በአከራካሪው የ3ሺህ ሜትር መሰናክል ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ አገኘች

ለሜቻ ግርማ
አጭር የምስል መግለጫ ለሜቻ ግርማ

ኳታር ዶሃ ላይ እየተካሄደ ባለው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ በወንዶች የሦስት ሺህ ሜትር የመሰናክል ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊው ለሜቻ ግርማ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አሸነፈ።

ይህ በሦስት ሺህ ሜትር የመሰናክል ውድድር በለሜቻ ግርማ የተገኘው የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ በዘርፉ የመጀመሪያ ሲሆን የተመዘገበው ሰዓትም ለአገሪቱ ክብረ ወሰን ነው ተብሏል።

ኬንያዊው አትሌት የወርቅ ሜዳሊያውን በወሰደበት በዚህ የመሰናክል ሩጫ ውድድር ላይ ለሜቻ የተቀደመው ከአንድ ሰከንድ በታች በሆነ ጠባብ ልዩነት ነው።

ለሜቻ አንደኛ ሆኖ የወርቅ ሜዳሊያን ካገኘው ኬንያዊው ሯጭ ኮንሴስለስ ኪፕሩቶ ጋር እኩል የመጨረሻውን መስመር በማለፋቸው አሸናፊው ማን እንደሆነ በውድድሩ ማብቂያ ላይ ወዲያውኑ አልታወቀም ነበር።

"ቤተ መንግሥቱን ለማስዋብ ለሙያችን የሚከፈለን ገንዘብ የለም" መስከረም አሰግድ

ተማሪዎች መገረፍ አለባቸው የሚሉት የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት

10 ሚሊዮን ሕዝብ ይታደምበታል የተባለው ኢሬቻ በአዲስ አበባ

የውድድሩ ዳኞች በቪዲዮ (ፎቶ ፊኒሽ) ታግዘው ከአንድ ሰከንድ ባነሰ የሰከንዶች ቅንጣት የመጨረሻውን መስመር ኬንያዊው ለሜቻን ቀድሞ እንዳለፈ ከለዩ በኋላ ነው አሸናፊው ሊታወቅ የቻለው።

በስፍራው የሚገኙት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለስልጣናት ለሜቻ አንደኛ ወጥቷል ብለው አምነው ሰለነበር ይፋ የተደረገውን ውጤት በመቃወም ቅሬታ ለማቅረብ አስበው የነበረ ቢሆንም፤ የመጨረሻውን ሰከንድ የውድድሩን ቪዲዮና ምስሎችን ተመልክተው ካጣሩ በኋላ ቅሬታቸውን ማንሳታቸውን የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።

19 ዓመት ሊሆነው ሁለት ወራት የቀሩት ወጣቱ ለሜቻ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ የጀመረው በቅርቡ ሲሆን በኬንያዊያን የበላይነት ስር በነበረው የሦስት ሺህ ሜትር የመሰናክል ውድድር ላይ የብር ሜዳሊያ ያስገኘበት የዶሃው ውድድር ሦስተኛው ዓለም አቀፍ ተሳትፎው ነው።

በውድድሩ አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ኬንያዊው ኮንሴስለስ ኪፕሩቶ በዚህ በፈረንጆች ዓመት በሦስት ሺህ ሜትር መሰናክል አራት ጊዜ ተሳትፎ የነበረ ቢሆንም በአራቱም ለማሸነፍ ሳይችል ቀርቶ በዓለም ሻምፒዮና ላይ እንደተሳካለት ተነግሯል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
"የአልቤርቶ ሳላዛር መታገድ በዮሚፍ ቀጀልቻ ላይ ምንም አያስከትልም" ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ

በዚህ ውድድር ላይ በማሸነፍ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ይገባል ተብሎ ተጠብቆ የነበረው የዳይመንድ ሊግ አሸናፊው ጌትነት ዋሌ አራተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

ለሜቻ ውድድሩን ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀበት ሰዓት እስካሁን በተካሄዱት የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ ከተመዘገቡት ለአንደኛው ከቀረቡት ውጤቶች ሁሉ የበለጠ እንደሆነም ተነግሯል።

እስካሁን በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የሦስት ሺህ ሜትር የመሰናክል ሩጫ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ሜዳሊያ አግኝታ የማታውቅ ሲሆን ይህ በዶሃ እየተካሄደ ባለው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በለሜቻ ግርማ የተገኘው ሜዳሊያ የመጀመሪያ ነው።

የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ለሜቻ ከውድድሩ በኋላ ለቢቢሲ እንደተናገረው በውጤቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ገልጿል።

አንደኛ በመሆን ያሸነፈው ኬንያዊው አትሌት ኮንሴስለስ ኪፕሩቶ ውድድሩ ላይ ከኢትዮጵያዊያኑ በኩል ከባድ ፈተና እንደገጠመው ተናግሯል።

"የማራቶን ሯጮቹ ላይ የተላለፈው እገዳ አይደለም" ዱቤ ጂሎ

"ኢትዮጵያዊያኑ በደንብ ተዘጋጅተው ነበር የገቡት። ውድድሩን ለመቆጣጠርና ከፊት ከፊት ሆኜ ለመምራት እቅዱ ነበረኝ ነገር ግን ሊሆን አልቻለም። ለሜቻና ጌትነት ግን እቅዴን እንዳላሳካ አድርገውታል" ሲል ገጥሞት የነበረውን ፈተና ለጋዜጠኞች ተናገሯል።

ኢትዮጵያዊያን ከኬንያዊያን በተሻለ ተዘጋጅተው መግባታቸውን የሚናገረው ኮንሴስለስ ኪፕሩቶ ለማሸነፍ የነበረው ጽኑ ፍላጎት በውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያውን እንዲወስድ እንደረዳው ገልጿል።

በዚህ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ እስከ ዛሬ ጠዋት ኢትዮጵያ አንድ ወርቅና ሦስት የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ላይ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ኬንያ በሦስት ወርቅና በሁለት የነሃስ ሜዳሊያ ሦስተኛ ስትሆን አሜሪካና ቻይና አንደኛና ሁለተኛ ሆነው የሜዳሊያ ሰንጠረዡን እየመሩ ነው።