ኤርትራ በዶይቼ ቬለ ዘገባ ሳቢያ የጀርመን አምባሳደር ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠየቀች

የዶቼ ቨለ ቢሮ Image copyright MARIUS BECKER

የኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር በዶይቼ ቬለ (የጀርመን ድምጽ ራዲዮ) ዘገባ ምክንያት በኤርትራ የጀርመን አምባሳደር ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠየቀ።

የኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር የማነ ገብረ መስቀል "ያልተቋረጠ የመረረ ትችት" ባሉት የዶይቼ ቬለ ዘገባ ምክንያት በኤርትራ የጀርመን አምባሳደር ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቃቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የዛሬዋን ኤርትራ የሚገልጹ አስደናቂ እውነታዎች

አሥመራን አየናት፡ እንደነበረች ያለችው አሥመራ

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ በጀርመን መንግሥት ፈንድ የሚንቀሳቀሰው የዶይቼ ቬለ የአማርኛ እና የእንግሊዘኛ አርታኢዎች የኤርትራን ብሔራዊ አገልግሎት በተመለከተ እንዲሁም በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት የተሳሳተ መረጃን ያስተላልፋሉ ሲሉ ነቅፈዋል።

የኤርትራን መንግሥት ያስቆጣው የዶይቼ ቬለ ዘገባ በትክክለ የቱ እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፤ በቅርቡ በድረ-ገጹ ላይ ይዞት የወጣው ጽሁፍ አንዱ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።

ይህ ከ10 ቀናት በፊት በአማርኛ ዴስክ ኃላፊ በሆነው ሉደር ሽዶመስኪይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈው የግል አስተያየት፡ ''ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የለውጥ አራማጅ ቢሆኑም ከኤርትራ ጋር በደረሱት ሰላም ምክንያት የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲሰጣቸው መወሰኑ ስህተት ነው'' የሚል ይዘት አለው።

ሉደር በጽሁፉ የኤርትራውን ፕሬዝደንት "ብስጩና ፈላጭ ቆራጭ መሪ" ሲል የገለጻቸው ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ". . . ስልጣን ላይ ለመቆየት ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ዜጎቹን በሰንሰለት ያስራል። . . . በዓለም ዓይን በግማሽ እድሜው በሚያንሰው መሪ መበለጥ የሚያስደስትው አይሆንም" በማለት ፕሬዝደንቱን ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር አነጻጽሮም አስነብቧል።

በጉዳዩ ላይ የጀመርን መንግሥትም ሆነ ዶይቼ ቬለ ያሉት ነገር የለም።

የኤርትራ ወጣቶችና ምኞታቸው

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ጨምረውም፤ ቢቢሲን በተመለከተም ከዚህ ቀደም "ከአንድም ሁለቴ [በኤርትራ] የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር በጉዳዩ ላይ የመንግሥታቸው አቋም እና አስተያየት ምን እንደሆነ" መጠየቃቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

"በዚህም አስፈላጊ እርምጃዎች የማይወሰዱ ከሆነ ሌሎች አማራጮች/ዘዴዎች እንከተላለን" ሲሉ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ