ያለ ዛፎች መኖር እንችላለን?

ዛፎች Image copyright Getty Images

ዛፎች ለምንኖርባት ምድር ካርቦንን ከማጠራቀም እስከ አፈር ጥበቃ፤ የውሃ ዑደትን ከመቆጣጠር በቀላሉ ጥላ አስከመሆን ድረስ አገልግሎት ይሰጣሉ። የአካባቢያችንንና የሰዎችን የምግብ ስርዓት ይደግፋሉ፤ ለብዙ ሺ እንስሳት መጠለያም ይሆናሉ።

ነገር ግን በሚያስገርም ሁኔታ ስለዛፎች ያለን አመለካከት የተዛባና ጎጂ የሚባል አይነት ነው። በአንድ ዓለማ አቀፍ ተቋም የተሰራ ጥናት እንደሚጠቁመው የሰው ልጅ እርሻ ከጀመረበት ከዛሬ 12ሺ ዓመታት በፊት በምድር ላይ ከነበሩት ዛፎች ግማሾቹ ወይም 5.8 ትሪሊየን የሚሆኑት ተጨፍጭፈዋል።

ወደ ጫካነት የተቀየረው ስታዲየም

የማዉ ጫካን ለማዳን 60 ሺ ኬንያውያን ከመኖሪያቸው ተባረሩ

ኢንደስትሪያል አብዮት ከተጀመረ ወዲህ ደግሞ የዓለማችን 32 በመቶ የሚሆነው የዛፍ ሽፋን ጠፍቷል። በተለይ ደግሞ በምድር ወገብ አካባቢ ከሚገኙ ዛፎች መካከል በየዓመቱ 15 ቢሊየን የሚሆኑት ይቆረጣሉ።

እያንዳንዱን በዓለማችን ላይ የሚገኙትን ዛፎች ሁሉ ጨፍጭፈን ብንጨርሳቸው ምን የሚፈጠር ይመስላችኋል?

በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌልስ የኢንቫይሮመንታል ዳታ መምህር የሆኑት ኢዛቤል ሮዛ እንደሚሉት ሁሉም ዛፎች ከምድረ ገጽ ቢጠፉ የሰው ልጅ ህይወቱን ማስቀጠል በእጅጉ ከባድ ይሆንበታል።

''ምድርም የሰውን ልጅ ፍላጎቶች ማሟላት ያቅታታል'' ይላሉ።

ምድር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ በረሃነት ትቀየራለች። ድርቅና ረሃብ ደግሞ ተከትለው የሚመጡ ክስተቶች ይሆናሉ። እንደው ምናልባት ዝናብ ቢመጣ እንኳን ውሃውን የሚቋጥሩ ዛፎች ባለመኖራቸው በጎርፍ እንጥለቀለቃለን።

ከዚህ ባለፈ ምድር ከዛፎች ውጪ ስትሆን ለውቅያኖሶች መስፋፋት ትልቅ እድል ይፈጥራል። ምድርም ቀስ በቀስ ጨዋማ በሆነው የባህር ውህ እየተሞላች ትመጣለች።

ዛፎች ካርቦንን በቅጠሎቻቸው አምቀው በመያዝና ከአባቢያቸው ደግሞ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን በማስወገድ በአየር ጸባይ ለውጥ ከሚመጣው ከፍተኛ ሙቀት ይጠብቁናል።

Image copyright Getty Images

የደን ምንጣሮ እስካሁን በዓለማችን ላይ እየጨመረ ለመጣው የካርቦን ልቀት 13 በመቶ አስተዋጽኦ አድርጓል። ዛፎች ከምድራችን ጠፍተው ሲያልቁ ደግሞ ወደ ከባቢ አየር ስንለቀው የነበረው የካርቦን መጠን ከእጥፍ በላይ ጨምሮ 450 ጊጋቶን ካርቦን ወደ ምንተነፍስው አየር ውስጥ ይለቀቃል።

ከዚህ ባለፈ ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን ወደ ውሃ አካላትም ጭምር ስለሚገባ በባህርና ውቂያኖሶች ውስጥ ያሉት እንስሳት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ይጠፋሉ። በዚህ ምክንያት የአሳ ምርት ቆመ ማለት ነው፤ አንድ የምግብ ምንጫችን በአጭሩ ተቀጨ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ዛፍ መትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ይረዳል?

የመጨረሻውና እጅግ አስፈሪው የሚባለው የምድር ሙቀት ከፍተኛ የመሆን ደረጃ ላይ እንኳን ሳንደርስ በቢሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችና እንስሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሞተው ያልቃሉ።

በአሜሪካ የሚገኙ ተመራማሪዎች በሰሩት ጥናት መሰረት በአሜሪካ ብቻ ዛፎች 17.4 ሚሊየን ቶን የተበከለ አየር የሚያስወግዱ ሲሆን በገንዘብ ቢተመን እስከ 6.8 ቢሊየን ዶላር ወጪ ሊያስደርግ ይችላል።

ከጤና ጋር በተያያዘ ደግሞ እንደ ኢቦላ፣ ኒፓ ቫይረስ እና ወባ ያሉ በሽታዎች በቀላሉ ተስፋፍተው የሰው ልጅን ህይወት አጭር ያደርጉታል። በተጨማሪም እስከዛሬ አይተናቸው የማናውቃቸውና ገና መድሃኒት ያልተገኘላቸው ብዙ ወረርሽኞች ትልቅ ፈተና መሆናቸው አይቀርም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ