የምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ጉዳይ ሐሰተኛ ዜና ወይስ የተቀለበሰ ውሳኔ?

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር ) Image copyright Addis Ababa city mayor

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መወሰኑና በምትካቸው ሌላ ሰው ሊሾም መሆኑ ተሰምቶ ነበር።

ይህ ወሬ ግን ሐሙስ ዕለት የከንቲባው ጽህፈት ቤት "ከንቲባው በሥራ ላይ ናቸው" በማለት ከሥልጣን አለመነሳታቸውን በመግለጽ ወሬውን 'ሐሰት ነው' ሲል አጣጥሎታል።

ባለፉት ቀናት የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ከዚህ ጉዳይ ጋር ቅርበት አለን የሚሉ አካላትን አናገርን በማለት ሲዘግቡ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ግን ምንም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦ ቆይቶ ነበር።

ቢቢሲ ኦሮምኛ በዚህ ጉዳይ ላይ በቂ መረጃ ካላቸው ሰዎች አጣርቶ ምክትል ከንቲባው ከኃላፊነታቸው ሊነሱ መሆኑ "እውነተኛ እንደሆነ" ዘግቦ ነበር።

"አዲስ አበባ የምንወዛገብባት ሳትሆን በጋራ የምንኖርባት ከተማ ናት" ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ

በወቅቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ያሉ መረጃዎችን መሰረት አድርጎ ለሚናገር ማንኛውም ግለሰብ፤ የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ስብሰባውን እስከ አጠናቀቀበት ድረስ ጉዳዩ ያለቀለት ይመስል ነበር።

ሐሙስ ዕለት አመሻሽ ላይ የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ ማጠናቀቁ በተገለፀ በጥቂት ሰዓት ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ ዝምታውን በመስበር "ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሥራ ላይ ናቸው፣ ከሥልጠጣናቸው ተነስተዋል ተብሎ የወጣው ወሬ ስህተት ነው" በማለት በማህበራዊ መገናኛ ገፁ ላይ አስፍሯል።

ይህ መረጃ የወጣው የኦዲፒ ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ የኦዲፒ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የስብሰባውን መጠናቀቅ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ከገለጹ ከአንድ ሰዓት በኋላ ነው።

ቢቢሲ ኦሮምኛ ያገኛቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ምክትል ከንቲባው ከስልጣናቸው እንዲነሱ ከሳምንት ቀደም ብሎ ከበላይ ኃላፊዎች ጋር በመነገሩ ምክትል ከንቲባው አስቀድመው ይዘዋቸው የነበሩ ፕሮግራሞቻቸውን ሰርዘው ነበር።

ከኃላፊነታቸው ሊነሱ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች

ለአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከሥልጣን መነሳታቸውን የሚገልፅ ምንም አይነት ደብዳቤ እጃቸው ላይ እንዳልደረሰ በዚህ ጉዳይ ላይ ቅርብ የሆኑ ሰዎችን በመጠየቅ ለማረጋገጥ ችለናል።

ይሁን እንጂ ጥቅምት 8 በፊት ምክትል ከንቲባው "በእጆችህ ላይ ያሉትን ሥራዎች አጠናቅቀህ ጨርስ፤ ሌላ ሠው ያንተን ቦታ ይተካል" ተብሎ ተነግሯቸው እንደነበር ለጉዳዩ ቅርበት ካነጋገርናቸው ሰዎች መካከል አንዱ ይገልጻሉ።

''አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ ናት'' ከንቲባ ታከለ ኡማ

ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከኃላፊነታቸው መነሳት እንደማይፈልጉና ይህም ጉዳይ ለእርሳቸው ከተገለጸላቸው በኋላ ደስተኛ እንዳልነበሩ፣ በሥራቸውም ላይ ጫና ፈጥሮ እንደነበር በሥራ አጋጣሚ ለእርሳቸው ቅርበት ያላቸው ሰዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ማክሰኞ የአድዋ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን እያስመረቁና እያስጀመሩ መቆየታቸው ለዚህ ሌላው ማሳያ ነው የሚሉት እኚህ ግለሰብ የተለያዩ አካላት 'በአንድ ጊዜ ይህንን ሁሉ ሥራዎች ለመስራት ለምን ተጣደፉ?' ብለው ሲጠይቁ እንደነበር መረዳት ችለናል።

ምክትል ከንቲባው ማክሰኞ ዕለት ቢሯቸው ቆይተው እንደወጡና የከንቲባው ጽሕፈት ቤትና ሌሎች የከተማው አስተዳደር ቢሮዎች አካባቢ የነበሩ ሰራተኞች ላይ ይታዩ የነበሩ ስሜቶችም ከንቲባው ይለቃሉ በሚል የሀዘን ድባብ ያጠላበት እንደነበር እኚሁ ግለሰብ ያስታውሳሉ።

ከንቲባው በመጨረሻ የከተማ አስተዳደሩ ፕሮግራም ላይ የተናገሩት መልዕክት የስንብት መሆኑን እንደተረዱ በስፍራው የነበሩና ቢቢሲ ያናገራቸው ሰዎች ይገልጻሉ።

በኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም የተቀሰቀሰው ውዝግብ

"እርሳቸውን የማንሳት ውሳኔ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጣ ነው ብለን እንጠረጥራለን" የሚሉት እኚህ ግለሰብ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በእርግጠኝነት ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባነታቸው ሊነሱ እንደነበር ተጨማሪ ማስረጃዎችን በመጥቀስ ያስረዳሉ።

ነሐሴ 27/2011 ዓ.ም የከንቲባው ጽህፈት ቤት በፌስ ቡክ ገፁ ላይ እደገለፀው ኢንጂነር ታከለ በኮፐንሀገን በተዘጋጀው የዓለም አቀፍ ከንቲባዎች ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ ተጋብዘው ነበር።

ይህ ጉባኤ ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት1/2012 ዓ.ም ድረስ ይካሄድ ለነበረው ጉባኤ ላይ ኢንጂነሩ ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በመሆን ለመሳተፍ ይዘውት የነበረውን ዝግጅት እንዲቀርና የአየር ቲኬታቸውም መሰረዙን ምንጮቻችን ሰምተናል።

በተመሳሳይ ደግሞ የሮማ ካቶሊክ ጳጳስ ለምክትል ከንቲባው ባደረጉት ግብዣ ወደዚያው ለማቅናት ይዘውት የነበረው ፕሮግራምም መሰረዙን ከምንጮቻችን ለመረዳት ችለናል።

የምክትል ከንቲባው ከሥልጣን የመነሳት ምክንያ ምንድን ነው?

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ መጀመሪያ ወደ ስልጣን ሲመጡ ሁሉም በደስታ ስሜት አልተቀበላቸውም ነበር።

በከተማዋ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የተለያዩ አካላት የእርሳቸውን ሹመት ተከትሎ የተለያዩ የተቃውሞ ድምጾችን ሲያሰሙ እንደነበር ይታወሳል።

ምክትል ከንቲባው ግን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር የከተማዋ ነዋሪዎችን ቀልብ ለመሳብ የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

ከእነዚህ መካከል ለከተማው ተማሪዎች ደብተርና የደንብ ልብስ በነጻ እንዲሰጥ ማድረጋቸው በተለይ ደግሞ ለ300 ሺህ ተማሪዎች የዘወትር ምሳና ቁርስ ምገባ እንዲጀመር ማድረጋቸውም የከተማዋ ነዋሪዎችን ልብ ካሸነፉበት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

"ታከለ ኡማ አዲስ አበባን መምራት የለባቸውም" እስክንድር ነጋ

ነገር ግን አሁንም ቢሆን ምክትል ከንቲባው ላይ ቅሬታ የነበራቸው አካላት መግለጫ ከማውጣት ባለፈ በግልፅ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተደምጧል።

በከንቲባው ላይ ከውጪ ከሚሰማው ተቃውሞ በተጨማሪ በዙሪያቸው ካሉ የገዢው ፓርቲ አባላት ጭምር ለዚህ ቦታ ሲታጩ ጀምሮ መሾማቸውን የሚቃወሙ ግለሰቦች ስለነበሩ የሥልጣን ጊዜያቸው የተደላደለ እንዳልሆነ ይነገራል።

በአዲስ አበባ መስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ ደግሞ ሐሙስ ወደማታ አካባቢ በከንቲባው ጽህፈት ቤት ሰራተኞች መካከል የነበረውን ስሜት ሲገልፁ "እንኳን ደስ አላችሁ፤ ውሳኔው ተቀልብሷል" እየተባባሉ እንደነበር በመግለፅ ከንቲባው ተመልሰው በሥራቸው ላይ አንዲቆዩ መደረጉ የፈጠረውነ ስሜት ይናገራሉ።

አርብ ዕለት ጠዋት የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ በስብሰባው ላይ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በተመለከተ በመግለጫው ስለምክትል ከንቲባው ጉዳይ ምንም ነገር አላለም።

የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት የፓርላማውን ውሳኔ ተቃወመ

ቢቢሲም ይህ የውሳኔ ሃሳብ በኦዲፒ ስብሰባ ላይ ቀርቦ መቀየር አለመቀየሩን ለማጣራት ያደረግው ሙከራም አልተሳካም።

ምክትል ከንቲባው በሥራ ላይ ናቸው የሚለው መረጃ የኦዲፒ ስብሰባ መጠናቀቁ ከተገለጸ ከአንድ ሰዓት በኋላ መውጣቱ ግን ጉዳዩ ተገጣጥሞ ነው ለማለት ግን እንደሚያስቸግር ጉዳዩን ያነሳንላቸው ምንጮቻችን ይናገራሉ።

ከተለያዩ ወገኖች መነሳታቸውን በተመለከተ የተሰማው መረጃ ተከትሎ የቀረበው ተቃውሞ ውሳኔው እንዲቀለበስ ድርሻ እንደነበረው እንደሚያምኑ እኚሁ ግለሰብ አክለው ተናግረዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ