በኬንያ ወርቃማ የሜዳ አህያ ተገኘች

ወርቃማ የሜዳ አህያ Image copyright Kenya Pics twiter page

በኬንያ ማሳይ ማራ ባለነጠብጣቧ የሜዳ አህያ ውርንጭላ ከተገኘች ሶስት ሳምንት በኋላ ወርቃማ የሜዳ አህያ ውርንጭላ መገኘቷ ተሰማ።

ረቡዕ ዕለት ወርቃማዋ የሜዳ አህያ ውርንጭላ የተገኘችው በስፍራው እያስጎበኘ በነበረው ጆን ማኔ ኪፓስ በተባለ ግለሰብ እንደሆነ በኬኒያ የሚታተመው ዴይሊ ኔሽን ዘግቧል።

" መጀመሪያ ያየኋት እኔ ነኝ። ለመታሰቢያነትም በአባቴ ስም ሰየምኳት" ማለቱን ጋዜጣው ዘግቧል።

አንበሶችን ያባረረው ወጣት ምን አጋጠመው?

ኬንያ ገንዘብ ከመቀየሯ ጋር ተያይዞ ከሰባት ቢሊዮን ሺልንግ በላይ ጥቅም አልባ ሆነ

ውርንጭላዋ ማኔን፣ አስጎብኚው ጆን ያገኛት የተለመደው የማለዳ ጉብኝት ስራውን እንደጀመረ ነበር፤ ወዲያውም ይላል ጆን፣ "አይኔን ማመን አልቻልኩም" በማለት ካሜራውን አውጥቶ ምስሏን እንዳስቀረ ተናግሯል።

" ከሜዳ አህያ ይልቅ የቤት ውስጥ አህያ ነው የምትመስለው" ሲል የተሰማውንም ለጋዜጣው አጋርቷል።

የውርንጭላዋ ማኔ ምስል በትዊተር ላይ ከተለቀቀ በኋላም በርካቶች ተጋርተውታል። ይህች ውርንጭላ የሜዳ አህዮች ወደ ታንዛኒያ ሴሬንጌቴ በሚፈልሱበት መስመር ላይ ነው የተገኘችው።

ምስሉ ላይ እንደሚታየው አንገቷ፣ እግሮቿ፣ ጭንቅላቷ እና ጭራዋ እንደ ዘመዶቿ በነጭና ጥቁር የተሸለመ ሲሆን ሌላው አካሏ ግን ወደ ቡናማ የሚያደላ ቀለም አለው።

የኬንያዋ ጭርንቁስ ሰፈር የዓለም 'የድሀ ድሀ' ጉባኤን ልታዘጋጅ ነው

አስጎብኚው ኪፓስ ይህች ውርንጭላ ድንበር አቋርጣ ታንዛኒያ እንዳትገባ የኬኒያ መንግሥት እንዲከለክል ጥሪ አቅርቧል።

ከሶስት ሳምንት በፊት አንቶኒ ቲራ የተሰኘ የፎቶግራፍ ባለሙያ በዚሁ ፓርክ ነጠብጣብ ያለባት የሜዳ አህያ ውርንጭላ ማግኘቱ ይታወሳል።

ይህች ውርንጭላ በመስመሮች ከመሸለም ይልቅ በነጠብጣብ የተዋበችው በሜላኒን እጥረት መሆኑ ተገምቷል። ውርንጭላዋ በአሁኑ ሰዓት ወደ ታንዛኒያ አቋርጣ መሄዷ ታውቋል።

ተያያዥ ርዕሶች