታስታውሳለች።

የዛሬ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ ጥበብ ልብስ አድርጋ ከቤት ልትወጣ እየተሰናዳች ሳለ አንድ ሀሳብ ብልጭ አለላት።

Image copyright HEWAN MERHA
አጭር የምስል መግለጫ ከጥበብ ልብስ ጋር አብሮ እንዲያዝ የተሠራው ጃንጥላ

"የገዛሁት ሐበሻ ቀሚስ ሁለት ነጠላ ነበረው። ከቤት ልወጣ ስል ጸሐይ ነበር። ከዛ አንዱን ነጠላ ለምን ጥላ አላደርገውም አልኩ? እናቴ 'ይቺ ልጅ ቀሚስም መቅደዷ አይቀርም' ብላኝ ነበር. . . "

ሀሳቧ ሀሳብ ሆኖ አልቀረም። ከጥበብ ጃንጥላ ሠራች።

የጃንጥላው መደብ ጥበብ ነው። ሰዎች ሐበሻ ልብስ አድርገው ሲወጡ ከልብሳቸው ጋር በሚመሳሰል ጥብበ በተሠራ ጃንጥላ እንዲዘንጡ፣ ራሳቸውን ከጸሐይ እንዲከላከሉም አስባ እንደሠራችው ትናገራለች።

"ጥለቱን ሽሮ ሜዳ ሸማኔዎች ጋር ሄጄ አሠራዋለሁ። ሰው ሐበሻ ልብስ ሲገዛ ከልብሱ ጋር 'ማች' የሚያደርግ [የሚመሳሰል] ጃንጥላ እኔን ማሠራት ይችላል።"

ጃንጣላው እንደሚሠራበት ጥበብ አይነት፤ ከ1000 ብር እስከ 2000 ብር ድረስ ትሸጠዋለች። ጃንጥላው በተጠቃሚው ፍላጎት መሰረት በክብ ወይም በዚግ ዛግ ይሠራል።

ሔዋን ጃንጥላውን ለልጆችና ለአዋቂዎችም ታዘጋጃለች። የጥበብ ኮፍያም ትሠራለች።

ባህላዊ ጃንጥላውን በአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ብታስመዘግበውም፤ የሙሉ ጊዜ ሥራዋ አይደለም። ለወደፊት አቅሟን አደራጅታ፣ ሱቅ ከፍታ፣ ንግዱን ማጧጧፍ እንደምትፈልግ ነግራናለች።

"ድሮ ነጠላቸውን ቆልፈውበት የሚሄዱት ቤተሰቦቼ፤ ሥራዬ ገንዘብ እንደሚያመጣ ሲያውቁ እኔን መደገፍ ጀምረዋል" ትላለች።

"በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንጀራ የሚጋገርበት መንገድ መለወጥ አለበት"

የ21 ዓመቷ ሰብለወንጌል ብርቁ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ተማሪ ናት። እንጀራ 'ፕሮሰሰር' የተሰኘ ማሽን ለመሥራት የወጠነችው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነበር።

ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ ናት። ከአንድ ጓደኛዋ ጋር ስለ ቤት ውስጥ ሥራ ጫና ሲያወሩ፤ 'በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንጀራ መጋገር የሚወስደውን ጊዜ እንዴት መቀነስ አይቻልም?' ትለዋለች።

እንጀራ ተቦክቶ ሲጋገር የሚወስደውን ጊዜና ጉልበት መቀነስ እንደሚቻል የነገረችው ጓደኛዋ፤ ሀሳቧ አልዋጥልህ አለው። እሷ ግን 'እንደውም ሀሳቤን እውን አድርጌ አሳይሀለሁ' ብላ ዛተች።

በትምህርት ቤቷ በሚገኝ 'ወርክሾፕ' ውስጥ ረዥም ጊዜ ታሳልፍ ጀመር። ሀሳቧን ያካፈለቻቸው ጓደኞቿም ከጎኗ ነበሩ። በስተመጨረሻም ለሙከራ የሚሆን እንጀራ አቡክቶ፣ የሚጋግር ከዛም በሰፌድ አውጥቶ የሚያስቀምጥ መሣሪያ ሠራች።

Image copyright SEBLEWONGEL BIRKU
አጭር የምስል መግለጫ ሰብለወንጌልና ጓደኞቿ እንጀራ 'ፕሮሰሰር' ሲሠሩ

በፈጠራው በትምህር ቤቷ ተሸላሚ እንደነበረች ታስታውሳለች። ሰብለወንጌል የፈጠራውን ሀሳብና ዲዛይን በአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ለማስመዝገብ የወሰነችው ዩኒቨርስቲ ስትገባ ነበር።

"የሰውን ሕይወት እንዴት ማቅለል ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ሁሌም ያቃጭልብኛል። ሕልሜ ችግርን በቀላሉ መፍታት ነው" ትላለች።

መሣሪያው ጥቅም ላይ ሊውል በሚችልበት መንገድ ማምረት አልጀመረችም። ሆኖም አገልግሎት እንደሚሰጥ ስለተረጋገጠ ለወደፊት እንደምትተገብረው ትናገራለች።

ሰብለወንጌል እንደምትለው፤ እንጀራ 'ፕሮሰሰር' ጤፍ አቡክቶ፣ አብሲት ጨምሮ፣ ሊጡ ኩፍ ሲል ይጋግራል፤ እንጀራውን ከምጣድ ላይ አውጥቶም ያከማቻል።

"እንጀራ አቡክቶ፣ ጋግሮ ለማውጣት የሚወስድበት ጊዜ እንጀራ በሰው ጉልበት ሲጋገር ከሚወስደው መደበኛ ሰዓት ጋር እኩል ነው። አንድ ሰው ሊጥ ቦክቶ መቼ እንደሚጋገር ወስኖ ማሽኑን 'ሴት አፕ' ማድረግ [ማስተካከል] ይችላል። ምን ያህል እንጀራ፣ በምን አይነት የውፍረት መጠን እንደሚጋገር አስቦ ማሽኑን ማስተካከልም ይቻላል።"

ሌሎች የ2011 ፈጠራዎች

ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ባገኘነው መረጃ መሰረት ባለፈው ዓመት ከተመዘገቡ ፈጠራዎች መካከል በቆሎ የሚዘራ ማሽን እና በዶሮ ኩስ እና በተረፈ ምርቶች የሚሠራ ማብሰያ ይገኙበታል።

የልብ ህመምን ለመከላከል የሚሆን ተጨማሪ ምግብ አዘገጃጀት ዘዬ እንዲሁም ቀላልና ጣፋጭ ምግቦች የሚሠሩበት መንገድ ዝርዝርም በፈጠራነት ተመዝግበዋል።

ተያያዥ ርዕሶች