ግብፅ በህዳሴ ግድብ ላይ አለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቀረበች

የህዳሴ ግድብ Image copyright Reuters

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ ለሁለት ቀናት ያህል መስከረም 23፣ 24 2012 ዓ.ም በህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ያደረጉትን የሦስትዮሽ ምክክር ተከትሎ ግብፅ አለም አቀፍ አደራዳሪዎች እንዲገቡ ጥሪ አቅርባለች።

ግብፅ የሦስትዮሽ ስምምነቶቹ ምንም ዓይነት ውጤት ባለማምጣታቸው አለም አቀፍ አደራዳሪ እንዲገባ ጥሪ ማድረጓን ተከትሎ ኢትዮጵያ በበኩሏ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል ገልፃለች።

በአባይ ግድብ ላይ ለዓመታት የተካሄድው ውይይት ውጤት አላመጣም፡ ግብጽ

''የሚፈርስ የግድቡ አካል የለም'' የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ

በሱዳን መዲና ካርቱም የተደረገውን የሦስትዮሽ ውይይት ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ የግብፅ የሦስተኛ ወገን ጥሪ እስካሁን በሦስቱ አገራት ላይ የተደረሱ አበረታች ስምምነቶችን የሚያፈርስ ከመሆኑ በተጫማሪ ሦስቱ አገራት በመጋቢት 2017 የፈረሟቸውን የመግለጫ ስምምነቶችም ይጥሳል ይላል።

መግለጫው አክሎም የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በሱዳን በኩል ተቀባይነት የሌለውና በአገራቱ መካከል ያለውን ዘላቂ ትብብር የሚጎዳ፣ በአገራቱ መካከል የነበሩ ቴክኒካዊ ውይይቶችን ዕድል ቦታ ያልሰጠ እንዲሁም የነበረውን የውይይት መንፈስ የሚያጠለሽ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ግብፅ ያቀረበችውን አደራዳሪ ኃሳብ እንደማይቀበሉት የገለፁ ሲሆን "ለምንድን ነው አዲስ አጋሮች የሚያስፈልገን? ስምምነቱ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ይፈለጋል ማለት ነው?" በማለት ለሪፖርተሮች መናገራቸው ተዘግቧል።

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ መዘግየት ምን አይነት መፍትሔዎች እየተሰጡ ነው?

ግብፅ ማን አደራዳሪ ይሁን በሚለው ላይ ምንም ባትልም የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ፤ አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላት ሚና ከፍ ያለ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ የመሙላት ሂደትና አጠቃቀም ላይ ትብብር፣ ዘላቂነትና የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥን በተመለከተ እየተደረገ ያለውን ድርድር እንደምትደግፈው አሜሪካ ከውይይቱ በፊት መግለጫ አውጥታ ነበር።

ይህ የተገለጸው ከኋይት ሃውስ የፕሬስ ጽህፈት ቤት በወጣና ዝርዝር ጉዳዮችን በማይጠቅሰው አጭር መግለጫ ላይ ሲሆን፤ መግለጫው የወጣበት ምክንያትም አልተገለጸም።

በዚህ አጭር መግለጫ ላይ "ሁሉም የአባይ ተፋሰስ አገራት በምጣኔ ሃብት የመልማትና የመበልጸግ መብት አላቸው" ይልና ሲቀጥል "አስተዳደሩ [የአሜሪካ] ሁሉም አገራት እነዚህን መብቶች ሊያስከብር የሚችልና የእያንዳንዳቸውን የውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያስከብር በጎ ፈቃደኝነትን የተላበሰ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ ያቀርባል" ይላል።

ከውይይቱም በኋላ የግብፅ ፕሬዚዳንት ግብፅ በናይል ላይ ያላትን መብት ለማስጠበቅ ቁርጠኝነት እንዳላት ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንቱ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት " ግብፅ በናይል ላይ ያላትን መብት ለማስጠበቅ በፖለቲካዊ ምክክር እንደምትቀጥልና በአለም አቀፉ ሕግጋት ማዕቀፍ ሥር አስፈላጊውን እርምጃ ትወስዳለች" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ስለአባይ አጠቃቀም ምላሽ ሰጡ

የህዳሴ ግድቡን የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ጉዳይ ከግብፅ በኩል ለፖለቲካ ምክክር እንዲቀርብ ኃሳብ መቅረቡ የጉዳዩን መፍትሔ ያላገናዘበ፤ የሦስቱ አገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉዳዩን ለመፍታት ቴክኒካዊ ምክክር አስፈላጊነቱን በተመለከተ የሰጡትን መምሪያ የጣሰና መፍትሔም እንደማያመጣ ኢትዮጵያ በምላሹ ገልፃለች።

ውይይቱን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በትዊተርና ፌስቡክ ገፁ እንዳሰፈረው በህዳሴ ግድብ ሙሌትና መለቀቅ ላይ የሚደረጉ ስምምነቶችን ለማስቀጠል እንደሚፈልግና ከሁለቱም አገራት ተመሳሳይ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

አስራ አንዱ የናይል ተፋሰስ አገራት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ያለምንም ጉዳት የሚጠቀሙበትና ኢትዮጵያም ከውሃ ኃብቷ በመጠቀም ሕዝቦቿ የሚጠቀሙበትን መንገድ ለመቀየስ እንደምተሠራ ተገልጿል።

አሜሪካ የአባይ ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተ መግለጫ አወጣች

ኢትዮጵያ የትኛውንም ዓይነት ያለመስማማቶችም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች በሦስትዮሽ ውይይቶች ለመፍታት እንደምትሠራ ብትናገርም ከግብፅ በኩል የሚሰሙት ውይይቶቹ ፍሬ አልባና ወደየትም የማያስኬዱ ናቸው የሚሉ ናቸው።

ባለፈው መስከረም 3 እና 4/2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን ባለሥልጣናት ካይሮ ላይ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ ባደረጉት የሦስትዮሽ ውይይት፤ ግብፅ የህዳሴ ግድቡ የውኃ አሞላልን በተመለከተ በተናጠል ያቀረበችው ሃሳብ በኢትዮጵያ ውድቅ መደረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከካይሮው ድርድር በኋላ አዲስ አበባ ላይ በሰጡት መግለጫ ግብጽ በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ አዲስ ሃሳብ እንዳቀረበችና ኢትዮጵያ ሃሳቡን ውድቅ እንዳደረገች ተናግረዋል።

ግብፅ በተናጠል ያቀረበችው የውሃ ሙሌቱን አለቃቅ ሰነድ ከአገራቱ ማዕቀፍ ትብብር ያፈነገጠና እየተካሄዱ ያሉ ስምምነቶችን የሚቃረን ነው ተብሏል።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ግብጽ ያቀረበችው ሃሳብ የግድቡ የውሃ የሚሞላው በሰባት ዓመት እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓመት 40 ቢሊየን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅና የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር ላይ ሲደርስ ግድቡ በዋናነት ውሃ እንዲለቅ የሚጠይቅ ነው።

ኢትዮጵያም ይህ የግብጽ ሃሳብ ቀደም ሲል በሦስቱ ዋነኛ የተፋሰሱ አገራት መካከል የተፈረመውን የአባይ ወንዝ ውሃን አጠቃቀም የተመለከተውን "የመርህ ስምምነት የጣሰና ጎጂ ግዴታን የሚያስቀምጥ ነው" በማለት እንደማትቀበለው አሳውቃለች።

ሚኒስትሩ በተጨማሪም ይህ የቀረበው ሃሳብ "ግብጽ የወንዙ ዓመታዊ የውሃ ፍሰት 40 ቢልየን ሜትር ኪዩብ እንዲሆን ያቀረበችው ጥያቄ፤ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን እንዳትጠቀም የሚከለክል በመሆኑ አልተቀበለችውም" ብለዋል።

"የሰለጠነና በሙሉ አቅም የሚዋጋ ኃይል ነው ችግሩን የሚፈጥረው" የማዕከላዊ ጎንደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ

ግድቦቹን ለመሙላት የሚያስፈልገው 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን ኢትዮጵያ ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት ብታስቀምጥም ግብፅ በበኩሏ የውሃ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል በሚል ረዘም ያለ ጊዜ እንዲሰጥ ጠይቃለች።

ግብፅ የህዳሴ ግድብ መገንባት በየአመቱ የምታገኘውን 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሊቀንሰው እንደሚችል ስጋቷን በተደጋጋሚ እየገለፀች ነው።

የሦስቱ አገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት ከመካሄዱ በፊት በግድቡ የውሃ አሞላልና የመልቀቅ ሂደት ዙሪያ ሁኔታዎች እንዲያጠና የተቋቋመው የአገራቱ ገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን ከመስከረም 19 እስከ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በካርቱም አምስተኛ ዙር ስብሰባውን አካሂዶ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት እና የውሃ አለቃቀቅ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስብሰባውን አካሂዷል።

የሦስቱ አገራት የውኃ ሚኒስትሮች በካይሮ ስብሰባቸው ላይ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌቱንና አለቃቀቋን ዕቅድንና ግብፅና ሱዳን የሚያቀርቡትን ሰነድ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ትንታኔና ምክረ ሃሳብ እንዲያቀርብ ታዞ ነበር።

በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ሳይንሳዊ ቡድኑ ለአራት ቀናት ያህል በካይሮ ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያን የግድብ ሙሌት እና የውሃ አለቃቀቅ እቅድ፤ ግብፅ እና ሱዳን ያቀረቡትን የሙሌትና እና የውሃ አለቃቀቅ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን በማዳመጥ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመስማማት ቢደረስም አንዳንድ ሃሳቦች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ማናቸውም ቴክኒካዊ ጉዳዮች ለሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ቀርበው ትንተና እንዲደረግባቸው የውይይት አካሄድ ቢከተሉም ግብፅ የሳይንስ ጥናት ቡድኑ ትንተናን አሻፈረኝ በማለት ያቀረብኳቸው ሃሳቦች በሙሉ ተቀባይነት ካላገኙ ውይይቱ ሊቀጥል አይችልም በማለቷ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ሥራውን በተሟላ አኳኋን ማከናወን ሳይችል እንደቀረ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው አትቷል።

በተሻሻለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ረቂቅ ጥፋተኛና አቃቤ ህግ ይደራደራሉ

ግብፅ አሻፈረኝ ማለቷ አዲስ አካሄድ ሳይሆንም ከዚህ ቀደምም በግድቡ ላይ ሦስቱ አገራት ሊያከናውኑት የነበረውን የውሃ፣ የአካባቢያዊ እና ማህበራዊ ተጽዕኖ ጥናት በግብጽ ወገን እንዲስተጓጎል በተደረገ ጊዜ የታየ የሳይንስ እና የምክክር የመፍትሔ አማራጭን የማፍረስ ዘዴ እንደሆነ ነው በማለት ኢትዮጵያ ትተቻለች።

በሁለቱ ቀናት ውይይትም ቡድኑ የደረሰበትን ተመልክተው ቀጣዩ ሂደትን ለማስቀመጥ ጥረት ቢደረግም ከግብፅ በኩል በነበረው እምቢተኝነት የጥናት ቡድኑ በቀጣይ ስለሚሠራቸው ጉዳዮች መመሪያ ሳይተላለፍ እንደቀረ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው አክሎ ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የናይል ውሃን አስመልክቶ ለተደረጉት እና በኢትዮጵያ ላይ ምንም ዓይነት ተፈጻሚነት የሌላቸውን ስምምነቶች እውቅና እንደማይሰይጥም በመግለጫው ተካትቷል።