"የማራቶን ሯጮቹ ላይ የተላለፈው እገዳ አይደለም" ዱቤ ጂሎ

ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ ሰለሞን ባረጋና ዱቤ ጂሎ
አጭር የምስል መግለጫ ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ ሰለሞን ባረጋና ዱቤ ጂሎ

የኢትዮጵያ የማራቶን ውድድር ሯጮች ላይ ምንም አይነት የእገዳ ውሳኔ እንዳልተላለፈ ከአትሌቶቹ ጋር ካታር የሚገኙት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክትር ዱቤ ጂሎ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በካታር ዶሃ እየተካሄደ ባለው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በማራቶን ውድድር ላይ የተሳተፉት አትሌቶች ለቀጣዮቹ ሦስት ወራት እረፍት አድርገው እንዲያገግሙ እንጂ እገዳ አለመሆኑን ገልጸዋል።

ቀነኒሳ 'ከሞት እንደመነሳት' ነው ባለው ሁኔታ ማራቶንን አሸነፈ

በዶሃ የሴቶች ማራቶን ሦስት ኢትዮጵያውያን ሯጮች አቋርጠው ወጡ

ውሳኔው ከ42 ኪሎሜትሮች በላይ በሚሮጥበት ከባድ በሚባለው የማራቶን ውድድር ላይ የሚሳተፉ ሯጮችን ጤንነትና ደህንነት ለመጠበቅ የሚወሰድ ተቀባይነት ያለው እረፍት ነው ብለዋል ዱቤ ጅሎ።

አትሌቶች የሦስት ወራት የማገገሚያ ጊዜ እንዲያገኙ ማድረግ በዓለም አቀፍ የውድድር ሕግና ደንብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውና በሌሎችም ሃገራት የሚሰራበት እንደሆነ አመልክተዋል።

ለሦስት ወራት ከውድድር እርቆ የሚወሰደው እረፍት ሁሉንም በማራቶን ውድድር የተሳተፉ አትሌቶችን የሚመለከት መሆኑን የጠቀሱት የቴክኒክ ዳይሬክተሩ፤ በተለይ በዶሃ ያለው ከባድ ሙቀት ላይ ለተወዳደሩ አትሌቶች እረፍቱ በጣም አስፈላጊያቸው ነው ብለዋል ለቢቢሲ።

ባለፈው አርብ ሌሊት በተካሄደው የሴቶች ማራቶን ላይ ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያዊያን ሯጮች በነበረው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ውድድሩን አቋርጠው መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ በርካቶችም ለማቋረጥ ተገደው ነበር።

''በኳታር የኢትዮጵያ ቡድን በሙቀቱ ተቸግሯል'' የቡድኑ መሪ

የሞ ፋራህ የቀድሞ አሠልጣኝ ከአትሌቲክስ ታገዱ

ስለዚህም የማራቶን ሯጮቹ ከነበሩበት ከባድ ሁኔታ እንዲያገግሙ በፌዴሬሽኑ ደንብ መሰረት ለሦስት ወራት ልምምድ እየሰሩ እረፍት እንዲያደርጉና ከውድድር እንዲርቁ መደረጉን አመልክተዋል።

በሴቶቹ የማራቶን ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩትና አቋርጠው ለመውጣት የተገደዱት ሯጮች የጤንነት ሁኔታን በተመለከተ በስፍራው የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ዱቤ ጅሎን ጠይቆ ባገኘው መረጃ መሰረት አንዷ ከገጠማት ቀላል ችግር በስተቀር ሁሉም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ታውቋዋል።

በዶሃ ባለው ከባድ ሙቀት ምክንያት በእኩለ ሌሊት ጎዳና ላይ በሚደረጉት የማራቶንና የእርምጃ ውድድሮች ተሳታፊዎች ላይ ከባድ ጫናን የሚያሳድር እንደሆነ የተናገሩት የቴክኒክ ዳይሬክተሩ ስታዲየም ውስጥ የሚደረገው ግን ብዙም አስቸጋሪ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች