በቤተ መንግሥት ግቢ የተገነባው አንድነት ፓርክ በውስጡ ምን ይዟል?

በቤተ መንግስት ግቢ የተሰራው የአንድነት ፓርክ ምን ምን ይዟል?

በቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ የተሰራው አንድነት ፓርክ 5 ቢሊየን ብር ተመድቦለት የተገነባ ሲሆን ዛሬ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት ተመርቆ ተከፍቷል።

ይህንን ፓርክ ለመገንባት የገንዘብ ድጋፍ የተገኘው ከዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለጋዜጠኞች ባስጎበኘበት ወቅት ተናግሯል።

ቤተ መንግሥቱ በ40 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በውስጡ ሦስት ዋነኛ የቱሪስት መስህቦች ይገኙበታል።

በታሪካዊው ቤተ መንግሥት ውስጥ ምን አለ?

ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ማዕድ የቀረቡት ምን ይላሉ?

አጭር የምስል መግለጫ ይህ ቤት ከቤተ መንግሥቱ በምሥራቃዊ አቅጣጫ የሚገኝ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ሲሆን፤ ከአጤ ሚኒሊክ ቤት ጋር በድልድይ የሚገናኘው የእቴጌ ጣይቱ ቤት ነው

ታሪካዊ መስህብ

ከ1880ዎቹ ጀምሮ የተገነቡ የነገሥታት መኖሪያና ጽህፈት ቤቶች በዋናኝነት እዚህ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን በዚህ ፕሮጀክት የነበሩበትን ይዞታ ሳይለቁ ዕድሳት እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የሚኒሊክ የግብር አዳራሽ ሲሆን ንጉሡ በዚህ አዳራሽ እንግዶቻቸውን ያስተናግዱ እንደነበር ታውቋል።

የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸውን የማልማት ሥራን ለመተግበር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ታቅዶ በነፍስ ወከፍ አምስት ሚሊዮን ብር በማበርከት የእራት ድግስ የተካሄደበት 'ገበታ ለሸገር' መርሃ ግብር የተደረገውም በዚሁ በታደሰው አዳራሽ ውስጥ መሆኑ ይታወሳል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ልጅ የተዳረችውም በዚሁ አዳራሽ እንደሆነ በጉብኝቱ ወቅት ተነግሯል።

እኚህ የታሪክ ቅርሶች ሦስት ጊዜ እድሳት እንደተደረገላቸው በገለፃው ወቅት መረዳት ተችሏል።

የመጀመሪያው በ1963 ዓ.ም በኃይለ ሥላሴ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደርግ 10ኛ ዓመቱን ሲያከብር፣ ሶስተኛው ደግሞ ቫርኔሮ በሚባል የኮንስትራክሽን ድርጅት ነው።

በዚህ ሥፍራ መጀመሪያ የምናገኘው የፊት አውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን (አባ መላ) መኖሪያ ነው። አባ መላ የአጤ ሚኒሊክ የጦር ሚንስትር የነበሩ ሲሆን ይኖሩበት የነበረ ትንሽ የእንጨት ቤት ከአጤ ምኒሊክ መኖሪያ ቤት ጎን ላይ ይገኛል።

አጤ ሚኒሊክ ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኋላም እንደ መኖሪያና ቢሮ አድርገው ሲጠቀሙበት ነበር። ቤቱ ፈርሶ የነበረ ሲሆን አሁን ሙሉ በሙሉ ታድሷል።

ወደ አጤ ሚኒሊክ ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያና ጽ/ቤት በሮች በእንጨት የተሠሩ ሲሆን በሚያምር መልኩ የአበባና የሐረግ ጌጥ የተፈለፈለበት ነው። ይህ ቤት ከሁለት ሌሎች ቦታዎች ጋር በድልድይ ይገናኛል። አንደኛው በሰሜናዊ አቅጣጫ የአጤ ምኒሊክ የፀሎት ቤትና የሥዕል ቤት ሲሆን እንቁላል ቤት በመባል ይጠራል። አንዳንዴም እንደ ጽ/ቤት ይጠቀሙበት ነበር።

ወደ አጤ ሚኒሊክ ባለ አንድ ፎቅ መኖሪያና ጽ/ቤት በሮች በእንጨት የተሠሩ ሲሆን በሚያምር መልኩ የአበባና የሐረግ ጌጥ የተፈለፈለበት ነው። ይህ ቤት ከሁለት ሌሎች ቦታዎች ጋር በድልድይ ይገናኛል። አንደኛው በሰሜናዊ አቅጣጫ የአጤ ምኒሊክ የፀሎት ቤትና የሥዕል ቤት ሲሆን እንቁላል ቤት በመባል ይጠራል። አንዳንዴም እንደ ጽ/ቤት ይጠቀሙበት ነበር።

በሌላ በኩል አጤ ምንሊክ ከጦር መኮንኖቻቸው ጋር የሚገናኙበት ክፍል ይገኛል። በወቅቱ የጦር ሚኒስትር የነበሩት ፊት አውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ እንደ ቢሮ ይጠቀሙበት ነበር።

አጭር የምስል መግለጫ የዘውድ ቤት

ሌላኛው የዘውድ ቤት ነው። ይህ ህንፃ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነገሥታትንና ዲፕሎማቶችን የተለያዩ ሀገራት ተቀብለው ያስተናግዱበት ነበር።

በዚህ ህንፃ ከተስተናገዱ የውጪ ሀገራት እንግዶች መካከል በ1965 ንግሥት ኤልሳቤጥ 2ኛ፣ በ1966 የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ቻርልስ ደጎል እንዲሁም በ1956 የዩጎዝላቪያው ፕሬዝደንት ቲቶ ይገኙበታል።

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም፣ የዚህን ህንፃ ምድር ቤት የአጼ ኃይለሥላሴን ባለስልጣናት አስሮ ለማሰቃየት ተጠቅመውበት እንደነበር ታሪክ ሰነዶች ያስረዳሉ።

የፀሎት ቤቱና የሥዕል ቤቱ ባለ ሁለት ፎቅ ነው። ሁለተኛው ፎቅ ላይ ከፍ ብላ የተሠራች በመስታወት የተሸፈነች ቤት አለች፤ ይህች ቤት 'ቴሌስኮፕ' ያላት ሲሆን አዲስ አበባን በሁሉም አቅጣጫ ማየት ታስችላለች።

በዚች እንቁላል ቤት መገናኛው ድልድይ ጋ የመጀመሪያው ስልክ የገባበት ቤት ይገኛል። ቤቱ ከድንጋይና ከእንጨት የተገነባ ነው። አርክቴክት ዮሐንስ የኪነ ህንፃውን ጥበብ ሲገምቱ ከአርመኖችና ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ሕንዶች ሳይሳተፉበት እንደማይቀሩ ይገምታሉ።

ይህ ቤት በደርግ ጊዜ የውይይት ክበብ በመሆን አገልግሏል።

አደጋ የተጋረጠበት የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት

ሌላኛው ከአጤ ሚኒሊክ ቤት ጋር በድልድይ የሚገናኘው የእቴጌ ጣይቱ ቤት ነው። ይህ ቤት ከቤተ መንግሥቱ በምሥራቃዊ አቅጣጫ የሚገኝ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ ነው።

በምድር ቤት የዙፋን ግብር ቤት ይገኛል። የነገሥታቱ መመገቢያ አዳራሽ ሲሆን ንጉሣዊ ቤተሰቦች ምግብ የሚመገቡበት ክፍል ነበር፤ ይህ ቤት በደርግ ጊዜ የደርግ ምክር ቤት መሰብሰቢያ በመሆን አገልግሏል።

የተፈጥሮ መስህቦች

በፓርኩ ከተሰሩ መስህቦች መካከል የእንስሳት ማቆያና አኳሪየም (የውሃ አካል) አንደኛው ነው። በዚህም ውስጥ የጥቁር አንበሳ መኖሪያ፣ የዝንጀሮ መጠለያ፣ የአሳ ማርቢያ (አኳሪየም) ጨምሮ የ46 ዓይነት ዝርያ ያላቸው 300 ለሚሆኑ እንስሳት መጠለያ የሚሆን ስፍራ ይገኛል።

ለእንስሳቱ ምግብ የሚዘጋጅበትና ሕክምና የሚሰጥበት ስፍራ በዚሁ አለ።

ይህ የእንስሳት መጠለያ ሕዳር 2012 ስራ እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል።

ባህላዊ መስህብ

በአንድነት ፓርክ ከተካተቱት አንዱ የብሔር ብሔረሰቦች ባህል የሚንፀባረቅበት ስፍራ ነው።

ይህ ስፍራ የተገነባው በብሔር ብሔረሰቦች ቤት፣ ባህል፣ ምጣኔ ኃብትና የሕዝቦችን አኗኗር መሰረት በማድረግ ነው።

በዚህ ሕንፃ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውን እንዲያንፀባርቁ እንደሚደረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ገልጿል።

በፓርኩ የጓሮ አትክልት፣ የሚገኝ ሲሆን የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር አቀማመጥ በጠበቀ መልኩ ተሰርቷል።

በዛሬው እለት የተመረቀው የአንድነት ፓርክ በነገው እለት የመከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንደሚጎበኙት ለማወቅ ተችሏል።

ቅዳሜ እና እሁድ ደግሞ አዛውንቶች እና የጎዳና ተዳዳሪዎች ይጎበኛሉ ተብሏል።

ከሰኞ ማለትም ከጥቅምት 3 2012 ጅምሮ ማንኛውም ዜጋ 200 ብር እንዲሁም በቪአይፒ (VIP) 1 ሺህ ብር በመክፈል ቤተ መንግስቱን መጎብኘት ይችላል የተባለ ሲሆን 1000 ብር የሚከፍሉ ጎብኝዎች ታሪካዊ ቁሳቁስ የሚገኙበትንና ሌሎች እንግዶች እንዲያዩ ያልተፈቀደላቸው ስፍራ መጎብኘት እንደሚችሉ ለመረዳት ችለናል።