"በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር የጥምር ኃይል ሊሰማራ ነው" የአማራ ክልል ደኀንነትና ጸጥታ ካውንስል

የኢትዮጵያ ካርታ Image copyright Google Map

በማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች፣ በጎንደር ከተማ እንዲሁም በቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር "ማንነትን ሽፋን" በማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት የጸጥታ መደፍረስ፣ የሰው ህይወትና ንብረት መጥፋት መከሰቱን የአማራ ክልል ደኀንነትና ጸጥታ ካውንስል ትናንትና አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ በመግለፅ፤ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ይሆናሉ ያላቸውን መመሪያዎች አስተላልፏል።

በክልሉ የማንነት ጥያቄዎችን ላነሱ ወገኖች ምላሽ መስጠቱን ያስታወሰው ይህ መግለጫ ቅሬታ ያላቸው አካላት ጥያቄያቸውን አቅርበው መስተናገድ "የሚችሉበት ዕድል እያለ" በኃይል ፍላጎታቸውን ለማስፈፀም መሞከራቸውን "ጸረ ህገ መንግስትና የለየለት ጸረ ሰላም ተግባር" ሲል ኮንኖታል።

መግለጫው አክሎም "የቅማንት የራስ አሥተዳደር ኮሚቴ የተከተለው አቅጣጫም ፍላጎትን በኃይል በብሔረሰቡና በክልሉ መንግስት ላይ የመጫን "ኢ ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴ" መሆኑን በመግለጫው ላይ አትቷል።

"መንገደኞች የሚጓዙት በመከላከያ ታጅበው ነው" የማዕከላዊ ጎንደር ኮሙኒኬሽን

"የሰለጠነና በሙሉ አቅም የሚዋጋ ኃይል ነው ችግሩን የሚፈጥረው" የማዕከላዊ ጎንደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ

ካውንስሉ በመግለጫው ላይ እንደጠቀሰው "ኢ ሕገመንግሰታዊ እርምጃ ለመቀልበስ በተወሰደው እርምጃ" ግጭት መከሰቱንና ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አንስቶ ክልሉና የፌደራል መንግሥት "በትዕግስትና በአርቆ አስተዋይነት" ችግሩን ለመፍታት ቢጥሩም ውጤት ሊመጣ አለመቻሉን ገልጿል።

በአካባቢው የተከሰተው ግጭት "አካባቢውን ወደ ተሟላ ትርምስ የሚያስገባና ለክልሉ ብሎም ለመላው ሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት" መሆኑንም የካውንስሉ መግለጫ አመልክቷል።

መግለጫው አክሎም የአካባቢው ሠላም መደፍረስ የገቢና የወጪ ንግድ ላይም ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ጠቅሷል።

በዚህም የተነሳ የፌዴራል የፀጥታ ኃይል መከላከያን ጨምሮ ማንኛውም ህጋዊ እርምጃ ወስዶ ቀጠናውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሟላ ሰላም እና መረጋጋት እንዲያሸጋግር መመሪያ መተላለፉ ተገልጿል።

የተላለፈውን መመሪያ በመከተል የክልሉ የፀጥታና ደኅንነት ካውንስል በማዕከላዊ፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር እና በጎንደር ከተማ ክልከላዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ መመሪያ መሰጠቱን አስፍሯል።

ከመመሪያዎቹ መካከል ማንኛውም የኃይል እንቅስቃሴን የኃይል እርምጃ በመውሰድ መቆጣጠር የሚል የሚገኝበት ሲሆን ጥፋተኞችን ለመቆጣጠር ተመጣጣኝ የኃይል እርምጃን በመውሰድ የኃይል ተግባርን ፍፁም እንዳይቀጥል ማድረግ የሚል ይገኝበታል።

ካውንስሉ የሠላም አማራጮችን ለማስፋት በሚል በአካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ግጭት የገቡ ቡድኖችና ግለሰቦች በአስቸኳይ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በመመለስ ያሏቸውን ልዩነቶች እንዲፈቱ ጥሪም አስተላልፏል።

እውን ድህነትን እየቀነስን ነው?

ህወሓት: "እሳትና ጭድ የሆኑ ፓርቲዎች ሊዋሃዱ አይችሉም"

በግልፅ በታወቁ የፀጥታ ኃይሎች ከተያዙት ትጥቅና መሳሪያ ውጪ በተጠቀሱት የክልሉ ዞኖች ላልተወሰነ ጊዜ ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ሲንቀሳቀስ ይዞ የተገኘ ግለሰብ የሚወረስበት መሆኑ ተገልጿል።

የቅማንት ብሔረሰብ አስተዳድር ከዚህ ቀደም በተወሰነው ህጋዊ ውሳኔ መሠረት በአፋጣኝ በሕዝብ ይሁንታ የሚደራጅ የራስ አስተዳድርን በማቋቋም ሁሉም አገልግሎት እንዲጀምር እንደሚያደርግም በመመሪያው ላይ ተካትቷል።

በአካባቢው ውስጥ በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ ገብተው የነበሩ ኃይሎች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች እስከ ጥቅምት 20/2012 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለሱ የክልሉ መንግሥት በድጋሜ ይቅርታ ማድረጉም ተገልጿል።

ነገር ግን በሰው ግድያ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች ጉዳያቸው በህግ አግባብ የሚታይ መሆኑ በመመሪያው ላይ ተካትቷል።

በየአካባቢው ለሚፈጠሩ "ወንጀሎች ፀረ-ሰላም ድርጊቶችና እንቅስቃሴዎች" ሁሉም አካላት የመቆጣጠር፣ የማሳወቅ፣ እርምጃ እንዲወስድ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው ያለው መመሪያው፤ ይህ ካልሆነ ግን ተጠያቂነትን ከማስከተልም በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኘው ትጥቅ ሙሉ በሙሉ ተራግፎ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል ሲል አስጠንቅቋል።

ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ረቂቅ ህግ የሞት ቅጣት ተካቶበታል

በኢ- መደበኛ አደረጃጀትና ባልተሠጠ ኃላፊነት ህግን ለማስከበር በሚል ሰበብ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ መከልከሉን ያስቀመጠው መመሪያው ተጠያቂነትም እንደሚያስከትል ገልጿል።

ከጎንደር ወደ መተማ፣ ሁመራ፣ ባሕር ዳር፣ደባርቅ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚወስዱ መንገዶች በማንኛውም ጊዜ ነፃ ይሆናሉ ያለው መግለጫው፣ የሕዝብ በነፃነት የመንቀሳቀስን መብት ለማደናቀፍ የሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ ይሆናል ሲል አስቀምጧል።

በአካባቢው ሠላምና መረጋጋት ለማምጣት የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ ክልል የፀጥታ ኃይል፣ በየደረጃው ያለው የክልሉ መስተዳድር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት በጥምረት እንደሚሰሩ መመሪያው አስቀምጧል።