የክልል እንሁን ጥያቄ ከከፋ ዞን ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ቀረበ

የክልል እንሁን ጥያቄ ከከፋ ዞን ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ቀረበ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ዛሬ ጠዋት ወደ ቦንጋ አቅንተው ከአከባቢው ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ያቀኑት ከቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን እና ከመከላከያ ሚንስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ጋር በመሆን ነው።

ዛሬ ጠዋት ከአዲስ አበባ ተነስተው እስከ ጅማ ድረስ በአውሮፕላን የተጓዙት ጠቅላይ ሚንስትሩ እና ልዑካቸው ከጅማ እስከ ቦንጋ የ100 ኪሎ ሜትር መንገድን በመኪና ተጉዘዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በቦንጋ ከተማ እስታዲያም ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤ ከዚያም ወደ ከተማ አስተዳደሩ ቢሮ በማቅናት ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድረገዋል።

ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል የክልል እንሁን የሚለው በተደጋጋሚ የቀረበ ነበር።

የደቡብ ክልል፡ ውስብስቡ የዐብይ ፈተና

ክልልነት ለጠየቀው ሁሉ ቢሰጥ ችግሩ ምንድነው?

"በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት አካላት የክልል የመሆንን ጥያቄ አቅርበናል" ያሉት አንድ ተሳታፊ "ለፍርድ ቤት አገልግሎት ሃዋሳ ለመድረስ 800 ኪ.ሜትሮችን ነው የምንጓዘው። ይህ ብቻም ሳይሆን የዞኑ ባለስልጣናት ለስብሰባ ወደ ሃሳዋሳ ሲያቀኑ ብዙ ወጪ ነው የሚያወጡት" ብለዋል።

"የከፋ ህዝብ ባለፉት ስርዓቶች ብዙ ጉዳቶችን ያስተናገደ ህዝብ ነው። የከፋ ዞን የክልል የመሆን ጥያቄ የህዝብ ጥያቄ ነው" ሲሉ አንድ ሌለኛው ተሳታፊ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በተደጋጋሚ ክልል እንሁን ለሚሉ ጥያቄዎች ሲመልሱ "ክልል ብትሆኑ ጥያቄዎቻችሁ ሁሉ ምላሽ ያገኛሉ ብላችሁ ካሰባችሁ ስህተት ነው" ብለዋል።

"ለምሳሌ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ክልል ሆነው ሳለ እናንተ የምታነሱትን ጥያቄ እነሱም ያነሳሉ" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ "በአሁኑ ሰዓት የከፋን ህዝብ እየስተዳደረ ያለው ሌላ አይደለም። እራሳችሁን በራሳችሁ እያስተዳደራችሁ ትገኛላችሁ" ብለዋል።

ይሁን እንጂ የክልል እንሁን ጥያቄው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እና ከክልሉ መንግሥት ጋር ተመክሮ ወደ ፌደራል የሚመጣ ጉዳይ ከሆነ ምንም አሳሳቢ የሚሆን አይደለም ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ።

የከፋ ህዝብ ያመነበት ጥያቄ ከሆነ ማንም ሊያስቆመው የሚችለው ጥያቄ አለመሆኑን ጠቅለይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

የቡና ብሔራዊ ሙዚያም

በከፋ ዞን ከዚህ ቀደም በብዙ ወጪ ግንባታው የተከናወነው ብሔራዊ የቡና ሙዚያም እስካሁን ሥራ አለመጀመሩን በመጥቀስ ሙዚየሙ ሥራ እንዲጀምር ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚንስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል።

ያልተነገረለት የኮንሶ ጥያቄ

በሙዚየሙ ጉዳይ ከባህል እና ቱሪዝም ሚንስቴር ጋር እንደሚነጋገሩ ቃል የገቡት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የቡና መገኛ ሥፍራ ጮጬ አይደለም ከፋ ነው የሚል ክርክር ከተነሳ፤ በጉዳዩ ላይ የፖለቲካ እሰጣ ገባ ማምጣት አያስፈልግም ብለዋል። የቡና መገኛ ስፍራ ይሄ ነው ለማለት "እውቀቱም ሆነ አቅሙ የለኝም" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ተመራማሪዎች በጉዳዩ ጥናት ማድረግ ይችላሉ ብለዋል።

የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች

ሌላው ከተሳታፊዎች በብዛት ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል የመሰረተ ልማት ጥያቄ ይጠቀሳል።

በደቡብ ኢትዮጵያ የመንገድ ልማት አነስተኛ መሆኑን በመጥቀስ በዚህ ዓመት መንግሥት አዳዲስ የመንገድ ግንባታዎችን ለማከናወን ከፍተኛ በጀት መመደቡን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ተናግረዋል።

"የተነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ከስር ከስር እየመለሰን እንሄዳለንም" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ። "ከተግባባን ከፋን ማልማት ከባድ አይደለም" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ልማት እና እድገት በትዕግስት እና በድካም ነው የሚገኙት የሚል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።