የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ "መደመር" መጽሐፍ ምን ይዟል?

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ "መደመር" መፅሐፍ Image copyright Office of the Prime Minister

"ከኢትዮጵያዊያን መሠረታዊ ሥሪት የሚነሳ፣ ችግሮቻችንን ሊፈታ የሚችል፣ እኛው እያቃናነውና እያሟላነው የምንሄደው፣ ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ፣ ሁላችንንም ሊያግባባና ሊያስተሳስር የሚችል አንዳች ሉዓላዊና ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ያስፈልገናል" ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፤

ባለፈው ቅዳሜ በመዲናዋ አዲስ አበባ እና በሌሎችም በርከት ያሉ ከተሞች በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ባስመረቁት አዲስ መፅሐፋቸው "መደመር" ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የአገሪቱን ከፍተኛ ሥልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች ደጋግመው ያወሱትና መደመር ሲሉ የሚጠሩትን የአመራር እሳቤያቸውን ጠቅለል ባለ አኳኋን ለመተንተን የሞከሩበት፣ በልዩ ልዩ የመንግሥት እንደዚሁም የአኗኗር አፅቆች እሳቤያቸው እንዴት ሊተገበር እንደሚችል ለማመላከት የጣሩበት፣ ከዚህም በዘለለ የአስተዳደራቸውን ቀጣይ አቅጣጫዎች በተመለከተ ፍንጭ የሰጡበት ድርሳን ነው "መደመር"።

"ለውጡ ሐዲዱን ስቷል ብዬ ነው የማምነው" አርቲስት ታማኝ በየነ

አዲስ አበባ ውስጥ ሲካሄዱ የነበሩ ስብሰባዎች በወጣቶች መስተጓጎላቸው ተነግሯል

በአስራ ስድስት ምዕራፋት የተቀነበበው መደመር የጠቅላይ ሚኒስትሩን ግላዊ ምልከታዎች ጥንስስ እና ዕድገት አስረድቶ አያበቃም፤ ኢትዮጵያ በእርሳቸው አመራር በፖለቲካ፣ በምጣኔ ኃብት እና በውጭ ግንኙነት መስኮች ምን መልክ እንዲኖራት እንደሚሹ የሚጠቁም ሲያልፍም በግላጭ የሚያስቀምጥ ጭምርም ነው።

"ጊዜያችንን የሚዋጅ እሳቤ ነው" የሚሉትን የመደመርን ፅንሰ ኃሳብ በጥቅሉ ሲበይኑት "ከትንተና አንፃር ሀገር በቀል"፣ ከመፍትሔ ፍለጋ አንፃር ደግሞ "ከሀገር ውስጥም ከውጭም ትምህርት በመውሰድ የተቀመረ ነው" ይሉታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመፅሐፋቸው ሙግታቸውን የሚጀምሩት ስለሰው ልጅ ፍላጎቶች ከፍልስፍናም ከሥነ ልቦና ሳይንስ ደጆች የሚታከክ ትንተና በማቅረብ ነው። ሰዎች በህይወቶቻቸው ቀጥተኛ የህልውና ፍላጎቶች፣ የስጋ ፍላጎቶች እንዲሁም የመልካም ስም ወይንም የክብር ፍላጎቶች ሰንገው እንደሚይዟቸው ያስረዱና የመደመር እሳቤ እነዚህን ፍላጎቶች በቅደም ተከተል ሳይሆን እንደነባራዊ ሁኔታው እየታዩ በእኩልነት እንደሚያስተናግድ ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያንም ዕጣ ፈንታ በዚሁ የሰው ልጆች የፍላጎቶች መስተጋብር ይተነትኑትና የስም እና የነፃነትን ጥያቄዎች በአግባቡ ሳትመልስ ህልውናዋን ለማረጋገጥ ስትሞክር ሊያጠፏት ይችሉ የነበሩ አደጋዎችን በራሷ ላይ ጋብዛለች ይላሉ።

ልዩ ልዩ የኢትዮጵያ መንግስታት ባለፉት አስርት ዓመታት የተከተሏቸውን ርዕዮተ ዓለማት በተቹበት ንዑስ ምዕራፋቸው ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በአገሪቱ "የነበረው ትርምስ ከውጭ ያገኘነውን ዕውቀት ከሀገራችን ሁኔታ ጋር በደፈናው ስናላትመው የተፈጠረ ችግር ነው" ይላሉ።

ከእርሳቸው ወደ መሪነት ማማ መምጣት በፊት ፓርቲያቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) እከተለዋለሁ ይለው የነበረውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ስድስት ነጥቦችን ነቅሰው የነቀፉት ሲሆን ችግሮችን ሁሉ በምጣኔ ኃብቱ ላይ ያሳብባል፤ ስለግሉ ዘርፍ ልሂቃን የተዛነፈ ምልከታ አለው፤ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታን ቸል ብሎ አውራ ፓርቲን አፈርጥሟል፤ ከጠንካራ የመንግስት ቢሮክራሲ ይልቅ ጠንካራ ፓርቲን ለማጎልመስ ታትሯል ብለውታል።

ይህም መፅሐፋቸው ለፓርቲያቸው አባላት እና ደጋፊዎች አዲስ ርዕዮተ ዓለማዊ መመርያ (ማኑዋል) የመስጠት ዓላማ የያዘ መሆኑን የሚያስጠረጥር ነው።

"ውስኪ ጠጪ ኢህአዴጎች እባካችሁ ውሃ የናፈቀው ሕዝብ እንዳለ አትርሱ" ጠ/ሚ ዐብይ

መደመርን እንቅፋት ሆነው ሊያሰናክሉት ይችላሉ ያሏቸውን ጉዳዮችም ዘርዝረዋል፤ ዋልታ ረገጥነት፣ የጊዜ እስረኛ መሆን፣ ውስብስብ ችግሮችን ያለቅጥ አቅልሎ መመልከት ይገኙባቸዋል። 

የብሔር ፖለቲካ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በመደመር መፅሐፋቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋስዖ የብሔር ማንነት ከሌሎች ማንነቶች አንፃር የተጋነነ ስፍራ መያዙን ይገልፃሉ።

ተቺዎች የሀገሪቱ የቡድን ሥሪት በአካባቢያዊነት እና በሃይማኖት እንጅ በብሔረተኛነት ዙርያ አልተገነባም ሲሉ መሞገታቸውን፣ የሰው ልጆች የተለያዩ ቡድናዊ ማንነቶች ያሏቸው ሆኖ እያለ በብሔር ላይ ብቻ ማተኮር የሕዝብን ችግር በአግባቡ ያለመረዳት ነው እያሉ መከራከራቸውን ያወሳሉ።

ይሁንና የተጠቀሱት መከራከሪያዎች "ብሔር ለምን ከሌሎቹ የቡድን ማንነቶች በላይ ገንኖ ሊወጣ ቻለ?" የሚለውን ግን አይመልሱም ሲሉ መልሰው ይተቿቸዋል። 

"ሌሎች ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆነው ብሔር ከሌሎቹ ማንነቶች ገንኖ የወጣበት አንዱ ምክንያት የብሔር ጭቆና መኖር ነው።"

የግለሰብ መብት መከበር ላይ የሚያተኮሩ የፖለቲካ ልሂቃንን "የቡድን ማንነትን በማጥፋት ስም ጭቆናን የሚያድበሰብስ" እና "የጭቆና ቅሪት" እንዲቆይ የሚያደርግ መፍትሔ ነው ያላቸው ይሏቸዋል።

የቡድን ማንነትን ይዞ ከጭቆና ለመውጣት መታገል ደግሞ "የቡድን አክራሪነትን በመፍጠር ከሚፈታው ይልቅ የሚፈጥረው ችግር እየባሰ መጥቷል" ይሉታል።

Image copyright facebook

የቡድን አክራሪነት ተጨቁነናል ብለው የታገሉ ቡድኖች "ትግላቸው ገደቡን አልፎና መሥመሩን ጥሶ እነርሱም በምላሹ" ሌሎችን ለመጨቆን የሚሞክሩበትን እና እርሳቸው "አፀፋዊ ጭቆና" ያሉትን ችግር ያመጣል ይላሉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "መደመር" መጽሐፍ ተመረቀ

በመፍትሔነትም እርሳቸው የሚሟገቱለት የመደመር ፍልስፍና ማኅበረሰባዊ ብሔርተኝነት ያሉትን ብሔር ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴ እና ሲቪክ ብሔርተኝነት ሲሉ የጠሩትን ዜግነት ወይንም አገር ተኮር ፖለቲካ እንቅስቃሴ አመቻምቾ እንደሚጓዝ ያስረዳሉ።፥

"በብሔር ልሂቃን መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብና" ተገቢ ቦታ አላገኘም ያሉትን ሲቪክ ብሔርተኝነት ለማካተት "ቀጣይ ተዋስኦ መር ድርድሮችን ማድረግ አስፈላጊ ነው" ይላሉ።

"የጥራት ችግር ያለበት" ዕድገት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምጣኔ ኃብቱን በተመለከተ በመፅሐፋቸው አራት ምዕራፎችንና 83 ገፆችን ሰጥተው ፅፈዋል።

ከመነሻቸው ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት ምጣኔ ኃብታዊ ዕደገት እና ማኅበራዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ያትታሉ፤ ይለጥቁናም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው አዲስ የኃይል አሰላለፍ ለምጣኔ ኃብታዊ ዕድገቱ ምቹ ከባቢ በመፍጠሩ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የልማት ፋይናንስ በብድርም በዕርዳታም ተገኝቶ መንግስት ማኅበራዊ አገልገሎቶችንና መሠረተ ልማትን እንዲያስፋፋ አስቸሎታል ይላሉ።

ሆኖም የተመዘገበው ዕድገት የጥራት ችግር ነበረበት ሲሉ ይሟገታሉ፤ ለሙግታቸውም በአስረጂነት "የኢኮኖሚ በሽታ ምልክቶች" ናቸው ያሏቸውን የኑሮ ውድነትን፣ የሥራ አጥነትን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን፣ የበጀት ጉድለትን፣ የኤክስፖርት ንግድ መዳከምን፣ ኮንትሮባንድን እና የመሳሰሉትን ይዘረዝራሉ።

ምርታማነት እንዲጨምር፣ በዚያውም ልክ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር መትጋትን የሚሰብኩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምጣኔ ኃብት ስርዓት ተዋናዮች የሚሏቸውን አካላት በቅንጅት እና በመናበብ መስራት አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው ይገልፃሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ የምጣኔ ኃብት ችግሮችን መንስዔዎች ገበያ ነክ፣ መንግስታዊ እና ሥርዓታዊ ብለው ይፈርጁና በገበያው ውስጥ ፍትሐዊ ውድድር እና ፉክክር እንዳይኖሩ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ገበያ ነክ ጉድለቶች ናቸው ይሏቸዋል።

"አሁን ያለው ሁኔታ ከቀጠለ ነገ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንደሚገባ ግልጽ ነው" አቦይ ስብሃት

የግሉን ዘርፍ ደካማ መሆን እና የገበያ መረጃዎች በደላላዎች አማካይነት መዛባትን ከዚህ ምድብ ያካትታሉ።

መንግስት ከሚገባው በላይ በገበያው ውስጥ ጣልቃ መግባቱ እና ዳተኛ ሆኖ መውሰድ ያለባቸውን የማረጋጋት እርምጃዎች ያለመውሰዱን ደግሞ መንግስታዊ የምጣኔ ኃብት ጉድለት አድርገው ያወሱታል፤ ቀዳሚው በኢትዮጵያ ጎልቶ እንደሚታይም አክለው ፅፈዋል።

Image copyright Office of the Prime Minister-Ethiopia

"የኢኮኖሚ ሥርዓት የደም ሥር" ነው ያሉትን ፋይናንስን በተመለከተ ሲፅፉ "በዓለም አቀፍ የለጋሽ እና አበዳሪ አገራት የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት ከውጭ የሚገኘው የልማት ፋይናንስ እንደሚቀንስ ይጠበቃል" ይላሉ። በመሆኑም "በዕዳ ጫና እና በፖሊሲ ለውጥ ምክንያት ባለፉት ዓመታት የተመዘገበውን የኢኮኖሚ እድገት በመጣበት ተመሳሳይ የፋይናንስ ግኝት ሞዴል ማስቀጠል አይቻልም።"

ከግብር የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እስካሁን በግብር ያልተካተቱ ዘርፎችን ማካተትን፣ ከግብር ነፃ ሆነው የቆዩ ዘርፎችን መከለስን እና ሕግን ማስከበርን በመፍትሔነት ይዘረዝራሉ።

የመንግስት እና የገበያ ጉድለትን "ለማከም"ም የመንግስት የፕሮጀክት ኃሳቦችን በፖሊሲ ተፅዕኖ ሳይሆን በአዋጭነታቸው ተመሥርቶ መፍቀድም መፈፀምም እንደሚገባ ይከራከራሉ።

"ወዳጅም ጠላትም የለም"

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከውጭ ግንኙነት ጋር በተያያዘ "ወዳጅና ጠላት ብሎ ነገር የለም የሚል መርሕ የምንከተል ይሆናል" ይላሉ።

የውጭ ጉዳይ ግንኙነቶች ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮችንም "ጎረቤት ሀገራትን ማስቀደም እና ብሔራዊ ክብርን ከፍ ማድረግ ናቸው" ሲሉ ፅፈዋል።

የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ከየት ወደ የት?

ከጎረቤት አገራት ጋር በተገናኘ በደህንነት ሥጋት ላይ ከተመሠረተ ግንኙነት ወጥቶ በምጣኔ ኃብታዊ ትብብር እና ውህደት ላይ ማተኮር እንደሚገባ የሞገቱት ዐብይ የአረብ ሀገራትንም እንደችግር እና ታሪካዊ ጠላት መመልከትን ትቶ እንደአጋር ማየት እንደሚገባ መክረዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ