"በሳዑዲ የደረሰው ጥቃት ውጥረቱን እንዳያባብሰው እንሰጋለን" የኔቶ ኃላፊ

ጥቃት ከደረሰበት የነዳጅ ማቀነባበሪያ የሚወጣ ጭስ Image copyright Reuters

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን አገራት (ኔቶ) ወታደራዊ ጥምረት የበላይ ኃላፊ፤ የሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ የውጥረቱ መጋጋል እጅጉን እንደሚያሳስባቸው ተናገሩ።

ጄንስ ስቶልትነበርግ ኢራን "ቀጠናውን እያመሰችው ነው" ሲሉ ከሰዋል።

ሰኞ ዕለት አሜሪካ የለቀቀችው የሳተላይት ምስሎች፤ እሁድ ኢራን አደረሰችው ተብሎ ጣት የተቀሰረባት "ያልተጠበቀ" ጥቃት ያስከተለውን የጉዳት መጠን አሳይቷል።

ኢራን በፕሬዝዳንቷ ሐሰን ሮሃኒ በኩል የለሁበትም ያለች ሲሆን፤ "በየመን ሕዝቦች የተወሰደ አፀፋዊ እርምጃ" ሲሉ ገልፀውታል።

የምዕራብ ኦሮሚያ ነዋሪዎች ስጋትና ሰቆቃ

በአባይ ግድብ ላይ ለዓመታት የተካሄድው ውይይት ውጤት አላመጣም፡ ግብጽ

ራማፎሳ በሌሎች አፍሪካውያን ላይ በደረሰው ጥቃት ማፈራቸውን ገለፁ

ከኢራን ጋር አብረዋል ተብሎ የሚነገርላቸው የየመን ሁቲ አማፂያን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስደዋል። ነገር ግን አማፂያኑ ያለ ማንም ድጋፍ ይህንን ያህል ጥቃት፣ በዚህ ያህል ትክክለኛነት ያከናውናሉ መባሉ ለአሜሪካ አልተዋጠላትም።

በሳዑዲ የሚመራውና በየመን ከሁቲ አማፂያን ጋር እየተዋጋ የሚገኘው ወታደራዊ ጥምረት ኢራን መሣሪያውን እንደሰጠች ያምናል።

ጄንስ ስቶልትነበርግ "እንዲህ አይነት ለቀጠናው በአጠቃላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለው ጥቃት ዳግመኛ እንዳይደርስ እንድንከላከል ጥሪ እናቀርባለን፤ ውጥረቱ እንዳይባባስም ከፍተኛ ስጋት አለብን" ሲሉ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል በሰጡት ቃለመጠይቅ ወቅት ተናግረዋል።

ሁቲዎች ከዚህ ቀደም በሳዑዲ ምድር የነዳጅ ማምረቻና ማቀነባበሪያ ላይ ጥቃት አድርሰው ያውቃሉ። ነገር ግን ይህ ጥቃት በመጠኑ የገዘፈ እና በዓለማችን ከፍተኛ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ስፍራና ሌላ የነዳጅ ማውጫ ቦታ ላይ የተፈጸመ ነው።

ከዚህ ጥቃት በኋላ የዓለማችን የነዳጅ አቅርቦት 5 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ዋጋውም መጨመር አሳይቷል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንዳሉት፤ ስፍራው ከደረሰበት ጉዳት ተጠግኖ ዳግመኛ ወደ ሥራ እስኪመለስ ሳምንታትን ይጠይቃል።

አሜሪካ ሳዑዲ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደባትም።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ፤ ቅዳሜ ዕለት የሳዑዲ ነዳጅ ማውጫ ተቋማት ላይ ለተሰነዘረው የድሮን ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርገዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በበኩላቸው "ለጥፋቱ ማን ተጠያቂ እንደሆነ ስለምናውቅ አቀባብለን የሳዑዲ መንግሥት ምክረ ሃሰብ ምን እንደሆነ እየጠበቅን ነው" በማለት ወታደራዊ አማራጭ ከግምት ውስጥ እንደገባ አመላክተዋል።

በስም ያልተጠቀሱት የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን ሲናገሩ፤ ዒላማ የተደረጉት 19 ቦታዎች እንደነበሩ እና ጥቃቱ የተሰነዘረው ከምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው፤ ጥቃቶቹ የተነሱባቸው ስፍራዎች በየመን የሁቲ አማጺያን የሚቆጣጠሯቸው ቦታዎች አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ ጨምረው እንደተናገሩት፤ የተገኘው መረጃ ጥቃቱ የተሰነዘረው ከኢራን ወይም ኢራቅ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል ብለዋል።

አሜሪካ ይፋ ያደረገቻቸው የሳተላይት ምስሎች በነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማቱ ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳትም አመላክተዋል።

በሳዑዲ ላይ የተሰነዘሩት የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶች መሆናቸውን እና ሁሉም ዒላማቸውን መምታት አለመቻላቸውን የአሜሪካ የደህንነት ቢሮ መረጃ ጠቁሟል።

'ኤቢሲ' ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣኑን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ፕሬዝደንት ትራምፕ ለጥቃቱ ተጠያቂዋ ኢራን መሆኗን አምነዋል።

የሳዑዲ ባለስልጣናት ጥቃቱ በሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም በማለት የድሮን ጥቃቱ ስላደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ቀርተዋል። ነገር ግን ጥቃቱ የሳዑዲ አረቢያ የድፍድፍ ነዳጅ የማምረት አቅምን በግማሽ መቀነሱ ተረጋግጧል።

ሳዑዲ አረቢያ የዓለማችን ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች ስትሆን በየቀኑ ወደ 7 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ውጪ አገራት ትልካለች።