የራይድና የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ውዝግብ

የራይድ ታክሲዎች Image copyright RIDE

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ ስምሪትን በተመለከተ ያወጣው መመሪያ እንደ ራይድ ካሉ በቴክኖሎጂ ታግዘው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ቅሬታ አስነስቷል።

በመመሪያው ከተካተቱ ነጥቦች አንዱ የሆነውና ሰሌዳቸው ኮድ 3 የሆኑ ተሽከርካሪዎች የኪራይ አገልግሎት ፍቃድ ካላወጡ በስተቀር የመጓጓዣ አገልግሎት መስጠት አይችሉም የሚለው የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በመመሪያው፤ በዘርፉ የታክሲ አገልግሎት ለመስጠት የሚሰማሩ አሽከርካሪዎች ሰሌዳቸውን ወደ ኮድ 1 እንዲቀይሩ እንዲሁም መኪናቸውን ቀለም እንዲቀቡ ተወስኗል። በተጨማሪም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አካላት በድርጅት መታቀፍ አለባቸው ተብሏል።

በተለይም እንደ ራይድ ያሉና በቴክኖሎጂ በመታገዝ አሽከርካሪዎችና ተጓጓዦችን የሚያገናኙ ድርጅቶች መመሪያው ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ከሰሌዳ ቁጥር ጋር የተያያዘ ብቻ አይደለም።

«ሰው ሲበሳጭ ማስታወሻ እይዝ ነበር» አዲስ ዓለማየሁ

አረጋውያንን በነጻ የሚያሳፍረው ባለታክሲ

የፍቃድ ጥያቄ

የራይድ ሥራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ እንደምትናገረው፤ ራይድ ከአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ ፍቃድ እንዲያወጣ ተጠይቋል። ራይድ ከቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚንስትር ፍቃድ አውጥቶ አገልግሎት እየሰጠ ሳለ፤ በድጋሚ ፍቃድ እንዲያወጣ መጠየቅ ለምን አስፈለገ? ስትል ትጠይቃለች።

ሳምራዊት፤ "የምንሠራው በቴክኖሎጂ ዘርፍ ፍቃድ አውጥተን ነው። ፍቃድ እያለን ተጨማሪ ፍቃድ ማውጣት ለምን አስፈለገ?" በማለት ቅሬታዋን ትገልጻለች።

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚንስትር ፍቃድ የመስጠት ስልጣን የለውም ይላሉ።

ሚንስትሩ እውቅና መስጠት የሚችለው ለመተግበሪያው ብቻ እንደሆነም ያክላሉ። "ፈጠራው የራሳቸው ከሆነ ፓተንት ይሰጣቸዋል እንጂ የንግድ ፈቃድ አይሰጣቸውም" ሲሉ ያብራራሉ።

ኃላፊው እንደሚሉት፤ በኤሌክትሮኒክ የታክሲ ስምሪት (ኤታስ) ዘርፍ ሰሌዳቸው ኮድ 1 ከሆኑ መኪናች ጋር ለመሥራ ከትራንስፖርት ቢሮው ጋር ውል መግባት ግዴታ ነው።

አንድ አሽከርካሪ ኮድ 1 ለመውሰድ ጥያቄ ሲያቀርብ፤ ቢሮው የሚያቀርበው ቅድመ ሁኔታ አሽከርካሪው ራይድን ከመሰሉ የኤታስ ድርጅቶች ጋር እንዲዋዋል ነው። ሰሌዳ የሚሰጠው፤ ቢሮው ከመዘገባቸው የኤታስ ድርጅቶች ጋር ለሚዋዋል አሽከርካሪ ብቻ እንደሆነም ያስረዳሉ።

"ኮድ 1 እየሰጠን ያለነው ለመከታተልም እንድንችል ነው። የኤታስ ድርጅቶች ከኛ ጋር ውል የሚገቡት፤ በኔ ስም ተመዝግበው ኮድ 1 የሚወስዱትን ለመከታተል እንድትችሉ፣ ሲስተሙን ማየት እንድትችሉ እንፈቅድላችኋለን እንዲሉ ነው። ውል አልገባም ያለ ገበያውን ያጣል" ሲሉም ይገልጻሉ።

የዳታ ቤዝ ጥያቄ

ሳምራዊት የምታነሳው ሌላው ጥያቄ፤ ራይድ ዳታ ቤዙን ለትራንስፖርት ቢሮ ይስጥ፤ የሲስተሙን መነሻም ኢትዮጵያ ያድርግ መባሉ ላይ ነው።

ራይድ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት፤ ታክሲ ስለጠራው ሰው ማንነት፣ ስለታክሲው አሽከርካሪ፣ ጉዞው ከየት ወደየት እንደተካሄደ የሚገልጸው መረጃ የሚከማችበት የመረጃ ቋት መነሻው አሜሪካ ነው።

ሳምራዊት እንደምትለው፤ የዚህን ሲስተም መነሻ ኢትዮጵያ ማድረግ አለባችሁ ተብለዋል።

"ሲስተሙ ከአሜሪካ እንዲሆን የተደረገው ኢትዮጵያ ውስጥ ምቹ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስለሌለ ነው" የምትለው ሳምራዊት፤ ሲስተሙ ወደኢትዮጵያ ከተዘዋወረ በሚፈለገው ጥራት አገልግሎት ለመስጠት እንደማይቻል ታስረዳለች።

የራይድ የጥሪ ማዕከል የሚገኘው ኢትዮጵያ እንደሆነና የኔትወርክ መቆራረጥ ሥራቸው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ትናገራለች። የጥሪ ማዕከሉ የገጠመውን መሰናክል እንደማሳያ በመውሰድ፤ የድርጅቱን ሲስተም ወደ ኢትዮጵያ ማዘዋወር አዋጭ አለመሆኑንም ትገልጻለች።

ድርጅቱ አሁንም በኔትወርክ መቆራረጥ፣ የመብራት መጥፋትና መሰል ችግሮች እየተፈተነ መሆኑን በመጥቀስ፤ የአገሪቱ መሰረተ ልማት ሳይሻሻል ሲስተሙ ይምጣ ማለት እንደማይቻልም ታክላለች።

ሳምራዊት አያይዛም፤ ራይድን የሚጠቀሙ ሰዎችን ግላዊ መረጃ የያዘውን ዳታ ቤዝ ለትራንስፖርት ቢሮ እንደማይሰጡም ትናገራለች። ራይድ የግል ድርጅት እንደመሆኑ ይህን መረጃ ለሦስተኛ ወገን አስተላልፎ እንዲሰጥ የሚያስገድደው አሠራር አለመኖሩንም ታነሳለች።

"ሰዎች ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ መረጃውን ለሦስተኛ ወገን እንደማንሰጥባቸው አምነው ነው። እኛ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ነው የምንፈልገው። ለምን የግለሰብ ሚስጥር አሳልፈን እንሰጣለን? ሪፖርት ከጠየቁን እንሰጣለን እንጂ ዳታቤዝ አንሰጥም" ስትል ታብራራለች።

መረጃው አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ የፍርድ ቤት ማዘዣ ይዞ፣ ራይድ መረጃውን ይፋ እንዲያደርግ መጠየቅ እንደሚቻል ትናገራለች።

ሰለሞን (ዶ/ር) በተቃራኒው፤ "ዳታ ቤዝ ለኛ ስጡን አላልንም። መመሪያው ዳታ ቤዙ ኢትዮጵያ ውስጥ ይሁን ነው የሚለው። ስለ ግለሰቦች ያለው መረጃ ከኢትዮጵያ ውጪ እንዳይወጣ ነው ያልነው" ይላሉ።

ከአንድ ቦታ ወደሌላው የሚዘዋወር ግለሰብ ማንነት እንዲሁም እንቅስቃሴውም ከኢትዮጵያ ውጪ ከወጣ፤ የግለሰቡን ደህንነት አደጋ ውስጥ ሊከት እንደሚችል ኃላፊው ይገልጻሉ። እሳቸው መረጃው ያላግባብ ሊደርሰው ይችላል ብለው የሚሰጉት ከኢትዮጵያ ውጪ ያለ ኃይልን መሆኑንም ያስረዳሉ።

ዳታ ቤዙ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን የሚያዘው አሁን የወጣው መመሪያ ሳይሆን፤ የአገሪቱ የመረጃ ደህንነት አዋጅ እንደሆነ ገልጸው፤ ዳታ ቤዙ ውጪ አገር ከሚሆን ይልቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆን ደህንነቱ የበለጠ አስተማማኝ እንደሚሆን ያክላሉ።

ይህ ዳታ ቤዝ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጣ በኋላ፤ በድርጅቱ ምርጫ መሰረት በድርጅቱ ስር አልያም በኢትዮ-ቴሌኮም ስር ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

በራይድ በኩል የሚነሳው የአገሪቱ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት አመርቂ አለመሆን ኃላፊው የሚቀበሉት መከራከርያ ነጥብ አይደለም። አሁን ባለው የቴክኖሎጂ ዝርጋታ ድርጅቱ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ በማጣቀስ፤ ዳታ ቤዝ ወደ አገር ውስጥ ላለማምጣት ምክንያት አይሆንም ይላሉ።

ተፈራ ነጋሽ፡ "በነገራችን ላይ ሙዚቃ አልተውኩም"

'ኡበር' በለንደን ከተማ የሥራ ፈቃድ ተከለከለ

በተደጋጋሚ የተነሳው ውዝግብ

ራይድና የትራንስፖርት ቢሮው ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ይህ የመጀመሪው አይደለም። ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ከንቲባ ታከለ ኡማ ጣልቃ ከገቡ በኋላ የረገበ እሰጣ ገባ ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ ራይድ አገልግሎት እንዳይሰጥ ተደርጎ፤ ለቀናት ሥራ አቋርጠው ነበር።

የራይድ አሽከርካሪዎች በተለይም ከላዳ ታክሲ አሽከርካሪዎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸውም የሚዘነጋ አይደለም። የላዳ አሽከርካሪዎች ራይድ "ቢዝነሳችንን እየወሰደው ነው" በሚል የራይድ አሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት እስከማድረስና መኪና እስከመስበር መድረሳቸውን ሳምራዊት ትናገራለች።

ውዝግቦቹን ተከትሎ "IStandWithRide"[ከራይድ ጎን እቆማለሁ ወይም ራይድን እደግፋለሁ] የተባለ የማኅበራዊ ሚድያ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። ራይድን ከተጠቃሚዎች ደህንነት መጠበቅ አንጻር በበጎ የሚያነሱ ግለሰቦች ድርጅቱን እንደሚደግፉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገልጸዋል።

ሳምራዊት፤ ራይድ በሜትር ታክሲ፣ በጥሪ ማዕከሉና በተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ትናገራለች ። ሆኖም ግን በቅርቡ ይፋ የተደረገው መመሪያ ሲወጣ ቢሮው ከራይድ ጋር ውይይት አለማድረጉን ትገልጻለች።

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ራይድ ብቻ ሳይሆን፣ ዛይ ራይድ፣ ፒክ ፒክ፣ ዘ ሉሲና ሌሎችም የኤሌክትሮኒክ የታክሲ ስምሪት ተቋሞች መመሪያው ከመውጣቱ በፊት ለውይይት የተጋበዙ ሲሆን፤ መድረኩ ላይ የትኛውም ድርጀት ተቃውሞ አላሰማም ነበር።

አዲስ የመጡትና ቴክኖሎጂን መሰረት በማድርግ አገልግሎት የሚሰጡት ድርጅቶች መቀጨጭ የለባቸውም የሚሉት ኃላፊው፤ መመሪያው የአሠራር ሂደቱን የሚያቃና እንጂ የሚያደናቅፍ አለመሆኑን ያስረግጣሉ።