ከ57 ዓመታት በኋላ የተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ምን አዲስ ነገር ይዟል?

የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ Image copyright Getty Images

የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሻሻያ ቢደረግበትም፤ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህጉ ግን ምንም አይነት መሻሻያ ሳይደረግበት 57 አመታትን አስቆጥሯል። በቅርቡም ይህ ከአምስት አስርት አመታት በላይ ያስቆጠረው የሥነ ሥርዓት ህጉ ተሻሽሎ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተመርቷል። የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ህግ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ረቂቅን ለማዘጋጀት አስራ አምስት አመት እንደወሰደ በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል።

ከአምሳ አመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሊሻሻል ነው። ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው?

የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሥርዓት ህጉ የተደነገጉ የወንጀል ድንጋጌዎችን ማስፈጸሚያ መሣሪያዎች ናቸው። ከምርመራ ጀምሮ እስከ ፍርድ ማስፈጸም ወይም ታራሚዎችን እስከማረምና ማነጽ ያለውን ሂደት ይመራሉ። ምርመራ እንዴት ይጀመራል? የተጠርጣሪዎች መብት ምንድን ነው? ከዋስትና ጋር ተያይዞ ያለው ነገር ምንድን ነው? ፖሊስ ማድረግ የሚችለው ምንድን ነው? የሚሉ ዝርዝር ነገሮችን የሚመሩት በሥነ ሥርዓት ሕጎች ነው።

“ኢትዮጵያ አዲስ የጥላቻ ንግግር ህግ አያስፈልጋትም” አቶ አብዱ አሊ ሂጂራ

"ፍቅር እስከ መቃብርን አልረሳውም" ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም

በ1954 ዓ. ም. የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ማሻሻል ያስፈለገባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። በ1949 ዓ. ም. ወጥቶ የነበረው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በ1996 ዓ. ም. ተሻሽሏል።

የ1954 ዓ. ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ በ1949 ዓ. ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አይነት ሥርዓት ያለው ከሆነ፤ የ1949ኙ ሕግ ከተሻሻለ የግድ የ1954ቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ መሻሻል ይኖርበታል ማለት ነው። ስለዚህ አንዱ ምክንያት ይሄ ነው።

ሁለተኛው ምክንያት የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ሲረቀቅ አገራችን አሁን ያላትን ቅርጽ የያዘች አልነበረችም። ያን ጊዜ የነበረው አሃዳዊ ሥርዓት ነው። ፌደራላዊ ሥርዓት አልነበረም። ስልጣን በክልልና በፌደራል መንግሥቶች የተከፋፈለ አልነበረም፤ ስለዚህ ሕጉ ሲረቀቅ አሀዳዊ ሥርዓትን ታሳቢ ያደረገ ነው።

አሃዳዊ ሥርዓትን ታሳቢ ያደረገ ከመሆኑ አንፃር አሁን የፌደራል ሥርዓት ሲደራጅ፤ የፌደራል መንግሥቱ ሥልጣን ምንድን ነው? የክልሎች ሥልጣን ምንድን ነው? የሚለውና የፍርድ ቤቶቻችን አደረጃጀት በ1954 ዓ. ም. እንደነበረው አይደለም። ያን ጊዜ አውራጃ፣ ወረዳ የሚባል አደረጃጀት ነው የነበረው።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ ፍርድ ቤቶች አሉ። የነዚህ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ምንድን ነው? ከዚህም በተጨማሪ የክልልና የፌደራል መንግሥት ሥልጣን ምን መሆን አለበት የሚለው መሰረታዊ ለውጥ ይፈልጋል።

ከዛ ውጪ አሁን ከደረስንበት የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት አንጻር፣ ከደረስንበት ዘመናዊ ዓለም አንጻር በ1954ቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ውስጥ ያልተካተቱ አዳዲስ መሰረታዊ ፅንፀ ጽንሰ ሀሳቦች መካተትና መሻሻል ስለነበረባቸው ነው።

የጤፍ ቢራ አሜሪካ ውስጥ ገበያ ላይ ዋለ

ምን ያህል አዳዲስ ሕጎች ናቸው የተጨመሩት? ምን ያህሉስ ተሻሽለዋል? ጥፋተነት ድርድሩንም እስቲ ዘርዘር አድርገው ንገሩኝ?

አጠቃላይ የተሻሻለው ሕግ ምን ያህል ነው የሚለውን ብዙ ነው እዚህ መዘርዘር ትንሽ አስቸጋሪ ይሆናል። ረቂቅ ህጉን ከሰራን በኋላ ሕግ አውጪውም ሌላውም አካል እንዲረዳው በሚል ሠንጠረዥ አዘጋጅተናል። በዚህም መሰረት አንደኛ ከነባሩ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ እንዳሉ የተወሰዱ ድንጋጌዎች፤ ነባሩ ወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ የነበሩና ግን በተወሰነ መልኩ ተሻሽለው ወይም ደግሞ አገላለፃቸው፣ ሃሳባቸው ተስተካክሎ የገቡና አዳዲስ የመጡ ፅንሰ ሀሳቦች (ድንጋጌዎች) ይዟል።

ብዙ አዳዲስ ፅንሰሃሳቦች ገብተዋል፤ ለምሳሌም ያህል አንዱ የጥፋተኝነት ድርድር (Plea bargain) ነው። አቃቤ ሕግና ተከሳሽ የሚደራደሩበትና በብዙ አገሮች ለምሳሌ በአሜሪካ፣ በካናዳ = ተግባራዊ የሚደረግ ሥርዓት ነው

ለምሳሌ 15፣ 20 ክሶች የሚመሰረቱባቸው ተከሳሾች አሉ እነርሱ ጋር አቃቤ ሕግ ሊደራደር ይችላል። በዚህም መሰረት ይህን ያክል ወንጀል ፈፅመኻል፤ በዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ማስረጃ አለኝ። ይህንን ይዘን ወደ ፍርድ ቤት ብንሄድ ክርክሩ እና የፍርድ ቤት ውጣ ውረዱ ብዙ ዓመት ይፈጃል፤ ማስረጃ ማሰማቱ እና ሌሎች ሌሎችም። ስለዚህ የቀረቡብህ ማስረጃዎችንና መሰል ጉዳዮችን እይና የምታምነው አለ ወይ? ካመንክ ከዚህ ውስጥ፣ ለምሳሌ በ15 ክስ የሚከሰስ ተከሳሽ ከሆነ፣ አምስቱን ክስ እተውልህና በአስር ብቻ እከስሃለሁ ሊለው ይችላል።

ጥፋትህ ተደምሮ ተቀንሶ ይህን ያህል ዓመት የሚያስቀጣ ነው። ነገር ግን ይህን ያህል ዓመት እንድትቀጣ ልንስማማ እንችላለን ብሎ ይደራደራል ማለት ነው። ስለዚህ አንድ ዓመት ሁለት ዓመት የሚፈጅ ጉዳይ በአንድ ቀን ያልቃል ማለት ነው።ፍርድ ቤት ስምምነታቸውን ሲያፀድቅ ወዲያውኑ ቅጣት ይፈፀማል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያላት አገር ከመሆኗ አንፃር ለዘመናት ወንጀልን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን መፍትሔ የሚሰጡባቸው የራሳቸው ሥርዓቶች አሏቸው። እነዚህ ባህላዊ ሥርዓቶች መደበኛ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ከሚሰጠው የተሻለ እልባት መስጠት የሚችሉ ከሆነ ባህላዊ ስርዓቶች እውቅና መስጠት ያስፈልጋል። ባህላዊ ስርአቶችም ተካትተዋል።

እስካሁን ሲሰራበት የነበረው ተጠርጣሪ ይያዛል፣ ምርመራ ይደረጋል፣ ፍርድ ቤት ይሄዳል፣ ይቀጣል፣ ማረሚያ ቤት ይሄዳል፤ አማራጭ መፍትሄ የሚባል አልነበረም።

ነገር ግን ሱስ ውስጥ ያሉ፣ የአዕምሮ ችግሮች ያሉባቸውና እንዲሁም ለሌሎች ብዙ አደጋዎች የተጋረጡ ግለሰቦች አሉ። እነዚህን ግለሰቦች ማረሚያ ከመላክ ይልቅ ሌሎች አማራጭ መንገዶችን ወደ ማገገሚያ ወይንም በማህበራዊ ግንባታ ውስጥ አስተዋፅአ የሚያደርጉበት መንገድ በረቂቁ ውስጥ ተካቷል። ይህ አሰራር በተለያዩ ሃገራት ይጠቀሙበታል።

ከዚህም በተጨማሪ አሁን ያለው የዕርቅ አሰራር የሚያሻሽል የመንግሥት ጥቅም የሌለባቸውን እስከ 3 አመት በሚደርስ ቀላል እስራት በሚያስቀጡ የወንጀል ጉዳዮች ላይ በሙሉ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የማሻሻያ ሀሳብ ቀርቧል፡፡ እርቅ ማስጨረስ ቢቻል የተሻለ ውጤት መምጣት እንደሚችል በተግባር አይተነዋል።

የመጨረሻ ፍርድን (ብይንን) እንደገና ስለማየት ፤ አሁን ባለው የፍትህ ስርአት ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ የሰጠው ውሳኔ መሆኑ በተጨባጭ ቢረጋጋጥ፤ ለምሳሌ ሰው ሞቷል ተብሎ በግድያ ሰዎች ከተፈረደባቸው በኋላ ሞተ የተባለው ሰው በአካል ቢመጣ ፍርድ ቤቱ ያንን ጉዳይ መልሶ የሚያይበት ስርዓት የለም። ውሳኔውን ለማስቀልበስ በይግባኝ ነው መሄድ ያለበት፤ አንዳንዴ ይግባኝ ሊያልፍ ይችላል። የተፈረደበት ግለሰብ ከእስር ሊወጣበት የሚችል ምንም አይነት አሰራር የለም። በሌሎች ሀገሮች ግን የዳበረ ፅንሰ ሀሳብ አለ። የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድን እንደገና ማየት የምንለው ማለት ነው።

ሌላኛው የሞት ፍርድ አፈፃፀምን በተመለከተ ነው። በረቂቁ መሰረት ውሳኔ ከተሰጠ ጀምሮ ከተቀመጠለት ከሁለት አመት በላይ ከቆየ ወደ እድሜ ልክ ጽኑ እስራት ይቀየራል። ከዚያ ውጪ በእኛ ሀገር የሞት ቅጣት አፈፃፀም ተፈርዶባቸው 20 ዓመት ለ15 ዓመት አስር አመታት ያለምንም ውሳኔ የተቀመጡ ሰዎች አሉ።

ኢትዮጵያውያን 'የሌሉበት' ስለ ኢትዮጵያ የሚዘክረው ሬድ ሲ ዳይቪንግ ሪዞርት ፊልም

መቆየታቸው ጥሩ ቢሆንም፣ አንዳንዴ ግን ሳይኮለጂካል ቶርቸርም [የስነልቦና ስቃይ] ነው። ከአሁን አሁን ተፈፀመብኝ እያለ ሲሰጋ ይኖራል። መፈፀሙ የሚመረጥ ላይሆን ይችላል። ግን የሆነ መፍትሔ ሊኖረው ይገባል። በረቂቁ ያስቀመጥነው ወደ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት መቀየር ትልቅ 'ፓራዳይም ሺፍት' [ለውጥ] ነው ይኼ።

ከዚህ በተጨማሪ አሁን ባለው አሰራር ሞት ቅጣት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከፈረደ እና ለምሳሌ ግለሰቡ ይግባኝ ካልጠየቀ እንደሚፈፀም ነው። ይህ ደግሞ በጣም አደገኛ አካሄድ ነው።

በርግጥ እኛ ብዙም እየፈፀምን ስላልሆነ አሁን ስጋት ላይ ላይከተን ይችላል። ግን ከሞተ በኋላ ሰውየው ተመልሶ ስለማይመጣ የተፈረደበት ግለሰብ ራሱ የይግባኝ ባይጠይቅ ፍርድ ቤቱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው መላክ ያለበት ብለን አካትተናል። የግድ በይግባኝ መታየት አለበት። በአምስተኛ ወይንም በሰባተኛ ተሰይሞ ማፅደቅ አልያም መሻር አለባቸው።

የባህላዊ ስርዓቶችን በምን መንገድ ነው የተካተቱት?

የባህላዊ ስርዓቶች ለምሳሌ አፋር ክልል ላይ ብንሄድ የግድያ ወንጀል ቢፈፀም የሟች ዘመዶችና የገዳይ ዘመዶች ቁጭ ብለው የሚነጋገሩበት፣ የሚካካሱበትና የመጨረሻውን ዕልባት የሚሰጡበት ስርዓት አላቸው። የገዳ ስርዓትም እንዲሁ ለምሳሌ የወንጀል ጉዳዮች ላይ ራሱ እልባት ይሰጣል። ወደ ወሎ አካባቢ፣ ደቡብ ውስጥ ብንሔድ ትልልቅ ጉዳዮችን ዕልባት የሚሰጡባቸው ስርዓቶች አሏቸው። የወንጀል ጉዳይን ጨምሮ ማለት ነው።

ስለዚህ ባሕላዊ ስርዓቶች ስንል የዳበሩ ባህላዊ ስርዓቶችን ዕውቅና መስጠት ነው። እዚህ ጋር ጥንቃቄ የሚደረጉባቸው የሉም ማለት አይደለም። አንዳንዶቹ ስርዓቶች ሰብዓዊ መብትን የሚጥሱ፣ ለምሳሌ አንዳንድ ቦታ ላይ ስናይ ባልና ሚስት ተጣልተው ሲያስታርቁ 'ምንም አትናገሪ፣ ዝምብለሽ ተስማምተሽ ቤትሽ ግቢ' የሚል ዓይነት ወደ አንድ ጎን ያጋደለ ሽምግልና አለ። ይህ ትክክለኛ ያልሆነኛ የሴቶች መብትን የሚጎዳና ሰብዓዊ መብትንም የሚጥስ ነው።

ይህ ሲከናወን ከጥንቃቄ ጋር ነው፤ በባህላዊ ስርዓቶች የማይታዩ ወንጀሎችም አሉ።

ረቂቅ ሕጉ ከዚህ በፊት ይነሱበት የነበሩ ለምሳሌ ከተጠርጣሪዎች አያያዝ እንዲሁም ተደጋጋሚ ቀጠሮዎችና የመሳሳሉ ቅሬታዎችን ይደፍናል?

አዎ በደንብ አድርጎ ክፍቱን ይሞላል። በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓቱ ላይ ግን ከዋስትና ጋር ተያይዞ፣ ከጊዜ ቀጠሮ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ሰብዓዊ መብትን የሚጥሱ ድንጋጌዎች አሉ።

ባልተለመደ ሁኔታ በተደጋጋሚ አስራ አራት ቀን በማለት ፖሊስ ምርመራየን አልጨረስኩም እያለ በርካታ ጊዜ እንደሚገፋ ነው በተግባር እየታየ ያለው። በዚህ አሰራርም ለአመታት የሚቆይ ምርመራ አለ።

አስራ አራት ቀን ለምን ያክል ጊዜ? መጨረሻ ገደብ ሊኖረው ይገባል፤ ሰብዓዊ መብትን ይጥሳል። ያው በረቂቅ ደረጃ ነው ያለው የሚሰጠው ጊዜ ቀጠሮ ለቀላልና ለከባድ ሊለያይ ይችላል። በረቂቁ የተካተተው ለከባድ ወንጀል አራት ወራት ብለናል። በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ካልጨረሰ ፍርድ ቤት 'አውቶማቲካሊ' [ወዲያውኑ] ተጠርጣሪውን ይለቅቀዋል ነው የሚለው። የተያዘ ንብረትም ካለ ይለቀቃል። ቶሎ ለፖሊስ ክስ እንዲመሰርት ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል ካልሆነ ግን ይለቅቀዋል።

ሌላኛው የዋስትና መብትን በተመለከተ ነው። የድሮው አሻሚ ነው በአሁኑ ግን ግልፅ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በመርህ ደረጃ ሰው በዋስትና መለቀቅ ነው ያለበት። በልዩ ሁኔታ በጣም ውስን ከሆኑ ጉዳዮች በስተቀር ህገ መንግሥቱም ሆነ አለም አቀፍ የመብትና የህግ ማዕቀፎች ይህንን መብት ሰጥተዋል።

የተረቀቀው ሕግ ከስያሜው ጀምሮ ከዚህ ቀደሙ ይለያል። የአሁኑ ሕግ ስያሜው 'የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዐትና የማስረጃ ሕግ' ሲሆን በይዘትም ደረጃ የማስረጃ ጉዳዮችንም አካትቶ ይዟል። ይህ ትልቅ ለውጥ ነው። ከዚህ ቀደም ማስረጃን በተመለከተ የተደራጀ ህግና ዝርዝር ሁኔታዎች አልነበሩም። በአሁኑ ግን ማስረጃ ሆነው የሚቀርቡት ምንድን ናቸው? ተቀባይነት ያለው መረጃ፣ የኤሌክትሮኒክስ ማስረጃና የመሳሰሉት ላይ ዝርዝር ጉዳይ በረቂቁ ተቀምጧል። ስለዚህ እነዚህን ክፍተቶች ይሞላል።

“ጭኮ እወዳለሁ” ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

ሥነርዓት ህጉን ለማሻሻልለምንድን ነው ይህን ያህል ጊዜ የወሰደው?

እኛ አሁን አሻሽለን እያቀረብን ነው ስንል፤ እኛ አሁን ተነስተን ያረቀቅነው ሕግ አይደለም። ከዚህ በፊትም በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች አሉ። የማርቀቅ ስራው የቆየ ስራ ነው ወደ አስራ አምስት አመታትም ወስዶበታል።

ዛሬ ሲባል፣ ነገ ሲባል፣ ይጀመራል እንደገና ይተዋል፣ በባለቤትነት መንፈስ በአግባቡ ይኼ መጠናቀቅ አለበት በሚል ስሜት የራሱ የሆነ ባለሙያ ተመድቦለት እንደ ተቋምም የሞት የሽረት ጉዳይ ነው ተብሎ በባለቤትነት ስላልተያዘ ይመስለኛል።

ዞሮ ዞሮ ግን እንደ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ይህንን ሕግ አርቅቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቀረብን ስንል ከዚያ ጀምሮ የነበሩትን ግብዓቶች እየወሰድን እያሻሻልን፣ እየጨመርን፣ እየቀነስን ነው፤ የዛ ሁሉ ውጤት ነው።

ተግባራዊም ለማድረግ ጊዜ ይወስዳል፤ ቀላልም ስላልሆነ ፤ የጁሪዚዲክሽን (ስልጣን ክፍፍልን) ለውጥ ያመጣል። ፌደራል ላይ የነበሩ ወደ ክልል ይኼዳሉ። ክልል ላይ የነበሩ ወደ ፌደራል የሚሳቡ አሉ። በቀጣዩ የሚወጡ መመሪያዎችና ደንቦች ይኖራሉ፤ ተቋማትም ጭምር ይቋቋማሉ። ይህ ህግ ፀደቀ ማለት በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ትልቅ ለውጥ ይመጣል። የፍትሕ ስርዓቱ በጣም ዘመናዊ እንዲሆን ያስችላል ብዬ አስባለሁ።

የፌደራል ስልጣን ወደ ክልል ሊሄድ ይችላል ሲሉ....

በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕግ አለ። እዚያ ላይ የተደነገጉ ድንጋጌዎችን በሙሉ ለቅመን ይህኛው የፌደራል ነው ይህኛው የክልል ነው፤ ይህኛው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው፤ ይህኛው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፤ ይህኛው የጠቅላይ ነው ብለን በዝርዝር አስቀምጠናል።

አሁን ባለው አሰራር ክልሎች የወንጀል ጉዳይን በቀጥታ የማየት ስልጣን የላቸውም። የፌደራል መንግሥቱ የሚያወጣቸውን ሕጎች በፌደራል መንግሥቱ ስር ነው የሚወድቁት። ስለዚህ አሁን ባለው አሰራር እኮ ክልሎች በውክልና ነው እየሰሩ ያሉት የሚል አንድምታ ነው ያለው። ነገር ግን አሁን በዚህኛው ረቂቅ ላይ ለክልል ተብሎ በግልፅ ተዘርዝሮ ተሰጥቷቸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ