ህወሓት: "እሳትና ጭድ የሆኑ ፓርቲዎች ሊዋሃዱ አይችሉም"

የህወሓት አርማ Image copyright TPLF FACEBOOK

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሰባት ቀናት ሲያካሄድ የነበረውን ስብሰባ በማጠናቀቅ መግለጫ አውጥቷል።

ዘለግ ባለው በዚህ መግለጫ ህወሓት የኢህአዴግ መዋሃድ እርምጃን በተመለከተ ያለውን አቋም አንጸባርቋል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር -ኢህአዴግ መስራች እና ዋነኛ አባል የሆነ ህወሓት ፤ የኢህአዴግ የውህደት እንቅስቃሴን አጥብቆ ኮንኗል።

ህወሓት በመግለጫው "ከኢህዴግ ርዕዮተ ዓለም እና መተዳደሪያ ደንብ ውጪ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመመስረት እየተደረገ ያለው ሩጫ ሕገ-ወጥ ነው" ብሏል።

"ለስልጣን ተብሎ የሚፈጠር ውህደትን ህወሓት ፈጽሞ አይቀበለውም" አቶ ጌታቸው ረዳ

"አገሪቷ አሁን ለምትገኝበት የፖለቲካ ብልሽት ህወሓት ተጠያቂ ነው" አዴፓ

"እንዲፈጠር እየተፈለገ ያለው ፓርቲ በቅርጽ ብቻም ሳይሆን በይዘትም፤ ከነበረው ኢህአዴግ ፕሮግራም በመሰረቱ የተለየ አዲስ ፓርቲ የመመስረት ጥረት ነው" ያለ ሲሆን፤ . . . "የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዴግን የመረጠው በያዘው ፕሮግራም መሰረት ነው። አገር እንዲመራ በህዝብ ኃላፊነት ያልተሰጠው አዲስ ፓርቲ ለመመስረት እየተሞከረ ነው ያለው።" ሲል መግለጫው ይቀጥላል።

"ይመሰረታል የተባለው ውህድ ፓርቲ በህዝብ ስልጣን ላይ እንዲቆይ ፍቃድ ያልተሰጠው ፓርቲም ብቻ ሳይሆን፤ ስልጣን ለመያዝ መወዳደር የማይችል ፓርቲ ይሆናል" ብሏል።

"እሳት እና ጭድ የሆኑ ፓርቲዎች በውስጥ የተሸከመው ግንባር፤ አይደለም ውህደት ፓርቲ በግንባርነት አብሮ የሚያቆይ የጋራ አስተሳሰብ እንኳን የላቸውም" ሲል ጠንከር ያለ እገላለጽን በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

የህወሓትና የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ተዋህዶ አንድ ወጥ ሃገራዊ ፓርቲ ይሆናል እየተባለ የሚነገረውን ጉዳይ ህወሓት ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማይኖረው መናገራቸው ይታወሳል።

"በየእለቱ እርስ በርስ እየተናቆሩ የሚውሉ አባል ፓርቲዎችን ይዘን የሃገር ችግርን በመረዳትም ሆነ ችግርን ለመፍታት በምንከተለው መንገድ ጭምር እርስ በእርሱ በሚጋጩበት ሁኔታ ውሁድ ፓርቲ ለመመስረት መሯሯጥ፤ የጥቂት ግለሰቦች የስልጣን ጥማት ለማርካት ካልሆነ በስተቀር የሃገሪቷን ችግር የሚፈታ ሃገራዊ ፓርቲ ይፈጠራል ብሎ ህወሓት አያምንም" በማለት አቶ ጌታቸው ገልጸው ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ህውሓት ለትግራይ፣ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ህዝብ መልዕክት አስተላልፏል።ህውሓት በመግለጫው፤ "የተከበርክ የትግራይ ህዝብ፤ አሁንም ቢሆን ሁኔታዎች እየከበዱና እየባሱ በመምጣታቸው ደህንነትህንና ህልውናህን ለማስጠበቅ የምታደርገው ትግል ይበልጥ አጠናክረህ ልትቀጥልበት ይገባል" የሚል መልዕክት ለሚያስተዳደርው ክልል ህዝብ መልዕክት አስተላልፏል::አክሎም "ህገ መንግስታችንና ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓታችን የሚሸረሽሩና የሚጥሱ ተግባራት በየቀኑ ማየት የተለመደ ተግባር ሆኗል። . . . መላው የሀገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓታችንን ለማዳን በሚደረገው ወሳኝ ትግል ከማንኛውም ጊዜ በላይ አገራችንን ለማዳን ሊረባረብ ይገባል" በማለት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ጥሪ አቅርቧል።በመጨረሻም ህውሓት በመግለጫው፤ ለኤርትራ ህዝብ "የትግራይና የኤርትራ ህዝብ ለጋራ መብትና ጥቅም በጋራ የታገሉ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው። የነበረውና አሁንም ያለው ዝምድናና መደጋገፍ ወደ ዘላቂ አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ ባለፈው ዓመት የተጀመረው የሰላም ጭላንጭል በዚህ ዓመትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብሏል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ