የዛሬዋን አዲስ አበባ በፎቶ መሰነድ ለምን አስፈለገ?

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የእለት ከእለት ሕይወት የሚያሳዩ ፎቶዎች በፌስቲቫሉ ተካተዋል Image copyright Mikiyas Melesse

አዲስ አበባ በፈጣን ለውጥ ውስጥ ናት። ትላንት የነበረ ቤት ዛሬ ፈርሶ ሊሆን ይችላል። ዛሬ የሚታይ ሰፈር ነገ ገጽታው ሊቀየር የሚችልበት እድልም ሰፊ ነው።

የአዲስ አበባን ለውጥ ለማስተዋል ዓመታት መጠበቅ አያስፈልግም። በሳምንታት ውስጥ ተገንብተው ያለቁ የሚመስሉ አንጸባራቂ ህንጻዎች የከተማዋን ገጽታ በፍጥነት እየቀየሩት ይገኛሉ።

ስዕልን በኮምፒውተር

ትኩረት የተነፈገው የባህር ዳር መለያ ባህላዊ ጥበብ

ቀደምትና የከተማዋ ታሪክ ቋሚ ምስክር የሆኑ አካባቢዎች ለውጥ እየተሰነደ ነው ወይ? የብዙዎች ጥያቄ ከሆነ ሰነባብቷል።

እድሜ ጠገብ ሰፈሮች ወይም ታሪካዊ ህንጻዎች መፍረሳቸው በበርካታ ባለሙያዎች ይተቻል። እነዚህ አካባቢዎች ከመፍረሳቸው ባሻገር በአንድ ወቅት ስለመኖራቸው የሚዘክር መረጃ በአግባቡ አለመያዙም ጥያቄ ያጭራል።

አዲስ አበባ ምን ትመስል ነበር? የሚለውን በታሪክ መዝገብ ለማስፈር ቆርጠው የተነሱ ፎቶ አንሺዎች የከተማዋን ገጽታ የሚያሳዩ ፎቶዎች በማንሳት ዓውደ ርዕዮች አዘጋጅተዋል። አዲስ አበባን በመሰነድ ዙርያ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄዎች መጀመራቸው ይታወቃል።

"ስትሪትስ ኦፍ አዲስ" በፎቶ አንሺ ግርማ በርታ የተጀመረ የማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ነው። የተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎችን እንዲሁም የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ ፎቶ በማንሳት፤ በዋነኛነት በኢንስታግራም ላይ በማጋራት ይታወቃል።

"ቪንቴጅ አዲስ" በከተማዋ በ1970ዎቹ አካባቢ የተነሱ ፎቶግራፎች ስብስብ ላይ ያተኮረ ነው። ከተማዋን ወደኋላ መለስ አድርገው የሚያስቃኙ ፎቶዎችን በመሰነድ የሚታወቅ ሲሆን፤ "የአዲስ አበባ ትዝታ" የተሰኘ የፎቶ መጽሐፍም ታትሟል። "ቪንቴጅ አዲስ" የተመሰረተው በወንጌል አበበ፣ ፊሊፕ ሹትዝ እና ናፍቆት ገበየሁ ነው።

Image copyright Mikiyas Melesse

"አዲስን እናንሳ"

የአዲስ አበባን ነባራዊ ገጽታ መመዝገብን አላማው ያደረገ የፎቶግራፍ ፌስቲቫል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መተዋወቅ ከጀመረ ቆይቷል።

ፌስቲቫሉ "ካፕቸር አዲስ" ወይም "አዲስን እናንሳ" ይሰኛል። ፎቶ አንሺዎችን ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የከተማዋን ገጽታ ማሳየት የሚፈልግ ሰውን ያሳትፋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከተማዋን የሚገልጹ ፎቶዎችን ለፌስቲቫሉ አዘጋጆች እንዲያስገቡ ጥሪ መቅረቡን ተከትሎ፤ ብዙዎች የአዲስ አበባን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተጋሩ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመፅን በፎቶ

ስለ ጠልሰም ወይም በተለምዶ የአስማት ጥበብ ተብሎ ስለሚጠራው ምን ያህል ያውቃሉ?

አንበሳ አውቶብስ፣ የተለያዩ ጎዳናዎች እና ሰፈሮች፣ ሀውልቶች፣ በመፍረስ ላይ ያሉ ቤቶች፣ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች እንዲሁም ሌሎችም ከተማዋን የሚገልጹ ፎቶዎች ይገኙበታል።

Image copyright Aron Simeneh

ሌላ ቀለም የተባለ ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፎቶግራፍ ፌስቲቫል ከጥቅምት 15 እስከ 21፣ 2012 ዓ. ም. በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ግቢ ውስጥ ይካሄዳል።

ከፌስቲቫሉ አዘጋጆች አንዷ የሆነችው ሀምራዊት ግዛው፤ ፌስቲቫሉ ከተሰናዳበት አላማ አንዱ የአዲስ አበባን ለውጥ በፎቶ በመመዝገብ ለታሪክ ማስቀመጥ እንደሆነ ትገልጻለች።

"በየጊዜው ያለውን የአዲስ አበባ የለውጥ ሂደት መመዝገብ፣ ለውጡንም ለታሪክ ማቆየት እንፈልጋለን። ባለፈው ዓመት የነበሩ ህንጻዎች አሁን ምን ይመስላሉ? የሚለውን ለማየትም ይረዳል" ስትል ትገልጻለች። የከተማዋን ፈጣን ለውጥ ሙሉ በሙሉ መመዝገብ ባይቻልም በተቻለው መጠን ሂደቱን ማሳየት አስፈላጊ መሆኑንም ታክላለች።

የአዲስ አበባ ለውጥ በተገቢው መንገድ እየተመዘገበ አለመሆኑን የምታስረዳው ሀምራዊት፤ ፌስቲቫሉ ክፍተቱን በመጠኑም ቢሆን እንደሚደፍነው ታምናለች።

"ሥነ ቃል እና ሌሎችም እንደሚመዘገቡት የከተማዋ ለውጥ እየተመዘገበ አይደለም። ብዙ ሥራ ይቀረናል። ተሳታፊዎች ፎቶ መነሳት ያለባቸው የፈረሱ ታሪካዊ ቦታዎችን ወይም ቅርሶችን ፎቶ እንዲያነሱም አበረታተናል" ትላለች።

ከስልክ እስከ ካሜራ. . .

ፌስቲቫሉ ላይ የሚካተቱ ፎቶዎች በቴክኖ ስልክ አልያም በአይፎን ወይም ደግሞ በማንኛውም ዘመናዊ ካሜራ የተነሱም ሊሆኑ ይችላሉ። አንድ ሰው የሚጠቀመው መሣሪያ ሳይሆን ስለከተማዋ ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ትኩረት እንደሚሰጠው ሀምራዊት ትናገራለች።

ሀምራዊት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ እስካደረገችበት የጥቅምት ወር የመጀመሪያው ሳምንት ድረስ 500 ፎቶዎች ለፌስቲቫሉ አዘጋጆች ተሰጥተዋል። ከነዚህ መካከል ወደ 250 የሚጠጉት በከተማዋ ነዋሪዎች የተነሱ ፎቶግራፎች ናቸው።

አርባ ምንጭ፡ የዶርዜ የሽመና ጥበብ መናኸሪያ

ተፈጥሮን በብሩሽ የሚመዘግበው መዝገቡ

ለአዘጋጆቹ ከቀረቡት ፎቶዎች 150ው ተመርጠው ለሰባት ቀናት በዓውደ ርዕይ ይቀርባሉ። ከፎቶግራፎቹ መካከል በሦስት ዘርፍ፣ ሦስት ፎቶዎች ተመርጠውም ፎቶ አንሺዎች ይሸለማሉ።

Image copyright Mikiyas Melesse

በፌስቲቫሉ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች የሚወደደሩበት ዘርፍ በሦስት ተከፍሏል። በመጀመሪያው ዘርፍ ፎቶ አንሺነትን እንደ ሙያ የያዙ ሰዎች ይወዳደራሉ። ሁለተኛው ዘርፍ ለዲፕሎማቶች ወይም ዓለም አቀፍ ተጓዦች የተሰጠ ሲሆን፤ በሦስተኛው ዘርፍ ማንኛውም ሰው መሳተፍ ይችላል።

"ብዙ ፎቶግራፈር የሚጀምረው በስልክ ፎቶ ከማንሳት ነው" የምትለው ሀምራዊት፤ በተራቀቀ ካሜራም ይሁን በእጅ ስልክ የተነሱ ፎቶዎችን በፌስቲቫሉ እንዳካተቱ ትናገራለች።

ተሳታፊዎች ይህንን ቦታ፣ በዚህ አይነት የፎቶ ጥራት ፎቶ ያንሱ የሚል ገደብ ባለመጣል ሁሉንም አካታች አሠራር መዘርጋቱን ታስረዳለች። በተሳታፊዎች ዘንድ የኔ እይታም ዋጋ አለው የሚል ስሜት መፍጠርን ግባቸው አድርገዋል።

ብዙዎች በስልክ የተነሳ ፎቶግራፍ በካሜራ የተነሳ ፎቶ ያህል ጥራት ላይኖረው ይችላል ሲሉ ስለ ውድድሩ ቢጠይቁም፤ ውድድሩ ሲካሄድ ፎቶው የተነሳበት መሣሪያ ከግምት ገብቶ ሁሉም ተሳታፊ ባለበት ደረጃ እንደሚመዘን ሀምራዊት ትናገራለች።

"ያልታየችው" አዲስ አበባ

"ካፕቸር አዲስ" የአዲስ አበባን ገጽታ በመሰነድ ከሚታወቁት "ስትሪትስ ኦፍ አዲስ" እና "ቪንቴጅ ኢትዮጵያ" ጋር በጥምረት ይሠራል። የዩጋንዳ እና የኬንያ ፎቶ አንሺዎችን ወደ አዲስ አበባ በመጋበዝ የከተማዋን የተለያዩ ገጽታዎች በካሜራቸው የሚያስቀሩበት መሰናዶ (ፎቶ ዋክ) ይካሄዳል።

በፌስቲቫሉ የአዲስ አበባን ህንጻዎች፣ ቀለበት መንገዶችን ወይም ታዋቂ ሰፈሮችን ከማሳየት ባሻገር የከተማዋን ነዋሪዎች የእለት ከእለት ሕይወት ለማንጸባረቅም ታልሟል።

"አዲስ አበባ ትልቅ ናት። በፌስቲቫሉ ሁሉንም ሰው ያካተትነው በፕሮፌሽናል ፎቶግራፈር ያልታዩ ገጽታዎችም እንዲካተቱ ነው። ማንኛውም ሰው አዲስ አበባ ውስጥ እየኖረም፣ እየሠራም የሚያየውን በፎቶ ማሳየት ይችላል" ትላለች ሀምራዊት።

ብዙ ጊዜ በፎቶ አንሺዎች እይታ ከሚገቡ አካባቢዎች ጎን ለጎን፤ ያልታዩ ወይም ትኩረት ያልተሰጣቸው ገጽታዎችም ማካተት አስፈላጊ እንደሆነም ታክላለች።

ገበያ ላይ ወይም የአደባባይ በዓሎች ሲከበሩ የተነሱ ፎቶዎችን እንደ ምሳሌ ታነሳለች። በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በስፋት የተሰራጨውን በመስቀል አደባባይ ደመራ ተደምሮ በሕዝብ መሀል እያቆራረጠ የሚሮጥ በሬ ፎቶንም ትጠቅሳለች።

Image copyright Mikiyas Melesse

የፌስቲቫሉ አዘጋጆች፤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ወይም ከተማዋን የሚጎበኙ የውጪ አገራት ዜጎችም ፎቶ እንዲያነሱ፣ ያነሱትን ፎቶ ለተቀረው ማኅበረሰብ አንዲያጋሩ ማነሳሳት እንደሚፈልጉም ሀምራዊት ትገልጻለች።

"አዲስ አበባን በአገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በጥሩ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ማሳየት እንፈልጋለን።"

ፎቶ ማንሳት የሰው፣ የቁስ ወይም የእንቅስቃሴን ምስል በካሜራ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን አንዳች መልዕክት ማስተላለፊያ መንገድ ጭምር እንደሆነም ታስረዳለች። ስለዚህም በፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች መካከል ውድድር ሲካሄድ ታሪክ ነገራ ከግምት ይገባል።